አለምን እየናጣት ያለው ኮቪድ 19 (ኮሮና ቫይረስ) ዛሬም የጥፋት አድማሱን በማስፋት ላይ ይገኛል። የማይታየው የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ገዳይ ቫይረስ የአለም ሀገራትን አዳርሶ በስልጣኔና በቴክኖሎጂ መጥቀናል ያሉትን ሁሉ አንበርክኳል። ምእራባውያን ሀገራትን ባላሰቡትና ባልገመቱት ፍጥነት ገብቶ እንደ ሰደድ እሳት እየለበለበ መድረሻም አሳጥቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን በድንገተኛ ሞት እየነጠቃቸው ይገኛል።
ሞት እንደ ዘንድሮ የረከሰበት፣ ገዳዮች ሟች የሆኑበት ዘመን መቼም ታይቶ አይታወቅም። የምጽአት ቀን የደረሰ እስኪመስል ዘር፣ ቀለም፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ስልጣን፣ ሀብት፣ ድሀ ሳይል እየመተረው ይገኛል። ለካስ የቀድሞው የአብሮነት ደግ ቀን እንዲህ ይናፍቃል የሚባልበት ጎዶሎ ዘመን ላይ ተደርሷል። አብሮ መብላት፣ መጠጣት፣ መሳቅ፣ ማውካካቱ፣ መጨፈሩም ብቻ ሳይሆን መቀባበሩም ቀረ። ኮሮና ቫይረስ ድፍን የሰውን ልጅ መውጪያና መግቢያ አሳጥቶ አንገቱን አስደፋው።
አብሮነት፣ ማሕበራዊ ቁርኝትና ትስስርን በጣጥሶ ሰውም ከሰው እንዳይገናኝ አፈራርቶ አላደራርስ ብሎ መላና መፍትሄ አሳጥቶ በፍርሀት የሚያርድ ከየት መጣ ሳይሉት የሚደርስ ቀሳፊና ገዳይ ወረርሽኝ በሽታ ሆኖ ቀጥሏል። ለካስ አባቶች ‹ቀባሪ አታሳጣኝ› ይሉ የነበረው እውነት መሆኑን ያረጋገጥንበት ጊዜ ላይ ደረስን።
ለዚህ ተላላፊ በሽታ ለጊዜው የተገኘው ማስታገሻ መራራቅ እንዲሁም ርቀትን ጠብቆ መሄድ ብቻ ነው። የሞት ነጋዴውን ኮቪድ 19 ምንነትና መነሻ ገና በቅጡ አጥንቶ ሳይደርስበት ከእንቅልፉ ያልነቃውን የሳይንሱን አለም ቀድሞት ተገኘ። ‹‹ኃያላን›› የሚባሉትን ውዝግብ ውስጥ ከቶ እርስ በእርሱ አንዱን ከአንዱ ጋር እንዳይግባባ እያደረገ ይገኛል። የፈጣሪ ቁጣም ይሁን ሰው ሰራሽና ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ እሱን ጊዜ ይፈተዋል። አውሮፓውያን ዛሬም ከጅምላ ሞትና መቃብር አልወጡም። ኮቪድ ብሔራዊ ኢኮኖሚያቸውንና ዜጎቻቸውን ሰቅጣጭ በሆነ ሁኔታ ቆርጥሞ እየበላው ይገኛል። ማስታገሻም ሆነ መላወሻ አልተገኘለትም።
በሀገራችን በጤና ሚኒስቴር በተረጋገጠው መሰረት በቫይረሱ የተያዙት ዜጎች ቁጥር ከ100 በላይ አሻቅቧል። እስከዛሬ 3 ወገኖቻችን ሕይወታቸው አልፏል። ከበሽታው ያገገሙም አሉ። በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ከ100 በላይ በእንግሊዝና በኢጣሊያ ነዋሪ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም ህይወታቸው አልፏል። ለእኛ ዜጎች ብቻም ሳይሆን የሁሉም የሰው ልጅ ሞት በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያስለቅሳልም። ልብን ይሰብራል። ሙሉ ቤተሰብ መንደር
ያለቀበትን ክስተት እያየን እየሰማን ነው። ይሄ ሁሉ ትምህርት ሊሆነን ይገባል። የኢትዮጵያ መንግስት ይሄንን በሽታ ቀድሞ ለመከላከል የወሰዳቸው እርምጃዎች በእጅጉ የሚደነቁ ናቸው።
የጤና ሚኒስትሯ፣ እለታዊ መግለጫ አስተምህሮ ያለውና ጥንቃቄ ማድረግን የሚያበረታታ ግልጽነትና ተደራሽነትን ለሕዝብ ያሳየ ነው። አይደለም የእኛ የሚውተረተረው ታዳጊ ኢኮኖሚ ቀርቶ በብልጽግና ማማ ጫፍ ላይ ነን ያሉትም ታላላቅ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው ተሸመድምዷል። በአጠቃላይ አለም በኮሮና ወረርሽኝ ጥቃት መንስኤነት ስምንት ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ውስጥ ወድቃለች። ስራዎች፣ ንግዶች፣ ግብይቶች፣ መዝናኛዎች፣ የአየርና የምድር ግንኙነቶች በሙሉ ተዘግተዋል፤ ተቆልፈዋል። ማንም ከማንም አይገናኝም። ይሄ ሁሉ ሆኖ ባለበት ሁኔታ እኛ ዘንድ የሚታየው መዘናጋትና ግድ የለሽነት ‹‹ምንም አይመጣብንም›› የሚል የቸልተኝነት ቀረርቶና ትከሻ ማሳበጥ ነገ ምን ይዞብን ሊመጣ እንደሚችል ሲታሰብ እሪ! ኡኡ! ያሰኛል።
መንግስትም ሆነ የጤና ባለሙያዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች ለማሳወቅና ለማስተማር ያደረጉትን ልፋትና ድካም ሁሉ መና የሚያስቀር ቸልተኝነትና ግዴለሽነት ‹ምንም አይነካንም፤ አይመጣብንም› በሚል ዋጋ እያሳጣው ነው። ነገ ምን ሊመጣ ይችላል ብሎ አለማሰብና አለመጠንቀቅ የሚያስከፍለው ዋጋ በቀላሉ አይሰላም።
‹ተያይዘን እንለቅ፤ እንጥፋ፤ ወደ መቃብር እንውረድ› የሚል መጠፋፋትን ማእከል ያደረገ ትእይንት ነው በየአደባባዩና በየቦታው እየታየ ያለው። እንዲህ አይነቱን የዘመንና የጊዜ ክፉ አደብ ይዞ ተሰብስቦ በየቤቱ ተከትቶ ማሳለፍ አለመቻል የከፋ ዋጋን ያስከፍላል። ‹ከእኛም በላይ ላሳር› ይሉ የነበሩትን እንዴት እንዴት አድርጎ አምዘግዝጎ ስርቻ ጥሎ ደም እንባ እንዳስለቀሳቸው አለም በገሀድ እያየች ነው።
በኮረና ቫይረስ ፊት ኃያል ሀገር ኃያል መንግስት የለም። እንዲያውም በእነሱ ላይ ነው የከፋ የጥፋት በትሩን የሰነዘረው። ለወትሮው ‹አንድ ዜጋዬ ተገድሏል› ብላ ወይንም በጠላትነት የፈረጀችውን ሀገር ያለምንም ሰብአዊ ርህራሄ በበጀትና በሚሳኤል የምታደባየው ኃያሏ ሀገር ዛሬ ቀኑ ጨልሞባት መዘባበቻ ሆናለች። ሁሉም አቀርቅረው እያነቡ ነው። ‹ሰውረነ ከመአቱ አድነነ በምህረቱ› የሚባለው ይሄኔ ነው። ሌሎቹም እንደዚሁ። ኃያል ሁሉን አድራጊና ፈጣሪ አንድ አምላክ በመሆኑ እነሱም እሱኑ እየተማጸኑ ነው። አውሮፓውያን እነሱ ዘንድ የወረደው መአትና መልአከ ሞት ቀጥሎ የሚመታው አፍሪካን ነው እያሉ ነው። ለጊዜው ሟርታቸው ይቆየን።
እኛ ግን እየተነገረን የማንሰማ፤ የሚወርደውን መአት እያየን የማንማር፤ ጭርሱንም እኛ ዘንድ ምንም አይመጣም እስካአሁን የሞተው ሶስት ሰው ብቻ ነው ብለን እራሳችንን የምንደልል፤ ከፊታችን ጥርሱን አግጥጦና አይኑን አፍጥጦ የመጣውን የማይመለስ ጠላት ‹የለም› እያልን ወደአዘቅትና ጥልቅ ገደል እየተምዘገዘግን ነው።
መንግስት የዜጎቹን ሕይወት ከሞትና ከጥፋት ለመታደግ ረዥም ርቀት ሄዶ ታላቅ ስራ ሰርቷል። እየሰራም ነው። ሊመሰገን ይገባል። የጎደለውና የሚያስፈራው ዜጎች የሚሰጣቸውን ትምህርትና የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ አለመቻላቸው ነው። ተዉ ሲባል የሚብስብን፤ አትሰብሰቡ ሲባል አደባባዩን አስጨንቅን እየተጋፋን መተራመስ የምንወድ፤ ስንመከር የሚብስብን፤ ተራራቁ ሲባል የምንተዛዘል፤ ዓመት በአል እያልን የምንንጋጋ ጉዶች ነን።
እንግዲህ እድር፣ ልደት፣ ለቅሶ፣ ቀብር፣ አርባ፣ ሰማንያ፣ ሰርግ፣ ማህበር፣ ጽዋ መጠጣት ወዘተ ለጊዜው ይቅር አስከፊው ገዳይ በሽታ እስኪያልፍ ይዞን እንደ ድንገተኛ አስገምጋሚ ደራሽ ውሀ እንዳይወስደን ተጠንቅቀን ተጠባብቀን ይሄን ክፉ ቀን እንለፈው ቢባል ከሚሰማው ጥቂት ሰው የማይሰማው ብዙሃኑ በልጦ በመገኘቱ እያውካካ ይገኛል። ከመደብደብ አደብ ይበጅ ነበር።
የሚያሳዝነው ሁሉንም አነካክቶ የሚያጠፋ አይምሬ በሽታ መሆኑ ነው። ሀገር ካለ ሕዝብ፣ ካለ ልጆቿ አትደምቅም፤ ጎጆና ትዳርም ካለሰው አይሞቅም። ባለሀብት፣ ባለገንዘብ፣ ባለአጀብ፣ ባለፎቅ ቢሆኑ ምንም የሌለው ምስኪን ድሀ ቢሆን፤ በእውቀት ማማ መጥቄአለሁ፤ የተማርኩ የተመራመርኩ ነኝ ቢል፤ ኮሮና ቫይረስ እንደሁ አይምሬ አያዳሌም ነው። ስንትና ስንት ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ምሁራን እንዲሁም መሪዎችን እየጠለፈና እያንደፋደፈ በሞት ነጥቆ እንደወሰዳቸው እያየን ጥንቃቄ ከማድረግ መዘናጋት እጅግ አደገኛ ነው።
መንግስት ቢከለክልም ጭፈራና መጠጥ ቤቱ፣ ዝሙቱ፣ ድሪያው፣ ማጅራት መምታቱ፣ ዝርፊያው፣ ሕገወጥ ስራው በሕቡእ ተስፋፍተው ቀጥለዋል። ይሄንን ገዳይ ወረርሽን በተለመደው ሸቃይና ቸርቻሪ እሳቤያቸው የደለበ ገቢ ማስገኛ አድርገው በአደባባይና በስውር እየነገዱ ያሉትንም ከርሳሞች እያየን ነው። ምንም እንኳ ጥቂት ደጋጎች እያደረጉ ያለውን መልካም ተግባር እያየን ቢሆንም፤ በሀገር ጭንቀትና ምጥ፣ በወገን ስቃይና መከራ ነግጄ አተርፋለሁ፤ ሀብት አካብታለሁ የሚሉ አውሬዎች የበዙባትም ሀገር እንደሆነች እያስተዋልን ነው።
ያለቀው ይለቅ ምን አገባን ለማለት መጀመሪያ ይህን ባዮቹም በሽታው ከተዛመተ እነሱም ለመኖራቸው ምንም ዋስትና እንደማይኖራቸው ሊረዱ ይገባል። የሚሻለው እንደ አባቶቻችንና እናቶቻችን እኔንም ጎረቤቴንም ሰላም
አውለን ሰላም አሳድረን ማለቱ ነበረ። መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ አለማድረግ በእጅጉ አሳዛኝ ነው። በእምነት አባቶች የሚደረገው ጸሎትና ልመና አሁንም ትልቅ ትርጉም አለው። እኛን አይነካንም የሚለው ድንቁርና የትም እልፍ አያደርገንም። የትኛው ንጽህናችንና ለአምላክ የቀረብን፣ የተንበረከክን፣ የተገዛን ሆነን ነው ከጥፋት የሚያድነን? በዘርና በቋንቋ የምንባላ፤ ስንት ዘመን ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረውን ቤተሰብ ውጣና ሂድ የምንል፤ ንጹህ ሰርቶ አዳሪ ድሀ ወጣት በአደባባይ ዘቅዝቀን የምንሰቅል፤ በቆንጨራ የሰው አንገት የምንበጥስ፤ በጦር እንደ አውሬ ሰው ወግተን የምንገድል፤ የሰው ንብረትና ሀብት፣ ትዳር ጭምር የምንዘርፍ የምንነጥቅ በግፍ የምንገድል፤ ቤተክርስቲያንና መስጂድ የምናቃጥል፤ በእብሪትና በዘረኝነት በሸታ የተጠመድንና የተለከፍን፤ ሕሊናችን በክፋትና በምቀኝነት እንዲሁም በተንኮልና በሴራ በሸፍጥም ጭምር የታወረ፤ ወንድሙን ወንድሙ ለገንዘብ ብሎ የሚገድልባት ሀገር ላይ ሆነን እንዴት ነው የእግዚአብሄር ሀገር ናት የምንለው፤ አጀብ ያሰኛል። ሀገሪቱ ምንም አላደረገች። የከፋው ሰው ነው።
ጥንት ደጋጎች፣ ቅኖችና የዋሆች ለአምላክ የቀረቡ ሰዎች ነበሩባት። ዛሬ ግን እነዛን የመሰሉ ሰዎች እፍኝ አይሞሉም። ለዚህ ነው አጉል መመጻደቅ የሌለብን። ድሮ ድሮ አዎ ንጹኀን ሞልተው ተርፈው ነበር። እነሱን ሊሰማ ይችላል። ዛሬም ጥቂት ቢሆኑም አሉ። የእነሱን ልመና ፈጣሪ ይስማ። ምህረትም ያውርድ። የአለም ሕዝብም ሆነ የእኛ በዚህ ክፉ በሽታ ምክንያት በስጋትና በጭንቀት ተወጥሮ ባለበት ሰዓት ስለፖለቲካ የሚዶልቱ፣ ስለምርጫ የሚያወሩ አውሬዎችን ማየት ምንኛ ሰብአዊነት የጎደላቸው ጨካኝ ፍጡሮች መሆናቸውን እያረጋገጡልን ነው። መጀመሪያ እስቲ እንኑር። የሕዝብ ጤናና ሰላም ይቅደም። ሌላው ይደረስበታል።
ለሕዝብና ለሀገር ሰላም ጤናና ደህንነት ነው በቅድሚያ መጨነቅ ያለባቸው? ወይንስ ገና ለገና እንይዛለን ብለው ለሚያስቡት የፖለቲካ ስልጣን ነው እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩት? አረ ነውር ነው ጎበዝ። ከሰብአዊነት የተፋቱ መሆናቸውን በአደባባይ ስላስመሰከሩ ሕዝብ በዚህ የክፉ ቀን መዝገብ ውስጥ አስፍሯቸዋል። ኋላ ላይ ማየት ነው። በተለያዩ የአለም ማእዘናት እንደ ቅጠል እየረገፉ ያሉት የሰው ልጆች ሁሉ ነገን እያለሙ ዛሬ በድንገት የቀሩ ናቸው። ለሁሉም መዘናጋቱን ትቶ መጠንቀቁ፤ ሕግና ስርአትን ማክበሩ፤ መመሪያና ደንቦችን መጠበቁ ለጋራ ሰላም ደሕንነትና ሕልውና መሰረት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። መዘናጋቱ ያብቃ!!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2012