የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም ዓለምን ማስጨነቁን ቀጥሏል። አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ከቀን ወደ ቀን ቁጥሩ እያሻቀበ ይገኛል።
ለቫይረሱ ክትባትም ሆነ መድሃኒት ለማግኘት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ የተመሰከረለት መድሃኒትም ሆነ ክትባት አልተገኘም። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በኮሮና የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ሲሆን በሞት የተለዩት ደግሞ ከ197 ሺህ በላይ ናቸው።
በዚህ ሰዓት የወረርሽኙ ስርጭት እየተስፋፋ ያለው በአፍሪካ ውስጥ መሆኑ ደግሞ ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
በአፍሪካም ከ27 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ ሰዎችን ደግሞ በሞት ተለይተዋል። ወረርሽኙ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ ሀገሮች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እጅግ ከባድ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም ላይ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ አስቀድሞ የጥንቃቄ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ህዝቡም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ጥንቃቄም እንዲያደርግ የጤና ባለሙያዎች ሲወተውቱ ከርመዋል።
ቫይረሱ ወደ ሀገር ቤት መግባቱን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወሳኝ ናቸው የተባሉ እርምጃዎችም ተወስዷል።
የትምህርት ቤቶችና የዩኒቨርሲቲዎች መዘጋት፣ የመንግስት ሰራተኞች የዓመት እረፍት እንዲወጡ ሌሎች ደግሞ በቤታቸው ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ መደረግ፣ የትራንስፖርት ስምሪትንና የተሳፋሪ ቁጥርን መቀነስ እንዲሁም ሌሎችም በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የጤና ሚኒስቴር በየዕለቱ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተያዙ ፣ ያገገሙ እና መሰል ሪፖርቶችን በማሳወቅ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን መረጃ እንዲያገኝ እና ለራሱም ጥንቃቄ በማድረግ በመከላከሉ ስራ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን አድርጓል።
ታዋቂ ሰዎች ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ፣ ባለስልጣናት ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ሁሉ አስቀድሞ ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች በማስተማር ላይ ናቸው። መጨባበጥ ይቁም፣ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ ፣ በጣም ወሳኝ ላልሆኑ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ከቤት አንውጣ፣ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ አትገኙ በሚሉት ላይ አተኩረው ሰርተዋል።
ይሄን ማንኛውም ሰው ሊተገብረው የሚችል ፤ በጣም ቀላልና ከቅንነት ውጪ ብዙም ወጪን የማይጠይቅ ሥራ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ በሚጠበቀው ልክ በዜጎች እየተተገበሩ አይደሉም።
አካላዊ መራራቅ እስከአሁንም ለውጥ አልታየበትም። በገበያ ስፍራዎች ፣ በትራንስፖርት መጠበቂያ፣ በጎዳና ላይ ንግድ አሁንም የሰዎች እንቅስቃሴና መገፋፋት ቀጥሏል። በተለይ ሜክሲኮ፣ መርካቶ፣ መገናኛ፣አውቶብስ ተራ … በመሳሰሉት አካባቢዎች ከፍተኛ የሰው ቁጥር የሚታይባቸው ናቸው።
ይሄ የሚያሳየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ሆነ ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶች እና መመሪያዎች በአግባቡ እየተተገበሩ አለመሆናቸውን ነው። ይህም መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል እሙን ነው።
ከዓለም ተሞክሮ መረዳት የሚቻለው ቫይረሱ ጉዳት አያደርስም ብለው የተዘናጉ ሀገሮች ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል። ወደ አፋጣኝ እርምጃ የገቡ መንግስታትና የመንግስታቸውን መመሪያ አክብረውና አድምጠው ወደ ተግባር የገቡ ሀገሮችና ዜጎች ደግሞ በአጭሩ ለመቆጣጠር ችለዋል። ኢትዮጵያም ከዚህ ብዙ መማር አለባት። ህዝብ የመንግስትን መመሪያ የሚተገብረው ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለሀገሩ መሆኑን መገንዘብ ይጠበቅበታል።
በሀገራችን ባለፉት ተከታታይ ሁለት ቀናት በተካሄዱት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በቫይረሱ ተይዞ የተገኘው አንድ ሰው ነው። ይሄ መሆኑ ግን ሊያዘናጋና በሽታው እየጠፋ ነው ወደሚለው መደምደሚያ የሚያደርስ አይደለም።
ከዚህ ይልቅ በአንዳንድ የጎረቤት ሀገሮች በተለይም የቅርብ ግንኙነት ባለን እንደ ጅቡቲ እና ኬንያ ባሉ ሀገራት የሚታየው የኮሮና መስፋፋት ለሀገራችንም ትልቅ ስጋት መሆኑን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማጠናከር ብልህነት ነው።
ይህንን ስጋት ማቆም የሚቻለውም ከመንግስት እና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ትዕዛዛትን በትክክል መተግበር ሲቻል ብቻ ነው። ይሄ ካልሆነ ግን ሀገርና ህዝብን የሚያስከፍለው ዋጋ የከፋ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2012