ባህል የሰው ልጅ የህይወት መንገድና የአንድ ሰው የመኖሪያ መርህ በመሆን ያገለግላል። ባህል ከአለባበስ፣ ከአመጋገብ፣ ከአኗኗር ዘይቤ፣ ማህበራዊ ህይወት፣ አምልኮ ሥርዓት፣ የሥራ ባህሪ እና የመሳሰሉት ጋር ይያያዛል።
ሃይማኖት የባህል አንዱ አካል ሲሆን ሰፊና ጠንካራ መሠረት አለው። ሃይማኖት አምልኳዊ ሥርዓት መፈፀሚያ ተቋማዊ መሠረት ያለው ማህበር ነው። ሃይማኖት ከነባር እስከ ዘመናዊ አደረጃጀት ያላቸው የአምልኮ ማህበራትን ያካትታል። ጥንታዊና ተቋማዊ መሠረት የሌላቸው የአምልኮ ሥርዓቶች ባላቸው የአመላለከት ባህሪና ተቀባይነት ከሃይማኖት ተርታ ይመደባሉ፡፡
ባህልና ሃይማኖት ጥንታዊ መሠረት አላቸው። ከህዝብ ህይወት ጋር ባላቸው ትስስር የህይወት አንዱና ዋነኛ ከሚባሉት አካላት ተርታ ይመደባሉ። በፈጠሩት የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ ብዙ ሰዎች ለባህልና ለሃይማኖት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ፡፡
ባህልና ሃይማኖት በህዝብ ላይ የተለያየ የእሴት፣ የእምነት፣ የወግና የአመለካከት ዓይነቶችን ቀርፀዋል። በዚህም የብዙ ሰዎች አኗኗር ከባህልና ከሃይማኖት የተቀዳ ሆኗል።
በ21ኛው ክፍለ-ዘመን የሀገር ለሀገር እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በግሎባላይዜሽን (አለማቀፋዊነት) በመጠናከሩ የባህልና የሃይማኖት ልውውጦሹ ከፍተኛ ሆኗል። የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ቱሪዝም እና የንግድ ሥራዎች መበራከት በፈጠሩት ተጽዕኖ በነባር ባህሪው ያለ ባህል ወይም ሃይማኖት ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡
አንድ ባህል ከሌላ ባህል ጋር ሲገናኝ የባህል ልውውጥ ይፈጠራል። አንደኛው ባህል ከሌላኛው ባህል የሚሰጠውና የሚቀበለው ነገር ይኖራል። ይህም ተፈጥሯዊ ወይም ነባር ባህሪውን የጠበቀ ባህል እንዳይኖር ያደርጋል።
ልውውጥ ያላደረገ ባህል ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በአማዞን ደን ከሚኖሩ ጎሳዎች እና አንዳንድ ከቀሪው ህዝበ ጋር ንክኪ ያልፈጠሩ ማህበረሰቦች ሲቀሩ ብዙ ማህበረሰቦች በተፈጥሯዊ ባህሪው ያለ ባህል አይኖራቸውም። በዝግመታዊ ለውጥ ደግሞ ብዙ ባህሎች ከነባር ባህሪያቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ይለወጣሉ። ለዚህም ባህልና ሃይማኖት ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ እና ይሞታሉ የሚባለው፡፡
ባህልና ሃይማኖት ለብዙ ነገሮች አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች እንዳላቸው የተለያዩ ጽሁፎች ይተነትናሉ። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ከሀገር ዕድገት ጋር ይነሳል። አንዳንድ ባህሎች ለዕድገት አዎንታዊ ጎኖች አሏቸው። ጠንካራ የሥራ ባህልን የሚያበረታቱ ባህሎች ለዕድገት ጠቃሚ ናቸው። የሀገር ዕድገት ላይ መሰናክል የማይሆኑና ሳይንሳዊ አሠራሮችን የሚያበረታቱ ባህሎች አወንታዊነታቸው የላቀ ነው፡፡
በሌላ መልኩ ባህልና ሃይማኖት ለሀገር ዕድገት መሠናክል በመሆን ደንቃራ የሚሆኑበትም ጎን አለ። ደካማ የሥራ ባህልንና ተመፅዋችነትን የሚያበረታቱ ባህሎች ለሀገር ዕድገት ዕንቅፋት ናቸው። የሰው ልጅ ኑሮውን ለማሸነፍ እንዳይታትር ህሊናውን በመቆጣጠር ስንፍናንና ተመፅዋችነትን/ልመናን የሚያበረታቱ ባህሎች አሉ። ከሰማይ እህል እንደ መና ይወርዳል ብለው የሚያስተምሩም አሉ። የሰው ልጅ ከረሃብ፣ ድህነት፣ አለመማርና አለመመራመር ችግሮች ለመውጣት ከሚያደርገው ጠንካራ ትግል ወደኋላ የሚያስቀሩ ባህሎች አሉታዊነታቸው የከፋ ነው፡፡
ምዕራብ አውሮፓዊያን የ16ኛው ክፍለ-ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ሲነሳ ባህልና ፈጣን የህዝብ ዕድገት መሠናክል መሆናቸውን ተረድተው ነበር። የማህበራዊ ዕድገትና የባህል ነቂሳዊ ለውጥ ለማምጣት አላስፈላጊ የሆኑ ባህሎች መቅረት እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር። የኢንዱስትሪ አብዮቱ እየጠነከረ ሲመጣ ለዕድገት ደንቃራ የሆኑ ጎጂ ባህሎችን በማስወገድ ዛሬ ላይ ዘርፈ-ብዙ ዕድገት ማምጣት ችለዋል።
በአንፃሩ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን የምሥራቅ ኢሲያዊያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ባህልን በሰፊው ሳይነካ የመጣ ነው። ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ ነው። ማለትም ባህል ከዕድገት ጋር እንዲቻቻል ማድረግ ችለዋል። በዚህም በኢኮኖሚ አድገው ነገር ግን ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን መጠብቅ ችለዋል። እሴት ያለው ያደገ ማህበረሰብ መፍጠር ችለዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወዲህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸው በመጨመሩ ባህልና ሃይማኖት ተከታይነታቸውን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡
ለምሳሌ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በፊት የነበረው የጥቂቶች የመሬት ከበርቴነት ባህል ጥቂት ሥራ የማይሠሩ እና ብዙ ሥራ የሚሠሩ ነገር ግን ድህነት የተፈረደባቸው ዜጎችን አፍርቷል። ይህም ከመሥራት ይልቅ ከበርቴ መሆን ሀብታም ለመሆን እንደሚረዳ የተሳሳተ አተያይ ይፈጥራል፡፡
እንደ አሜሪካዊው ፔው የጥናት ማዕከል በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ98 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው ዜጋ የሃይማኖት ተከታይ ነው። ከዚህም እስልምናና ክርስትና ይህን አብዛኛውን ድርሻ ይይዛሉ። በዚህ ምክንያትም አብዛኛው ለሀገራችን ህዝብ ሃይማኖት ሰፊ መሠረት አለው።
በሀገራችን ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ባህሎች አሉ። እነዚህ ባህሎች ልክ እንደ ሃይማኖት ከማህበረሰብ ሕይወት ጋር ጠንካራ ትስስር አላቸው። ይሁን እንጂ ከከተማማ አካባቢዎች ይልቅ በገጠራማ አካባቢዎች ባህሎች ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው፡፡
በገጠራማ አካባቢዎች የማህበረሰባዊ ብዝሃነት የለም። የማህበረሰባዊ ወጥነት ስላለ ወጥ የሆነ ማህበረሰብ (Homogeneous Society) ተፈጥሯል። ይህ ሁናቴ የባህል ብዝሃነት እንዳይኖር አድርጓል።
በከተማማ አካባቢዎች የማህበረሰባዊ ብዝሃነት በሰፊው አለ። በዚህም ወጥ ያልሆነ ማህበረሰብ (Heterogeneous Society) ተፈጥሯል። የተለያዩ ማህበረሰቦች በአንድ አካባቢ ሲኖሩ ከመጡበት ማህበረሰብ ያለውን ማህበራዊ ማንነት ይዘው ስለሚመጡ የባህል ብዝሃነት እንዲኖር ያደርጋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ በከተማማ አካባቢዎች የባህልና ሃይማኖት ቅቡልነት ከገጠራማ አካባቢዎች ሲታይ አነስተኛ ነው። በዚህ ምክንያትም ለዕድገት ጎጂ ባህላዊ አሠራሮች የሚመሩ ሰዎች አነስተኛ መሆን የባህል ተፅዕኖ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጋል። በገጠራማ አካባቢዎች ግን ለዕድገት ጎጂም የሆኑ ባህላዊ አሠራሮች ቅቡልነት ሰፊ በመሆኑ የባህል ተፅዕኖ ከፍተኛ ይሆናል።
በሀገራችን ያሉ ባህሎች በሰፊው አልተጠኑም። የተጠኑትም በተለይ ከጤናና ከሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ጋር ይገናኛሉ። በዚህም ምክንያትም ጎጂ ወይም ጠቃሚ ባህሎች ተብለው መለየት አልተቻለም። መለየት ቢቻል ኖሮ ይሄ ባህል ጎጂ እና መቅረት ያለበት ያኛው ደግሞ ጠቃሚና መቀጠል ያለበት ማለት ይቻል ነበር። ይህን ችግር ለመቅረፍም በሀገራችን የሚገኙ ባህሎችን በጥልቀት በማጥናትና በመርመር ለዕድገት ጠቃሚና ጎጂ የሆኑትን በመለየት ጠቃሚዎችን አሻሽሎ ማስቀጠልና ጎጂዎችን ማስቀረት ያስፈልጋል። አበቃሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 / 2012
በላይ አበራ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ