የኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም መከሰቱን ተከትሎ ስለበሽታው ምንነትና የመተላለፊያ መንገዶች ብዙ ተብሏል። የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በየ አገራቱ ያሉ የጤና ተቋማት፣ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች መላው ዓለም ስለበሽታው የተሻለ ግንዛቤ ኖሮት የበሽታው ወረርሽኝ የከፋ አደጋ ሳያደርስ መቆጣጠር እንዲቻል በስፋት ሠርተዋል፤ እየሰሩም ነው። ሁኔታው ግን ስለበሽታው በተለያየ መልኩ በተፈጠሩ መዘናጋቶች ምክንያት እንደታሰበው የከፋ አደጋ ሳያደርስ መቆጣጠር አልተቻለም። ዛሬም ከወራቶች በኋላ በሽታው ዓለምን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
በኛም ሀገር ቫይረሱ ከመግባቱ በፊት ሆነ ከገባም በኋላ በሽታው ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን መቆጣጠር እንድንችል ሊደረጉ ስለሚገባቸው ስለሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች በጤና ባለሙያዎችና በመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጭምር በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እነዚህ ጥረቶች ለውጥ ያመጡ ቢሆንም ከቫይረሱ የሥርጭት ፍጥነትና ከአደገኛነቱ አንፃር እየተወሰዱ ያሉት የጥንቃቄ እርምጃዎች በቂ ባለመሆናቸው መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዷል፡፡
ኮሮና ቫይረስን መከላከል የሚቻለው በተቻለ መጠን እንቅስቃሴን በመገደብ፣ ሰዎች የሚበዙባቸው ሥፍራዎች ባለመገኘት፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና በመታጠብ ወይም በፀረ ተዋህስያን በማጽዳት እንደሆነ በሚመለከታቸው የጤና አካላት እየተነገረ ቢሆንም አሁንም ያልታረሙ ተግባራት ከዚህም ከዚያም ይስተዋላሉ፡፡
የትራንስፖርት ሰልፍ ተጠጋግቶ መጠበቅ፤ በየገበያ ቦታው ተጨናንቆ መገበያየት፤ አሳቻ ሰዓትን እየጠበቁ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ መጠጥ ቤቶች መገኘት፣ በጫት መቃሚያዎችና በሺሻ ማጨሻዎች መታደምና በየመንደሩ መሰባሰብ አሁንም ያልተቀረፉ አሳሳቢ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከሉ ገደቦች ሲሆኑ እነዚህንና መሰል ጥፋቶችን ተላልፎ መገኘት በሕግ የሚያስጠይቅ ነው፡፡
ሆኖም ግን እነዚህ የሕግ መተላለፎች በየቀኑ እየተጣሱ መሆኑን እየተመለከትን ኃላፊነቱን ለመንግሥት ብቻ የምንተው ዜጎች ቀላል አይደለንም፡፡ መንግሥት ይህን እያየ እንዴት ዝም ይላል፤ አጥፊዎችን ለምን አይቀጣም፤ መንግሥት ሕግ ማስከበር ተስኖታል፤ ወዘተ የሚሉ የሕግ ማስከበር ትግባራትን ለመንግሥት ብቻ የምንወረውርና መንግሥት በሁሉም ቦታና በየስርቻው ተገኝቶ ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ የምናቀርብ ሰዎች በዝተናል፡፡ ሆኖም በየትኛውም አገር ቢሆን መንግሥት በሁሉም ቦታና ጊዜ የሚገኝ መንፈሳዊ አካል ባለመሆኑ ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆሩ ዜጎች የመንግሥትን ኃላፊነት በመካፈል አጥፊዎችን ማጋለጥና ለፍትህ አካላት የማሳወቅ ተግባራት ሲያከናውኑ ይታያሉ፡፡ በሰለጠኑት አገራት በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ በሚታወጅበት ወቅት ከመንግሥት ባልተናነሰ ዜጎች የራሳቸውን፤ የወገናቸውንና የአገራቸውን ሰላም ያስጠብቃሉ፤ ኮሮናን ከመሳሰሉ ወረርሽኞችም ይታደጋሉ፡፡
ይህ በእኛ ሀገር ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ አይቶ እንዳላየ መሆን የተለመደ ተግባራችን ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት አንዳችን ለአንዳችን ካላሰብን፤ አንዳችን ለአንዳችን ዘብ ካልቆምን የምንከፍለው ዋጋ መጠን የለሽ ይሆናል፡፡
የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመግታት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመንግሥት ብቻ ከተውነው አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ ተጠጋግቶ የትራንስፖርት ሰልፍ የሚጠብቁ ሰዎች ሲያጋጥሙ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ፤ ከተፈቀደው በላይ የሚጭኑ ታክሲዎችና አውቶቢሶች ሲያጋጥሙ ድርጊቱን መቃወም፤ ሰዎች ከአራት በላይ ሆነው ሲሰበሰቡ እንዲበቱን መምከርና በገበያ ቦታዎች ላይ ተሰባስበው ሲገባያዩ አግባብ አለመሆኑን መንገር ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
ይህ ሲሆን ሁላችንም ከቫይረሱ በቀላሉ እንድንጠበቅ ከማድረጉም ባሻገር አንዳችን የአንዳችን ጠባቂና አስተዋሽ መሆን እንችላለን፡፡ መንግሥትም የከፉ በሚባሉ የሕግ ጥሰቶች ላይ እንዲያተኩርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዋነኛ ዓላማ ለማሳካት አቅምና ጉልበት እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 / 2012