ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ተነስቶ ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራትን ያዳረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት የምድራችን ዋነኛ የጤና ስ ጋት ሆኗል።
ኮቪድ-19 በመባል የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ሲሆን፤ መጀመሪያ ትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል።
እስካሁን በቫይረሱ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ170 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል ክትባትም ሆነ መድኃኒት አልተገኘም።
የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ምንድናቸው?
የኮሮናቫይረስ ሁለት ዋነኛ ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳትና ደረቅ ሳል ናቸው። በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ እነዚህ ምልክቶች ወደ ትንፋሽ ማጠር ይወስዳሉ። ደረቅ ሳል ሲባል በጣም ጠንካራ የሆነ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ ነው። ከዚህ በፊት ደረቅ ሳል ካለብዎ የኮሮናቫይረስ ሳል በጣም ለየት ያለና ከባድ መሆኑን ማስተዋል ይችላሉ።
ከፍተኛ ትኩሳት የሚባለው ደግሞ የሰውነት ሙቀት መጠን ከ37.8 ዲግሪ ሴልሺየስ ሲልቅ ነው። ይህ ትኩሳት ሰውነት እንዲግል ወይም ደግሞ ከፍተኛ ብርድና መንቀጥቀጥ እንዲሰማን ያደርጋል።
ከእነዚህ ሁለቱ ዋነኛ ስሜቶች ባለፈ ራስ ምታትና ተቅማጥ አንዳንድ የበሽታው ታማሚዎች የሚያሳይዋቸው ምልክቶች ናቸው። የማሽተትና የመቅመስ አቅም ማጣትም ምልክቶች ሆነው ተመዝግበዋል።
ምልክቶቹ ቫይረሱ ሰውነት ውስጥ በገባ በአምስት ቀናት ሊታዩ ይችላሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ ምልክቶቹ እስከ 14 ቀናት ድረስ ሳይታዩ ሊቆዩ እንደሚችሉ ያስረዳል።
መቼ ነው ወደ ሆስፒታል መሄድ ያለብን?
በርካታ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች በቂ እረፍትና እንደ ፓራሲታሞል ያለ ሕመም ማስታገሻዎች ከወሰዱ ያገግማሉ። ሰዎች ወደ ሕክምና ጣቢያ መሄድ ያለባቸው የአተነፋፈስ ችግር ካጋጠማቸው ነው። ዶክተሮች የታማሚን ሳንባ ከመረመሩ በኋላ አስፈላጊውን ሕክምና ያዛሉ። አስፈላጊ ከሆነ ኦክስጂንና ቬንቲሌሽን ሊታዘዝ ይችላል።
ነገር ግን ሰዎች በሽታው ይዞኛል ብለው ከጠረጠሩ አስቀድመው ወደ ነፃ የእርዳታ መስጫ ቁጥሮች ቢደውሉ ይመከራል። የኢትዮጵያ ነፃ መስመር 8335 ወይም 952 ነው።
የመተንፈስ ችግር ካለብዎ በተለይ ደግሞ ጥቂት ቃላትን ማውጣት ካልቻሉ ደውለው ሐኪም ቢያማክሩ ይመረጣል።
በአሜሪካ፣ በቻይና እና በአውሮፓ አገራትም አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ የተደረገውም ቁጥሩ በመጨመሩ መሆኑንም ያስረዳሉ። ሆኖም ግን መተንፈስ የሚቸገሩ ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እንዲከታተሉ እንደሚደረግም አያይዘው ያነሳሉ።
“ቤታቸው ሆነው እንዲያገግሙ የሚጠበቁ ሰዎች ሌላ ጊዜ ጉንፋን ሲይዛቸው ለራሳቸው የሚያደርጉትን እንክብካቤ እንዲያደርጉ ይመከራል። ትኩሳት እና ሳል የሚያስታግስ ነገር በቤታችን ማድረግ እንችላለን” ይላሉ።
ሆኖም ቤት ውስጥ በእድሜ የገፉ ሰዎች ካሉ፤ በሽታው በነሱ ላይ ሊበረታ ስለሚችል፤ ከነሱ ጋር ንክኪ አለማድረግ ወይም መራቅ እንደሚያስፈልግ ዶክተሯ ይናገራሉ። ቤት ውስጥ ለታመመ ሰው እንክብካቤ የሚያደርጉ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ፤ ታማሚው/ዋ በአግባቡ እጅ መታጠብ ይጠበቅበታል (ይጠበቅባታል)። በተጨማሪም ህሙማን ለብቻቸው በአንድ ክፍል እንዲቆዩ ከሰዎች በሁለት ሜትር እንዲርቁም ይመክራሉ።
ፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ምን አለ?
አይሲዩ የሚል ሙያዊ ስያሜ የተሰጠው የፅኑ ሕሙማን ክፍል በጣም ለታመሙ ሰዎች የተዘጋጀ ሥፍራ ነው።
እዚህ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ለመተንፈስ እንዲረዳቸው ኦክሲጅን ይሰጣቸዋል። ቬንቲሌሽን የተሰኘው ቁስ የሚገጠመው በጣም ለታመሙ ሰዎች ብቻ ነው። መሣሪያው በርከት ያለ ኦክሲጅን ለታማሚው ያቀርባል።
መካከለኛ ምልክት ከታየብኝ ምን ላድርግ?
መካከለኛ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ይመከራሉ። በርካታ ሀገራት መለስ ያለ ምልክት ያሳዩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያገሉ ነው የሚያደርጉት እንጂ የሚሰጣቸው ለየት ያለ ሕክምና የለም። የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን ሰዎች ራሳቸውን እንዲያገሉ ነው የሚመክረው።
ሰዎች ቴርሞሜትር የተሰኘውን መሣሪያ በመጠቀም የሙቀት ልኬታቸውን ማወቅ ይችላሉ። የሰውነት ሙቀታቸው ከ37.8 በላይ የሆኑ ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ ይመከራሉ።
ኮሮና ቫይረስ ምን ያህል ገዳይ ነው?
ምንም እንኳ ይህ መረጃ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ባይሆንም ከኮሮና ቫይረስ የመሞት ዕድል በጣም ዝቅ ያለ ነው (በመቶኛ ሲሰላ ከ2 በመቶ አይበልጥም)።
የቫይረሱን ገዳይነት ዝቅ ያደረገው ምናልባትም ብዙ ታማሚዎች ባለመርመራቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የዓለም ጤና ድርጅት 56 ሺህ ሰዎች ላይ ምርመራ አካሂዶ፡-
• 6 በመቶ በጣም የታመሙ ሆነው ተገኝተዋል – ከሳንባ አለመሥራት እስከ ለሞት መጋለጥ
• 14 በመቶ ጠንከር ያለ ምልክት ታይቶባቸዋል – የመተንፈስ ችግርና ትንፋሽ ማጠር
• 80 በመቶ ደግሞ መካከለኛ የሚባል ምልክት አሳይተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በርካታ ሰዎች ባይመረመሩም በቫይረሱ ተይዘዋል ይላል።
ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህመም አልቀዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለቫይረሱ ተጋልጠው ይገኛሉ። እስካሁን ግን ከቫይረሱ እንደሚፈውስ የተረጋገጠለት መድኃኒት አልተገኘም።
ግን ግን ከኮቪድ-19 ጨርሶ የሚፈውስ መድኃኒት ለማግኘት ምን ያህል ተቃርበናል?
ከቫይረሱ የሚፈውስ መድኃኒት ለማግኘት ምን ተከናወነ?
በመላው ዓለም የሚገኙ ተመራማሪዎች ከ150 በላይ የሆኑ የተለያዩ መድኃኒቶች ላይ እየተመራመሩ ሙከራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ምርምር እና ሙከራ እየተደረገባቸው የሚገኙት አብዛኞቹ መድኃኒቶች በገበያ ላይ ያሉ ወይም ከዚህ ቀደም የሚታወቁ ናቸው።
• የዓለም ጤና ድርጅት ‘ሶሊዳሪቲ ትሪያል’ የተሰኘ ለኮቪድ-19 ፍቱን የመሆን ተስፋ ያለውን መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ይገኛል።
• ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ ከ5 ሺህ በላይ ታማሚዎች የሚሳተፉበት የዓለማችን በመጠኑ ሰፊ የሆነ የምርምር ሥራ እያከናወንኩ ነው ብላለች።
• በርካታ የምርምር ማዕከላት ደግሞ ከበሽታው የዳኑ ሰዎችን ደም በመጠቀም ኮቨድ-19ን ለማከም ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።
ከበሽታው ሊፈውሱ የሚችሉት መድኃኒቶች ምን አይነት ሊሆኑ ይችላሉ?
ከበሽታው ሊፈውሱ የሚችሉ መድኃኒቶችን ለማግኘት እየተደረገ ያለው ምርምር በሦስት ከፍሎ መመልከት ይቻላል። እነዚህም፤
- የመጀመሪያው ኮሮናቫይረስ ወደ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ የመቆየት አቅሙን የሚፈታተን ወይም በሰውነት ውስጥ መቆየት እንዳይችል የሚያስችል ጸረ- ተህዋሲ (አንቲቫይራል) መድኃኒት የማግኘት ምርምር አንዱ ነው።
- በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሰውነትን በሽታን የመከላከል ሥርዓት ለኮሮናቫይረስ የተመጠነ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ መድኃኒት ማግኘት ነው። ምክንያቱም የሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓት፤ አካላችን በበሽታ ሲጠቃ ከመጠን በላይ ምላሽ ሲሰጥ ታማሚው በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚታመም መድኃኒቱ ተዛማጅ ጉዳትን ለመቆጣጠር ይረዳል።
- ሦስተኛው ደግሞ በላብራቶሪ የተዘጋጀ ወይም ከኮሮናቫይረስ ካገገሙ ሰዎች ‘አንቲቦዲ’ በመጠቀም ለኮቪድ-19 መላ መፈለግ የሚለው ነው።
ኮቪድ-19ን ሊፈውስ ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መድሃኒት የቱ ነው?
የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ዶ/ር ብሩስ አለዋርድ ከቻይና ጉብኘታቸው በኋላ ኮሮናቫይረስን ያድናሉ ተብለው ከተሞከሩ መድኃኒቶች መካከል ውጤታማ ስለመሆኑ ምልክት ያሳየው ሬምዴሲቪር (remdesivir) ብቻ ነው ብለዋል።
ይህ መድኃኒት ከዚህ ቀደም ይውል የነበረው በኢቦላ የተያዘን ሰው ለማከም ነበር።
መድኃኒቱ ከኢቦላ በተጨማሪ ሌሎች የኮሮናቫይረስ አይነቶችን ለማከም በእንስሳት ላይ ተሞክሮ አመርቂ ውጤት አሳይቷል። በዚህም ኮቪድ-19ን ሊያክም ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
አንድ ሾልኮ የወጣ መረጃ እንደጠቆመው በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ በተመራ የላብራቶሪ ሙከራ መድኃኒቱ በኮቪድ-19 የተያዘን ሰው ለማከም ውጤታማ መሆኑ ተደርሶበታል።
ይህ መድኃኒት የዓለም ጤና ድርጅት በ’ሶሊዳሪቲ ትሪያል’ ማዕቀፍ ውስጥ ከያዛቸው አራት መድኃኒቶች መካከል አንዱ ይህ ነው። የዚህ መድኃኒት አምራች የሆነው ጊሊድ የተሰኘው ተቋምም በመድኃኒቱ ላይ ምርምር እያካሄደ ይገኛል። Image copyright Science Photo Library
የጸረ ኤችአይቪ መድሃኒቶች ኮሮናቫይረስን ሊያክሙ ይችላሉ?
ሎፒናቪር (lopinavir) እና ሪቶናቪር (ritonavir) የተባሉ የጸረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች በኮቪድ-19 የተያዘን ሰው ለማከም ይውላሉ የሚሉ መላምቶች በስፋት ቢኖሩም ለዚህ ማረጋገጫ አልተገኘም።
በላብራቶሪ ደረጃ መድኃኒቶቹ ውጤታማ ስለመሆናቸው ማረጋገጫዎች ቢኖሩም በሰዎች ላይ የተደረጉ የሙከራ ውጤቶች ግን አጥጋቢ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
መድኃኒቶቹ በኮቪድ-19 ተይዘው በጠና ለታመሙ ሰዎች ቢሰጡም የመጨረሻ ውጤታቸው፤ ታማሚዎቹ ከበሽታው አላገገሙም፣ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም አልቀነሰም አልያም በሰውነት ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ መጠን አልቀነሰም።
ጸረ-ወባ መድኃኒቶችስ ኮሮናቫይረስን መግታት ይቻላቸዋል?
የጸረ-ወባ መድኃኒቶች የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩናይትድ ኪንግደም የሚያደርጓቸው ምርምር አካል ናቸው።
ክሎሮኪን እና ሃይድሮክሎሮኪን የተባሉ የጸረ- ወባ መድኃኒቶች ፕሬዝደንት ትራምፕ ኮቪድ-19ን ለማከም ሊውሉ እንደሚችሉ መጠቆማቸውን ተከትሎ መድኃኒቶቹን የመጠቀም ዝንባሌ በስፋት ተይቷል። ይሁን እንጂ መድኃኒቶቹ ከኮቪድ-19 ስለመፈወሳቸው ማረጋገጥ አልተቻለም።
የዓለም ጤና ድርጅትም የመድኃኒቶቹ ውጤታማነት ላይ እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም ብሏል።
የበሽታ መከላከል አቅምን ከፍ የሚያደርጉ መድኃኒቶችስ?
የሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓት ቫይረሱን ለመዋጋት ከተገቢው በላይ ምላሽ ከሰጠ፤ ሰውነታችን ይቆጣል። ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓት ላይ መመርኮዝ ጠቃሚ ቢሆም፤ ይህን ሥርዓት ከተገቢው በላይ ከፍ ማድረግ ግን አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
የዓለም ጤና ድርጅት እያከናወነ ያለው ‘ሶሊዳሪቲ’ የተባለው ሙከራ ‘ኢንፌርኖ ቤታ’ የሚባል ኬሚካልን እየመረመረ ይገኛል። ‘ኢንፌርኖ ቤታ’ የንጥረ ነገሮች ስብስብ ሲሆን ሰውነታችን በቫይረስ ሲጠቃ ቫይረሱን ለመከላከል በሰውነታችን ውስጥ ይለቀቃሉ። የሰውነት መቆጣትንም ይቀንሳሉ ተብሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ የሰውነት መቆጣትን የሚቀንስ የመድኃኒት አይነትን እየመረመረች ትገኛለች።
ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ደም በሽታውን ለማከም ይውል ይሆን?
ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቫይረሱን የሚዋጋ አንቲቦዲ ይኖራቸዋል።
ሃሳቡ ከበሽታው ያገገመ ሰው አንቲቦዲ ያለበት ደም በመውሰድ በበሽታው የሚሰቃይን ሰው ለማከም ጥቅም ላይ ማዋል ነው።
አሜሪካ እስካሁን 500 ሰዎችን በዚህ መንገድ እክማለች። ሌሎች አገራትም የአሜሪካንን ፈለግ እየተከተሉ ነው።
መድኃኒት እስኪገኝ ምን ያክል ጊዜ እንጠብቅ?
በቅርቡ ከኮቪድ-19 የሚፈውስ መድኃኒት መቼ ተግባር ላይ እንደሚውል እንሰማለን።
ከዚያ በፊት ግን በቀጣይ ጥቂት ወራት የመድኃኒቶቹ ውጤታማነት ላይ የላብራቶሪ ግኝቶችን እንሰማለን። በትክክል መናገር የሚቻለው ግን ከክትባት ቀድሞ መድኃኒት ተግባር ላይ ይውላል።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ተመራማሪዎች እና ዶክተሮች የሚመራመሩበት ወይም ለታማሚዎች የሚሰጡት የመድኃኒት አይነቶች ደህንነታቸው የተረጋገጠና ከዚህ ቀደም የሚታወቁ ወይም የነበሩ መድኃኒቶች በመሆናቸው ነው።
ክትባት ለማግኘት ምርምር የሚያደርጉት ተመራማሪዎች ግን ሥራቸውን ከዜሮ ነው የጀመሩት፤ ይህም ምናልባት ወራትን ወይም ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል።
አሁን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚታከሙት በየትኛው መድኃኒት ነው?
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሽታው ካልጠናባቸው በቤት ውስጥ እራሳቸውን ለይተው በመቀመጥ እረፍት እንዲያደርጉ፣ የህመም ማስታገሻዎችንና በርከት ያለ ፈሳሽ እንዲወስዱ ይመከራል።
በጽኑ የታመሙ ደግሞ በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆነው ለመተንፈስ የሚያግዛቸው ቬንቲሌተር ተገጥሞላቸው እንደየ ሃገሩ መመሪያ መሠረት መድኃኒቶች ሊሰጣቸው ይችላል።
ምንጭ -ቢቢሲ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2012
ጌትነት ተስፋማርያም