በተለያዩ በጎ ስራዎች ይታወቃሉ። የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት፤ በተለያዩ የጤና እክሎች ለሚሰቃዩ ወገኖች ጤና ጣቢያዎችን በመገንባት፤ ትምህርት ላልደረሳቸው ወገኖች ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ በማድረግና ልክ እንደ አሁኑ የኮሮና ቫይረስ አይነት ሀገራዊ ቀውስ ሲፈጠርና የዜጎች በጎ ምላሽ ሲፈለግ ቀድሞ ደራሽ በመሆን ይታወቃሉ። አልቢር ዴቭሎፕመንት ኤንድ ኮፕሬቲቭ አሶሴሽን የሚባል ምግባረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመው የተራቡትንና የታረዙትን ከመደገፍ በተጨማሪ በተለያዩ የልማት ስራዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል።
ከዓመታት በፊት ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎች ተከትሎም ጥያቄዎቹ መፍትሄ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረቶች ካደረጉ የሃይማኖት አባቶች አንዱ ናቸው። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአዲስ መልክ እንዲዋቀርና ተቋማዊ ቁመና እንዲይዝ ጥረት ካደረጉ የእምነቱ አባቶች መካከል ተጠቃሽም ናቸው። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በአዲስ መልክ ከተዋቀረ በኋላም ላለፉት ሰባት ወራት ምክር ቤቱን በፕሬዝዳንትንት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። እኒህ የሃይማኖት አባት ሸህ ሱልጣን አማን ይባላሉ ። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ወቅታዊውን የኮሮና ቫይረስንና የሮመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግም ከእኒሁ የሃይማኖት አባት ጋር ቆይታ አድርጓል። እንዲህ አቅርበነዋል፦
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ቀደም ባሉት ጊዜያት በሙስሊሙ ዘንድ ብዙም ተቀባይነት አልነበረውም። አዲሱ መጅሊስ ከተቋቋመ ወዲህ ህዝበ ሙስሊሙ ምን ያህል ተቀብሎታል?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- ህዝበ ሙስሊሙ በትክክል የሚወክለው መጅሊስ (የእስልምና ምክር ቤት) እንዲኖረው ለዘመናት ሲታገል ቆይቷል። የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ለውጥ እንዲመጣ ታግሏል። መጅሊስ ሙስሊሙን የሚወክል ብቸኛ ተቋም ቢሆንም በነበረው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሙስሊሙ ያልመረጣቸው ሰዎች በብዛት የተሰገሰጉበት ተቋም በመሆኑ ሙስሊሙ በተቋሙ ላይ እምነት አጥቶ ቆይቷል። ይህንንም ቅሬታ አንስቶ በተለያዩ መድረኮች ብሶቱን ሲገልጽ የቆየ ከመሆኑም ባሻገር እስከ መታሰር፤ መደብደብና ህይወቱንም እስከ ማጣት የደረሰ መስዋዕት ከፍሎ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል።
መጅሊስ ሙስሊሙን በሚወክሉ የሃይማኖት አባቶች ሊተዳደር እንደሚገባውና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲጸዳ የተከፈለው መስዋዕትነት ፍሬ እያፈራ መጥቷል። ዛሬ የሙስሊሙ ብቸኛ ተቋም በሃይማኖት አባቶች ብቻ የሚመራና ከየትኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ ተቋም መገንባት ተችሏል። በመሆኑም ሙስሊሙ ባለው ለውጥ ደስተኛ ነው። የዛሬ ስምንት ወር ገደማ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች የተሳተፉበት መድረክ በሸራተን አዲስ ስብሰባ ተካሂዶ አዲሱ መጅሊስ በአዲስ መልክ ተቋቁሟል። በዚህ ስብሰባ ላይ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ300 በላይ የሃይማኖት አባቶች የተሳተፉበትና ከሞላ ጎደልም ተመሳሳይ አቋም በተያዘበት ሁኔታ ሙስሊሙ ማህበረሰብን ሊወክል የሚችል ተቋም በአዲስ መልክ መቋቋም እንደሚኖርበት ከስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ ተገብቷል። ይህንኑ መሰረት በማድረግም ከኡለማ በተመረጡ 26 ሰዎችና ከቦርድ በተመረጡ ሰባት ሰዎች የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
እኔን ጨምሮ በአዲስ መልክ መጅሊሱን እንድንመራ የተወከልን ሰዎች መጅሊሱን እንድንመራ ውክልና የተሰጠን ለስድስት ወራት ብቻ ነው። ጊዜያዊ ነን። በቋሚነት መጅሊሱን የሚመሩ ሰዎች የሚወከሉት መላው ሙስሊም ማህበረሰብ በሚያደርገው ምርጫና ያስተዳድሩኛ ብሎ በሚወክላቸው የሃይማኖቱ መሪዎች ነው። ምርጫውም በቀጣይ የሚካሄድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው የሚካሄደው መቼ ነው?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- እኛ ወደዚህ ስንመጣ በዋነኝነት ተቋሙን በአዲስ መልክ በማደራጀት ሙስሊሙን የሚመጥን ተቋም መፍጠርና በቀጣይም ሙስሊሙን የሚወክሉትን የሃይማኖት አባቶች ለማስመረጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ሆኖም ግን እንዳሰብነው ስራዎች በፍጥነት አልሄዱልንም። ተቋሙ ለረጅም ጊዜ በችግር የተተበተበ ከመሆኑም በሻገር ሀገራዊ ሁኔታውም ምርጫ ለማካሄድም ምቹ አልነበረም። በየቦታው ግጭትና አለመረጋጋት ሰፍኖ በመቆየቱ ህብረተሰቡን አስተባብሮ ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ አመቺ ሁኔታዎች አልነበሩም። በዚህ ላይ አሁን የተጋረጠው የኮሮና ቫይረስ እንቅፋት ሆኖብናል።
ሙስሊሙ የጣለብንን አደራ ለመወጣት ቀን ከሌሊት እየሰራን ነው። የሚገርመው እኮ አዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አለ ቢባልም ፤ወደ ውስጥ ገባ ተብሎ ሲታይ በጣም የተዳከመና የእለት ተዕለት ስራዎችን እንኳን ለማካሄድ የሚያስችል ቁመና የሌለው ተቋም ነበር። እንደተቋም ሊያስጠራው የሚያስችል ቁመና ካለመኖሩም በሻገር ስራዎች የሚከናወኑት በደንብና በአሰራር አልነበረም። ሰራተኞች ለማስተዳደር የሚያስችል መመሪያም ሆነ ማንዋል የለም፤ የገንዘብ ፍሰቱን የሚቆጣጠር የሂሳብ ማንዋልም አልነበረውም። መዋቅሩ በከተማ ደረጃ ብቻ ተንጠልጥሎ የቆመና በሚፈለገው ደረጃ ህብረተሰቡ ድረስ ያልረገጠ ተቋም ነው። ተቋሙና ሰፊው ሙስሊም ህብረተሰብ የሚተዋወቁበት አንዳችም መንገድ አልነበረም።
በአዲስ መልክ የተመረጥነው የመጅሊሱ አመራሮች ወደ ተቋሙ ከመጣን በኋላ ተቋሙን እግር ከወርች ሰቅዘው የያዙትን ችግሮች በማጥናት የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረናል። ከችግሮች በመነሳት አዳዲስ መመሪያዎችንና ማንዋሎችን በማዘጋጀት ተቋሙ በደንብና በሥርዓት እንዲተዳደር ለማድረግ ሞክረናል። ከላይ ተንጠልጥሎ ያለውን መዋቅርም ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግም አዲስ መዋቅር እየዘረጋን እንገኛለን። እነዚህና ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫውን ለማካሄድ እንዳንችል አድርጎናል። ህብረተሰቡ ጋር በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ የማይሆን ተቋም ይዞ ደግሞ ምርጫ ማካሄዱ የሚፈለገውን ውጤት ስለማያመጣ ተቋሙን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረጉን ስራ ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው። በፌዴራል መጅሊስ በኩልም ያልተጠናቀቁ ስራዎች ስላሉ እነሱ ሁሉ ፈር መያዝ አለባቸው። የኮሮና ቫይረስም ሌላው ስጋት ነው። የሆኖ ሆኖ ግን የኮሮና ቫይረስ ስጋት እንደተወገደና የተጀመሩ ስራዎችም እንደተጠናቀቁ ምርጫውን እናካሂዳለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ መጅሊስ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምን ያህል የጸዳ ነው?
ሸህ ሱልጣን አማን ፡-ጥሩ ጥያቄ ነው። አሁን ያለው አካል ሙሉ ለሙሉ ከፖለቲካ ነጻ የሆነና ሃይማኖታዊ ተግባራትን ብቻ የሚከውን ነጻ አካል ነው። በዚህ ማንም ጥርጣሬ ሊገባው አይገባም። አዲሱ መጅሊስ ስራውን ከጀመረ ከሰባት ወራት በላይ ሆኖታል፤ በነዚህ ጊዜያት ከአንድም የመንግስት አካል ይህን ስራ፤ ይህንን አትስራ የሚል ትዕዛዝም ሆነ መመሪያ ደርሶን አያውቅም። እኛ ግን ከመንግስት እገዛ ስንፈልግ መንግስት ሁል ጊዜም በሩ ክፍት ነው፤ በብዙ ጉዳዮች እገዛ ያደርግልናል።
የመስኪዶች ጉዳይ፤ የኡቃፎች ጉዳይ፤ የቦታ ጥያቄና የመሳሰሉት ጉዳዮች ሲኖሩን ከመንግስት ጋር በቅርበት እንሰራለን፡ በመመካከርም በርካታ ችግሮችን ለመፍታት እየሞከርን ነው።
አዲስ ዘመን፡ – ወደ ወቅታዊ ሁኔታ ልመለስና እንደ ሃይማኖት አባት አሁን በዓለማችን ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምን ያህል ያሰጋዎታል?
ሸህ ሱልጣን አማን ፡- የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ነው። ድሃ ሃብታም፤ እስላም ክርስቲያን፤ ነጭ ጥቁር ሳይል ሁሉንም የሰው ዘር የሚያጠቃ ክፉ በሽታ ነው። በቅርብ ጊዜያት ዓለማችን ካየቻቸው በሽታዎች ሁሉ በፍጥነት የሚስፋፋና በርካታ ሰዎች ለሞት የሚዳርግ ቫይረስ ነው። ሰውን ከሰው የለያየ፤ መስኪዲችን ያስዘጋና ሰውን በገደብ ውስጥ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ያስገደደ በሽታ ነው። በሽታው የሰውን ልጅ ጤንነትና ህይወትን ብቻም ሳይሆን ኢኮኖሚውንም የሚፈታተን ነው። አንድ ሁለት ተብሎ የማይቆጠር በርካታ ችግሮችን ይዞ የመጣ በሽታ ነው። በሽታው በጣም አስከፊ በመሆኑ የታመሙ ሰዎችን እንኳን ማስታመምና አጠገባቸው ሆኖ ማጽናናት አይቻልም። የሞቱትን መቅበር የሚታሰብ አይደለም። ይህ እንደ ሃይማኖት አባት ሆነህ ስታየው በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳስብ ነው። ሰው የራሱን ወገን ማስታመም፤ መንከባከብ ብሎም ሲሞት መቅበር ካልቻለ ትንሽ ስሜት የሚጎዳ ነገር ነው። ሆኖም ሰዎች በተለያዩ በሽታዎችና ችግሮች ስለሚፈተኑ ሃኪሞች የሚሰጧቸውን ምክሮችና ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉና ወደ ፈጣሪያቸውም ከተመለሱ ይህንን ወረርሽኝ ማለፍ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡ -ሰዎችን የሚጎዱ ወረርሽኞች በየጊዜው ሲከሰቱ ይታያሉ፤ ለመሆኑ የእነዚህ ወረርሽኞች መከሰት ምክንያት ምንድን ነው?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- ወረርሽኞች ወይም ሰዎችን የሚጎዱ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚመጡት በሰዎች ጥፋት ነው። ሰዎች የሚሰሩት ሃጢያት ከልክ ሲያልፍ አሁን የተከሰተው አይነት ወረርሽኞች በየጊዜው ይከሰታሉ። በአሁኑ ዓለማዊ ሁኔታ በርካታ ግፎች እየተሰሩ ነው። ሰዎች ኃጢያት ቢሰሩም ከልክ ሲያልፍ ግን ፈጣሪ ሰዎች ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና እንዲታረሙ ለማድረግ ወረርሽኞችን ያመጣል። ፈጣሪ መሃሪ ነው፤ ነገር ግን ሰዎች ይህንን መሃሪነቱን ባለመረዳት የሚሰሯቸው ግፍና በደሎች ወረርሽኞች እንዲነሱ ያደርጋል። ንጹሃን ሰዎች ያለአግባብ ሲፈናቀሉ፤ ሲቆስሉ፤ ሲደሙ ሲገደሉ በየቀኑ እንያለን። ህጻናት በግፍ በየቦታው እንደቅጠል ሲረግፉ ተመልክተናል። ሰዎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ውጡ ተብለው ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ተመልክተናል ፤ ሰዎች በአደባባይ ሲገደሉና ሲሰቀሉ ተመልክተናል። በሌላም በኩል ከተፈጥሮ ህግጋት ውጭ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና እርቃናቸውን ተጋልጠው የሚሄዱ ሰዎች ማየት የተለመደ ሆኗል። ከመታመንና በሃቅ ሰርቶ ከማግኘት ይልቅ አታሎና አጭበርብሮ ለመክበር የሚደረገው ሩጫ የበዛ ነው። ህጻናት ልጆች የሚመገቡትን ምግብ ሳይቀር ባዕድ ነገር ጨምሮ መሸጥ የንግድ ዘይቤ መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል። በእነዚህና መሰል ማህበራዊ ቀውሶች የሚጎዱ ንጹሃን ደግሞ ወደ ፈጣሪያቸው ማልቀሳቸው አይቀርም። የእነዚህ ሰዎች እንባ ደግሞ በፈጣሪ ዘንድ መሰማቱ ስለማይቀር አጥፊዎችን ለመቅጣትና ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ አላህ አስተማሪ ቅጣት መላኩ አይቀርም። በኖህ ህዝቦች ላይ የደረሰውም ጥፋት የዚሁ አንድ ማሳያ ነው። የኮሮና ቫይረስም አሁን በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን ላይ በመሰሉ ግፍና በደሎች አማካኝነት የመጣ ቅጣት ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ችግር ለመውጣት ምን ማድረግ አለብን?
ሸህ ሱልጣን አማን ፡- አሁን ከተጋረጠብን የኮረና በሽታ ለማምለጥ ያለው ብቸኛ መንገድ ወደ ፈጣሪ ተመልሶ ምህረት መጠየቅ ነው። የሰራናቸውን ሃጢያቶች ተገንዝበን ከልብ በመጸጸት ፈጣሪን መማጸን ያስፈልጋል። ማረን ማለት ይገባል። ሰው ሰራሽ ቫይረስ ነው፤ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ በሽታ ነው የሚሉ አዘናጊ ሰበቦችን ትተን ፤የችግሩ ምንጭ እራሳቸውን የሰራናቸውን ኃጢያቶችና ግፎች መሆናቸውን ተገንዝበን ወደ ቀናው መንገድ መመለሱ ተገቢ ነው። አላህ እየቀጣን ያለው በሰራነው ግፍና በደል ልክም አይደለም። እንደምንሰራው ግፍና በደል የበለጠ ቅጣት ነበር የሚገባን። ሆኖም ግን አላህ መሃሪ በመሆኑ ከጥፋታችን እንድንታረም ብቻ ነው ለማስተማር ያህል እየቀጣን ያለው። ይህን ካላደረግንና በጥፋታችን ለመቀጠል ካሰብን እንኳን ይህ በሽታ ሊጠፋ ቀርቶ የባሰ ችግር መምጣቱ አይቀሬ ነው። ስለዚህም ነገ ዛሬ ሳይሉ ወደ ፍቅር፤ መተሳሰብና ደግነት መመለስ ችግሩን በቀላሉ ለማስወገድ ሁነኛው መፍትሄ ነው። ለጊዜውም ቢሆን ክትባትም ሆነ መድሃኒት ያልተገኘለት በሽታ በመሆኑ ሀኪሞች የሚሰጡትን ምክር መቀበልና መልካም ተግባራትን መከወን ከበሽታው ለመዳን ያስችላል።
አዲስ ዘመን ፡- አሁን በየቴሌቪዥኑ የሚደረጉ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ምን ያህል ያግዛሉ ብለው ያምናሉ?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- እኔ በኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ አለኝ። ኢትዮጵያውያንና መንግስታቸው ጥፋቱ የራሳቸው መሆኑን አምነው ማረን ብለው መማጸን በመጀመራቸው የኮሮና ቫይረስ ብዙ ሳይጎዳን እንገታዋለን ብዬ አስባለሁ። በህይወቴ አይቼ በማላውቅ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን እንደየምነታቸው ፈጣሪያቸውን መማጸን ጀምረዋል። መንግስትም ሁሉም እንደየእምነቱ ፈጣሪውን እንዲማጸን ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ይህንን ማንም ሀገር አላደረገውም። ስለዚህም በኢኮኖሚያቸው የጠነከሩ፤ በቴክኖሎጂያቸው የተመነደጉ፤ የሰለጠኑና የተማረ የሰው ሃይል ያላቸው ሀገራት ሁሉ በሽታውን መቋቋም አቅቷቸው ተብረክርከዋል። ከፈጣሪ በስተቀር ኢኮኖሚም ሆነ ቴክኖሎጂ ዋጋ እንደሌላቸው በገሃድ ታይቷል። በሽታው በርትቶ የሚታየው ሰለጠኑ በሚባሉ ቁንጮ ሀገራት ላይ ነው። ብዙ ግፍና በደልም ሲሰራ የነበረውም በነዚሁ ሀገራት አማካኝነት ነው። ግፍና በደሉን ቆጥሮም ብዙዎች የሞቱትና አሰቃቂ ሁኔታዎችም የታዩት በነዚሁ ሀገራት ነው። አዳኝም ሆነ ገዳይ አንድ ፈጣሪ እንጂ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ገንዘብ እንዳልሆነ ፍንትው ብሎ ታይቷል። ስለዚህም አሁን ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ፈጣሪ መመለስዋ ብቸኛው የመዳኛ መንገድ ስለሆነ ኢትዮጵያ ብዙ ችግር ሳይደርስባት ከበሽታው ትድናለች የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ፡- ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጋራ ተሰባስቦ መስገድ እንደሌለበት የተላለፈውን መልዕክት ምን ያህል ተግባራዊ አድርጎታል?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- ሙስሊሙ ማህበረሰብ በቤቱ እንዲሰግድና አላህን እንዲማጸን የተላለፈውን መልዕክት አሁን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አድርጎታል። በመጀመሪያ አካባቢ አንዳንድ ብዥታዎች ስለነበሩ ወጣ ገባ ማለት ነገር ቢኖርም ብዙም ሳይቆይ በሃይማኖት አባቶችና በመንግስት የተላለፉትን መልዕክቶች ተቀብሎ ተግባራዊ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ። ሙስሊሙ ይህንን በማድረጉም እራሱንም፤ ቤተሰቦቹንም ፤ ወገኖቹንም ከበሽታው ታድጓል። ይህ ሊያስመሰግነው ይገባል። ከምስጋና በተጨማሪም በሽታው ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ለሰዎች አስቦ እቤቱ መቅረቱ ከአላህ የሚያስገኝለት ምንዳም አለ።
አዲስ ዘመን፡ – በዚህ በረመዳን ወር የመስኪዶች መዘጋት ምን ያህል ተገቢ ነው ይላሉ?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- የኮሮና ቫይረስ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ገዳይ በሽታ ነው። መስኪዶች ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሰው ጥግግት የሚስተዋልባቸው፤ ሰዎች በጋራ በአንድ ምንጣፍ ላይ የሚሰግዱባቸው፤ በጋራ ውሃ የሚጠቀሙባቸው፤ በጋራ ተሰባስበው የሃይማኖት ትምህርት የሚወስዱባቸው ቦታዎች በመሆናቸው ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። ስለዚህም ከመስኪዶች በፊት የሰዎች ህይወት መትረፍ ስላለበት ሰዎች ወደ መስኪድ ሄደው እንዳይሰግዱ መደረጉ ተገቢ ነው። በእስልምና ከሁሉም ነገር በፊት ለሰው ልጆች ቅድሚያ ይሰጣል። ከ1440 ዓመት በፊትም በነብዩ ሞሃመድ ጊዜም ሰዎች በተላላፊ በሽታዎች ከተያዙ ወደ መስኪድ እንዳይመጡ ትዕዛዝ ተላልፏል። ይህ በእኛ ጊዜ የተጀመረና አዲስ ነገር አይደለም። ሌላው ቀርቶ የሰዎችን ሰላምና ምቾት ለመጠበቅ ነጭ ሽንኩርት የበሉ ሰዎች እንኳን ወደ መስኪድ እንዳይመጡ መልዕክት ተላልፏል። የኮሮና ቫይረስ ደግሞ ሰዎችን ለሞት የሚያበቃ በሽታ በመሆኑ ሰዎች በየቤታቸው እንዲሰግዱ መደረጉ አግባብነት ያለው ከመሆኑም በላይ ሃይማኖታዊ መሰረት ያለው ትዕዛዝም ነው።
በሁለተኛው ከሊፋ በኡመር ጊዜም ተመሳሳይ ውሳኔዎች መወሰናቸውን በሃዲስ የተላለፈ መልዕክት አለ። ኡመርና ተከታዮቻቸው ሻም ወደ ምትባል ሀገር እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ተላላፊ ወረርሽኝ መከሰቱን ሰምተው ወደ ከተማዋ ከመግባት ተቆጥበዋል። ስለዚህም ሰዎች ለአደጋ የሚያጋልጡ ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ገለል ብሎ ችግሩን ማሳለፍ በእስልምና የሚደገፍ ተግባር ነው። በተለይም የኮረና በሽታ ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ ከሰዎች ተቀራርቦና ተጠጋግቶ መገኘት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ችግሩ እስኪያልፍ ድረስ ሰዎች በየቤታቸው ሰላትም ሆነ ጸሎት ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው እንጂ አንዳችም የሚያስወቅሳቸው ነገር የለም። ይህ በሽታ የሚስፋፋውና በቀላሉም የሚሰራጨው ሰዎች በሚያደርጉት ቅርርብ ነው። ልክ እሳት በቀላሉ የሚያያዘው እንጨቶች አንድ ላይ ሲሆኑ እንደሆነው ሁሉ ይህም በሽታ ጉልበት የሚያገኘው ሰዎች በአንድ ቦታ ተሰባስበው ሲገኙ ነው። ስለዚህም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ሰዎች ለየብቻቸው መሆናቸው በአሁኑ ወቅት ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሰዎች ከመስኪድ ቀርተው እቤት ውስጥ በሚቆዩባቸው ወቅቶች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራት ምንድን ናቸው?
ሸህ ሱልጣን አማን፡-አላህ አንድ ነገር እንዲከሰት ሲያደርግ የራሱ የሆነ ዓላማ አለው። ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልህ የኮረና ወረርሽኝ የመጣው ሰዎች በሰሩት ኃጢያት የተነሳ ቢሆንም እግረመንገዱን ሰዎች
ወደ ፈጣሪ እንዲመለሱና ከመጥፎም ተግባር እንዲርቁ ምክንያት ይሆናቸዋል። አሁን ባለው ዓለማዊ ሁኔታ ሰዎች በሚያደርጉት ጥድፊያ የተሞላበት የኑሮ ዘይቤ ከፈጣሪያቸው ብቻ ሳይሆን ከቤተሶቦቻቸውም ጭምር ርቀዋል። ባልና ሚስት እንደ ድሮ ጊዜ አግኝተው ሲመካከሩ ፤ሲጨዋወቱ አይታይም። ልጆች የቤተሰቦቻቸውን ፍቅር ሳያገኙ እያደጉ ነው። እናት አባቱን ጊዜ ሰጥቶ የሚጠይቅና የሚንከባከብ ብዙም የለም። አጠቃላይ ማህበራዊ መስተጋብራችን ተናግቷል። ለማይሞላ ኑሮ ሁሉም በየፊናው ሲዋትት ከመዋል በስተቀር የጥሞና ኑሮ እርቆታል። ስለዚህም አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሰዎች በየቤታቸው ሲከተቱ እነዚህን የተናጉ ማህበራዊ ዕሴቶቻችንን ዳግም ነፍስ እንዲዘሩ ማድረግ ይችላሉ። ባልና ሚስት ለመወያየት፤ ለመመካከርና ለመተሳሰብ ጊዜ ያገኛሉ። ልጆችም የወላጆቻቸውን ፍቅር ለመጥገብ ዕድሉን ያገኛሉ። ቁርዓን ለመቅራት፤ ሃዲሶችን ለማዳመጥና ጽሞና ሰጥቶ ከአላህ ጋር በቅርብ ለመገናኘት ያስችላል። እስከዛሬ ጠፍቶ የነበረው ጊዜ እንጂ የሚሰራ ነገር አይደለም። ሰዎች ሶላትን በቤት ውስጥ ለመስገድ፤ ቁርዓን ለመቅራትና የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ምቹ ጊዜ ያገኛሉ። እነዚህን መልካም ነገሮች ማድረግ የቻለ ሰው እራሱንና ቤተሰቦቹን ከበሽታው ከመታደጉ በተጨማሪ ከቤተሰባዊና ማህበራዊ ህይወቱ አትራፊ መሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ሙስሊሙ በሮመዳን ጾምን ላይ ይገኛል። በዚህ ወቅት እራሱን ከኮሮና ቫይረስ በምን መልኩ ነው መጠበቅ ያለበት?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- የሮመዳን ወር የአብሮነት፣ የፍቅር፣ መተሳሰብና የስጦታ ወር ነው። በዚህ የተቀደሰ ወር የሰዎች አንድንትና አብሮነት ይጠነክራል። በአንድነት መስገድ፤ በአንድነት ማፍጠር፤ መጠያየቅና የተራቡትንና የታረዙትን መጠየቅና መመጽወት የተለመዱ ተግባራት ናቸው። ሆኖም ግን ዘንድሮ የተወሰኑትን ነገሮች ተወት አድርገን በሌሎቹ ላይ ማተኮር አለብን። ከኮሮና ቫይረስ መተላለፊያ መንገዶች ዋነኛው የሰዎች መሰባሰብና መጠጋጋት ስለሆነ ለዘንድሮ ይህንን ከመተግበር መቆጠብ አለብን። በመስኪዶች ተሰባስቦ መስገድ ቀርቶ ሰዎች በቤታቸው እንዲሰግዱ ቢደረግም መሰባሰቡ ካለ በሽታው በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው ሊተላለፍ ይችላል። ስለሆነም መጠራራቱና አብሮ ማፍጠሩ በቀላሉ ለቫይረሱ ሊያጋልጠን ስለሚችል ሁሉም በየቤቱ እንዲያፈጥርና ከመጠራራትም እንዲቆጠብ ላሳስብ እወዳለሁ።
ሰዎች ከመስኪድ ቢቀሩም በየሰፈሩ ተሰባስቦ ከመስገድም መታቀብ አለባቸው። የሙስሊሙ ኑሮ ማህበራዊ መስተጋብር የበዛበትና ቤተሰባዊ መጠያየቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑንም አውቃለሁ። ነገር ግን ግዴታ የሆነውን የአርብ የጁምዓ ሰላት በጋራ መስገድ እንዲቆም የተደረገው ሰዎችን ለማዳን መሆኑን ተገንዝቦ በረመዳን ወር የሚኖሩትን ግንኙነቶችና እንቅስቃሴዎች መገደብ ያስፈልጋል። ይህንን በማድረግ ሰዎችን ማዳንና ከአላህም ምንዳ ማግኘት ይቻላል። በሌላ በኩል የሮመዳን ወር የስጦታ ወር ነው። ያለው ለሌለው የሚሰጥበት የእዝነት ወር ነው። ይህ ተግባር ከመቼው ጊዜ በላቀ መልኩ ሊተገበር ይገባል። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስራ የፈቱ፤ ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር የተሳናቸው፤ የሚላስ የሚቀመስ ያጡ በርካታ ሰዎች የተፈጠሩበት ወቅት ነው። እነዚህን ሰዎች መደገፉና አይዟችሁ ማለቱ ትልቅ አጅር (ምንዳ) ያስገኛል። መተጋገዝ እስላማዊ ግዴታችን ነው።
አዲስ ዘመን፡ – በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በኩል ድጋፎችን በማስተባበር በኩል እየተጫወተ ያለው ሚና እንዴት ይገለጻል?
ሸህ ሱልጣን አማን፡- እያንዳንዱ ሙስሊም በግሉ ከሚያደርገው የመስጠትና የመለገስ ተግባር በተጨማሪ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ የተለያዩ የድጋፍ ተግባራትን በማስተባበር ላይ ይገኛል። ሰላሳ የሚጠጉ መስኪዶችን በማስተባበር ዕርዳታ እንዲሰበሰብ አድርገናል። በተለይም በረመዳን ወር ይህን በጎ ተግባር የበለጠ በማጠናከር ለተቸገሩ ወገኖች ለመድረስ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን። ኢንሻ አላህ ውጤታማ ስራ እንሰራለን ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
ሼህ ሱልጣን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2012
እስማኤል አረቦ