አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2025 ብርሃን ለሁሉም የሚል ፕሮጀክት ነድፎ ፍትሀዊ ተደራሽነትን በማስፋት ጨለማ ውስጥ ያሉ ዜጎች ብርሃን እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የአገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን፤ ይበልጡንም በገጠር ኤሌክትሪክ አገልግሎት አማካይነት በስፋት እየተሠራ ነው፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ከ2.9 ሚሊዮን የበለጠ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል አስተማማኝ ካለመሆኑም በላይ የተደራሽነትና የፍትሀዊነት ችግርም አለበት ፡፡
አገልግሎቱ ህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት በፌዴራል ደረጃ ብቻ የነበረውን አደረጃጀት ወደ ክልሎች በማውረድ ያልተማከለ አደረጃጀትና አሠራር ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤቶች አዋቅሯል፡፡ ይህም ወደ ህብረተሰብ በመቅረብ ተደራሽነትን ማረጋገጥ አስችሏል፡፡ ከዚህም ባለፈ 28 ዲስትሪክቶችንና 517 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በአዲስ መልክ በማደራጀት ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ክልል ላይ ያለ አንድ ባለሀብት ኤሌክትሪክ እንዲገባለት ከፈለገ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት በፌዴራል ደረጃ ያመለክት እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ በአሁን ወቅት ባለው አዲስ አደረጃጀት ክልሎች በራሳቸው ለአመልካቾች ምላሽ ይሰጣሉ ብለዋል፡፡
የኃይል ማስተላለፊያዎቹን ከማዘመን አኳያም መስመሮቹን ለማሻሻል ከልማት አጋሮችና ከመንግሥት ጋር በመተባበር እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ በተለያዩ ከተሞች አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ አዳማና ባህርዳር የነበሩትን የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት ምሰሶ እየተተኩ ሲሆን፤ በሁለተኛው ምዕራፍም አዲግራት፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ሻሸመኔ፣ ሐረር እና በመሳሰሉት ከተሞች መስመሮቹን የማሻሻሉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ አገልግሎቱ ሲቋረጥ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይታወቃል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ተቋሙ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር በመከተል ችግሮቹን ለመቅረፍና ህብረተሰቡ ዘመናዊ፤ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኝ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011
በፍሬህይወት አወቀ