የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥር 7 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም፣ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እና የለውጥ እንቅስቃሴ ሂደት፣እንዲሁም የድርጅት እና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በጥልቀት ተወያይቶ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የገዢው ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ የሚደረገው ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት፤ ዘረፋ እና ሁከት በተመሰቃቀለችበት፣ በኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል አለመተማመንና ልዩነት በጎላበት ወቅት ነው፡፡ከዚህ አኳያ ከስብሰባው ምን ይጠበቃል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና ጥቃቶች እየተፈጸሙ ባለበትና በተለይ ደግሞ በአማራ ክልል ግጭቶች ሆን ተብለው በሚቀሰቀሱበት ሁኔታ ወቅት የሚካሄድ ስብሰባ በመሆኑ የህግ የበላይነትንና የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር ቁርጠኛ ውሳኔና አቋም ይዞ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ በአሁኑ ጊዜ እንደ ግንባር ነው ብሎ ለማሰብና ለመቀበል አይቻልም፡፡ ህወሓት የኢህአዴግ አባል ነው ወይም ለሊቀመንበሩና ለድርጅቱ እየተገዛና እየታዘዘ ነው ብሎ መውሰድ አስቸጋሪ ነው፡፡በተዘዋዋሪ ህወሓት ከግንባሩ ወጥቶ ከፊል ነጻ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢህአዴግ አንድ ድርጅት ነው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ለውጡም በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ተንገራግጮ አንድ ቦታ ላይ ሊቆም እንደሚችልም ከወዲሁ አንዳንድ ሁኔታዎች እያሳዩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለለውጡ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ የአማራ ህዝብ ሰጥቶት የነበረው ከፍተኛ ተስፋ እየተሸረሸረ መምጣቱን በተለያየ መንገድ እየገለጸልን ነው ያለው ዶክተር ደሳለኝ ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመሩት የለውጥ ኃይል አስተማማኝ እንዳልሆነና በማንኛውም ጊዜ ሊቀለበስ እንደሚችል ብዙ አመላካች ነገሮች አሉ ብለዋል፡፡ከዚህ አኳያ ገዥው ፓርቲ ሰላምና መረጋጋትን ማስከበር የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎችን ማሳለፍ ይኖርበታል፤ግጭቶችን ለማስቆምና ለመፍታት ሥራ አስፈጻሚው ጠንካራ የሆነና የማያወላዳ ውሳኔ መወሰን እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም ብዙ የመንግሥት ተቋማት መከላከያን ጨምሮ በህገ ወጥ ድርጊቶች እየተሳተፉ ሰላማዊ ሰዎች እየተጎዱ ነው፡፡ይህንንም አቅጣጫ የሚያሲዙ ውሳኔዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢኮኖሚውም በከፍተኛ ደረጃ በህገ ወጦች ቁጥጥር ሥር ያለ ነው፡፡ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ አሁንም በጥቁር ገበያ የሚዘዋወርበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡የነዳጅ አቅርቦትም ከፍተኛ ችግር ይታያል፡፡የዋጋ ንረቱም እየጨመረ ነው፡፡የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ለእነዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጦ በፍጥነት ወደ ተግባር ይገባል የሚል ሃሳብ አለኝ ብለዋል፡፡የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ የጎላ ችግር የለበትም ሲሉም መስክረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የተሻለና የተጠናከረ ኢህአዴግ አለ ብለው የሚያምኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕጩ ዶክተር የሆኑት አቶ በዳኔ ገመቹ ህዝቡ ለውጡን ተቀብሎታል፡፡ሆኖም በአመራሩ ረገድ መሬት አልወረደም፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን ገኖ የወጣውን ለውጥ የግንባሩ አባል ድርጅቶች የማስፈጸምም ይሆን ተቀብሎ የመሄድ ዝንባሌ አይታይም፡፡እነዚህን ችግሮች የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያበቃ ውሳኔ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በፀጥታ አካሉ ረገድ ሰላም ለማደፍረስ ችግር የፈጠሩን ሰዎች ለይቶ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በጅምላ ይፈጸማል፡፡ይህ ደግሞ የሚደረገው የህዝብን ብሶት ለማነሳሳት ሆን ተብሎ ነው፡፡የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዚህ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ የማስተካከያ ውሳኔና ሥራ መስራት ይገባዋል የሚል ሃሳብ እንዳላቸው ዕጩ ዶክተሩ ገልጸውልናል፡፡
የአረና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ በበኩላቸው ኢህአዴግ እንደ ግንባር እየሰራ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ምክንያቱም በአባል ድርጅቶቹ መካከል ያለመተማመንና ድብብቆሹ ገኗል፡፡የዚህ ደግሞ ምክንያቱ የስልጣን ሽኩቻ ነው፡፡መዋቅሩም አጥጋቢ ሥራ እየሰራ አይደለም፡፡ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ የለም ቢባል እውነት ቢሆንም ግልጽ ፍቺ ግን አላደረጉም፡፡ ከዚህ ተነስቶ አንድነቱን የሚያጠናክርና ያለመተማመንን የሚያስወግድ ጠንካራ ውሳኔ ያሳልፋል ብለን እንጠብቃለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች እዚህም እዚያ ግጭት እየተከሰተ ነው፡፡ኢህአዴግም ሥራ አስፈጻሚ እነዚህ ግጭቶች እልባት የሚያገኙበትን መንገድ መቀየስ ይኖርበታል፡፡የሰዎችን መፈናቀል በዘላቂነት ማስቆም የሚያስችል ውሳኔ መወሰን ይጠበቅበታል፡፡ሌላው ነገር ደግሞ ለውጡ ወደ መሬት አልወረደም፡፡በተለይ በትግራይ ምንም የለውጥ እንቅስቃሴ የለም፡፡ይህ ለውጥ ወደ መሬት እንዲወርድ በማድረግ ረገድም ከሥራ አስፈጻሚው የተግባር ውሳኔ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011
በጌትነት ምህረቴ