አዲስ አበባ፡- የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሃገሪቱ የቱሪዝም እድገት የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት ጠየቀ፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ትናንት በተካሄደው ውይይት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወ/ት ሌንሴ መኮንን እንደገለጹት፣ ቱሪዝም ያለ ኪነጥበብ ባለሙያዎች እድገቱን ማፋጠን አዳጋች ነው፡፡ ከቱሪዝም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ኪነ ጥበብ ሀገራዊ ወግ ባህልና እሴቶችን በማስተዋወቅና ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
የቱሪዝም ድርጅት በዘርፉ ከፍ ያለ ደረጃ ለመድረስ የኪነ ጥበብ ባለሙያውን ማሳተፍ አስፈላጊ እንደሆነና ተቋማቸውም ለዚህ ትኩረት ሰጥቶ አንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የድርጅት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬስብሃት በበኩላቸው፣ ኪነ ጥበብ የቱሪዝም ዘርፍ በማሳደግ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመው፣ ለዚህም ተቋማቸው በአዲስ መልክ የተጠናከረ ስራ ለመስራት እቅድ መያዙን አንስተዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በጥበብ ስራቸው ውስጥ የሀገሪቱን መለያ/ብራንድ /እና ልዩ ልዩ እሴቶችን በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ዘርፉ የላቀ ሚና ማበርከት እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
በውይቱ ላይ ተሰታፊ የሆኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በኪነ ጥበብ በስራቸው ሀገራዊ ባህል ወግና እሴትን የተመለከቱ ጉዳየች ትኩረት አድረገው እንደሚሰሩና የቱሪዝም ዘርፍ ማደግ ለኪነ ጥበቡ ትልቅ ግብዓና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኪነ ጥበቡ ለቱሪዝም ልዩ ጥኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልና በአንጻሩ ደግሞ የቱሪዝም ሀብትን ማስተዋወቂያና ማሳያ የሆነው ኪነ ጥበብ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
በተገኝ ብሩ