ሐሳቦችን በጥንቃቄ መመርመር እንዳለብን አበክራ የምትመክረን ታላቋ እንስት አሳቢ አያን ራንድ ደጋግማ የምታነሳልን አንድ ሐሳብ አለ። ሐሳቦችን በሚገባ አጢናቸው “Take Ideas Seriously” ትለናለች ብርቱ አሳቢዋ አያን ራንድ። ከነብዙ መአቶቹም ቢሆን ኮሮና ካስተማረን በጎ ነገር አንዱም ይኸው ይመስለኛል። ከዚህ ቀደም እንደዋዛ አይተን ስናልፋቸው የነበሩ ብዙ ነገሮችን ቆም ብለን እንድናስታውሳቸው፤ መልሰን መላልሰን እንደገና እንድናጤናቸው ዕድሉን አመቻችቶልናል። እናም ይህ አስጨናቂ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ ከተከሰተ ወዲህ ዓለም እያንዳንዷን ነገር ትኩረት ሰጥቶ ማጤን ጀምሯል።
አዳዲሶቹን ብቻ ሳይሆን ከበርካታ ዓመታት በፊት የነበሩ ሃሳቦችን፣ የተባሉ ንግግሮችንና የተፈፀሙ ድርጊቶችን ሳይቀር ወደኋላ ተመልሶ ፍጥረታቸውን መመርመርና ማጤን ጀምሯል። እኔም አንዳንድ ትኩረቴን በሳቡኝ ጉዳዮቸ ላይ ማሰብና ማሰላሰል ከጀመርኩ ሰነባበትኩ። ማሰብ ብቻ ሳይሆን ራንድ እንዳለችው ትኩረቴን የሳቡትን ጉዳዮች “መመርመርና ማጤን” ፈለኩ። ስለሆነም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምልከታዬን የማካፍላችሁ ይሆናል። ለዛሬው ሳይንሳዊ ልብ ወለድን አስቀደምኩ።
የሣይንሳዊ ልብ ወለዶች ጉዳይ
የሥነ ጽሁፍ ተማሪ እንደመሆኔ መጠን ኮሮና ከተከሰተ በኋላ መልሼ እንዳጤናቸው ከተገደድኩባቸው ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያውና ዋነኛው የሳይንሳዊ ልብ ወለዶች እውነታ ነው። ልብ ወለድ ማንበብ ለአብዛኛው ሰው መዝናኛ ነው። ቋንቋና ሥነ ጽሁፍን ሊያጠና ዩኒቨርሲቲ ለገባ ሰው ግን ልብ ወለድ ማንበብ ምርጫ ሳይሆን ግዴታም ነው። ለማንኛውም ልብ ወለድ መሠረታዊ ነባራዊ እውነቶችን ሳይንስ ከህብረተሰቡ አኗኗርና ህይወት የሚቀዳ ራስን መልሶ የሚያሳይ ገሃዱን ዓለም የሚያንፀባርቅ ለዛ ባለው መንገድ የሚቀርብ የፈጠራ ድርሰት ነው። በስሩም በርካታ ዘውጎችን አካቶ የያዘ ሲሆን፤ ሳይንሳዊ ልብ ወለድ አንደኛው የልብ ወለድ ዓይነት ነው። ታዲያ ሁሉም የልብ ወለድ ዓይነቶች የፈጠራ ድርሰቶች ቢሆኑም ሳይንሳዊ ልብ ወለድን ለየት የሚያደርገው ግን ያለፈውንና የአሁኑን ጊዜ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም “ፈጥሮ” የሚያሳይ መሆኑ ነው።
ልብ ወለድ የፈጠራ ድርሰት ነው ሲባል የሚፈጠሩት በልብ ወለዱ ውስጥ ያሉት “ሰዎች” ወይም ገጸ ባህርያቱ፣ ታሪኩ፣ ሴራው፣ ወዘተ… እንጅ ጭብጡ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው። ከስምንቱ ዋና ዋና የልብ ወለድ አላባውያን መካከል ጭብጡ ብቻ ሳይሆን “መቼት” የሚባለውም (ታሪኩ የተፈፀመበትን ጊዜና ቦታ የሚያመላክተው የልብ ወለዱ ኤለመንት) ከጠቅላላው እውነታ ለማውጣትና ፈጠራ ለማድረግ ያስቸግራል። ምክንያቱም ጊዜ ያለፈ ከሆነ ያለፈ ነው፤ ሌላ ያለፈ ጊዜ መፍጠር አይቻልም፤ ቦታም እንደዚሁ ፈጠራም ቢሆን ስሙ ይለወጥ ይሆናል እንጂ በእውነተኛው ዓለም ያለ ወይም ምድር ላይ የሚገኝ መሆን አለበት። በሳይንሳዊ ልብ ወለድ ግን ከዚህ ሕግ መውጣት ይቻላል። ያለፈውን ወይም የአሁኑን ጊዜ ነፀብራቅ ማሳየት ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ የሌለውን ወደ ፊት የሚሆነውንም ፈጥሮ መንገር ይቻላል። ቦታውንም እንደዚሁ እንደ “ዩቶፕያ” በነባራዊው ዓለም ወይም ምድር ላይ የሌለ ቢሆንም ደራሲው የራሱን “ቦታ” ወይም “ዓለም” ሊፈጥር ይችላል። ይሄ ሁሉ ሆኖም ግን በጭብጥ ደረጃ ሳይንሳዊ ልብ ወለድም ቢሆን ነገ ሊሆኑ፣ ሊከሰቱ፣ ሊደረጉ የሚችሉ ነገሮችን ዛሬ ካለው እውነታ ላይ ተመስርቶ ይገምታል፣ ትንበያ ይሰጣል እንጂ መልዕክቱ በከንቱ የሚታይ ቅዠት ወይም ሙሉ በሙሉ ከገሃዱ ዓለም የወጣ ውሸት አይደለም።
የኮንታጅን ፊልም ነገር
በነገራችን ላይ ፊልም በልብ ወለድ መልክ ይጻፋል፤ ፊልም የሚባለው ለዚህ ጽሁፍ አውድ እንዲመች ተደርጎ በአጭሩ ሲተረጎም ልብ ወለድ (አጭር ወይም ረጅም) ጽሁፎች በተንቀሳቃሽ ምስሎችና በድምጽ ታጅበው ከማንበብ ይልቅ ሰዎች እንዲያይዋቸው ሲደረጉ ነው ማለት ይቻላል። ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት በፈረንጆቹ 2001 ዓ.ም ተሠርቶ ለዕይታ የበቃ የአሜሪካ ፊልም ነው። ዘውጉ ደግሞ ከሳይንሳዊ ልብ ወለዶች የሚመዘዝ ነው። ታዲያ በስኮት ዜድ. በርንስ ተጽፎ በስቴቨን ሶደርበርግ ዳይሬክት የተደረገውና እንደነ ማት ዴመንና ኬት ዌንስሌት የመሳሰሉ የፊልሙ ዓለም ዝነኛ ኮከቦች የተሳተፉበት ‹‹ኮንታጅን›› የሚል መጠሪያ ተሰጠው ይህ ፊልም ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ መላ ዓለምን እንደ አዲስ እያነጋገረ ይገኛል። ምክንያቱ ደግሞ በዘመናችን አሉ ከተባሉ ሁሉንም ነገር ቀድመን እንድናውቅ ከላይ ተቀብተናል ከሚሉ “እግዜር በምድር” ነን ባይ ነቢያት ይልቅ አሁን ላይ ዓለምን እያስጨነቃት የሚገኘውን የኮሮና ወረርሽኝ በትክክል መተንበይ መቻሉ ነው። በኮንታጅን ፊልም ውስጥ የተካተቱ ጉዳዮች ከ “ሀ” እስከ “ፐ” አሁን ላይ በኮሮና ወረርሽኝ ጥላ ሥር ባለችው በገሃድዋ ዓለማችን ውስጥ እየተፈፀሙ መሆናቸው መላ ዓለሙን አጃኢብ አስብሏል። መደነቅ ብቻም ሳይሆን “ይህ ነገር በሳይንሳዊ ልብ ወለድ የተተነበየ የፊልም ትንበያ ወይስ እንደ ኦሪት ዘመን በነቢያት የተነገረ የትንቢት ቃል?” ብለን እንድንጠይቅና አያን ራንድ እንዳለችው “ሐሳቡን ቆም ብለን እንድንመረምረውና እንድናጤነውም” አስገድዶናል።
ይህን ለማለት የተገደድንበትን ምክንያት በጥቂቱ ገለጥ አድርገን ለማየትና ለማሳየት እንሞክር ። መቼቱ ከላይ እንዳመላከትነው በፊልሙ ውስጥ ታሪኩ የሚከወንበት ቦታና ጊዜን የሚያመላክት ሲሆን፤ የኮንታጅን ፊልም መቼት መነሻ ቻይና ውስጥ፣ ከቻይናም ሁዋን የተባለችው ግዛት ናት። የአሁኑ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መነሻም ይህችው የቻይናዋ ማዕከላዊ ግዛት መዲና የሆነችው ሁዋን ከተማ ናት።
የኮንታጅን ቫይረስ እና የኮሮና ቫይረስ
በፊልሙ ውስጥ በስፋትና በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው እየተላለፈ ዓለምን ሲያስጨናንቅ የምንመለከተው አደገኛ ተላላፊ ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው ከሌሊት ወፍ ሲሆን፤ የኮሮና ቫይረስ መገኛም ይህችው የሌሊት ወፍ መሆኗን ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። የበሽታው መንስኤው ደግሞ ቫይረስ ሲሆን ዝርያውም “Novel” (አዲስ) መሆኑን ፊልሙ ውስጥ እንመለከታለን። በታህሳስ 2019 በቻይናዋ ሁዋን ግዛት የተከሰተውና አሁን ላይ ዓለማችንን እያስጨነቃት የሚገኘው የኮቪድ-19 ወረርሽኝም እንደ ኮንታጂኑ ወረርሽኝ ሁሉ መንስኤው ቫይረስ ሲሆን ዝርያውም እንደዚሁ ከዚህ በፊት ተከስቶ የማያውቅ አዲስ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ነግረውናል።
ኮንታጅን ላይ የምንመለከተው በሽታ የሚያጠቃው የመተንፈሻ አካላትን ሲሆን ዋነኛ ምልክቱ ማስነጠስ፣ ሳልና ትኩሳት ናቸው። የኮሮና ቫይረስም የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ሲሆን በተለይም ጉረሮን አልፎ ሳንባ ጋር ከደረሰ ለህልፈት ይዳርጋል። የፊልሙ በሽታ ዋነኛ ምልክቶች የሆኑት ማስነጠስ፣ ሳልና ትኩሳት ምንም ሳይጨመሩ ሳይቀንሱ የኮቪድ-19 መለያ ምልክቶችም ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። የፊልሙ በሽታ ዋነኛ መተላለፊያ መንገዱ የእጅ ሰላምታን ጨምሮ አካላዊ ንክኪ ሲሆን፤ በዚህም በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ማናቸውም ዕቃዎች በሚነኩበት ጊዜ ቫይረሱን ወደ ጤነኛ ሰው ያስተላልፋሉ። ስለሆነም የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጠጣርና ለመከላከል ሰዎች ከሰላምታና ከመጨባበጥ ሲታቀቡ፣ እንደ ትምህርት ቤት፣ የገበያ ማዕከላትና ሱቆችን የመሳሰሉ ሰው የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ሲዘጉና ማህበራዊ መስተጋብር የሚፈጠርባቸው ሁነቶችም ማዕቀብ ሲጣልባቸው፣ የበሽታውን መዛመት ለመከላከል ሰዎች አካላዊና ማህበራዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ሲደረግ በአስገራሚው ፊልም ውስጥ እንመለከታለን።
እነሆ ያኔ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በኮንታጅን ፊልም ውስጥ ያለውን በሽታ ለመከላከል ሲደረጉ ያየናቸው እነዚህ ዘዴዎች ዛሬ ላይ ከኮሮና ወረርሽኝ ለመትረፍ ብቸኛ የመዳኛ መንገድ ሆነው ከጤና ጠበብቶቻችን እንደ አቅጣጫ ወርደውልን ሁላችንም እየተገበርናቸው እንገኛለን። አገራት ሱቆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ድንበሮቻቸውንም ዘግተው፣ ዜጎቻቸው በር ዘግተው ቤታቸው ውስጥ እንዲውሉ በማድረግ ኮሮናን እየተዋጉ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ የኮንታጅኑን በሽታ ለመከላከል ዋነኛው አማራጭ እጅን ቶሎ ቶሎ መታጠብ ሲሆን ይኸው በእኛ ዘመን የተከሰተው የጋሃዱ ዓለም የኮሮና በሽታ መፍትሔም እጃችን ላይ መሆኑ በጥብቅ ስለተነገረን አዘውትረን እጃችን እየታጠብን እንገኛለን።
ምን ይሄ ብቻ፣ “ተአምረኛው” ፊልም ገጸ ባህሪያትን ሳይቀር ተንብይዋል። በኮንታጅን ፊልም ውስጥ ያለው ወረርሽኝ በሽታ በተቀሰቀሰበት ወቅት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጥቁር መሆኑን እንመለከታለን። እነሆ የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት የዓለም የጤና ድርጅት ግማሽ ምዕተ ዓመትን ባስቆጠረ ዕድሜው በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያዊው ጥቁር ሰው በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ዋና ዳይሬክተርነት እየተመራ ይገኛል። ሌላም አለ፤ በፊልሙ ውስጥ ቻይናዊ ገጸ ባህርይን ወክሎ የሚጫወት ሰው ቫይረሱን አሜሪካ ሆን ብላ እንደለቀቀችውና የዓለም የጤና ድርጅት በድብቅ እንደያዘው ይገልፃል። እነሆ በአሁኑ ሰዓት በእውነተኛው ዓለም በገሃድ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ልክ ፊልሙ ላይ እንዳለው “ኮሮና ቫይረስን እኛን ለማጥቃት አስባ አሜሪካ ናት ሆን ብላ የፈጠረችው” በሚል ቻይና ከአሜሪካ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ እንዳለች ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው።
አሜሪካ በበኩሏ ቫይረሱን ቻይና ናት የፈጠረችው በሚል ተቀናቃኟን አጥብቃ የምትከስ ሲሆን በሌሎች ተወግዛ እስክትመለስ ድረስ ለበሽታው “የቻይና ቫይረስ” የሚል ስም እስከመስጠት ደርሳ እንደ ነበር ሁላችንም እናውቃለን። ጉዳዩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ኮሮናን በሚመለከት “ቫይረሱ ወደ ሌላው ዓለም እስኪሰራጭ ድረስ ሆን ብላ አፍናው ቆይታለች” በሚል አሜሪካ ከቻይና ጋር የገባችበትን እስጥ አገባ ከማባባስ ባሻገር “ለቻይና አዳልቷል” በሚል የዓለም የጤና ድርጅትንም እስከመክሰስና ለድርጅቱ የምታደርገውን የገንዘብ መዋጮ በጊዜያዊነት እስከመከልከል ደርሳለች።
ታዲያ “ኮንታጅን” ምንድነው?
እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ማሳያዎች ስንመለከት የኮንታጅንን ጉዳይ እንደ ተራ ግጥምጥሞሽ አይተነው እንደ ዋዛ ልናልፈው እንችላለን? አናልፈውም! የአያን ራንድን ቴክኒክ ተጠቅመን ጉዳዩን “ሲሪየስሊ” ልናጤነው እንገደዳለን እንጂ! እናም እንጠይቃለን “በውኑ ይህ ፊልም እንደ ሌሎች ሳይንሳዊ ልብ ወለዶች ሁሉ በተወሰነ ደረጃ የወደፊቱን ሁነት አስቀድሞ ያመላከተ ነው በሚል ብቻ ልናልፈው እንችላለን?” “እውን ኮንታጅን ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልም ብቻ ነውን?” “እና ታዲያ ኮንታጅን ምንድነው?”
እዚህ ላይ አንድ መቶ ፐርሰንት እርግጠኛ የሆነ መረጃና ማስረጃ ማቅረብ ስለማይቻል “ኮንታጅን ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልም አይደለም” የሚል ድምዳሜ ላልሰጥ እችላለሁ። ልብ ወለድ ብቻ አለመሆኑን ግን እርግጠኛ ሆኜ ልነግራችሁ እችላለሁ። ይህ የራሴ እይታ ነው፤ ይህንንም በበቂ ማስረጃ በማስደገፍ እስከ መጨረሻው ልከራከርበት እችላለሁ። ለማንኛውም እይታችንን ለመጋራት እንጅ ማንም በእኔ ሐሳብ የመስማማት ግዴታ ስለሌለበት በጉዳዩ ላይ መርምሬ የደረስኩበትን የራሴን እይታ አካፍያችሁ ልለፍ። በግሌ ኮንታጅን ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልም ብቻ ነው የሚለውን ሃሳብ አምኖ ለመቀበል ይቸግረኛል። ይህን የምልበት የመጀመሪያው አመክኖዬ ከላይ “የሣይንሳዊ ልብ ወለዶች ጉዳይ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ለመጠቆም እንደሞከርኩት ልብ ወለድ “የፈጠራ ድርሰት” ነው ሲባል በእውነታ ላይ ተመስርቶ የሚጻፍ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ እንጂ የሌለውን የሚያወራ በሬ ወለደ ዓይነት ውሸት አይደለም።
ሳይንሳዊ ልብ ወለድም እንዲሁ በሌሎች የልብ ወለድ ዓይነቶች የማይቻለውን ያለና የነበረውን ብቻ ሳይሆን የሌለውንም ግን ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የወደፊቱንም ጊዜ “የመፍጠር” እና ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችንም አስቀድሞ የማለም (Imagination) ነፃነት የተሰጠው ቢሆንም ጭብጡ ግን “ካለው ነገር ላይ ከአሁኑ ጊዜ ተነስቶ” ወደፊት ሊሆን የሚችለውን መገመት እንጂ መተንበይ የማይችል በመሆኑ ነው።
በዚህ መሰረት ከስሙ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ከኮቪድ-19 ጋር አንድ ዓይነት የሆነ በሽታን አስቀድሞ መፍጠር የቻለው በሳይንሳዊ ልብ ወለድ መንገድ ተጽፎ ወደ ፊልም ተቀይሮ ለዕይታ የበቃው ኮንታጅን ፊልም ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ትንበያ ለመስጠት የሚያስችል ነባራዊ መሰረት ነበረው ማለት ነው። ወይም በሌላ አባባል ፊልሙ በሚሰራበት ወቅት ኮሮናን የሚመስል በሽታ በገሃዱ ዓለም ነበረ ማለት ነው። እናም በገሃዱ ዓለም የነበረውን እውነታ መነሻ አድርጎ መጭውን ጊዜ በምናብ በመሳል (Visulalize) በማድረግ የተሰራው ኮንታጅን ፊልም መጭውን ጊዜ በትክክል “መተንበይ” ችሏል ማለት ነው። ይህም ደግሞ ሁሉን ከሚያውቀው ከእግዚአብሔር መንፈስ ካልተሰጠ በቀር በሰዎች አቅም ብቻ የማይቻል ነውና! መተንበይ ወይንም ትንቢት መናገር መገመት ሳይሆን የወደፊቱን ጊዜ ቀድሞ ማወቅን ይጠይቃልና!
ኮንታጅንን የሰሩ ሰዎች ያደረጉት ግን ይህን ነው። ወደፊት የሚሆነውን መገመት ብቻ ሳይሆን በትክክል መተንበይ “ችለዋል”። ይሄ ደግሞ ሰዎቹ ወደፊት ስለሚሆነው ክስተት የሚያውቁት ነገር ነበር ማለት ነው ወደሚለው ይወስደናል። ስለዚህም ኮንታጅን ልብ ወለድ ብቻ አይደለም፤ በሳይንሳዊ ትንበያ (Hypothesis) መገመት ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚሆነውን ቀድሞ አውቋልና!
ኮሮና ኮንታጅን ሪሚክስ ወይስ…?
“ወደፊት ስለሚሆነው ክስተት የሚያውቁት ነገር ነበር ማለት ነው” የምትለውን አመክንዮዋዊ መዳረሻዬን በልባችሁ ያዙልኝና በጥሞና ተከተሉኝ። “እንዴ ይሄ ነገር!” የሚያስብል ይፋዊ ማስረጃ (Officiall evidence) እጨምርላችኋለሁ። የኮንታጅንን ፊልም አሰራር አስመልክቶ ዊኪፒዲያ ላይ በግልጽ የተቀመጠው መረጃ እንደወረደ ላቅርብላችሁ “…Soderbergh (film director) and Screen writer Scott Z. Burns discussed a film depicting the sprid of the virus, inspired by pandemics such as the 2002-2004 SARS outbreak and the 2009 Flu pandemic” አያችሁ! “ዳይሬክተሩ ሶደርበርግና ድርሰቱ ጸሐፊ ስኮት በርንስ የ2002-2004ቱን ሳርስ ወረርሽኝና የ2009ኙን የኢንፍልዌንዛ ወረርሽኝ ከተመለከቱ በኋላ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በፍጥነት የሚዛመት ቫይረስን የሚያሳይ ፊልም ለመሥራት ተወያዩ” እኮ ነው የሚለን። ይሄ ብቻ መስሏችሁ ነው እንዴ? ፊልም ሠሪዎቹ ብቻቸውን እኮ አይደለም አምሳለ ኮሮና የሆነውን የኮንታጅን ቫይረስ በፊልም ለመሥራት የተወያዩት፤ በዘርፉ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን አማክረዋል፤ ያውም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የታላቁ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካዮችንና እንደ ደብልዩ. ኢያን ሊፕኪን እና ላውረንስ (ላሪ ብሪሊያንት) የመሳሰሉ እውቅ የህክምና ጠበብቶችን አማክረዋል። ታዲያ ይሄ እንዴት “ልብ ወለድ ፊልም ብቻ” ሊሆን ይችላል? ልብ ወለድ ፊልም እኮ የገሃዱን ዓለም የሚያንፀባርቅ አዕምሯዊ ፈጠራ እንጂ የተፈፀመን እውነት ድጋሚ አሻሽሎ የሚያቀርብ የዲጄ “ሪሚክስ” አይደለም። ኮንታጅን ያደረገው ግን ይህንኑ ነው።
የኮሮናን መንትያ የሳርስ ቫይረስ ወረርሽኝን መሰረት አድርጎ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን አካል እና የህክምና ተመራማሪዎችን አማክሮ ነውና ፊልሙ የተሠራው! እናም ኮንታጅን ላይ በፊልም መልክ የተሠራውና አሁን ላይ በገሃዱ ዓለም የተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት ሆነው አረፉት! ታዲያ ይሄ ልብ ወለድ ፊልም ነው? እናም በእኔ እይታ ኮንታጅን እንደሌሎች ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልሞች ነባራዊውን እውነታ መሠረት አድርጎ ስለ መጭው ጊዜ ሳይንሳዊ ትንበያ ወይም ግምት (Scientific prediction) በፈጠራ የተሰራ “ልብ ወለድ ፊልም” ሳይሆን ሰሪዎቹም እንዳመኑት የኮሮናን መንትያ መሠረት አድርጎ በባለሙያ ምክር በጥናት የተሠራ “ዘጋቢ ፊልም” ነው።
አይ የወደፊቱን ክስተት “በትክክል” ያስቀመጠ “ጥበበኛ” ፊልም ነው ካላችሁኝ ደግሞ ኮንታጅን ዳይሬክት የተደረገው በሰው ሳይሆን በመንፈስ ዳይሬክት የተደረገ መሆን አለበት፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ፊልምነቱ ቀርቶ ትንቢት ይሆናል ማለት ነው። የወደፊቱን ጊዜ በትክክል መተንበይ የሚችል ልብ ወለድ ወይም ፊልም ሳይሆን ትንቢት ነውና! ትንቢት አልኩ እንዴ? በዚሁ ካነሳነው አይቀር ሳምንት ስለ ትንቢት እንነጋገራለን፣ ኮሮናን ተንተርሰን ትንቢተኞቻችን በትንቢት ሚዛን ላይ አስቀምጠን ሃሳብን እንመረምራለን! ይቆየን፣ ኮንታጅን ላይ ያለውን ወረርሽኝ ያሳለፈ አምላክ ኮሮናንም ያሳልፍልን፤ ፈጣሪያችን በቃችሁ ይበለን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012
ይበል ካሳ