በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ የንግድ ማዕከል በሆነችው ሌጎስ የህዝብ እንቅስቃሴ ከታገደ ሳምንታትን አስቆጠሯል። የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ‹‹የቫይረሱን መዛመት ለመከላከል ብቸኛው አማራጭ ይሄ ነው ፤ ይህ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው›› ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ አዋሳኝ የድንበር መግቢያዎች ሁሉ እንዲዘጉና ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግም ውሳኔ አስተላልፈዋል።
በርግጥም በሁሉም አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ተገድቦ የመቀመጡ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ የሚሆንበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። በኢትዮጵያ በመጀመሪያ ተሕዋሱ ከተገኘበት ጃፓናዊ ጀምሮ ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸውና ሌሎች እስከ ዛሬ ድረስ በቫይረሱ መጠቃታቸው እየተገለጸ በማቆያ የተቀመጡት ሁሉ ራሳቸው ከወረርሽኙ እንዲፈወሱና ለሌሎች እንዳያስተላልፉ ለመቆጣጠር ሲባል መሆኑ ግልጽ ነው።
አብዛኖቹ በቫይረሱ የተያዙት ዜጎቻችን በተለይ ከዱባይ ተመላሾች መሆናቸው በመረጋገጡ ከውጭ አገራት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በልዩ ማቆያ እንዲቀመጡ መደረጉ፣ የቆይታ ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ ምርመራ ተደርጎላቸውም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸው ችግሩ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስና የሕይወት ዋጋ እንዳያስከፍል የሚደረግ የጥንቃቄ አካል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ከቻይና ዉሀን ግዛት ተነስቶ መላው ዓለምን ያጥለቀለቀው ኮሮና ቫይረስ ትናንት ማምሻው ድረስ በአሜሪካ ከ43 ሺ 518 ፣ በስፔይን 20 ሺ 852፣ በጣሊያን 24 ሺ 114፣በፈረንሳይ 20 ሺ 265፣በእንግሊዝ 16 ሺ 509 በላይ ዜጎቻቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአገራችንም በቫይረሱ የተጠቁት 114 የደረሱ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሯ በየቀኑ ከሚሰጡት መግለጫ እየተረዳን ነው።
ይሁን እንጂ በአገራችን የተጠቂዎች ቁጥር አነስተኛ ቢመስልም፤ የበለጠ ተስፋፍቶ በርካታ ዜጎች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች፣ አርቲስቶችና ታላላቅ የኃይማኖት አባቶች ማሳሰቢያና ትምህርት ቢሰጡም ፤በቤት ውስጥ በመቀመጥ መከላከል እንዲደረግ ቢነገርም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ክልከላውን በቸልታ በማለፍ ያሻቸውን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይታያል።
በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈሪው ጉዳይ በቤት ውስጥ መቀመጥን ያለመፈለግና ራስን አግልሎ ደህንነ ትን ለመጠበቅ ያለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ህጋዊ ሆነው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት እንዲሁም ካለ ቁጥጥር ሰፊውን የአገሪቱን ድንበር እያቋረጡ ከህብረተሰቡ ጋር የሚቀላ ቀሉት ወገኖቻችን ናቸው። እነዚህ ወገኖቻችን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የቱን ያህል ጥንቃቄ እንዳደ ረጉ ማስረጃ ባይኖርም ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው በማሰብ በመዘናጋት ሊከሰት ከሚችለው የቫይረስ ስርጭት ራሳቸውን ጠብቀው ቤተሰቦቻቸውንም እንዲታደጉ ማድረግ ይጠበቃል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከደቡብ፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ የአገሪቱ አዋሳኝ አገሮች ወደ አገራችን የሚገቡ ዜጎች ከህብረተሰቡ ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት ተገልለው የሚቆዩበት የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት በአፋጣኝ ተግባራዊ ካልተደረገ ከቫይረሱ ጋር ንክኪነት ያልነበራቸውና በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኙ በርካታ ወገኖቻችን ለወረርሽኑ ተጋልጠው መቆጣጠር የማይቻል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባን በመሆኑ የክልል የአስተዳደር አካላትም ሆኑ ለቁጥጥር የተሰማሩ የፀጥታ አካላት በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14 ቀን 2012 ዓም