የሃይድሮጂን ጋዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ሰራሽ መልክ የተሠራው በ16ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ የመጀመሪያው የነዳጅ ምርትና እና ኤሌክትሮላይትስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ተሠርተዋል። ሆኖም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከውሃ ሃይድሮጂን እና ኦክስጅንን በኤሌክትሪክ በመከፋፈል ሃይድሮጂንን የሚያመርተው የኤሌክትሮላይዜሽን ምርት ዋጋ በጣም ውድ ነበር። በአሁን ወቅት ይህ ሁሉ ተቀይሯል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የኤሌክትሮክላውተር በሜጋ ዋት ከሁለት እስከ አራት ሚሊየን ዩሮ የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ግማሽ ሚሊየን ደርሷል:: ይህ ማለት ሃይድሮጂንን ለማመንጨት የሚያስፈልገው ኤልክትሪክ በአሁኑ ወቅት የምርት ዋጋውን ሦስት አራተኛ የሚወስደው ራሱ ሆኗል። የአረንጓዴ ኤሌክትሪክ በየቀኑ እየቀነሰ ሲመጣ አነስተኛ ዋጋ ያለው ሃይድሮጂን እንዲፈጠር አድርጎታል። ከፀሐይ እና ከነፋስ ጋር በተመሳሳይ መልኩ የምርት መጠን እያደገ ሲሄድ የሃይድሮጂን ምርት ዋጋ በጣም እየቀነሰ መጥቷል።
የመጀመሪያውን ሃይድሮጂን ሃይል የሚጠቀም ማህበረሰብ ለመፍጠር ደቡብ ኮሪያ ሩጫዋን ለማሸነፍ እየጣረች ነው። በአረንጓዴው ቴክኖሎጂ ውስጥ መሪ እንደመሆኗ መጠን ሦስት በሃይድሮጂን ሃይል የተሠሩ ከተሞችን እ.ኤ.አ በ2022 ለመገንባት ዕቅድ ይዛ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ዕቅዱ ከተሞች ሃይድሮጂንን ለማቀዝቀዣነት፣ ለማሞቂያነት፣ ለመብራት ኤሌክትሪክ እና ለመጓጓዣነት እንዲያውሉ ታስቦ ነው። ሦስቱ ከተሞች የት እንደሚሆኑ ምክክር በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ለሙከራ በሚገነቡ ከተሞች ውስጥ አውቶቡሶችንና የግል መኪኖችን ጨምሮ ሃይድሮጂን የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ይጠቀማሉ። የሃይድሮጂን ኃይል መሙያ ጣቢያዎች በአውቶቡስ ጣቢያዎች እና በመኪና ማቆሚያዎች ውስጥ ይገነባል።
ዕቅዱ እ.ኤ.አ 2030 በአገሪቱ የሚገኙ ከተሞች 10 በመቶ የሚሆነውን ሃይል ከሃይድሮጂን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ 2040 ላይ ደግሞ ከተሞቹ 30 በመቶ የሃይል ምንጫቸው ሃይድሮጂን እንዲሆን ታስቧል:: ይህ ሁኔታ በቀጣይ ሦስት ዓመታት በሃይድሮጂን የሚሠሩ መኪናዎችና ኃይል (ቻርጅ) መሙያ ጣቢያዎች ግንባታ እንዲጨምር ያደርጋል:: ለሃይድሮጂን ሃይል የሚሠሩ መኪናዎች ለመገጣጠምና ሃይል መሙያ ጣቢዎችን ለመገንባት የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ድጎማ ያደርጋል::
እ.ኤ.አ 2019 ህዳር ወር የደቡብ ኮሪያ የመሬት፣ መሠረተ ልማት፣ የትራንስፖርትና የቱሪዝም ሚኒስቴር የሚጠቀሙ የተመረጡ ከተሞች ላይ የሃይድሮጅን ሃይል ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረው ነበር:: በእ.ኤ.አ 2020 ታህሳስ ወር ላይ የሃይድሮጅን ሃይል የሚጠቀሙ ከተሞች የሚመረጡ ሲሆን፣ ከተሞች ላይ ከሦስት እስከ አስር ኪሎ ሜትር የሃይድሮጂን ሃይል የሚጠቀሙ የትራንስፖርት አገልግሎት መሰጠት ይጀምራል:: በወቅቱም 825 ሺህ በሃይድሮጂን የሚሠሩ መኪናዎች እና 12 ሺህ አውቶቡሶች አገልግሎት ላይ መዋል ይጀምራሉ::
ጀርመን፣ ጃፓንና ቻይናን ጨምሮ አገራት ለወደፊቱ የሃይድሮጂን ሃይል የሚጠቀም ህብረተሰብን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ይገኛል። አገራቱ ከሃዩንዳይ፣ ከቶዮታ እና ከሆንዳ መኪና አምራች ድርጅቶች ጋር በሃይድሮጂን ሃይል የሚሠሩ መኪኖችን ለመፍጠር ድርድር እያደረጉም ይገኛሉ። በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ከኤሌክትሪክ ከሚሠሩ ተሽከርካሪዎች የበለጠ ሰፋ ያለ እና ፈጣን የነዳጅ ሙሌት ይፈልጋል። በሃይድሮጂን ሃይል የሚሠሩ መኪናዎች ወደ ንፁህ አየር ንብረት ለመፍጠር የሚደረገውን ሽግግርን ያፋጥናሉ የሚል ታላቅ ተስፋ አለ።
ነገር ግን የተለያዩ ችግሮች ከቴክኖሎጂው ጋር አብረው መምጣታቸው አይቀርም። ምንም እንኳን በነዳጅ የሚሠሩ መኪናዎች አሁን በገበያው ላይ ቢሆኑም ለብዙ ወጪዎች የሚዳርጉ በመሆናቸው ወደ ዋነኛ መጠቀሚያነት ከመግባታቸው በፊት አሁንም ክልከላ ሊደረግባቸው ይገባል። በሃይድሮጂን ከሚሠሩ መኪናዎች የሚመጣው ውጤት ጥሩ ቢመስልም ከመኪናዎቹ የሚወጣው ውሃ የተበከለ ሰለሚሆን እንደታሰበው ንፁህ አየር ላይፈጥሩ ይችላሉ። ሃይድሮጂንን ማምረት እራሱ ጉልበት የተሞላበት ሂደት የሚፈጥረው እንጂ ታዳሽ በሆኑ የሃይል ምንጮች የተገነባ አይደለም።
ሌላው ዋነኛው ጉዳይ የሃይድሮጂን የመፈንዳት ሁኔታው ከፍተኛ በመሆኑ የደህንነት ሥጋቶችን እየፈጠረ ይገኛል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በደቡብ ኮሪያ መንግሥት የምርምር ፕሮጀክቶች ውስጥ የሃይድሮጂን ማጠራቀሚያ ታንክ ፍንዳታ ምክንያት ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ሠራተኞች ቆስለዋል። የጋዝ ማከማቻው ብዙ መሠረተ ልማት የሚጠይቅ ሲሆን፣ መንግሥት የልማት ሥራዎችን ለማበረታታት የሚያደርገው ማበረታቻ ቢኖርም ሃይድሮጂን በጣም የተስፋፋ እንዲሆን የግል ባለሀብቶች መታገል አለባቸው።
ነገር ግን እነዚህ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የሃይድሮጂን ሃይል አጠቃቀም የግድ መተግበር አለበት። በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት የሙቀት መጨመርን ለመገደብ በሚያስቡበት ጊዜ የሃይድሮጂን ሃይል ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ለውጦች ውስጥ ቁልፍ ሊሆን ይችላል። አማካሪ ማኪንሴይ እና የኩባንያው የሃይድሮጂን የሃይል አማራጮች በሰባት ቁልፍ መንገዶች እንደሚቀይር ይገምታሉ። እናም በነዳጅ የሚሠሩ መኪናዎች ከገበያ የመውጣት ዕድላቸው የሚያሰፋ እንደሚሆን ይጠበቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ መንግሥታት በየዓመቱ ለሃይድሮጂን ሃይል ግንባታ ወደ 850 ሚሊየን ዶላር ያህል መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ መሆኑን የማኪንሴይ የ2017 ሪፖርት ያሳያል:: ነገር ግን ከፍተና ደረጃ ላይ ለማድረስና በዝቅተኛ ወጪ ለማቅረብ አሁንም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012
መርድ ክፍሉ