
ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ተፎካካሪ ሊያደርጋት የሚችል አቅም እንዳላት ብዙ ጊዜ ሲነገር ቆይቷል። እንደ ሀገር እግር ኳሱ ለሚጓዝበት የኋሊት መንገድ በዋናነት ችግሩ ከታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ከምልመላ አንስቶ እስከ ሥልጠና ያለው ሂደትና አሠራር ኋላ ቀርና የተበላሸ መሆኑ ትልቁ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል።
እንደ ሀገር የሚስተዋለው የተጫዋቾች የምልመላና ሥልጠና ያለበት ሰፊ ክፍተት ወደፊት ስፖርቱን መለወጡ የሚችሉ በርካታ ታዳጊና ወጣት ተስፈኛ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾችን ወደፊት እንዳይመጡ እንቅፋት መሆኑ አያከራክርም። ያምሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች አንዳንድ ታዳጊና ወጣት ተስፈኛ ተጫዋቾች በዚህ ረገድ እንደ ሀገር ያለውን ችግር በመረዳት ህልማቸው እውን ይሆን ዘንድ በሌሎች የተሻለ የእግር ኳስ የሥልጠና ሥርዓት ባላቸው ሀገራት ክለቦችና አካዳሚዎቻቸው የሥልጠና እድል ለማግኘት በግላቸው ሲጥሩ ይስተዋላል።
ከአራት ዓመት በፊት ከወላይታ ዞን ሁምቦ ወረዳ የተገኘው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ይበልጣል ኤልያስ በራሱ ጥረት ከኢትዮጵያ ቡና ታዳጊ ቡድን ተነስቶ ወደ ስፔኑ የባርሴሎና ታላቅ አካዳሚ ላሜሲያ የመሰልጠን እድል ማግኘቱ ይታወሳል። ወጣት ይበልጣል ኤሊያስ በወቅቱ ወደ ስፔን ካቀና በኋላ በአካዳሚው ለመቆየት የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ስለነበረበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ ብዙዎች እገዛ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የስፔን እግር ኳስ ሕይወቱን እንደ አዲስ በባርሴሎና አካዳሚ በማጎልበት ወደ ታላቅ ደረጃ ለመሸጋገር ህልም የነበረው ተስፈኛ ታዳጊ ይበልጣል ኤልያስ 11 ቁጥር ማለያ በመልበስ የመጀመሪያው ወዳጅነት ጨዋታ አሰላለፍ ምርጥ-11 ውስጥ ለመካተት ብዙ ጊዜ አላስፈለገውም። ከዚያ በኋላ በባርሴሎና አካዳሚ የእግር ኳስ ሥልጠናውን እየወሰደ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ እንደሚገኝም ዘገባዎች ወጥተዋል። በ2023 በካታላን የአካዳሚዎች የሊግ ውድድር ላይ በተሳተፈው ኮሴካ የመጨረሻ ጨዋታ ሳንታን 7-3 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ይበልጣል ኤልያስ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ሁለት ጎል ለሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ማቀበሉም በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።
ልክ እንደ ይበልጣል ሁሉ በተመሳሳይ የእግር ኳስ ጎዳና ላይ የሚገኝ አንድ ታዳጊ ተስፈኛ ብቅ ብሎ የሌሎችን ድጋፍ እንደሚሻ ኢቢሲ በቅርቡ ዘግቦ ነበር። ይህ ታዳጊ ተጫዋች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሚስተዋሉበት የጎሉ ችግሮች አንዱ የሆነው የግብ ጠባቂ ተጫዋች ነው።
እግር ኳስን ከትምህርት ቤት የጀመረው እና በስፖርቱ ትልቅ ደረጃ የመድረስን ህልም ያነገበው ወጣት አማረ አደላ፤ ከአማራ ክልል ደቡብ ሜጫ ወረዳ የተሻለ ሥልጠናን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ይናገራል። ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘው ወጣት ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በፕሪሚር ስኪል አካዳሚ የግብ ጠባቂነት ሥልጠናውን እየተከታተለ ይገኛል።
በአካዳሚ ቆይታው ባሳየው ድንቅ ብቃት የእግር ኳስን ሕይወቱን ወደ ፕሮፌሽናልነት የሚቀይርበት ዕድልም ገጥሞታል። ወጣቱ የማህበራዊ ትስስር ገፁን በአግባቡ በመጠቀም፤ ስፔን ሀገር ወደሚገኝ የታችኛው እርከን የእግር ኳስ ክለብ የሚወስደውን ዕድል አግኝቷል።
በስፔን የታችኛው እርከን የቅድመ ፕሮፌሽናል ዕድል ያገኘው ግብ ጠባቂው፤ ወጪውን በተመለከተ የእግር ኳስ ክለቡ 75 በመቶውን ሲሸፍንለት እርሱ ደግሞ 25 በመቶውን መሸፈን እንደሚጠበቅበት ታውቋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ድጋፍ ተደርጎለት የጉዞ ሂደቱን ቢያጠናቀቅም ከደቡብ ሜጫ የተነሳውን ህልሙን ወደ አውሮፓ ለማድረስ 25 በመቶውን የወጪ ድጋፍ ይፈልጋል።
“ህልሜ የሀገሬ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን መለያ ለብሶ መጫወት ነው” የሚለው አማረ፤ ወደ አውሮፓ ሄዶ መጫወት ደግሞ እንደ አንድ የስፖርት ሰው በተሻለ መንገድ እራስን ለመገንባትና ለብሔራዊ ቡድን ለመመረጥም ትልቁን አስተዋጽኦ ያደርጋል ሲል ለኢቢሲ ተናግሯል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም