አገራችን ኢትዮጵያ በችግሯ ጊዜ ከጠላት አብረውና ዜጋቸውን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው ጡቷን የነከሱ ክፉዎችን አላጣችም። በኢጣሊያ ወረራ ዘመን ለፋሽሸት ያበሩ ሚስጢር ያቀበሉና ወገናቸውን ከጀርባ የወጉ ባንዳዎች ታሪካቸውን አበላሽተው አልፈዋል።
ህዝብ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ጊዜም የፍጆታ ዕቃዎችን በመደበቅና ከችግሩ እልፍ በማትረፍ በህዝብ ስቃይ ለመነገድ የሞከሩ ባንዳዎች በፊትም ነበሩ አሁንም በኮሮና ዘመን ታይተዋል። በዚያም ሆነ በዚህ መልኩ አገራቸውን ያደሙና ወገናቸውን የጎዱ ባንዳዎች አስተሳሰብ እኔና እኔ ብቻ ነውና አገር ወገን ይሉት ነገር ለእነሱ ምንም አይደለም።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከአገሬና ከህዝቤ በፊት እኔ ያሉ መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን ለመስዋዕትነት ያቀረቡና በደምና በአጥንታቸው ክፋይ የዛሬዋን ኢትጵያን ጠብቀው ያሰረከቡን እልፍ ዜጎች ከእምዬ ኢትዮጵያ ተገኝተዋል። እኒህ ወድ ኢትዮጵያውያን በኢጣሊያ፣ በግብጽ፣ በሶማሊያና በባድሜ ወረራ ወቅት የአገራችን ህልውና ሲደፈር ቆመን ከምናይ ሞታችንን እንመርጣለን በማለት አኩሪ የህይወትና የአካል መስዋዕትነትን ክፍለው ታሪካቸውን በወርቅ መዘገብ ላይ ጽፈዋል። በዚህም የአገራቸውን ሉኣላዊነት አስከብረው የዜጎቻቸውን ነፃነትና ደህነነት አስከብረዋል።
ከጦር ሜዳው ባሻገር አገርና ሀዝብ በማናቸውም ሁኔታ ለአደጋ ተጋልጠው ህልውናቸው አሳሳቢ ሲሆን ከእኔ በፊት አገሬና ወገኔ ብለው ድጋፍ በማሰባሰብና ያላቸውን በማጋራት ዘመን የማይሽረው ታሪክን የፈፀሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። እኒህ ወድና ብርቅ ኢትዮጵያውያን አገራችንና ህዝቧ በተለያየ ጊዜ በገጠማቸው የድርቅ፣ የርሃብ፣ የጎርፍ፣ የወረርሽኝ አደጋ ወቅት ለወገናቸው ደርሰው የብዙዎችን ህይወት ታድገዋል፣ አሁንም እየታደጉ ይገኛሉ። የአገርና የህዘብ ጉዳይ ደንታ ከማይሰጣቸው ስግብብ ባንዳዎች በተቃራኒ ለአገርና ለወገን ሲሉ ያላቸውን ላካፈሉና ደጀን በሆኑ በእነዚህ ኢትጵያውያን ደስ ይለናልና ደግመን ደጋግመን ስናመሰግናቸው ክብር ይሰማናል!
በአሁኑ ወቅትም በአገርና በህዝብ ህልውና ላይ አደጋ የደቀነውን የኮሮና ወረርሽኝ በአገራችን በተከሰተበት ወቅትም ከላይ እንደተመለከትነው ሁለት ተቃራኒ ዜጎች በአገራችን ተከስተው አስተውለናል። በዚህ አስከፊ ወቅት በዜጎች ችግር ላይ በመንተራስ ሀብት ለማካበት ያሰፈሰፉ ስግብግቦችና ያጡና የተቸገሩ ወገናቸውን ለመታደግ ያላቸውን የለገሱና ሌሎች እንዲለግሱ ሌት ተቀን የለፉና እየለፉ ያሉ ቅን ዜጎች። ስግብግቦችን ሥራቸው አሳፋሪ ነውና ስናወግዝ ቅን ዜጎቻችን ደግሞ በምድርም ሆነ በሰማይ ትልቅ ዋጋ ያለው ሥራ ሠርተዋልና ምስጋናችንን ላቅ ባለ ክብር ልናቀርብላቸው እንወዳለን።
አገራችንን ከገጠማት ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ ለመታደግ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ህይወት ሳይሳሱ ህሙማንን በማከም ላይ የሚገኙ ሐኪሞችና በጤና ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎች እየከፈሉት ያለው መስዋዕትነት ታላቅ ነውና ክብር ልንሰጣቸው ግድ ይላል። እኒህ ዜጎቻችን በተለይም በንክኪ እና በትንፋሽ የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ የሆነውን የኮረና ቫይረስ ተጠቂዎችን ነውና እየረዱ ያሉት ህይወታቸውን ቀብድ አስይዘው እየከፈሉት ላሉት ለዚህ ታላቅ ገድል ደግመን እናመሰግናቸዋለን። የህክምና ሙያ የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር አሟልተው የገቡትን ቃለ መሐላ ፈጽመዋልና በዚህ እጅግ ሊኮሩ ይገባል።
በሌላም በኩል መንግሥት ህዝብን ከአደጋ ለመታደግ ያወጣቸውን መመሪያዎች ለማስፈፀም የተለያዩ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ሌት ተቀን እየለፉ ነውና ከልብ የመነጨ ምስጋና ሊቀርብላቸው ይገባል። ከራስ በፊት አገርና ሀዝብ የሚለውን የተቋማቶቻቸውን መርህ ተግባራዊ እያደረጉ ነውና በዚህ ሥራቸው ኩራት ሊሰማቸው ይገባል።
አስፈላጊውን ግንዛቤ በመፍጠርና የመረጃ ክፍተቶችን ከአገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ በማፈላለግ ዜጎችን በዕውቀት እየገነቡና አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ በትጋ በመሥራት ላይ ያሉት መገናኛ ብዙሃንም በዚህ አስከፊ ወቅት በቁርጠኝነት እየፈፀሙት ላለው ለዚህ በጎ ተግባር ላቅ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል።
ከዚህም በተጫማሪ የሥራ ባህሪያቸው ከበርካታ ህዝብ ጋር የሚያገናቸውና በዚህም የተነሳ ለቫይረሱ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ በሆነበት የትራንስፖርት ዘርፍ እያገለገሉን ላሉ ውድ ዜጎቻችን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለአገርና ለህዝብ ብለው እየከፈሉ ያሉት መስዋዕትነት ታላቅ ነውና ከጉልበታችን ዝቅ ብልን ምስጋናችንን ልናቀርብላቸው እንወዳለን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012