ዓለም ተፈጥሮዋ ሆኖ ሁሌም ባላሰብቧት መልክ የመገኘትዋ እውነት በአንድ ጊዜ ገሀድ አድርጎ ያሳየ ሁነት ከሰሞኑ አስተናግዳለች። በዚህ ሁነት ሁለት መልኮች ተገልፀዋል። ጥሩ መሆኑ ካለመሆን ጋር አንድ ላይ ተሰልፏል። መስጠትና መንሳት፣ ክፋና ራሮት፣ ልገሳና ቅመያ በሰው ልጆች ባህሪያ ላይ የተለዩ ፀባዮች ሆነዋል።
አንዱ ሰው ለማዳን እራሱን ሳይሰስት በመስጠት ከፍ ብሎ ታይቷል። ሌላው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባይ ሆኖ አርፎታል። መልካምነት ተፈጥሮው ስላልሆነ ስለ ወገን ምን ገዶኝ ይሄን ክፉ አጋጣሚ ግሳንግሱን ሰብስቤ የኔ ላድርግ በዚህም ልለወጥ በሚል ራስ ወዳድነት ተገቢ ባልሆነ ምግባር ታይቷል።
ሁለቱ ፀባዮች ሰው በተባለ ፍጡር ውስጥ የበቀሉ ሰውን የተዋሀዱ ልዩነቶች ናቸው። አንዱ እንደ ብርሀን ፈንጥቆ ውስጥን ስያስደስት ሀሴትን ሲዘራ ሌላው ስታሰብ ሁላ ፅልመት ስያስታውሱት ምነው ባልሰማው ያስብላል። ሁለቱ መልኮች ፍካትና ጥልሸት ይወክላሉ።
ተስፋን የሚያለመልም ፍካትና ተስፋ የሚያስቆርጥ ጥልሸት። ወዳጄ ፍካቱን ምረጥ። ካልሆነ ያግባብ በድለህ በሰበሰብከው ምትበላው እየመሰለህ ሆድህ ባዶ መሆኑ፤ የምትጎነጨው ጣፋጭ መጠጥ ጣዕሙ ቢሸውድህም ውስጥህ ማጎምዘዙና መጎምዘዙ አይቀርም።
ሰው የመሆን ከባድ ሚዛን መቀላቀልን ትፈልጋለህ? ያ ሰው ነህና ማለፍህ አይቀርም እመን። ታዲያ ስታልፍ እሱ መልካም ነበር ጎደለብን እንጂ፤ ኧፉ ይሄ መጥፎ ጎደለልን መባልን ፍራ።
ስታልፍ ያ ሰው የምር ሰው ነበር መባልን ትመኛለህ አይደል? ፍላጎትህ ከሆነ ሰውነትን ተላበስ። ሰው ሆነህ ሰው ሰው ሽተት። ያኔ ሚዛንህ ከፍ ይላል። ህይወት ጣዕም የሚኖራት በመኖር ነው። መኖር ደግሞ የሚለካው ሌላውን በማኖር ለሌላው ጥላ በመሆን ነው።
ዛሬ ስለ ሀገርህ መጨነቅ ስለ ህዝብህ ስጋት እንደ ህዝብ አሳስቦህ የመለወጥህ ምክንያት የሀብት ምንጭ የሆነው ህዝብ መደናገጥ አንተን ካላስደነገጠህ አደጋ ነው። አብረህ ክፉውን ጊዜ ለመውጣት አብረህ ለመሻገር ካልሞከርክ ወዳጄ ነገ እረስህን ማግነትህን ተጠራጠር።
ሰው በሁለት መልክ ይለካል፤ ይለያልም። አንድም በበጎ ቀን ሌላም በክፉ። በበጎው ቀን ብታስመስል በክፉ ቀን ትለያለህ። መክፋትና መራራት የሰውነት ከፋታና ዝቅታ ሚዛን ናቸው። ይህ ሚዛን ስራውን የሚጀምረው በቁርጥ ቀን ነው። ይህ መጥፎ አጋጣሚና ቀን አንጥሮ ያስቀምጣል።
ወደፊት በሚገለጥ ታሪክ ውስጥ ከመልካሞቹ መዛግብት ውስጥ እራስህን ማስገኘት ለአንተ የተሰጠ ታላቅ እድል ነው። ይህን ለማድረግ ባለ ፀጋ መሆን የለብህም ሰዎችን የሚረዳ ስለ ሰው የሚያስብ መልካም ልብና ቀና የሆነ እሳቤ አቅም ከፈቀደ ድርጊት ጋር መከወን እንጂ።
ይህንን ካደረክ ስለ ሰዎች መልካም ከሆንክ አንተ እድልኛ ነህ። የቀን መለዋወጥ የሁነቶች መቀያየር ላንተ ምንም ነው። መጀመሪያውኑ ስሪትህ ያ ነበራ። አሁን የተገኘኸው እውነተኛ ማንነትህ ላይ ስለሆነ መልካሙ ውስጥትህ አድርግ የሚልህም መልካም ነገርን ታደርጋልህ።
ከኔ ውጪ ወደ ውጪ ያልከው ራስ ወዳድ የሆን እንደሆንክ ግን ዛሬ ድረስ በመልካም ሁነት ውስጥ ለዝበህ ብትታይ ክፉ ቀን ግን ማንነትህን ገሀድ ያወጣዋል። ጭንቅ የያዘለት፤ ህዝብ ግራ ገብቶት ችግር የተጋረጠበት ዕለት በዚያ በክፉው ቀን ላይ ትለያለህ። ይሄ አደጋ ነው። ያኔ ጭንቁ የሚበረታው አንተ ላይ ነው። ወዳጄ በክፉ ቀን አይለኩህ። ያኔ የተላበስከው ማንነት ለሁሉም ግልፅ ይሆናል።
ዛሬ ላይ በየመንደሩ የሚታዩ ራስ ወዳድ ስግብግብ ነጋዴዎች ስለ ሰው መጨነቅ ግድ የሰጣቸው አይመስልም። ነጋዴው ከገበሬው 2,000 ብር የገዛው ጤፍ ከተማ አምጥቶ ከ4,500 ብር ፍንክች አልልም ይላል። “ምነው ወዳጄ! ይሄ ደግም አይደል። ለዚያውም በክፉ ቀን እንተዛዘን እንጂ ይሄን ያህል መጨካከን ተገቢ ነው?” ስትለው “ ምን እናድርግ? እኛም ጨንቆን ለናንተ አስበን ነው ያስመጣነው” ይልሀል።
ነጋዴዎች ኧረ ተው ደስ አይልም! ወዴት እንሄድባችዋለን? ዛሬን ተባብረን በትንሽ በትንሹ እያተረፋችሁብንም ቢሆን አብረን ብንሻገር አይሻልም። በመጣው ችግር የደንበኞቻችሁ ቁጥር ቢቀንስ ለእናንተም ችግር እኮ ነው እንኑር እንጂ የት እንሄድባችኋለን። ቀስ እያላችሁ ብትነጥቁን አይሻልም። ከበረገግን እኮ ለእናንተም መጥፎ ነው። የኛ ገቢ አድሮም ውሎም መድረሻው ወደ እናንተው ነው ምን መሄጃ አለው እኛም አለን ብላችሁ ተው ተው ግን እንተዛዘብ።
በእውነት የትም አይሄድባችሁም ያ ማስቀመጥ በሉት የትም አይሄድባችሁም። እኛ ከሌለን እናንተስ በምን ታድራላችሁ? ሰው እንጀራውን ይገፋል እንጀራው ላይ ይጨክናል? ተው ደግም አይደል።
ጭካኔያችሁ ደግሞ መክፋቱ ደግማችሁ እንዳትደርሱብኝ የማለትን ያህል “ስንት ነው?” ብለን ስንጠይቅ ለመቁጠር ቀርቶ ለመጥራት የሚከብድ የገንዘብ መጠን መንገራችሁ አያስተዛዝበንም?
ለኛ ባታዝኑ ለወገን ባትራሩ እንኳን ይሄ ለኛ ብርቅ የሆነው ገንዘብ እንዴት ነው የናቃችሁት? ቢያንስ ያስከበራችሁ ያህል ክብር ሰጥታችሁት አብሮዋችሁ እንዲቆይ ብታደርጉ አይሻልም። ገንዘብ አንዴ ካኮረፈ፤ አኮረፈ ነው እንደኛ መሄጃ ያጣ አይምሰላችሁ ጥሎዋችሁ እብስ ነው የሚል።
በዚህ በጭንቅ ሰዓት ሀገር ግራ ገብቶት ወገን የሚያደርገው አጥቶ እያያችሁ የወገን ኪስ ማጠብ፤ ያላግባብ በትርፍ ላይ ትርፍ መሰብሰብ እንደው ደስታን ያጎናፅፍ ይሆን? እኔ አይመስለኝም። እውነተኛ ደስታ የራስን አሳልፎ ከመስጠት ጋር የሚያያዝ በመቸር የሚገኝ ልዩ ጉዳይ ነው።
ይህ በልቦለዳዊ ድርሰት ዓለም ውስጥ የሚሰበክ ፈጠራ አይደለም እውን ነው። ንጹህ ያልሆነ ትርፍ ልክ የሌለው ጥቅም በእርግጥም ምንም አይነት እውነተኛ ደስታ አያስገኝም። እውነተኛ ደስታ በውስጣችን ለመፍጠር ቀድመን ማስደሰትን እንወቅ። እናም ነጋዴዎች ተው ለወገን ማሰብ መልካም ነው ተው።
ይልቅ ውድ ነጋዴዎች፤ የደንበኛዬን እድሜ ያቆይልኝ፣ በሽታው ያጥፋልኝ ሀገሬን ወደ ፍፁም ጤንነትዋ ይመልስልኝ የሀገር የወገን ገቢ ያሳድግልኝ ብሎ በፀሎት ትጉ። ስለራሳችሁ ብላችሁ ስለሌላው አስቡ። ስለናንተ ነገ መለወጥ ዛሬ ሌላውን ለመለወጥ ለማጥፋት የመጣን በማጥፋት ቀዳሚ ሁኑ። ለወገን ጥሪ ለሀገር መድህን ሳትሰስቱ መልካምነት በመክፈል ደጀን ሁኑ። ዛሬ መልካም መሆን ነገ በራሱ የሚከፍል የመልካምነት ካሳ ነውና በጎ ነገር ላይ ማዘውተር የማንጠግብ ደጎች ሆነን እንገኝ። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2012
ተገኝ ብሩ