አዲስ አበባ፡- በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቤት የሚውሉ ሰዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸው ባለሙያዎች ገለፁ።
የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ከስራ በመራቅ በቤታቸው መዋል የጀመሩ ሰዎች ቤት የዋሉበትን አጋጣሚ ውጤታማ በሆነ መልክ መጠቀም እንደሚገባቸው የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የማህበረሰብ ጤና ሳይንስ ልዩ ሀኪም የሆኑት ዶክተር የኔነህ ጌታቸው ኮቪዲ 19 ለመከላከል ሰዎች በድንገት በቤት ሲውሉ መጥፎ አልያም ደግሞ መልካም የሆኑ ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል ይገልፃሉ።
ሰዎች የቤት ውስጥ ቆይታቸው ስኬታማ ለማድረግ እቅዶችን መንደፍና መተግበር ይኖርባቸዋል በማለት ይመክራሉ። ሰዎች መልካም ያልሆነ ስሜት የሚሰማቸው ያለ ተግባር ቤት ውስጥ በመቀመጥ የሚያሳልፉና እንቅስቃሴ የማያደርጉ ከሆነ ለአእምሮ ጤና ችግር፣ ጭንቀትና ድብርት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
ቤት መዋሉ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ በሽታው ለመካለከል መሆኑን በመገንዘብ በቀኑ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት ዶክተር የኔነህ ጌታቸው፤ ለጭንቀትና ድብርት ሊዳርጉ የሚችሉ አሉታዊ አስተሳሰቦችን በማስወገድ አእምሮአቸው የሚያረጋጋ መልካም ነገር ላይ ትኩረት ቢያደርጉ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ይናገራሉ።
ቀደም ሲል በስራ ምክንያት ጊዜ የሌላቸው ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እርስበርስ ለመቀራረብ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል:: አብሮ ሰፊ ጊዜ ለማሳለፍና ከልጆች ጋር ለመጫወት፣ ለመወያየት ረጅም ጊዜ እንዲያገኙ ሰፊ እድል ይፈጥርላቸዋል በማት ባለሙያው አስተያየታቸውን ይገልፃሉ። በየሃይማኖታቸው በመጸለይ፤ የተለያዩ መጽሐፍቶች በማንበብ፤ አስተማሪ ፊልሞች በማየትና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ጭንቀትን መከላከል እንደሚችሉ ይመክራሉ።
ረጋ ብለው በጥሞና ውስጣቸው በማዳመጥ፤ እራሳቸው ሊመረምሩ የሚችሉበት ጊዜ በማግኘታቸው፤ ጊዜውን ወደ መልካም አጋጣሚ በመለውጥ ማሳለፍ፤ እስከዛሬ ያልሰሩት ተግባር አስበው ለመስራት እንዲችሉ እድል ይሰጣል ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚቻለው በመጨነቅ ሳይሆን የባለሙያዎች ምክር በመስማት መሆኑ የሚናገሩት የስነልቦና ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ሰዎች ቤት ውስጥ ሲውሉ እራሳቸው ከድብርትና ከጭንቀት ለማላቀቅ ውስጣዊ ፍላጎታቸውን መለየት ይጠበቅባቸዋል። መጽሀፍ በማንበብ፤ ፊልም በማየት፤ የተቸገሩት ወገኖችን በስልክ በመጠየቅ፤ አካላዊ ርቀት ጠብቆ በመርዳት፤ በጎ ተግባራትን በመፈጸም መንፈሳዊ እርካታ ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ከዚህ በፊት በስራ አጋጣሚ በአንድ ላይ ተገናኝተው የማያውቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት በመሆኑ ቤተሰብ ግንኙነት በማጠናከር ይረዳል። አጋጣሚውን በመጠቀም ቤተሰባዊ ቅርርቦሽን ለማጠናከር ቤት ውስጥ የሚሰሩ ስራዎች በመተጋገዝ፤ በግልጽ በመመካከር ክፍተቶች በመለየት በጋራ በመወያየት ጊዜያቸውን መጠቀም እንደሚገባ ያስረዳሉ።
“በሽታ ለመከላከል ቤት መዋላችን እራሳችንን በመከላከል ሌሎችንም ለማዳን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እስካሁን ለበሽታ መድኃኒት ያልተገኘለት በመሆኑ ብቸኛ የመከላከያ ዘዴው እራሳችን በመጠበቅ ስለ ቫይረሱ ከባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን በአግባቡ መተግበር ነው። በግዴለሽነት መመልከት ግን በኋላ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል” ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2012