የኮሮና ቫይረስ ዛሬም ለመላው ዓለም ከፍተኛ ሥጋት ሆኖ ቀጥሏል። ዓለምን እያስጨነቀ፣ ህዝብን እያስደነገጠና እያሸማቀቀም ይገኛል። ይሄ ቫይረስ ሃያላንን ለማንበርከክ ጊዜ አልፈጀበትም። ሚሊዮኖችን ከመማረክ መቶ ሺዎችን ከመቅጠፍ የሚያግደው ነገር አልተገኘም። ሥርጭቱን ከአድማስ አድማስ ዘርግቶ የሰውን ልጆችን ለአሰቃቂ እልቂትና መከራ ዳርጓል። ለጠቢባን ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
በአገራችንም የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ አገራዊ የሥጋት ምንጭ ሆኗል። እስካሁን ባለው መረጃ በቫይረሱ የተያዙ ዜጎቻችን ቁጥር 105 ደርሷል። ሦስት ወገኞቻችንንም በዚሁ ቫይረስ ጦስ በህይወት አጥተናል። በሽታው በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካ ሕይወታችን ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ እየበረታ ነው። በዜጎቻችን ላይ እያሰከተለ ያለውም የሥነ ልቦናና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ ሆኗል። የምርጫ ቀንንም አስቀይሮናል።
ይሄ ዓለምን ብሎም አገራችንን የገጠማትን ከባድ ፈተና አንድ ሆነንና በአንድ ልብ ተሳስበን መንቀሳቀስ ከቻልን በአጭሩ ልንገታውና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ እንችላለን። ለዚህ ቻይናን በምሳሌነት መውሰዱ በቂ ነው። በቻይና ሁዋን ግዛት ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ በተወሰደው እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ችለዋል። እነሱ የሄዱበት መንገድ፤ የወሰዱት እርምጃ ዛሬ ከመንግሥትና ከጤና ባለሙያዎች ከሚሰጡን መመሪያዎች የተለዩ አልነበሩም።
ውጤታማ የሆኑት የመከላከያ መልዕክቶችን በትክክል በመተግበርና የራሳቸውንም ኃላፊነቶች በተገቢው መንገድ መወጣት በመቻላቸው ነው። ዛሬ ተከርችመው የነበሩ ቤቶች ተከፍተዋል። የተቋረጡ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል። ይህ የሆነው ደግሞ ጥንቃቄዎች በተሞላበት መልኩ በመደማመጥና ከሁሉም በላይ ደግሞ ኃላፊነትን በተገቢው መንገድ መወጣት በመቻላቸው ነው።
እኛም እዚህ ደረጃ እንደምንደርስና የህማማቱ ጊዜም አጭር የትንሣኤው ጊዜም ቅርብ እንደሚሆን እናስባለን። ይህ የሚሆነው ግን ከመንግሥት፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ከሃይማኖት አባቶች የሚሰጡ መመሪያና መልዕክቶችን ሙሉ ለሙሉ መቀበልና መተግበር ስንችል ብቻ ነው። ዛሬ የዘጋናቸው በሮች፣ የሥራ ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ማምለኪያ ስፍራዎች ወዘተ በአጠረ ጊዜ እንዲከፈቱ ማድረጊያው መድሃኒቱ ያለው በእኛ እጅ ላይ ነው።
በሽታውን መከላከል እንችል ዘንድ የሚሰጡንን ምክረ ሀሳቦች በትክክል ከተጠቀምንበት ከፊታችን የተደቀነው የጽልመት አደጋ ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን ልንሻገር እንችላለን፤ ካልተጠቀምንበት ግን የምንመኛቸው መልካም ቀናት ይርቃሉ፤ የምናጣቸው ዜጎች የሚሰቃዩ ወገኖቻችንም እንዲሁ የበዙ ይሆናሉ። በየቀኑ የምንሰማቸውን መጥፎ ዜናዎች ወደ መልካም ለመቀየር የጥንቃቂ ምክሮችን በቁርጠኝነት መተግበር፤ የነገ ተስፋዎቻችንን በእጃችን ለማስገባት በአንድ ልብ ሆነን ለመንቀሳቀስ ቃል መግባት ያለብን አሁን ነው።
የኮሮና ቫይረስ በብዛት የሚተላለፈው በእጅ መጨባበጥ፣ በአካላዊ መቀራረብ ነው። ለዚህ ደግሞ ፍቱን መድሃኒቱ አለመጨባበጥ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ላልሆኑ ጉዳዮች ከቤት አለመውጣት መሆኑ በተደጋገሚ በባለሙያዎች ተገልጿል። በመሆኑም በገበያ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት መጠበቂያ አካባቢዎች እና በሌሎችም ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እና የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦችን በመተግበር የቫይረሱን ሥርጭት መመከት ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እንኳን ለትንሣኤው በዓል አደረሳችሁ በማለት ባስተላለፉት መልዕክት ያስገነዘቡትም ይህንኑ ነው። አሁን ከገጠመን በላይ እንዳይገጥምን፣ እንደ መንግሥትና እንደ ህዝብ እንደ አንድ ልብ መክረን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለተግባራዊነቱ መጽናት ይኖርብናል።
ለኮሮና ቫይርስ በሚገባ ከተዘጋጀን ያለከባድ ጫና ቫይረሱ ሊያስከትል ከሚችለው አስከፊና አሰቃቂ አደጋ ልንወጣ እንችላለን። ፈተናውን የምናልፈው በዝግጅታችን መጠንና ለተግባራዊነቱ በምናሳየው ጽናት ልክ ነው። የትንሣኤ በዓልንም ስናከብር ተገቢውን ጥንቃቄ እያደርግንና ላጡ ወገኖቻችን በመድረስ መሆን አለበት። ይሄን ስናደርግም ትንሣኤያችን ሙሉ ተስፋችንም ብሩህ ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም