‹‹ተማር ልጄ….›› ያለው ድምጻዊ ይህንን ዜማ ያወጣው ያለትምህርት የብዙ ነገሮች ውል እየጠፋበት ስለተቸገረ ይመስለኛል። እርግጥ ነው ትምህርት የችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው።
ይሁን እንጂ ከሁለት አስርት ዓመታት አስቀድሞ የጀመረው የትምህርት ተቋማት የፖለቲካ አተካራ እስከአሁን ድረስ ሲቋጠር ሲፈታ፣ ሲከፈት ሲዘጋ፣ ሲጣላ ሲስማማ፣ ሲታረቅ ሲፋታ፣ ሲገድል ሲገደል፣ ሲያቆስል ሲቆስል መቀጠሉ ትምህርት የችግር መፍቻ ሳይሆን የችግር መበለቻ ቢያስመስለውም ቅሉ እውነታው የሚያሳየው ያለ ትምህርት ተቀብላ የምታስተናግደው ዓለም መዘጋቷን ነው።
ስለሆነም በዚህ ቅኝት የአገሪቱ የትምህርት ተቋማትን ፈተናዎች፣ የተማሪዎችን እንግልትና እጣ ፋንታቸውን ከነባራዊ ሁኔታዎችና ከተሰጡ መግለጫዎች በመነሳት ለማስቃኘት እንሞክራለን።
ከላይ በግርድፉ ቢነሳም የትምህርት ተቋማት ቁመናቸው እውቀት ተኮር ሳይሆን ፖለቲካ ተኮር ተደርገው፣ ምሁር አብቃይ ሳይሆኑ ምሁር ነኝ ባይ አፍሪ ሆነው የጃጁ ናቸው። በዚህ የተነሳም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ሽንጡን ገትሮ መሰረታቸውን ለማስተካከል ቢዋትትም በዋዛ የሚወጣው አልሆነም። በአንዱ በኩል ሲያጠብቅ በሌላው በኩል ላልቶ እየፈሰሰ፣ በአንዱ በኩል ሲጠግን በሌላ በኩል ተቀድዶ እየፈረሰ በእሳት ማጥፋት ተግባር እንደተጠመደ ዓመታት እንዲያልፉ በሂሳብ ሊቅ የተሰላ ይመስላል። ከዚያም አልፎ ከማስፋፊያ ጋርም ይያያዝ በቀጥታ የባለቤትነት ጉዳይ (የካሳ አልተከፈለኝም) ጥያቄ ያለባቸው እንደ ጅግጅጋ አይነት ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ናቸው። ጣጣቸውን ያልጨረሱ ውጥኖች ናቸው፤ ምሁር ለማፍራትም ፣ ለአቅመ ተቋምነትም።
ከፍኖተ ካርታ መዳረሻ እስከ ስርዓተ ትምህርት ፍተሻ የተከናወኑ የዘርፉ ስር ነቀል ተግባራት መሬት ወርደው ትውልድ እንዲቀርጹ ለማድረግ የተሄደባቸው ርቀቶች ረዥም ቢሆኑም በፈተናዎች የተወጠሩ ነበሩ። በትምህርት ገበታ ላይ የሚያልፉት ወጣት ምሩቃን ያሉባቸው ክፍተቶች በጥናት ተለይተው እነዚያን ክፍተቶች መሙላት የሚያስችሉ ከ16 የማያንሱ የትምህርት ዓይነቶች ተዘጋጅተው በተግባር ላይ እንዲውሉ ቢታሰብም ተግባራዊ የተደረጉት ከ14ት አልበለጡም። ሌሎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ሂደታቸው አልተቋጨም።
በሌላ በኩል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማሩ ሂደት ካለፈው ሕዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ አንዱ ሲገባ ሌላው ሲወጣ የነበረበት ሂደት እንደነበር ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በመንፈቅ አፈጻጸሙ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጭምር መግለጹ የሚታወስ ነው።
በዚህ ሁኔታ አንዱ ችግር ሲፈታ ሌላ ችግር እየተወለደ በሰከነ የመማር ማስተማር ሂደት፣ የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት የትምህርት ከባቢ ተፈጥሯል በሚል አፍን ሞልቶ መናገር የሚያስችል ቁመና ላይ መድረስ አቅቶታል። ከተማሪዎች አንደበት የሚሰማውም ይሄን ሐቅ የሚያጎለብት አስተያየት ነው።
በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ወይም በትምህርት ተቋማት መደበኛ ተግባራት ላይ መሰናክሎች ሲፈጠሩ የኖሩት በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ አለመሆኑ ሌላ ራስ ምታት ነበር። በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪ እንደናፈቃቸው ያሳለፉት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
በአገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶችና የሰላም እጦት ችግሮች ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው በማፈናቀል ጭምር ጦሳቸውን በታዳጊዎች ሕይወት ላይ ያሳረፉ ናቸው። በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሽ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች፣ መተከል ዞን ማንቡክ፣ ማንዱራና የተለያዩ ወረዳዎች ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው አንዴ ሲለዩ ሌላ ጊዜ ሲመለሱ ያሳለፉ ናቸው። እነዚህ ለማሳያ ያህል የተጠቀሱ እንጂ በርካታ አካባቢዎች የተስተዋለ ችግር ነው።
የትምህርት ተቋማት ከስራቸው እየተስተጓጎሉ፣ እውቀት ለመቅሰም ትምህርት ቤት የሚውሉ ታዳጊዎች ስለምን በመከራ ያሳልፋሉ? እነዚህን ችግሮች መንግስት እንዲቀርፍ እየገፉ መሄዱስ ተገቢ ነወይ? መልሱን ለማህበረሰቡ መተው የተሻለ ነው። ምክንያቱም አቅምም፣ ብልሃትም፣ ዘላቂ መፍትሄውም ከማህበረሰቡ አይን የሚሰወር አይደለም።
ማህበረሰቡ ራሱ ከመቀነቱ እየፈታ ባጠራቀመውና ግብር እየከፈለ በሚሰራቸው የትምህርት ተቋማት ልጆቹን ያለስጋት እንዲማሩ የማድረግ አቅምም፣ መብትም አለው። እስከዚህ ድረስ የአካባቢው ማህበረሰብ በትግላቸው ስርዓት ያስያዙባቸው በርካታ አካባቢዎች መኖራቸውም መረሳት አይገባም።
ያም ሆነ ይህ ታዳጊ ህጻናትም ሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዓላማቸው እውቀት መገብየት ነው። በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ ችግሮች እነዚህ ዓላማዎች ሲስተጓጎሉ መንግስት ማህበረሰቡን ከጎን በማሰለፍ ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት ያደርጋል።
ከሰሞኑ የአገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት በመላው አገሪቱ የተማሪዎችን የክልል እና አገር አቀፍ ፈተናዎች የመስጫ ወቅት ቀደም ሲል ተገልጾ ከነበረው ፕሮግራም ሊሸጋሸግ እንደሚችል ገልጾ ነበር። በተጨማሪም ከዚህ በፊት በተለመደው የትምህርት መዝጊያ ወቅት የዘንድሮው የትምህርት ዘመን የሚራዘምበት መንገድ እንደሚኖር ፍንጭ ሰጥተው ነበር። ለዚህ በምክንያትነት የተጠቀሱት አገራዊ ምርጫው ፕሮግራም ጋር የተጣጣመ እንዲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ምክንያት የባከኑ የትምህርት ጊዜያትን ለማካካስ ሲባል እንደሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ አሁን ላይ በመላው ዓለም የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያም መከሰቱን ተከትሎ ስርጭቱን ለመግታት ሲባል የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸው ይታወቃል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ከመጋቢት ሰባት ጀምሮ ትምህርት በመዝጋት ተማሪዎች ከማንኛውም እንቅስቃሴ ተቆጥበው በዶርማቸው እንዲያሳልፉ ተገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ተማሪዎች ዘንድ ከ50 በመቶ በላይ ከግቢ መውጣት፣ ከከተማው ማህበረሰብ ጋር ወጥቶ ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየት፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው እና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በመጋቢት 15 ሌላ መግለጫ አውጥቷል። በዚህ መሰረትም ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙን በተገቢው ጥንቃቄ ማሳለፍ እንዲችሉ በማለት አሳውቋል። እነዚህና መሰል ጥረቶች በመንግስት በኩል ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
በዚህ መንገድ የተወሰዱ እርምጃዎችን በበጎ ጎናቸው የሚመለከታቸው አካል የመኖሩን ያህል በድክመት የሚያነሳቸውም አይጠፋም። በሚዛኑ ማየትን ይጠይቃል። እንደዚህ አይነት ሰፊ ጥንቃቄ በማድረግ ሊታለፉ የሚችሉ ችግሮችን በተለይም ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙን የትምህርት ተቋማት ተዘግተው እና ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው ማሳለፋቸው በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ምሁራን ያነሳሉ።
የሚጎድላቸውን ቁሳቁስ ለማሟላት የገንዘብ ችግር፣ የሚያስፈልጋቸውን በመመገብ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያለ ናፍቆት፣ ያለ ሐሳብና ያለ ጭንቀት ማሳለፋቸው ተማሪዎች በተረጋጋ ስነልቦና ከወረርሽኙ መከላከል እንዲችሉ ብርታት ይሰጣቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012
ሙሐመድ ሁሴን