የኮሮና ቫይረስ ሁለት ዋነኛ ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳትና ደረቅ ሳል ናቸው። በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ እነዚህ ምልክቶች ወደ ትንፋሽ ማጠር ይወስዳሉ። ደረቅ ሳል ሲባል በጣም ጠንካራ የሆነ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ ነው። ከዚህ በፊት ደረቅ ሳል ካለብዎ የኮሮና ቫይረስ ሳል በጣም ለየት ያለና ከባድ መሆኑን ማስተዋል ይችላሉ።
ከፍተኛ ትኩሳት የሚባለው ደግሞ የሰውነት ሙቀት መጠን ከ37.8 ዲግሪ ሴልሲየስ ሲልቅ ነው። ይህ ትኩሳት ሰውነት እንዲግል ወይም ደግሞ ከፍተኛ ብርድና መንቀጥቀጥ እንዲሰማን ያደርጋል።
ከእነዚህ ሁለቱ ዋነኛ ስሜቶች ባለፈ ራስ ምታትና ተቅማጥ አንዳንድ የበሽታው ታማሚዎች ያሳይዋቸው ምልክቶች ናቸው። የማሽተትና የመቅመስ አቅም ማጣትም ምልክቶች ሆነው ተመዝግበዋል።
ምልክቶቹ ቫይረስ ሰውነት ውስጥ በገባ በአምስት ቀናት ሊታዩ ይችላሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ ምልክቶቹ እስከ 14 ቀናት ድረስ ሳይታዩ ሊቆዩ እንደሚችሉ ያስረዳል።
መቼ ነው ወደ ሆስፒታል መሄድ ያለብን?
በርካታ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች በቂ እረፍትና እንደ ፓራሲታሞል ያለ ሕመም ማስታገሻዎች ከወሰዱ ያገግማሉ። ሰዎች ወደ ሕክምና ጣቢያ መሄድ ያለባቸው የአተነፋፈስ ችግር ካጋጠማቸው ነው። ዶክተሮች የታማሚን ሳንባ ከመረመሩ በኋላ አስፈላጊውን ሕክምና ያዛሉ። አስፈላጊ ከሆነ ኦክስጂንና ቬንቲሌሽን ሊታዘዝ ይችላል።
ነገር ግን ሰዎች በሽታው ይዞኛል ብለው ከጠረጠሩ አስቀድመው ወደ ነፃ የእርዳታ መስጫ ቁጥሮች ቢደውሉ ይመከራል። የኢትዮጵያ ነፃ መስመር 8335 ወይም 952 ነው።
የመተንፈስ ችግር ካለብዎ በተለይ ደግሞ ጥቂት ቃላትን ማውጣት ካልቻሉ ደውለው ሐኪም ቢያማክሩ ይመረጣል።
በአሜሪካ፣ በቻይና እና በአውሮፓ አገራትም አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ የተደረገውም ቁጥሩ በመጨመሩ መሆኑንም ያስረዳሉ። ሆኖም ግን መተንፈስ የሚቸገሩ ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እንዲከታተሉ እንደሚደረግም አያይዘው ያነሳሉ።
“ቤታቸው ሆነው እንዲያገግሙ የሚጠበቁ ሰዎች ሌላ ጊዜ ጉንፋን ሲይዛቸው ለራሳቸው የሚያደርጉትን እንክብካቤ እንዲያደርጉ ይመከራል። ትኩሳት እና ሳል የሚያስታግስ ነገር በቤታችን ማድረግ እንችላለን” ይላሉ።
ሆኖም ቤት ውስጥ በእድሜ የገፉ ሰዎች ካሉ፤ በሽታው በነሱ ላይ ሊበረታ ስለሚችል፤ ከነሱ ጋር ንክኪ አለማድረግ ወይም መራቅ እንደሚያስፈልግ ዶክተሯ ይናገራሉ። ቤት ውስጥ ለታመመ ሰው እንክብካቤ የሚያደርጉ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ፤ ታማሚው/ዋ በአግባቡ እጅ መታጠብ ይጠበቅበታል (ይጠበቅባታል)። በተጨማሪም ህሙማን ለብቻቸው በአንድ ክፍል እንዲቆዩ ከሰዎች በሁለት ሜትር እንዲርቁም ይመክራሉ።
ፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ምን አለ?
አይሲዩ የሚል ሙያዊ ስያሜ የተሰጠው የፅኑ ሕሙማን ክፍል በጣም ለታመሙ ሰዎች የተዘጋጀ ሥፍራ ነው።
እዚህ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ለመተንፈስ እንዲረዳቸው ኦክሲጅን ይሰጣቸዋል። ቬንቲሌሽን የተሰኘው ቁስ የሚገጠመው በጣም ለታመሙ ሰዎች ብቻ ነው። መሣሪያው በርከት ያለ ኦክሲጅን ለታማሚው ያቀርባል።
መካከለኛ ምልክት ከታየብኝ ምን ላድርግ?
መካከለኛ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ይመከራሉ። በርካታ ሃገራት መለስ ያለ ምልክት ያሳዩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያገሉ ነው የሚያደርጉት እንጂ የሚሰጣቸው ለየት ያለ ሕክምና የለም።የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን ሰዎች ራሳቸውን እንዲያገሉ ነው የሚመክረው።
ሰዎች ቴርሞሜትር የተሰኘውን መሣሪያ በመጠቀም የሙቀት ልኬታቸውን ማወቅ ይችላሉ። የሰውነት ሙቀታቸው ከ37.8 በላይ የሆኑ ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ ይመከራሉ።
ኮሮና ቫይረስ ምን ያህል ገዳይ ነው?
ምንም እንኳ ይህ መረጃ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ባይሆንም ከኮሮና ቫይረስ የመሞት ዕድል በጣም ዝቅ ያለ ነው [በመቶኛ ሲሰላ ከ2 በመቶ አይበልጥም]።
የቫይረሱን ገዳይነት ዝቅ ያደረገው ምናልባትም ብዙ ታማሚዎች ባለመርመራቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የዓለም ጤና ድርጅት 56 ሺህ ሰዎች ላይ ምርመራ አካሂዶ፡-
• 6 በመቶ በጣም የታመሙ ሆነው ተገኝተዋል
- ከሳንባ አለመሥራት እስከ ለሞት መጋለጥ
• 14 በመቶ ጠንከር ያለ ምልክት ታይቶባቸዋል - የመተንፈስ ችግርና ትንፋሽ ማጠር
• 80 በመቶ ደግሞ መካከለኛ የሚባል ምልክት
አሳይተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በርካታ ሰዎች ባይመረመሩም በቫይረሱ ተይዘዋል ይላል።
የቫይረስ(Viruses) ልክፍት
ቫይረስ በህይወት ለመቆየትና ለመባዛት ህይወት ያለው የበሽታ ተቀባይ(Host) ህዋስ የሚፈልግ የልክፍት በሽታ ነው፡፡ ቫይረስ በሽታ ተቀባይ(Host) ህዋስ ካገኘ በመባዛት ተጨማሪ ህዋሶችን በመውረርና በመስፋፋት በተቀባዩ ላይ እየነገሰ ይሄዳል፤ የፀረ ተዋሲያን ወይም የአንቲባዮቲክ ሕክምና ቫይረስን ሊያጠፋ የሚችል አይደለም፤ በመሆኑም የሰውነት መድኅን ስርዓት (Im¬mune System) በቫይረስ አማካኝነት የሚፈጠረውን የልክፍት በሽታ የመፋለም ኃላፊነት አለበት፤ እንደ ኤች አይ ቪ(HIV) ላሉ ልክፍቶች ፀረ-ቫይረስ የሆኑ መድኃኒቶች ያሉ ሲሆን ቫይረሱ የሚራባበትን ፍጥነት ለመቀነስ የሚያስችል ተግባር አላቸው፤ ያቅማቸውን ያበረክታሉ፤ ቫይረሱን ግን ሊገድሉት አይችሉም፡፡ አንዳንድ ቫይረሶች በጣም ገዳይና ብዙ ሕዝብ የፈጁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ህመምተኛውን አዳክመው ከቆይታ በኋላ ይሸነፋሉ፤ ብዙ ሕዝብ ከፈጁ የቫይረስ በሽታዎች ውስጥ ኤች አይ ቪ ኤድስ(HIV/ AIDS) እና ኢቦላ(Ebola) የሚጠቀሱ ሲሆን እንደ ጉንፋን ያሉት ደግሞ ለሞት የማያበቁ የቫይረስ ልክፍቶች ናቸው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ባክቴሪያና ቫይረስ በመሳሰሉ ተዋሲያን አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን የግል ንፅህናችንን በሚገባ በመጠበቅ መከላከል ይቻላል፤ አብዛኛዎቹ በሽታ አምጪ ጀርሞች የሚተላለፉት በሰው ለሰው አካላዊ ንክኪ ነው፤ አንድ ሰው ምንም የበሽታ ምልክት ሳይታይበት እነኝህን ጀርሞች ሊሸከምና በሽታን ሊያስተላልፍ ይችላል፤ መፍትሔው ችግሩ በብዛት የሚኖርባቸው አካባቢዎች የምንገኝ ከሆነ ንፅህናችንን መጠበቅ ነው፤ በተለይ እጃችንን በሳሙናና በውኃ በየጊዜው መታጠብ አለብን፡፡ እነኝህን ጀርሞች እንስሳትም ሊሸከሙ ስለሚችሉ የጥሬ ስጋም ሆነ የእንስሳቱ ንክኪ ባጋጠመን ቁጥር በደንብ መታጠብ ጥሩ ልማድ ነው፡፡ በቫይረስ አማካኝነት ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ኢቦላ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ ጉድፍ፣ ኩፍኝ፣ ፓሊዮ እና ሌሎችም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም( The Immune System)
ማናቸውም ባዕድ ዘአካሎች(Foreign Organisms) ወደ ሰውነታችን ሲገቡ፣ ሰውነት ራሱን የሚከላከልበት ብዙ መንዶች አሉት፤ ሁኔታውን ምንግዜም በንቃት ነው የሚጠብቀው፡፡ ለምሳሌ ከባዕድ ዘአካሎች(Foreign Or¬ganisms) የመጀመሪያው መከላከያችን ቆዳችን ነው፤ በቆዳ ላይ ያረፈ ነገር ሁሉ ሰርጎ ወደ ውስጠ አካላችን እንዳይገባ ይከላከላል፡፡ እንዲሁም አንድ ባዕድ ነገር ወደ ዓይናችን ሲገባ ዓይናችን ፈጥኖ ያለቅሳል፤ አጥቦ ለማስወጣትም በተፈጥሯዊ መንገድ ይሰራል፡፡ አንድ ነገር ወደ መተንፈሻ አካላችን ሲገባም ወደ መጣበት ለመመለስ ወይ እናስነጥሳለን አሊያም እናስላለን፡፡ በከርሳችን ውስጥ የሚመነጨው አሲድም እያመለጡ የሚመጡ ጀርሞች ካሉ በመግደል ጉዳት እንዳያደርሱብን ያደርጋል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ሰውነታችን በተፈጥሯዊ መንገድ አካላችን ለባዕድ ዘአካሎች(Foreign Organisms) ለመኖር የሚያስችላቸው ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡
ምንጭ፤-ሰርቫይቫለ 101 ድረገጽ
አንድ ባዕድ ዘአካል ከዚህ በላይ የተመለከትናቸውን ተፈጥሯዊ መከላከያ መንገዶች ሁሉ አልፎ ወደ ውስጠ አካላችን ዘልቆ ሲገባ የሰውነት የተፈጥሮ የመከላከል አቅም ወይም ድኅነት(The Immune System)፣ እነኝህን ባዕድ አካሎች የመከላከል ስራ ድርሻ ይወስዳል፤ የተፈጥሮ የመከላከል አቅም ወይም ድኅነት(The Immune Sys¬tem) ልዩ ከሆኑ ህዋሶች፣ ህብረ ህዋሶችና አባላተ አካሎች ተዋቅሮ የተሰራ ሲሆን አንድ የውጭ ወራሪ አካልን ለመከላከል በቅንጅት ይሰራል፡፡ ታይመስ(Thymus)፣ ጣፊያ(Spleen) እና መቅን(Bone marrow) ሊንፎይድ ኦርጋንስ(Lymphoid organs) ይባላሉ፤ ልዩ የሆኑና በሽታ ተከላካይ ህዋሶች በመላ አካላችን ውስጥ በፍርንትት(Lymph nodes) ውስጥ እንዲከማቹ ይደረጋል፤ አንድ ቁስለት ወይም በበሽታ የመጠቃት ሁኔታ ሲያጋጥም ነጭ የደም ህዋሶች(Leukocytes or White blood cells) በዘውረ ደም(Circulatory System) እና በፍርንታዊ ስርዓት(Lymphatic System) በመዘዋወር ያገኙትን ባዕድ ነገር ወይም የበሽታ አምጭ እንቅስቃሴ ላይ ከበባ በማድረግ ጥቃት ይፈፅማሉ፡፡ ሶስት ዓይነት የነጭ ደም ህዋስ ያሉ ሲሆን ባዕድ በል(Macrophages)፣ ቲ-ህዋሶች(T-Cells) እና ቢ-ህዋሶች(B-Cells) ይባላሉ፤ ባዕድ በል(Macrophages) እና ቲ-ህዋሶች(T-Cells) በሽታ አምጪ ባዕድ ነገሩን ወይም አካሉን በመክበብ ይሰባብሩታል፤ ቢ-ህዋሶች(B-Cells) ደግሞ ባዕድ ነገሩን ወይም በሽታ አምጭ ዘአካሉን(Foreign Organ¬ism) ለይቶ የሚያጠቃ ፀረ እንግዳ አካል (Antibod¬ies) በማዘጋጀት በአካላችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ይከላከለዋል፡፡
አንዳንድ ፀረ እንግዳ አካል(Antibodies) የሚያዘጋጁ ቢ-ህዋሶች(B-Cells) የተከላከሉት በሽታ ከዳነ በኋላ፣ በሽታ አምጪ ጀርሞቹ ቢወገዱም እንኳን በሰውነት ውስጥ ይቆያሉ፤ የሰውነት የተፈጥሮ የመከላከል አቅም ወይም ድኅነት(The Immune System) አንድ አካል በመሆን አጥቅተው በነበሩት ባዕድ ነገር ላይ ቂም በመያዝ ይቆያሉ፤ ወደፊት እንኳን ቢመጡም አይዘነጓቸውም፤ ተዘጋጅተውም ይጠብቃሉ፤ ነገሩ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም ነውና፡፡ ለምሳሌ ሰውነታችን ከዚህ ቀደም ለጉድፍ(Chicken pox) በሽታ አምጪ አካል(Pathogens) ተጋልጦና ድኖ ከነበረ፣ ይህ አካል ድጋሚ ወደ ሰውነታችን ለመግባት ቢሞክር የሰውነት የመከላከል አቅም የተዘጋጀ ፀረ እንግዳ አካሉ(Antibodies) ስለሚኖረው በፍጥነት በመዋጋት ምንም ጉዳት ሳያደርስ ያጠፋዋል፡፡
እንዲህ ያለው የመቋቋም ኃይል መድኅን(Immunity) ይባላል፡፡ ይህንን የመድኅን ዘዴ በክትባቶች መልክ በማዘጋጀት ዓለም ለረዥም ጊዜ ሲጠቀምበት ቆይቷል፤ አሰራሩም መጠናቸው በጣም አነስተኛ የሆኑ የሞቱ ወይም በጣም የተዳከሙ በሽታ አምጪ ናሙና(Pathogens) ለሰውነት በማስተዋወቅ ሰውነት ተነቃቅቶ ለዚህ በሽታ አምጪ ናሙና ፀረ እንግዳ አካል(Antibodies) እንዲያዘጋጅ በማድረግ ነገሩ በከፋ ሁኔታ እንኳን ቢያጋጥም፣ ሰውነት የከዚህ በፊት አውቅ ካለው ምላሽ መስጠት እንዲያስችል የሚያደርግ ነው፡፡ እንደ ፖሊዮ ያሉ አስከፊ በሽታዎች ከዓለም ላይ ማጥፋት የተቻለው በዚህ ዘዴ ክትባቶችን በማዳረስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012