የተወለዱትና ያደጉት በኦሮምያ ክልል ጅማ ዞን አጋሮ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በአጋሮ ራስ ደስታ ትምህርት ቤት ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአጋሮ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በመቀጠልም በቅድስት ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስነ መለኮት ትምህርት ወስደዋል። በተጨማሪም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፎክሎርና ስነፅሁፍ የትምህርት መስኮች ሁለት የማስተርስ ዲግሪዎችን ይዘዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደጨረሱ ወደ ትውልድ ስፍራቸው አጋሮ ተመልሰው ቤተክህነትን ማገልገል እንደጀመሩ ግን በተለይ በጅማ በተፈጠረው ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት በሙስሊምና በኦርቶዶክስ ክርስቲያን አማኞች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል። በወቅቱ ታዲያ ለዘመናት ተቻችሎ የኖረው የሁለቱ ቤተእምነት ተከታይ ህዝብ ሰላም ዳግም እንዲመለስ የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። እኚህ የእምነት አባት ለዚህ አላማቸው መሳካትም ከሙስሊምና ከፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ከሆኑ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል።
በተለይም ደግሞ በግጭቱ ምክንያት በርካታ የእምነት ተቋማት ተቃጥለዋል፥ በርካቶችም ተገድለው ስለነበር ነዋሪው ሆድና ጀርባ ሆኖ በክፉ ይፈላለግ ነበር። የተፈጠረውን ችግር ለማሳመንና ወደ ቀድመው ፍቅር ለመመለስ ቀን ከሌሊት ከእነዚሁ ጓደኞቻቸው ጋር ሰሩ። ግጭቱ ሃይማኖታዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ለህዝቡ በማስረዳት ከጥፋት አጀንዳ እንዲመለስ በማድረግ ግንባር ቀደም ሚና ተጫወቱ። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን «የሰላም አምባሳደር» ብሎ ሰየማቸው።
በተጨማሪም የእኚህ የሃይማኖት አባት ጥረት ያዩ በወቅቱ የኢንሳ ዳይሬክተር የነበሩትና የአሁኑ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህንን የሰላምና የፍቅር ስራ እንዲሰሩ ትልቅ ግፊትና ድጋፍ ያደርጉላቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት ከአካባቢ አልፎ የአገርና የአለም ችግር እንዳይሆን ስጋት ስለነበራቸው ከራሳቸው ኪስ ሳይቀር ገንዘብ በማውጣት ከውጭ አገር ልምድ እንዲወስዱ በተደጋጋሚ ትልቅ ስራ ሰርተዋል። በተጨማሪም አጋሮ በተከበረው ትልቅ የቡና እና የሰላም ቀን ላይ «የሰላም ሐዋርያ» ብለው ሰርተፍኬትና ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል። ይህንን ተከትሎም በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በጋራ የሚሰሩበት ተቋም በጅማ ከተማ ተመሰረተ። ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የፈጠሩት የሰላምና የመቻቻል ጥምረት ዛሬ እሳቸው በዋና ፀሃፊነት ለሚመሩት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሰረት ጣለ።
በ2005 ዓ.ም ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ፡ በመቀጠልም ወደ ቤተክነት ተዛውረው በሰበካ ጉባኤ የመምሪያ ምክትል ሃላፊ ሆኑ። ካለፈው አመት ወዲህ በሲኖዶስ ውሳኔ ተወዳድረው በማሸነፍ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባኤ ዋና ፀሃፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከዛሬው እንግዳችን ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ዋናው ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት እስቲ ከስምዎት እንነሳና ብዙዎች ወደ ሃይማት መሪነት ሲመጡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን ስም ይቀይራሉ፤ እርሶ ግን አልቀየሩም፤ የተለየ ምክንያት ይኖሮት ይሆን ?
ቀሲስ ታጋይ፡- ልክ ነው፤ ብዙ የማውቃቸው አገልጋዮች መጠሪያ ስማቸውን ይቀይራሉ። ጥቂት የማይባል ሰው የእኔን ስም ሲሰማ ይደናገጣል፤ አንዳንዶቹም እንድቀይረው ብዙ ሰው ግፊት ያደርጉብኝ ነበር። እኔ ግን እናቴ ስላወጣችልኝ ብዙ ታሪክ ስላለው መቀየር አልፈለኩም። እናቴ እኔን ስትወልድ ለሶስት ቀናት ያህል ብታምጥም ቶሎ ልትወልደኝ አልቻለችም ነበር። በኋላም ትኖርበት ከነበረው ገጠር በቃሬዛ ተሸክመዋት መጥተው ጅማ ሆስፒታል ነው የተገላገለችው። በወቅቱ ለሶስት ቀናት ያክል ብዙ ስቃይ አይታ ስለወለደችኝ ሰዎች እንዴት ተገላገልሽ ሲሏት በትግል ብላ መልስ ትሰጣቸው ነበር። ከዚህ በመነሳትም ታጋይ የሚል ስያሜ አወጣችልኝ። ይሁንና ዋጋ የከፈለችልኝ ወላጅ እናቴ ፍቅሯን ብዙም ሳልጠግባት ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለው በማረፏ ይህንን ታጋይ የሚለውን ስም ማስታወሻ ይሆናት ዘንድ እስካሁን መጠሪያዬ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ከኮረና ቫይረስ (ኮቪድ 19) መምጣት በፊት በአገርም ሆነ በሃይማኖት ተቋማት ረገድ እርስ በርስ ግጭቶች ተፈጥረው ብዙ አይነት ጉዳት ደርሶ እንደነበር ይታወሳል፤ በዚህ ረገድ ጉባኤውም ሆነ የእምነት ተቋማት ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ማለት ይቻላል ?
ቀሲስ ታጋይ፡- እንደምታውቂው ይህ ተቋም የተቋቋመው በችግር ነው። ይህም ማለት የሃይማኖታዊ ትንኮሳዎች ፥ አክራሪነቱና ፅንፈኝነቱ በመብዛቱ ያንን ለማርገብ ሲባል የተወለደ ተቋም ነው። በወቅቱ በተለይም አንደኛው ሌላውን የመጥላትና እስከጥግ ድረስ የመሄድ፤ አንደኛው ሌላውን የማውገዝ፤ «ከእኔ በቀር ሌላ መኖር የለበትም» የሚል አስተሳሰብ ነግሶም ነበር። አብሮነት፥ መቻቻልና ሰላም ከሌለ ደግሞ ሰውም እንደሰው፤ ቤተ-እምነትም እንደቤተ-እምነት ሊቀጥል ስለማይችል ከዚያ ችግር ተነስቶ የተፈጠረ ተቋም ነው። በነገራችን ላይ ለብዙ አገራት ሞዴልም መሆኑንም መግለፅ እወዳለሁ።
በተለይ ደግሞ የሃይማኖት አስተምህሮችን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል። ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል «ሰዎች ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን እንዲሁ ለሌላው አታድርግ» የሚለውን አይነት ወርቃማ ህጎችን መሰረት በማድረግ ሃይማኖቶች በመከባበር በመቻቻል አብረው እንዲኖሩ ለማድረግ የሚያስችል መሰረት አለን የሚል ነበር መነሻው። ከዚህ አኳያ ይህ ተቋም በርካታ ስራዎችን ሰርቷል ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ጉባኤ ባይኖር ኖሮ አሁን የምናየውን ያህል ሰላማዊ ሁናቴ አናገኝም ነበር። በእርግጠኝነት በበርካታ አካባቢዎች ተነስተው የነበሩ ግጭቶችን መፍታት የተቻለው ይህ ተቋም በመኖሩ ነው። የተለያዩ የሰላም እሴት ስልጠናዎችን በመስጠት አብነት የሆነ ተቋም ነው። ጉባኤው ባይኖር ኖሮ እዚህ እዚያም የሚታየው የቤተ-እምነቶች መቃጠልና ግጭቶች የበለጠ ይሰፋ ነበር። መንግስት ስህተት ሲሰራ እንዲታረም የማስጠንቀቅና ግልፅ መረጃ ለህዝቡ እንዲያቀርብ በጉባኤው ይሞገታል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የሚሉት እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ሰዎች ይህ ተቋም ከመንግስት ጋር የሚሰራቸው ስራዎች አንዳንድ ጊዜ ህገመንግስቱ በሃይማኖት ተቋማትና በመንግስት መካከል ያስቀመጠውን ቀይ መስመር ጥሶ የመግባትና መንግስታዊ የመሆን ዝንባሌዎች መኖራቸውን ያነሳሉ፤ ይህ ምን ያህል ተጨባጭነት አለው ብለው ያምናሉ ?
ቀሲስ ታጋይ፡- ሊባል ይችላል፤ ሌላው ይቅርና አገራዊ ፀሎት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ስናውጅ ተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቶ መልስ ሰጥቼበታለሁ። ግልፅ ለማድረግ ከመንግስት ጋር በትብብር እንሰራለን። ይህንን የምናደርገው የሰላም አጀንዳ የጋራ ጉዳያችን በመሆኑ ነው። ልማታዊ ጉዳዮችም በትብብር እንሰራለን። ማህበራዊ ጉዳዮችንም እንዲሁ። ያ ማለት ግን እንቀላቀላለን ማለት አይደለም። እኛ የራሳችን መንገድ አለን፤ መንግስትም የራሱ ፖለቲካዊ መንገድ አለው። ነገር ግን እኛ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የምንጋራቸው ህዝቦችም አንድ በመሆናቸው በጋራ እንሰራለን። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ 97 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ህዝብ አማኝ ነው። ይህ ተቋም ይህንን ያህል ህዝብን ይወክላል። ስለዚህ አማኙ ከመንግስት በበለጠ የሚታዘዘው ለሃይማኖት ተቋማት ነው። የምንጋራው ህዝብ ይህንኑ ህዝብ በመሆኑ በችግር ሰዓት አብሮ መስራት ይጠበቅብናል።
ደግሞም ማን ቢሆን ሃይማኖቱ ሲነካበት ዝም ብሎ የሚያይ የለም። ሃይማኖትን ይወዳል፤ የሃይማኖት አባቶች የሚሉትን ይሰማል። ይህ ተቋም ባይኖርና ይህንን የፖለቲካ ስም ከሰጠነው በእርግጠኝነት ችግሮቹ ይከፉ ነበር። ነገር ግን ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲቀጥል ነገም ኢትዮጵያን ማየት ስለምንፈልግ በዚህ ጉዳይ ላይ ወጥተን እየሰራን ነው። በእርግጠኝነት ተቋሙ በመንግስት ስራ ላይ እንደማይገባ ሁሉ መንግስትም በጉባኤው ስራ ጣልቃ የሚገባበት አግባብ የለም። ነገር ግን ከመንግስት ጋር በትብብር እየሰራን ነው፤ ወደፊትም እንሰራለን። የምንሰራው ግን በፖለቲካ አጀንዳ ላይ አይደለም። የምንሰራው ህዝባዊ አጀንዳና በማህበረሰቡ ችግሮች ላይ ነው። ይህንን ስራ መስራታችን ደግሞ ፖለቲከኞች ካስባለን ምንም ማድረግ አይቻልም።
በእርግጠኝነት የምናገረው ግን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መቶ በመቶ ከፖለቲካ ጥገኝነት ነፃ መሆኑን ነው። እኛ የሃማኖት ተቋማት ነን፤ ትናንት የነበረው የፖለቲካ ስርዓት ዛሬ የለም፤ ዛሬ ያለ ስርዓት ነገ ላይኖር ይችላል። የሃይማኖት ተቋማት ግን የፈጣሪ መመለኪያ አፀድ (ቤት) በመሆኑ ትናንት ነበሩ ዛሬም አሉ ነገም ይቀጥላሉ። የፈለገው መጥቶ የሃይማኖት ተቋማትን ሊያፈርስ አይችልም። ይህ አቋማችን ነው። ህዝቡም ሆነ መንግስት ይህንን ያውቃሉ። ለምሳሌ አሁን መንግስትን ንስሃ ግባ ብለን ጠርተናል። ህዝቡንም ንስሃ ግቡ ብለናል። የበደልነው አለ ብለናል። ምክንያቱም ባለፉት አመታት ቤተ እምነቶች ተደፍረዋል፤ በግፍ ተቃጥለዋል። ሰዎች ተገድለዋል። ሰዎች በማንነታቸው ተፈናቅለዋል። ስለዚህ ይህ በሆነበት ሁኔታ ሁሉም ዜጋ ሊያደርግ የሚገባው አንዱ ተግባር ንስሃ መግባት ፈጣሪውን መማፀን ነው። ሁሉም ከሰራው ሃጥያት መመለስ አለበት። በቤተመንግስትም፥ በቤተክነትም፥ በቤተመስኪድም በየትኛውም አመራሮች ሁሉም ህዝብ ማቅ ይልበስ ራሱን ካለበት ከፍታ ያውርድ። ይህንን ጥሪ ማቅረብ ሃላፊነት የእኛ ነበር። ይህንንም አድርገነዋል፡ ይህንን ማድረጋችን ፖለቲካዊ አንድምታ ከተሰጠው በጣም የተሳሳተ ነው።
በሌላ በኩልም በእኔ አረዳድ ለፖለቲካው ሲል መንግስት ሰላምና ልማት ሊያመጣ ይችላል። ነገር ግን ሰላም ፖለቲካ አይደለም፤ ልማት ፖለቲካዊ አይደለም። ለህዝብ ጥቅም እስከዋለ ድረስ የሚሰራው ልማት እኔ ፖለቲካዊ ትርጉም አልሰጠውም። ስለዚህ ይህንን እንደግፋለን። እዚህ አገር እገሌ የሰራው ስለሆነ ተብሎ የሰራ ልማት እንዲጠፋ ይደረጋል። ምክንያቱም ሁሉም ነገር ፖለቲካዊ ትርጉም ስለሚሰጠው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቤተ እምነት መካከልም ሆነ በፖለቲካው ረገድ ጦዞ የነበረው ውጥረት የኮረና መምጣት አረጋግቶታል፤ ሰዎች ሁሉ ትኩረቱን በሽታውን መከላከል ላይ አድርጎታል ብለው የሚናገሩ ግለሰቦች አሉ፤ በዚህ ሃሳብ እርሶ ይስማማሉ ?
ቀሲስ ታጋይ፡- እኛ ሲጀመር እውነት ለመናገር ከወቅታዊ ችግር ወቅቱ አለም እጅግ እየተሰቃየ ፤ መሄጃ አጥቶ እየተቸገረ ባለበት ሰዓት የኮረና ቫይረስ ተጨማሪ የቤት ስራ ሆኖ መምጣቱ እጅግ ያሳስበናል። ሰው ከፈጣሪ ርቆና ፈጣሪውን ረስቶ ሌላ አለም ውስጥ ገብቶ ነበር። እኛ የሃይማኖት ሰዎች ነን። በተለይ ኢትዮጵያ ከ40 ጊዜ በላይ በመፃሃፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሳለች። እንደተባለው አለም በተለይ አውሮፓና አሜሪካ በዓመታት ውስጥ የተሰሩት ወንጀሎች ፈጣሪን ያስቀየመ እንደአማኝ እንረዳለን። አንዳንድ አገራት ራቁታቸውን አስፋልት ላይ ምን ሲሰሩ እንደነበር እናውቃለን። በሁለተኛ ደረጃ ወንድ ከወንድ ጋር ሴት ከሴት ጋር ግብረሰዶም ሲፈፀም የነበረበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል። በነገራችን ላይ ፈጣሪ የሚቀየምበትና የሚያዝንበት ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው የሚሰጡን ዶላር ይቅርብን ግብረሰዶማውያን አይግቡብን ብለን መጀመሪያ መግለጫ የሰጠነው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ነው። ያለን የሰራነው ሃጥያት ይበቃናል። ሌላ ሃጥያት አይጨምሩብን ብለን ነው አቋም የያዝነው።
ከአራትና ከአምስት ወር በፊት እንደምታስታውሽው በአገራችን በከፍተኛ ሁኔታ በአንበጣ ተወረን ነበር። ይህ የሆነው እኛ በሰራነው ሃጥያት ነው። በወቅቱ አንድ ሚዲያ ላይ ተጠይቄ በአንበጣ አትገረሙ ገና እሳት ይዘንባል ብዬ ነበር። አሁን ከመጣብን ችግር በላይ እሳት የለም። እውነት ለመናገር ትንቢት ተናጋሪ ሆኜ ሳይሆን የሰራነው ሃጥያት ከዚህም በላይ ዋጋ የሚያስከፍለን በመሆኑ ነው። አሁን ላይ የፈጣሪን ቁጣ በተለያየ መልክ እያየን ነው። ኮረናን ብናስወግድም ከመንገዳችን ካልተመለስን ከኮረና የበለጠ ችግር ሊመጣብን ይችላል። ሰው በንስሃ መንበርከክና መመለስ አለበት። የትናንትናውን ኢትዮጵያዊ በጎነታችንን ማምጣት አለብን።
በቅዱስ መፃሃፍ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ አምላኳ ትዘረጋለች» ተበሎ ቢፃፍም ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ነው በጠራራ ፀሃይ ሰው ተዘቅዝቆ የተሰቀለው፤ እናት ተቸግራ ያስተማረችውን ልጇን ከፎቅ ላይ ተወርውሮ ሬሳውን የተቀበለችው እኮ እኛ አገር ውስጥ እኮ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ነው በማንነቱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የተፈናቀለው። ጎሳዎች በድንበር የተጋጩት እኮ ኢትዮጲያ ውስጥ እኮ ነው። ለዚህ ንስሃ ያስፈልገዋል። ታዲያ አሁን ላይ የንስሃ ጥሪ ካልጠራን መቼ ነው የምንጠራው? ። ስለዚህ አለም በሰራው ሃጥያት ሳይሆን እኛ በሰራነው ሃጥያት ነው ንስሃ መግባት ያለብን። ምክንያቱም አለም በራሱ መንገድ ዋጋውን እየከፈለ ነው ? እኛ ከአለም ጋር የምንፎካከር ሰዎች አይደለንም።
በእርግጥ እነሱ እምነት አያስፈልግም ብለው ቤተ መቅደሶችና የማምለኪያ ስፍራዎችን ወደ ዳንኪራና መሸታ ቤት እንዲሁም ወደ ሙዚየምነት ቀይረው ነበር። አሁን ኮረና ሲመጣ በዘጓቸው ቤተእምነቶች ደጃፍ ላይ ተንበርክከው ማልቀስ ጀምረዋል። በቀን ሁለትና ሶስት ሺ አስክሬን እየሰበሰቡ ነው። ፈጣሪ መኖሩን አሁን አለም እየመሰከረ ነው። ምክንያቱም በገንዘብና በሃብታቸው ማዳን የማይችሉት ፈውስ የሌለው በሽታ መጣባቸው። ስለዚህ ወደ ፈጣሪ መመለስ አማራጭ ሳይሆን የግድ ምርጫችን ነው። ወደ ፈጣሪ የማንመለስ፥ ንስሃ የማንገባና በፀሎት የማንተጋ ከሆነ በእርግጠኝነት ከዚህ የባሰም ሊመጣ ይችላል። ለዚህም ነው የፀሎት መርሃግብሩ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተገበር የተደረገው። አሁን ላይ ህዝቡ በዘርና በልዩነቶቹ ላይ መጋጨት በመተው በአንድ መንፈስ ይህንን መርሃግብር እየተከተለና ፈጣሪውን እየተማፀነ ነው የሚገኘው።
አዲስ ዘመን፡- የፀሎት መርሃ ግብሩ በክልሎች ላይ በተጨባጭ ተግባራዊ እየሆነ ነው ማለት ይቻላል? በተለይ በአንዳንድ ክልሎች ግጭቶች አሁንም አሉ፤ በዚህ ሁኔታ ንስሃ የመግባቱና ወደ አንድ የመመለሱ ሁኔታ ስኬታማ ነው ለማት አይከብድም ?
ቀሲስ ታጋይ፡- እንግዲህ የፖለቲካ በር የተዘጋባቸው ክልሎች ካሉ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ ለእኛ ግን የትኛውም በር ክፍት ነው። በቅርቡ ትግራይ ሄጂያለው፤ ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር ተወያይተናል።ስለዚህ እኛ የሃይማኖት ሰዎች እንጂ ፖለቲከኞች ስላልሆን የተዘጋብን በር የለም። በስራ ጉዳይ እየተገናኘን ነው። አሁንም ድረስ የትግራይ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ምህላና ፀሎታቸውን እያደረጉ ነውና ከእኛ ጋር እየሰሩ ነው። ለዚህ ነው ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለየዩ ናቸው የምንለው። በእርግጥ የፖለቲካ ችግር ካለባቸው ተወያይተው መፍታት እንዳለባቸው እናምናለን፤ ይፈቱታልም ብለን እንጠብቃለን። ይህም ቢሆን ግን ሰው እንደሚያስበው ተራራ የሚያክሉ ችግሮች አሉ ብዬም አላስብም። በመወያየት የሚፈቱ ችግሮች ናቸው ያሉት።
በሁለተኛ ደረጃ እዚህ እዚያም የሚታዩ ችግሮችም በውይይት መፈታት እንዳለባቸው እናምናለን። እኛ እንዳውም ፀሎት ከማድረጋችን በፊት እውነተኛ እርቅና ይቅር መባባል እንዲመጣ ጠይቀናል። እኛ ይቅርታ ስንጠይቅ የነበረው የተጣላነው ሰው ኖሮን ሳይሆን አብነት ለመሆን ከማሰብ ነው። ለጠቅላይ አቃቢ ህግም በደብዳቤ በተለየያ ምክንያት የታሰሩ ዜጎች በይቅርታ መንፈስ ይቅርታ እንዲደረግላቸው በይፋ ጠይቀናል። ይህ ወንጀል አይደለም። እኛ የሃይማኖት ሰዎች ነን። ከሜቴክ ጋር ተያይዞም ሆነ ከሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የተያዙ ሰዎች መንግስት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ጠይቀናል። ሰዎችን በማሰር ዋነኛ አላማው ማስተማር ስለሆነ መንግስት ይቅርታ እንዲያደርግ ጠይቀናል። ያንን ያዩ የታሳሪ ቤተሰቦች ተንደርድረው እኛ ጋር መጥተው ነበር። በነገራችን ላይ ይህን ያልነው ማንነት ላይ መሰረት አድርገን አይደለም፤ ሰው በመሆኑ ብቻ ነው። እርግጥ ነው ይህንን ጉዳይ ፖለቲከኞች ለራሳቸው አላማ ይጠቀሙበታል። ለእኛ ግን ከብሄርና ከአገርም በላይ ሰውነት ይቀድማል ባዮች ነን። በሰውነታችን መግባባት መቻል አለብን። ይህም ሲባል ማንነታችን እንረሳለን ማለት አይደለም። ለምሳሌ እኔ ኦሮሞ ነኝ፤ ግን ኦሮሞ ከመሆኔ በፊት ሰው ነኝ። ምክንያቱም ከፈጣሪ የተሰጠኝ ትልቁ ፀጋ በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደተናገሩት ከእምነት አኳያ ሁሉንም ይቅር ማለት ይገባ ይሆናል፤ ነገር ግን የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም ወይ? ወንጀሎችስ ይበልጥ እንዲበረታቱ ምክንያት አይሆንም ?
ቀሲስ ታጋይ፡- ልክ ነው፤ ይህንን የሚወስነው መንግስት ነው፤ እኛ ደግሞ እንደሃይማኖት አመራርነታችን ከማሸማገል አንፃር መደረግ አለበት የምንለውን ነው እየገለፅን ያለነው። የህግ የበላይነት ይከበር መባሉ ትክክል ነው። በሌላ በኩል ግን በርካታ ሰዎች ሞተው በህግ ያልተጠየቁ ሰዎች አሉ። የህግ የበላይነት በሁሉም ሰው ላይና አካባቢ እያስከበርን መሆኑ በራሱ አጠያያቂ ነው። ለነገሩ እዚያ ውስጥ ብዙ መግባት አልፈልግም። ነገር ግን እኛ እያልን ያለነው ዝም ብሎ ማንም ሰው እየተነሳ እንደፈለገ የሚያደርግ፥ ማንም የጎበዝ አለቃ ተነስቶ እንደፈለገ፣ ማድረግ የለበትም። እሱ እንዲመጣ አንፈልግም፤ መሆንም የለበትም። ማስተማር ያለበትን መንግስት ማስተማር አለበት። እኛ ደግሞ ነፃ እንደሆነ ሰው ይህንን ጥያቄ ማቅረባችን ደግሞ ተገቢነት አለው። ይህንን እያደረገ ነው፤ ነገር ግን ከፊሉን ሲፈታ ሌላውን እየተወ ነው። ስለዚህ ይቅርታ ማድረግ ካለበት ለሁሉም ነው የሚል መነሻ አለን።
እንዳልኩት ግን ሁሉም እየገባ የህግ የበላይነቱን እያከበረ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ይህ የሚሰራው ለከፊሉ ብቻ መሆን የለበትም የሚል አቋም ነው ያለኝ። እኔና አንቺ በተመሳሳይ ወንጀል ታስረን ላንቺ ይቅርታ ተደርጎ እኔ የምቆይበት ምክንያት ተቀባይነት አይኖረውም።
ማስተማር ወይም የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት ማለት እኮ ዝም ብሎ እስር ቤት መሰብሰብ ማለት አይደለም፤ ተምረሽ በይቅርታና በአመክሮ የምትወጪበትም አጋጣሚም አለ። ህግ ለማስከበር እኮ አንድ ቀን በቂ ነው። ስለዚህ ማድረግ ያለብን ለሁሉም እኩል የሆነ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው። በነገራችን ላይ ህግ ይከበር ብሎ እንደሃይማኖት ተቋማት የጮኸ የለም። ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት ሰው በደቦ እየወጣ መንገድ መዝጋት የሰውን የመንቀሳቀስ ነፃነት መገደብ አይነት ሁኔታዎች ሲከሰት ትክክል አይደለም ብለን ስንጮህ ነበር። ነገር ግን መንግስት ለማስተንፈስ የተጠቀማቸው ነገሮች ዋጋ አስከፍለውናል። ቤተእምነቶች የተቃጠሉት በዚያ መልኩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፤ አዋጁ ከደነገጋቸው ጉዳዮች አንዱ በጋራ መሰብሰብ መከልከሉ አንዱ ነው፤ በአንፃሩ ጥቂት የማይባለው አማኝ አሁንም በቤተ እምነቱ አለመሄድና አለመሰብሰብን በፀጋ ለመቀበል ተቸግሯል፤ ከዚህ አኳያ ተቋማቱ ምን እየሰሩ ነው ማለት ይቻላል?
ቀሲስ ታጋይ፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጣው ለህዝብ ጥቅም ነው ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ምንነት የህግ ሰዎች ከራሳቸው እይታ ሊተረጉሙት ይችላሉ፤ ለእኔ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህዝብን የማዳንና አገርን የመታደግ ጥሪ ነው። በታሪክም እንደምንረዳው ነጭ ወራሪ ከውጭ ሲመጣ አፄ ምኒሊክ « ምታ ነጋሪትና ክተት ሰራዊት» ብለው አስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል። ከተዋጓቸው አካላት ጋር ያላቸውን ልዩነት ይዘውም ቢሆን ወራሪ ሲመጣ በአንድነት ዘምተዋል። ህዝቡ በአንድነት ዘምቶ ያለምን የብሄር ልዩነት የመጣውን ወራሪ በመመከት አድዋ ላይ ተዋድቋል። በተመሳሳይ ዛሬ ነጭም ሆነ ጥቁር የማንለው ብሄር የሌለውና ብሄር የማይመርጥ ትልቅ ወራሪ መጥቶብናል። ኮቪድ 19።
አሁን የመጣብን ጠላት በስጋ ጦር ይዘን ጋሻ ይዘን የምንዋጋው አይደለም። ይልቁንም ልንዋጋው የምንችለው እንደሃይማኖት ሰው በመንፈሳዊ ትጥቅ ነው። እንደ ጤና ባለሙያ ደግሞ በመጠንቀቅ ነው። መንግስት ያወጀው አዋጅ የጥንቃቄ አዋጅ ነው። ይህ ወራሪ ደግሞ መሳሪያ ይዞ መጥቶ ፊት ለፊት የሚያጠቃን አይደለም። በስውር በመንፈስ የሆነ ደባ ነው የሚሰራብን። ይሄን ለማድረግ ደግሞ ጤና ባለሙያዎች የሚሉን እየተገበርን እኛ ደግሞ እንደሃይማኖት አባት መንፈሳዊ ትጥቅ ታጥቀን፥ የመለየትን፥ የክፋትን መንፈስ አጥፍተን አንዱ አንዱን የመርዳትና የመደገፍ ስራ ነው የሚጠበቅብን። የምንመክረውም መንፈሳዊነትን ተላበሱ በፀሎት ትጉ ብለን ነው። እርግጥ ነው ባለፉት ዓመታት ይህንን ትጥቅ አውልቀን ዘረኝነት ውስጥ ገብተን ነበር። አሁን ከዚያ ውስጥ ወጥተናል።
ስለዚህ መንግስት ያወጀውን አዋጅ እኔ በመልካም ጎኑ ነው የወሰድኩት። በአዋጁ መሰረት ከአራት ሰው በላይ መሰብሰብ አይጠበቅብንም። በነገራችን ላይ ይህንን ካልተገበርን መንግስት ባይገለንም በሽታው ሊገድለን ይችላል። አንዲት እናት ልጇን ክትባት የምታስከትበው ልጇን ለመግደል ሳይሆን ሊመጣ ከሚችለው በሽታ ለመታደግ እንደሆነ ሁሉ መንግስትም አዋጁን ያወጣው እኛን ለመታደግ ሲል መሆኑን አማኙ ተገንዝቦ የሚባለውን መተግበር ይጠበቅበታል።
በነገራችን ላይ መንግስት ከተማ መዝጋት እኮ አቅቶት አይደለም። ሰው በርሃብ ወረርሽኝ እንዳይሞት ከሚል እሳቤ ነው። ለዚህ ደግሞ ልናመሰግነውና ልንተባበረው ነው የሚገባን። ከዚህ አኳያ በእርግጥ ሁሉም ቤተእምነት በሚባል ደረጃ በጎና ጥሩ የሆነ ምላሽ ነው የሰጡት። ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ ወጣ ገባ የማለት ነገር ቢኖርም ማለት ነው። ይህንን ከማስፈፀም አኳያ ህዝቡ ከነበረበት ቤተእምነት ተለይ ሲባል የሚሰማው ስሜት እኔም አንቺም ጋር ያለ ነው። ይህ በክፋት መመንዘር የለበትም። ወደ ፖለቲካ መንገድ መውሰድም አይገባውም ። የሩሲያ መንግስት ህዝቡ እንደእኛ አማኝ በመሆኑ ትፅዛዙን ላይተገብሩ ይችላሉ ብሎ 800 አንበሳና ነብር እለቃለሁ በማለቱ ነው ህዝቡ ቤቱ የተሰበሰበው። የአገራቸው መንግስት ይህንን ያደረገው ህዝቡን ስለሚወድ እንጂ ስለሚጠላ አይደለም። ስለዚህ አዋጁ ለጥቅማችን የወጣ መሆኑን ህዝቡ ተገንዝቦ ይህንን ሳይሸራረፍ መተግበር አለበት። አገልጋዩ በቴሌቪዥን ሲያስተላልፍ ባለበት ሆኖ ምዕመኑ መቀበል መቻል አለበት። መንግስት የዚህ በሽታ ስርጭት ከቁጥጥሩ ካመለጠ ልንወጣው ከማንችለው አዘቅት ውስጥ ነው የሚከተን። በመሆኑም ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባናል። ምክንያቱም ይህ በሽታ በሚሳኤል ወይም በገንዘብ አይመለስም። የሚመለሰው በጥንቃቄና በፈጣሪ ሃይል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልክ እንደፖለቲከኞቹ አክቲቪስቶቹ ሁሉ ተከታይ ያላቸው የሃይማኖት ሰዎች ዝምታቸውን ሰብረው መውጣትና ህዝብን ማስተማር አይገባቸውም ይላሉ?
ቀሲስ ታጋይ፡- በነገራችን ላይ ፖለቲከኞቹ ማሰብ ይገባቸዋል ብዬ የማስበው ምርጫ የሚኖረው ይህ ህዝብ ሲኖር ነው። ሃገር የሚኖረው ይህ ህዝብ ሲኖር ነው። ስለዚህ ማንም ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ዝም ሊል አይገባም። ተነስቶ ሲናገር ደግሞ የፖለቲካ ታፔላ መስጠት ደግሞ አይገባም። በተመሰሳይ የሃይማኖት ሰዎች የሆኑና ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሰዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ግራ የተጋቡ ይመስለኛል። ሲጀመርም በቤተእመነት ውስጥ ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባል ነገር የለም። የሚናገረው ፈጣሪ ነው። እሱ ብቻ ነው ተፅእኖ ፈጣሪ። ከራሳችን ምንም አይነት ድርስት ደርሰን አማራጭ ብለን የምናቀርበው የለንም። የምናገረው መፅሃፍ ቅዱስ ወይ ቅዱስ ቁርዓን ነው። መደነቅ ካለበት ፈጣሪ ነው። ከዚያ ውጭ ሰዎች ልናደንቃቸው ልንከተላቸው አይገባም። ምክንያቱም ብዙዎችን ተከትለናቸው ሲወድቁ አይተናል። በራሳቸው ትምክህት ውስጥ የነበሩ ሲወድቁ አይተናል።
ከዚህ አኳያ እያስተማሩ እየተናገሩ ያሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ብዥታ ውስጥ ያሉ አሉ። ምክንያቱም ይሄ ነገር ከመምጣቱ በፊት ሌላ ነገር ሲሉ ነበር። ከመጣ በኋላ ግን ዝምታን መረጡ። አሁን ቢናገሩ ደግሞ ትናንትና ሲናገሩ የነበረው ማስረጃ ይቀርብባቸውና ሌላ ችግር ስለሚፈጥርባቸው ነው ዝምታን የመረጡት። እኔ ግን ዝምታቸውን ሰብረው ይቅርታ ጠይቀው አስተምህሮውን በትክክል ማስተማር ይገባቸዋል ባይ ነኝ። አባዛኞቹ ከዚህ ቀደም «ኮረና ቫይረስ በእኛ ዘንድ ስልጣን የለውም» ሲሉ የነበሩ ናቸው። እኔ ግን ለእነዚህ ሰዎች የምላቸው በትክክል መፅሃፍ ቅዱስን ወይም ቅዱስ ቁርዓንን እንዲያነቡ ነው። እርግጥ ነው የሚያድነን እምነታችን ነው። አማኝና እምነት ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው። በርካታ የእምነት ተቋማት ቢኖሩንም ትክክለኛ የሆነ አማኝ ማግኘት ግን አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ ፀበል እንደሚያድን አምናለሁ። ግን ያለ ግለሰቡ እምነት ፈውስ ሊመጣ እንደማይችል እረዳለሁ። ብዙ ሰው የሚታለለው እዚህ ጋር ነው። ሃዋርያት እንኳን የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት የላችሁም ከተባሉ እኛ ምን አይነት እምነት ሊኖረን ይችላል?።
አሁንም አንዳንድ የሃይማኖት አስተማሪ በእምነት ሰበብ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ህዝቡ እንዳይቀበል የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ። ይህ ትክክል አይደለም። ራሳቸው የማያደርጉትን ነገር ለህዝብ ማስተማር አይገባቸውም። እነሱ ቤታቸው ተሸሽገው በማህበራዊ ገፆቻቸው ህዝቡን ወደአጉል ድፍረት የሚገፋፉ አካላት ከዚህ ስራቸው ሊመለሱ ይገባል። ህዝባችንን ወደ እሳት እየማገድን እኛ ልንኖር አንችልም። ከበደ እሳት ውስጥ ገባና አየለም ተከትሎት ሊገባ አይችልም። መጠንቀቅ ማለት ደግሞ አለማመን ወይም ከሃይማኖት መውጣት ማለት አይደለም። ደግሞም እንድንጠነቀቅም ፈጣሪ አስተምሮናል። መንፈስንም እንድንመረምር ስልጣን ተሰጥቶናል። እርግጥ ነው ዛሬ የተደበቁ ሰዎች ነገ ሁሉም ሰላም ሲሆን አይናቸውን በጨው አጥበው መምጣታቸው አይቀርም። ሲመጡ ግን በእኛ ፀሎት ለውጥ ማለታቸው አይቀርም። ግን ክብሩንም ሆነ እውቅናውንም ሊወስድ የሚገባው ፈጣሪ ነው። በመሆኑም አየሩን እያዩ ህዝቡን ከማደናገር ወጥተው ለህዝቡ ሊጮሁ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በነበረው የፀሎት መርሃ ግብር ላይ ኢቪሲ የፕሮቴስታንት ወይም የወንጌል አማኞች ካውንስል ፕሮግራሙን ሲያካሂድ መልዕክቱ የቤተ እምነቱ እንጂ የተቋሙ አለመሆኑን መግለፁ፤ በሌላኛው ተቋም ላይ ያለመፃፉ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፤ አሁንም ልዩነት አለ በሚል በየማህበራዊ ድረገፁም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይህንን ጉዳይ እርሶ አጢነውት ነበር ?
ቀሲስ ታጋይ፡- እኔ እንዳውም አዲስ ሚዲያ ኔት ወርክ ለሁሉም ሲፅፍ ተመልክቻለሁ። ይህም ማለት የሚዲያው አቋም አለመሆን ለማስረዳት እንጂ የተለየ አንድምታ አለ ብዬ አላምንም። ደግሞም መብቱም ነው፤ ትክክልም ነው። እኛም የምናስተላልፈው የቤተ እምነቱን አምልኮ ስርዓት እንጂ የመገናኛ ብዙሃንን የአምልኮ ስርዓት አይደለም። ነገር ግን መደረግ ካለበት ሁሉም ቤተእምነቶች ላይ ነው። ግን ሆነ ተብሎ ተደርጓል ብዬ አላምንም። አንዳንድ ጊዜ ሰኔና ሰኞ ይገናኛል። በመሆኑም ሁሉንም ነገር በአንድ አቅጣጫ መመልከት ተገቢ አይደለም። ህሊናና ሙያዊ አስተሳሰብ መኖሩንም መዘንጋት የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ።
ቀሲስ ታጋይ፡- እኔም እዚህ ድረስ መጥታችሁ እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመስገናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012