በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩትና ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው በዓላት አንዱ የትንሳኤ ወይም የፋሲካ በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል ከበዓሉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሚከናወኑ መንፈሳዊ ሥነስርዓቶችና በበዓሉም ዕለት ወዳጅ ዘመድ በጋራና በመተሳሰብ የሚያከብረው የደስታ በዓል ነው፡፡ አብሮ መብላት መጠጣቱ አኩሪ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ከመሆኑም በላይ ለመደጋጋፍ መተጋጋዝ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ አንድነትንም ያጠናክራል። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን ባጋጠማት የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያትነትና ወረርሽኙም በአብዛኛው የሚተላለፈው በመጠጋጋትና በመሰባሰብ ከመሆኑ አንጻር የዘንድሮውን ፋሲካ በልዩ ጥንቃቄ ማክበር ያስፈልጋል፡፡
በፋሲካ በዓል በጋራ ሆኖ ከብት ማረድና ቅርጫ መቃረጥ የተለመደ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ተሰባስቦ ማረድንም ሆነ ስጋ መቃረጥን የሚፈቅድ ባለመሆኑና ይህንን ማድረግ በራስ ፍቃድ ሞት እንደመጥራት ስለሚቆጠር ሁሉም ሰው የርስ በርስ መቀራረብን በማስወገድና ከተቻለም በየመንደሩ የሚደረጉ የጋራ እርዶችን በመተው በዓሉን በተለየ ጥንቃቄ ማሳለፍ ይገባዋል፡፡ እንደሚታወቀው በተለይም የቅርጫ እርድ ሥጋውን ለብዙ ሰዎች እጅ ንክኪ የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በዚህ ላይ በባህላችን ጥሬ ስጋ መብላት ስለተለመደ ንክኪው የቫይረሱን ስርጭት በከፍተኛ መጠን እንደሚያሳድገው አይጠረጠርም።
በበዓሉም ዕለት እንደቀድሞው ከዘመድ አዝማድ ወይም ከጎረቤት ጋር በመሰባሰብ እለቱን ለማክበር መሞከር የራሱን አደጋ ይዞ ስለሚመጣና ለቫይረሱም ስርጭት ዓይነተኛ መንገድ ስለሚሆን ብሎም መጠራራቱና መሰባሰቡን ወረርሽኙ ከጠፋ በኋላ የምንደርስበት ስለሆነ ከዚህ በመታቀብ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጎ በዓሉን ማሳለፍ ብልህነት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በጥሬያቸው ከመመገብ ይልቅ አብስሎና ጠብሶ መመገቡ የኮሮና ቫይረስን የመተላለፍ ዕድልን ለመገደብ ይረዳል፡፡
የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ፣ ክፉ ቀንንና ጥይትን ጎንበስ ብሎ ማሳለፍ ይበጃል የሚሉት አገርኛ ብሂሎች ከላይ ለተንደረደርንበት ጉዳይ ሁነኛ አባባሎች ናቸው። ምክንያቱም ኮሮና ወቅታዊ ችግር ነውና መፍትሄ ተገኝቶለት፣ ማለፉ አይቀሬ ነው። በሌላ አነጋገር ኮሮና እንደሚያልፍ ዝናብ ነው። ትንሳዔ ወይም ፋሲካ ደግሞ የዛሬ ዓመትም ሆነ ከዚያም በኋላ ቀኑን ጠብቆ ለቀጣይ ዓመታት የሚከበር በዓል ነው። ስለሆነም ለማያልፈውና ለዘላቂው ስንል አላፊው ሳይጎዳን መዝለቅ መቻል ይኖርብናል።
እዚህ ላይ ግልጽ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ ግን ለኮሮና ጥንቃቄ ሲባል ልንታቀብ የሚገባን ከማህበራዊ ርቀት እንጂ ከማህበራዊ ግንኙነት እንዳልሆነ ነው። ይልቁንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄን በተላበሰ መልኩ ማህበራዊ ግንኑነታችን እና መተሳሰባችን ይበልጥ ሊጠናከር ይገባዋል። ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የብዙ ሰዎች ሥራ እንደተቀዛቀዘ ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት በዓሉን ማክበር ይቅርና የዕለት ጉሮሮን መድፈን ያዳገታቸው ብዙዎች መሆናቸውም አይካድም። እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች ማዕድ ማጋራትና መደገፍ ደግሞ ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ በረከቱ ብዙ ነው።
የእምነቱ አባቶች እንደሚያስረዱት ትንሳዔ የፍቅር፣ የመስዋዕትነት፣ የመተሳሰብና የአንድነት በዓል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞትን የሞተውም የሰው ልጆችን ከጨለማና ከሞት ለማዳን ብሎም ህዝብና አህዛብ የሚባሉ የልዩነት ድንበሮችን በማፍረስ የሰው ልጆችን አንድ ለማድረግ ነው። ስለሆነም ትንሳዔ ሲከበር የበዓሉ ምሰሶዎች የሆኑት ፍቅር፣ መዋደድ፣ አንድነትና መተሳሰብ በጎሉበት መልኩ ሊሆን ይገባል።
በተለይም የዘንድሮው የትንሳዔ በዓል የሚከበረው ዓለም አቀፍ ችግር የሆነው ኮሮና በብዙ የአገራችን ዜጎች ኢኮኖሚ ላይ ጥቁር ጥላውን ባጣለበት ወቅት ላይ እንደ መሆኑ ማዕድ በማካፋል፣ የተቸገሩትን በማገዝ እና የአንድነት ስሜትን በማጠናከር ሊከበር ይገባዋል እንላለን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012