ስላለንበት 21ኛው ክፍለዘመን ብዙ ተብሏል፣ በርካታ አዳዲስ ነገሮችም ታይተዋል፡፡ ከምጡቅ የቴክሎጂ እድገቶች፣ ተዓምር እስከሚመስሉ የሳይንስ ግኝቶች፣ የሰው ልጅን ይተካሉ ከተባሉ ሮቦቶች፣ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ይችላሉ እስከተባሉ አዳዲስ ፕላኔቶች ግኝት፣ ከሰው ልጅ አካላዊ ንቅለተከላ፣ ከአንድ ህዋስ ህይወት እስከመፍጠር፣ ወዘተ ተመልክተን ተደንቀናል፡፡ በዚህ የሰው ልጅ ድርጊት የተነሳም ፈጣሪ ስለመኖሩ እስከመጠራጠር የደረሱ ወይም የተዳፈሩ ሰዎችንም ታዝበናል፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬ ያ የቀደመ የሳይንስ ግኝት ወይም የቴክኖሎጂ እድገት ሞትን ማስቀረት አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎም ከዚህ ቀደም በሃብታቸውና በእድገታቸው ሰማይ የነኩና ዓለምን በእጃቸው መዳፍ ውስጥ ያስገቡ የሚመስላቸው አገራት ላይ የደረሰው ብርቱ ክንድ ቅጣቱን ተያይዞታል፡፡ በዚህ የተነሳ ጥቂቶች ፊታቸውን ወደፈጣሪ እንዲመልሱም እድል ሰጥቷል፡፡ በተለይ ዛሬ የምናከብረው የስቅለት በዓል ይህንን የሰው ልጅ ግብዝነት በአንክሮ እንድንመለከትና ከቴክኖሎጂ እድገት ባሻገር ፈጣሪንም መፍራት ተገቢ መሆኑን ያሳየ ሆኗል፤ ኮሮና፡፡ የዘንድሮ የስቅለት በኣልም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በመላው አለም ፈጣሪን በመለመንና በመረዳዳት እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የዛሬው አርብ ከሌሎች ቀኖች ሁሉ የተለየ ነው፡፡ እውነትና ሐሰት፣ ወዳጅና ጠላት፣ ተስፋና ስጋት፣ እምነትና ፍርሐት፣ እምባ እና ሳቅ፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ጽናትና ድካም የተቀላቀሉበት ጊዜ ነው። እየነጋ ባለ ፀሐይና በድቅድቅ ጨለማ መካከል ያለውን ቀጭን መስመር ለመለየት የሚያስቸግርበት ቀን ነው። በአንድ በኩል በጦር ጉልበታቸው የሚተማመኑ ሮማውያን፣ በሌላ በኩል እናውቃለን የሚሉ የአይሁድ ሊቃውንት አንድ ሆነው ፀሐይ እንዳትወጣ የሚታገሉበት ቀን ነው።
በዕለተ ዓርብ ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ደም ይለብሳል፣ ከዋክብትም ይረግፋሉ። በዚያ ሰዓት ነገን አሻግሮ ማየት፣ ከእውነትም ጋር አብሮ መቆም ከባድ ነው። ሀገር “ሆ”ብሎ ከሚነጉድበት ስሜት መውጣት፣ የግራ ቀኙን ጩኸት ታግሶ – ዓርብ በሃሳብ፣ እሑድ ግን በተግባር ከሚታየው ትንሣኤ ጋር ለመቆም፣ እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ ያለ ጽኑ ሰብእና ይጠይቃል። ስቀለው ከሚለው የዓርቡ ጩኸት ሣልስት የትንሣኤ ድል እንደሚኖር ማሰብ፣ ደም ከለበሰችው ጨረቃ ወዲያ አማናዊ ብርሃን እንደሚኖር ለማየት ከሚረግፉት እልፍ አእላፍ ከዋክብት ባሻገር ሞትን በሞት በሚገድል አምላክ ክንድ የሚረግፉ ችግሮች መኖራቸውን ለማመን ብርቱ ሰው መሆን ይፈልጋል። ዓርብ ዕለት ከበዛው ጩኸት ይልቅ ከተሰቀለው እውነት ጎን ለመቆም ልብ ያለው ሰው መሆን ይጠይቃል።
ዛሬም ያለንበት ጊዜ ከባድ ፈተና ይህንን እውነታ የሚያስታውስ ነው፡፡ በአንድ በኩል ኮሮና የሚባል ከመቶ አመት በኋላ በዓለም ላይ ሃያል ክንዱን ያሳየ ክፉ ደዌ በዓለማችን የተከሰተበትና ለአገራችም የሞት ጥላውን ያሳረፈበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለዘመናት ከተከማቸው ድህነትና ኋላቀርነት ጋር እንዲህ አይነት በሽታ ተጨምሮ ሊከሰት የሚችል የኢኮኖሚ አደጋ ከፊታችን የተደቀነበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን እንደሚያልፍ ለማሰብ እንደዮሃንስ ያለ የተስፋ ልብ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ አንድም ወደፈጣሪ አብዝቶ መፀለይ፣ በሌላም በኩል ራስንም፣ ሃገርንም ከበሽታው ለመከላከል ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን በትክክል ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ስቅለት እንዳስተማረን ፈጣሪ ራሱን አሳልፎ የሰጠው ለሰው ልጆች ህልውና ሲል ነው፡፡ እኛ ግን ልክ እንደፈጣሪ ህይወታችንን ሳንሰጥ የመንግስትና የፈጣሪ ህጎችን በማክበር ወደነገ መሻገር እችላለን፡፡ በተለይ አሁን በአገራችን የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝና ይህንን ተከትሎ የተከሰተውን የመሶብ መሳሳት ለመሙላት መጣር የግድ ነው፡፡ እኛ እየበላን ሌሎች ተርበው ፈጣሪ በእኩል ሊታደገን አይችልምና መረዳዳትን ዋነኛ መርሃችን ልናደርግ ይገባል፡፡ በትንሹ ቤት አከራዮች ለትንሽ ጊዜ ኪራዩን በመዝለል ወይም በመቀነስ፣ ድሆችን በማብላት፣ ያለንን በማካፈል፣ ወዘተ ዛሬን መሻገር እንችላለን፡፡
ይህንን የምናደርግ ከሆነ ልክ ትንሣኤ እንደመጣው የተስፋ ቀን መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊትም ብዙ ፈተናዎች መጥተው አልፈዋልና፡፡ የመከራ ቀን ለነገው ተስፋ ትልቅ ሃይል ነው፡፡ የጭለማውን ወቅት ተረድቶ የማለፊያ መንገዶችን የተገነዘበ ለትንሳኤው መድረሱ አይቀሬ ነው፡፡ ዛሬን በመረዳዳት፣ የህክምና ባለሙያዎችን ምክር በመስማት ጎንበስ ብለን ከዚህ ጊዜ ማለፍ ከቻልን ነገ ትልቅ ተስፋ ማየት እንችላለን፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2012