የፋሲካ በዓል በሀገራችን ከሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት አንዱና ዋነኛው ነው። በዓሉ ወደሁለት ወር የሚጠጋ የጾም / ከስጋ የመታቀብ ጊዜን ታሳቢ ያደረገ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም ሰፊ ግብይትና ከፍተኛ እርድ ይካሄድበታል።
የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቻችኝ ጾሙን ለመፍታት እንደየአቅማቸው ከዶሮ ጀምሮ አቅሙ ያለው በግ ከዛም በላይ በሬ ገዝቶ ቅርጫ ተካፍሎ በዓሉን በደስታና በፌሽታ ለማሳለፍ ደፋ ቀና የሚልበት ትልቅና ከፍተኛ ዝግጅት የሚፈልግ በዓል ነው።
እናቶች ሰፋ ላለ ግብይት ወደ ገበያ የሚሄዱበት በባህላዊ ግብይት ስርዓታችን መሰረት “እስቲ ያኛውን ዶሮ አምጣ፣ እስቲ ያኛውን ደግሞ “ እያሉ ከመልክ ጀምሮ “ ስጋ አለው የለውም የሚለውን ፤ “ ከዛም አልፈው ዋጋ እየተደራደሩ ዞረው ተዟዙረው በብዙ ድካም ግብይት የሚያደርጉበት የበዓል ገበያ ነው ።
በቀደመው ወቅት ይህ የግብይት ስርዓት በራሱ የበዓሉ አንድ ማድመቂያ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ከገበያ መልስ የሚመጣው የቡና ወግ ለበዓሉ በራሱ ተጨማሪ ውበት የሚሆን ነው።
ይህንን ለረጅም ዘመናት የመጣንበት የበዓል ገበያ ስርአት አሁን ባለንበት ዘመነ ኮሮና አስቀጥሎ ለመሄድ መሞከር ግን የሞትና የህይወት ጉዳይ ያህል አሳሳቢና ቆም ብሎ በአግባቡ ማሰብን የሚጠይቅ ሆኗል ።
በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ በመላው ህዝባችን ላይ የፈጠረው ስጋት፣ በሌላ በኩል ስጋቱን ለመከላከልና በሽታው ሊያስከትል የሚችለውን መጠነ ሰፊ አደጋ በተቀመጡ የጥንቃቄ መርሆዎች አሸንፎ ለመውጣት በገበያ ስፍራ የሚኖረን ቆይታ ተገቢውን ጥንቃቄ የሚሻ ይሆናል ።
እንደቀደመው ዘመን የምንገዛቸውን በግና ዶሮዎች “ እስኪ ይሄኛውን አምጣው ፣ እስቲ ያኛውን ደግሞ” እያልን የገበያውን ዶሮና በግ ስናገላብጥ የምንውልበት ዕድሉ የለም። እያንዳንዱ የገበያ ቦታ እንቅስቃሴያችን ከኮረና ቫይረስ ሥርጭት ስጋት የሚታደገን ሊሆን ይገባል።
በገበያ ስፍራ የሚኖረን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ አለመሆኑን ደግመን፣ ደጋግመን ማሰብ ያስፈልጋል። በግብይት ወቅት ተገቢውን የአካል ርቀትን መጠበቅ፤ አላስፈላጊ ንክኪዎችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የግድ ይላል። ቢቻል አፍና አፍንጫችንን በመሸፈን ከበዓሉ ባሻገር ያለውን የህይወት ተስፋችንን ማስቀጠል ይጠበቅብናል።
እንደ ቀደመው ዘመን የገበያ ወግ፣ በገበያ ስፍራ የምናሳልፋቸው ረጅም ሰዓታት የተሻለ እቃ በተሻለ ዋጋ ለማግኘት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታይበት አይደለም። ከዚህ በተጻራሪ እና በከፋ መልኩ በገበያ ስፍራ ረጅም ሰዓት መቆየት የበለጠ ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርገንን ዕድል የሚያሰፋ ይሆናል።
በገበያ ቦታ የሚደረጉ የትኛውም አይነት ንክኪዎች ለቫይረሱ ተጋላጭነታችን የሚያሰፉ በመሆናቸው ይህንን ችግር በአግባብ ለመከላከል ንክኪዎችን በተሻለ መልኩ መቀነስ ካልሆነም ወደ ገበያ ስፍራ ሲሄዱ ጓንት አድርጎ በመሄድ የተሻለ አማራጭ ይሆናል።
አባወራዎችም ቢሆኑ በበግ ተራ የሚኖራቸው ቆይታ ለበሽታው ያላቸውን ተጋላጭነት ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የሚችል ሊሆን ይገባል። “ እስቲ እሱን ዳልቻውን አምጣው “ ብለው ሻኛውን እያሻሹ፣ ላቱን ያዝ ያዝ እያደረጉ ገንዘብ ቆጥሮ ሰጥቶ “ያዋጣሀል ወይስ አያዋጣህም “ እየተባለ የሚደራደሩበት ጊዜ አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል ።
የከዚህ ቀደሞቹ የበዓል ገበያ ልምምዶቻችን እያንዳንዳችው ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሚያደርጉን ናቸው። አጋላጭነታቸውም ለሻጩም ለገዥውም ጭምር ነው። አብዛኛው በዓል ገበያ ሻጭ ነጋዴ ከገጠር የመጣ መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል።
ከበዓል ገበያው ለማትረፍ ወደ ከተማ የመጣው የገጠር ነጋዴ በግብይት ስርአት ወቅት በሚፈጠር ንክኪ በቫይረሱ ተያዘ ማለት የበሽታው ወረርሽን ወደ ገጠር ገባ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በገጠሩ አካባቢ ካለው የማህበረሰባችን የአኗኗር ስርአት አንጻር እንደ ሀገር ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ከተሜው በዚህ ወቅት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያደርገው ጥንቃቄ ከራሱ አልፎ በገጠር ያለውን ትልቁን ህዝባችንን የመታደግ ያህል ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነው። ስለሆነም ሀገርና ህዝብን ለመታደግ ትልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ በከፍተኛ ኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ።
ከበዓሉ የግብይት ስርአት ጋር በተያያዘ ከፊታችን ያለውን የበሽታውን ተግዳሮት ሰብሮ ለመሻገር ስለራሳችንም ሆን ስለሌላው ወገናችን ደህንነት በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ተጠንቅቀን ልንቀሳቀስ ይገባል። ለዚህም የሚሆን የኃላፊነት ስሜትም ሊኖረን ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2012