አዲስ አበባ፡- በግብርና ምርቶች ላይ እሴት መጨመርና የኮንትሮባንድ ንግድን በጥብቅ መቆጣጠር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣውን የወጪ ንግድ ዳግም እንዲያንሰራራ እንደሚያደርግ ተጠቆመ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት፣ ሀገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው አብዛኛዎቹ የግብርናና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ያለቀላቸው ባለመሆናቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነታቸውና የገበያ ተደራሽነታቸው ውስን ሆኗል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ ምርቶቹ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነት እንዲኖራቸውና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኙ በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመርና በተለያየ መልክ በማምረት ለገበያ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ምርትን ለመጨመርና ለማሻሻል የሚያስችል የኢኮኖሚ መዋቅር መገንባትና የፖሊሲ ለውጥ ማድረግም ይገባል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ አያይዘውም እየተባባሰ የመጣውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቀነስ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ፤ ለዚህም ጠንካራና ስልጡን የፋይናንስ ፖሊስ መደራጀት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ከሌሎች ወሰንተኛ ሀገሮች ጋርም የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስምምነት በመፍጠር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅም ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደገለፁት፣ ለወጪ ንግዱ መዳከም የግብርና ምርቶች ዋጋ በየጊዜው መዋዠቅና በግብርና ምርቶች ላይ ብቻ መንጠልጠል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ሥራዎቹ በቂ ባለመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ የወጪ ንግዱ አንዱ ፈተና መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ይህን ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው የገቢዎች ሚኒስቴር በመሆኑ የቁጥጥር ሥራውን ሊያግዙ ከሚችሉ የመንግሥት አካላት ጋር በተለይም ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር ፣ከፌዴራልና ከክልል ፖሊሶች ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
በአስናቀ ፀጋዬ