1122 መኮንኖችንና ወታደሮችን ያካተተው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቃኘው ሻለቃ ጦር ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥር ተሰማርቶ በኮሪያ ጦርነት ለመሳተፍ ከጂቡቲ ወደብ የተንቀሳቀሰው ከ69 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 8 ቀን 1943 ዓ.ም ነበር።
ከ70 ዓመታት በፊት ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን ወረረች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰኔ 19 ቀን 1942 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ሰሜን ኮሪያ የጠብ ጫሪነት ተግባሯን በአስቸኳይ እንድታቆም አስጠነቀቀ። ሰሜን ኮሪያ ግን ውሳኔውን ቸል በማለት ወረራዋን ቀጠለች። የጸጥታው ምክር ቤትም ለዓለም ሰላም ሲባል ወረራው እንዲቀለበስ ወሰነ። በዚህም መሠረት ውሳኔውን የደገፉ አሥራ ስድስት ሀገሮች ወታደሮቻቸውን ለመላክ ወሰኑ፤ ከነዚህም አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች።
ከአሥር መድፈኛ ሻለቆች ተውጣጥቶ የተመሰረተው ቃኘው ሻለቃ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በእንግሊዛውያን ወታደሮች ስምንት ወራት የፈጀ አንድ ሻለቃ ጦር ስልጠና ሲወስድ ቆየ። በመጨረሻም ሚያዚያ አምስት ቀን 1943 ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ባሉበት የቃኘው ሻለቃ አባላት ችሎታቸውን በመስክ አሳዩ። ንጉሡም “እነሆ በጋራ ደኅንነት መርሕ መሠረት እጅግ ቅዱስ ለሆነው ለዓለም ሰላም ዘብ ልትቆሙ የዓለምን ግማሽ የሚሆን ጉዞ ትጓዛላችሁ። ሂዱና ወራሪዎችን ድል ንሱዋቸው። በኮሪያ ልሳነ ምድርም ሕግና ሥርዓትን አስከብሩ” አሏቸው። ሲሸኟቸውም “ይሄን ሰንደቅ ዓላማ መመሪያ አድርጋችሁ እንድትዘምቱ፣ በተሰማራችሁበት ቦታ ጀግንነት ሠርታችሁ በደረታችሁ ላይ ልዩ ምልክት አድርጋችሁ በኩራት ስትመለሱ በአደራ የሰጠናችሁን አርማ መልሳችሁ እንድታስረክቡን” ብለው ተልዕኮ ሰጧቸው።
1122 የቃኘው ሻለቃ አባላት በባቡር ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ተጓዙ። ከጅቡቲም በመርከብ ፑዛን ወደተሰኘችው የኮሪያ የወደብ ከተማ ቀዘፉ። ደቡብ ኮሪያ ሲደርሱም የአገሪቱ መሪ ፕሬዚዳንት ሲንግ ማን በደስታ ተቀበሏቸው። ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ከአሜሪካ የጦር መሣሪያዎችና ከኮሪያ መልክዐ ምድር ጋር የሚያስተዋውቅ ስድስት ሳምንታት የወሰደ ሥልጠና ወስደው 85 መኮንኖችና 1037 የቃኘው ሻለቃ ወታደሮች በሰባተኛው የአሜሪካ ዲቪዚዮን ሥር ተሰለፉ።
የኢትዮጵያ ሻለቃ በተለያዩ አይነት ዋና ዋና ውጊያዎች ተሳትፏል። በሽምቅና በደፈጣ ውጊያዎች የሚስተካከለው አልነበረም። በአውደ ውጊያ የከባድ መሳሪያ ተኳሽና የሞርታር ዓላሚነትም ተመራጭ ነበር። በግግር በረዶ ሥር ተቀብረው የቆዩ ፈንጂዎች የሚመክኑት በቃኘው ሻለቃ አባላት ነበር። የቃኘው ሻለቃ አባላት ከአፍሪካ የሄዱ ብቸኛ ወታደሮች ነበሩ። በኮሪያ ምድር ከዘመቱ ምድቦች ሁሉ የተሰጣቸውን ሁሉንም ግዳጅ በድል የተወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ብቻ ነበሩ። በቁጥር 238 ግዳጅ ተሰጥቷቸው ሁሉንም በድል ነበር የደመደሙት።
በመጀመሪያው ጉዞ ከሄዱት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች መካከል የሃምሳ አለቃ ደቦጭ በርበሬን በርካቶች ያስታውሱታል። የሃምሳ አለቃ ደቦጭ በማቀዝቀዣ የቆየ ጉማጅ ሥጋ በቦርሳው ይዞ ወደ ውጊያው ሜዳ ገሰገሰ። በወቅቱ ከጠላት ጋር ጦርነቱ ተፋፍሞ ነበር። ለሰዓታት የቆየው ፍልሚያ አይሎ ሲጠናከርም የጨበጣ ውጊያው ቀጠለ። መታገሉ፣ ሳንጃ ለሳንጃ መሞሻለቁና መጣል መውደቁ በረታ። የሃምሳ አለቃ ደቦጭን የገጠመው ወታደር ጉልበቱን ፈትኖ ተገዳደረው። ደቦጭ ታግሎ ጠላቱን በሰደፍ በመጣል ለምርኮ ዳረገው። ወዲያውም በቦርሳው የያዘውን ጥሬ ሥጋ በምርኮኛው ትከሻ ላይ ተቀምጦም ሥጋውን እየቆረጠ ደጋግሞ ጎረሰ። ይህን ያየው ምርኮኛውና ሌሎችም በሆነው ነገር ሁሉ በጣም ተረበሹ። ወታደሮቹ የሰው ሥጋ እንደሚበሉ ተረድተውም በድንጋጤ በረገጉ።
በሁለተኛው ዙር የተጓዘው ቃኘው የጦር ግንባር ጦርነቱ በከፍተኛው የ”ቲቮ” በረዷማ ተራራ ነበር። ሦስተኛው ቃኘው ለገሃር ማክ በሚባል ወታደራዊ መኪና ወደ ጃንሜዳ ተጉዞ ከዚያ በባቡር ወደ ጅቡቲ፤ ከዚያም በአሜሪካ መርከብ ተሳፍረው 22 ቀናት ተጉዘው የኮሪያ ባህር በር ፑዛን ገቡ። ጦሩ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አባላት ነበሩት። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአምስት ዙር 6037 ወታደሮችን አዝምታለች። ሴቶችም ወደ ኮሪያ ዘምተዋል። ከእነዚህ መካከል 122ቱ በጦርነቱ ሞተዋል። 536 ወታደሮች ቆስለዋል። የተማረከ ግን የለም።
በጦርነቱ ማብቂያ ከአሜሪካ ወገን ሆነው ከተዋጉት ሃያ አንድ ሀገራት መካከል ሁሉም በኮሙኒስቶች እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች ሲኖሯቸው አንድም ምርኮኛ ያልተያዘባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። ይህን መሰረት በማድረግ የወቅቱ የጥበብ ሰዎች የኮሪያ ዘማቾችን ሲያወድሱ
አጨደው ከመረው ወቃው እንደ ገብስ፤
የኢትዮጵያ አርበኛ ኮሪያ ድረስ። እያሉ ዘማቾቹን ያወድሷቸው ነበር።
ጦርነቱ አብቅቶ የምርኮ ልውውጥ ሲደረግ ደቡብ ኮሪያ 8343፣ አሜሪካ 4714፣ እንግሊዝ 977፣ ቱርክ 244፣ አውስትራሊያ 26፣ ካናዳ 33፣ ፈረንሳይ 12፣ ግሪክ 3፣ ኮሎምቢያ 28፣ ታይላንድ 5፣ ኔዘርላንድ 3፣ ቤልጅየም 1፣ ፊሊፒንስ 97፣ ደቡብ አፍሪካ 9፣ ኒውዚላንድ 1 ፣ ኖርዌይ 3 ምርኮኛ ሲመለስላቸው ኢትዮጵያ ግን አንድም ሰው ያልተማረከባት ብቸኛ ሀገር ነበረች። የቃኘው ሻለቃ አባላት በጦርነት የተሠውትን አባሎቻቸውን አስከሬን ለጠላት ጥለው አይሮጡም። እሳት እየዘነበባቸው የጓዶቻቸውን ክቡር አስከሬን ተሸክመው ይወጣሉ። አንድ የኢትዮጵያ ወታደር የቆሰለ ኮሪያዊ ወታደርን እንደተሸከመ ተመትቶ ተሠውቷል።
የቃኘው ሻለቃ ጦር አባላት በኮሪያ ምድር በቆዩበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያዎች እንደ ልዩ አይቀመሴ ፍጡር ያዪቸው ነበር። እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን “ኢትዮጵያውያን እልኸኞች ናቸው። መማረክን አይቀበሉም። ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው፤ ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ” ብሏቸዋል።
የኮሪያ ጦርነት በሐምሌ ወር 1945 ዓ.ም ጦርነትን በማቆም ስምምነት ተጠናቀቀ። በቻይናና ሶቪየት ኅብረት በምትረዳው ሰሜን ኮሪያና በአሜሪካና በሌሎች 15 ሀገሮች በተደገፈችው ደቡብ ኮሪያ መካከል ድንበር ተሠመረ። ከድንበሩ ወደ ሰሜንና ደቡብ ሁለት ሁለት ኪሎ ሜትር ገብቶ 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ድንበራቸው ከወታደር ነጻ የሆነ ቀጣና ተመሠረተ። ከጦርነቱ በኋላ የቃኘው ሻለቃ አባላት ለሶስት ዓመታት በኮሪያ ምድር በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር ሰላም እያስከበሩ ቆይተዋል። የኮሪያ ዘማቾች የእረፍት ግዜአቸውን ጃፓን ድረስ እየሄዱ ያሳልፉ ነበር። ከጃፓን ሴቶችም የወለዱ አሉ ይባላል። ጃፓንን ለቅቀው ሲወጡም በፍቅር የተያዙ የጃፓን ሴቶች ያለቅሱ እንደነበር ይነገራል።
የቃኘው ሻለቃ አባላት ለመጨረሻ ጊዜ የኮሪያን ልሳነ ምድር የለቀቁት በመጋቢት ወር 1948 ዓ.ም ነው። በኮሪያ ዋና ከተማ ሴኡል ውስጥ ናምዮንግ ዶንግ ዮንግሳን ጉ በሚገኘው የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግድግዳዎች ላይ በጦርነቱ የወደቁት 121 የኢትዮጵያ ወታደሮች ስም በክብር ሰፍሯል። ወደፊትም የሁለቱ አገራት ወዳጅነት በደም የተጻፈበት ህያው ሰነድ ሆኖ ትውልዶች ሲዘክሩት ይኖራሉ። ቀዳሚዎቻቸው በፈጸሙት አኩሪ ገድል ኢትዮጵያውያን በሴኡል ሰማይ ስር አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት ይራመዳሉ። አበቃሁ!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012
የትናየት ፈሩ