ሚዛናዊነት ማንም ጋዜጠኛ ነኝ ባይ ብዕር ከመጨበጡ በፊት ሊገነዘበው የሚገባ የጋዜጠኝነት ሀሁ…ነው።
ሚዲያዎች ወይም ጋዜጠኞቻቸው በግል ስሜት ወይም በጥቅማቸው ላይ ተመስርተው በዜጎች እና ህጋዊ ሰውነት ባላቸው አካላት ላይ የስም ማጥፋት ወንጀልን እንዳይፈፅሙ ሲባል የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ብሎም የሀገራችን የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ በሚዲያዎች ላይ የሚዛናዊነት ግዴታን ያስቀምጣሉ።
መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር በሚታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ “ፍረዱኝ” በተባለ አምድ ስር “አዳማጭ ያጣ ጩኽት ከአንበሳ አውቶቡስ ግቢ” በሚል ርዕስ ዘላለም ግዛው በተባለ ግለሰብ በተሰራ ዘገባ ውስጥ የድርጅታችን የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ስም የተነሳበት መንገድ የጋዜጠኝነትን መርህ እና የመረጃ ነፃነት አዋጁን ህጎች የተላለፈ፤ በአዋጅ የተሰጠንን የድርጅታችንን ህልውና የካደ፤ የድርጅታችንን፣ የሰራተኞቻችንን እና የደንበኞቻችንን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለንን መልካም ዝና እና ተቀባይነት የሚያጠለሽ ሆኖ በማግኘታችን በድርጅታችን ስም ይህንን መልስ ለመስጠት ተገደናል፡፡
“አዳማጭ ያጣ ጩኽት ከአንበሳ አውቶቡስ ግቢ” የተሰኘው ዘገባ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ሰራተኞች በድርጅታቸው ስለደረሰባቸው በደል ለጋዜጣው አቤቱታ ያቀረቡበት እና የድርጅቱ ስራ አስኪያጅም ምላሽ የሰጡበት ዘገባ ነው፡፡
በዚህ ዘገባ ውስጥ የድርጅታችን የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ስም በክፉ እንዲነሳ የተፈለገበት ምክንያት ባይገባንም ከአንድ ሚዲያ እና ጋዜጠኛ በማይጠበቅ ስነ-ምግባር ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የማን እንደሆነ እንደማይታወቅ፣ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የአንበሳ የከተማ አውቶቡስን ሀብቶች አለአግባብ ስለመያዙ፣ የሸገር ሰራተኞች የተለየ ጥቅማ ጥቅም እንደሚከበርላቸው ወዘተ… ተፅፎ ተመልክተናል።
ድርጅታችን ራሱን መከላከል በማይችልበት እና ምላሽ ባልተጠየቀበት ሁኔታ በትጋት ከምናገለግለው ህብረተሰብ ጋር ቅራኔ ውስጥ የሚያስገባን እና የድርጅታችንን ህልውና እና የሰራተኞቻችንን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥል ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ ተሰርቶ በማየታችን የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት እና ጠቅላላ ሰራተኞች ከፍተኛ ድንጋጤ ተሰምቶናል፡፡
ሸገር የማን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ መልፋትን የሚጠይቅ አልነበረም።እንኳን እና በሀገሪቱ ሁሉ ሪፖርተሮችን አሰማርቶ መረጃ የመሰብሰብ እና የማሰራጨት ተግባርን ዋና ስራው ላደረገ የሚዲያ ተቋም ይቅር እና እያንዳንዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚያውቀው እውነታ ነው።
አራት አመታትን በተጓዘው የሸገር የአገልግሎት ጊዜ በህይወቱ አንድ ቀን ብቻ በሸገር አውቶቡሶች ለመጓዝ እድልን ያገኘ ሰው ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በአዋጅ የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት መሆኑን እንዲያውቅ በሁሉም አውቶቡሶች ላይ ይህንኑ መልዕክት በስቲከር አሰርተን አስቀምጠናል።
በዋናነት በ424 አውቶቡሶቻችን ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በየቀኑ ከምንሰጣቸው መደበኛ እና የተማሪ አውቶቡስ አገልግሎቶች በተጨማሪ በተቋማችን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት ስር ወቅታዊ መረጃዎችን ለደንበኞቻችን ስናደርስ ቆይተናል።
በዚህም በየሩብ ዓመቱ በምናሳትማቸው ዜና መፅሄቶች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ ብሮሸሮች፣ ፕሬስ ሪሊዞች እና በምንጠራቸው ፕሬስ ኮንፈረንሶች ሁሉ በየጊዜው የምናሳትፈው እና ሁሌም ወቅታዊ መረጃዎችን በቅድሚያ በምንልክለት የሚዲያ ተቋም ስር በሚታተም ጋዜጣ “ ሸገር የማን እንደሆነ አይታወቅም” የሚል የሀሰት መረጃ መውጣቱ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡
እውነቱ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የበላይ ጠባቂነት በደንብ ቁጥር 70/2008 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው፡፡
በዘገባው ላይ ስማችን በሀሰት የተነሳበት ሌላው ጉዳይ ሸገር የተሟላ መሰረተ-ልማት እንደሌለው እና የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅትን መሰረተ-ልማቶች በጥገኝነት እንደሚጠቀም መጠቀሱ ነው፡፡
በመሰረቱ መላው የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አመራሮች እና ሰራተኞች ከትንሽ እስከ ትልቅ በመዲናችን ነዋሪዎች ህይወት ውስጥ የ75 ዓመታት የታሪክ አሻራ ላለው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ትልቅ ከበሬታ እንዳለን ለመግለፅ እንወዳለን።
በተረፈው አንበሳም ሆነ ሸገር ሁለቱም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚተዳደሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ናቸው።በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ለብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎቶች ተብለው በሚገነቡ መሰረተ-ልማቶች እኩል የመጠቀም ህጋዊ መብት አላቸው።ይህም በአንበሳም ሆነ በሸገር ስም ከፍተኛ የህዝብ ሀብት ፈሶባቸው የተገዙ አውቶቡሶች የህዝብ ንብረት በመሆናቸው እኩል ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል በሚል የሁለቱም የበላይ አስተዳዳሪ በሆነው የከተማ አስተዳደሩ የተወሰነ ነው።
በመሆኑም ከፍተኛ የህዝብ ሀብት እና ንብረት ፈሶባቸው የተገዙ 424 የሸገር አውቶቡሶች መንግስት ባስገነባቸው መሰረተ ልማቶች አይጠቀሙም ብሎ የመከልከል መብቱ ለአንድ ድርጅት አልተሰጠውም።በዘገባው ላይ እንደተገለፀው ሸገር የመጠቀም መብቱ ሳይኖረው በግድ ወይም በጥገኝነት የገባ ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ በአሉባልታ እና ስም በማጥፋት ሳይሆን በህግ አግባብ መፍታት ይቻል ነበር።
ሆኖም የዘገባው ዋና ዓላማ እውነትን ለህዝብ ማሳወቅ ሳይሆን ሸገር በአጭር ጊዜ በደንበኞቹ ዘንድ ያገኘውን ተቀባይነት ለማሳጣት በመሆኑ የድርጅታችን፣ መሰረተ-ልማቱን ያስገነቡት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ትራንስፖርት ባለስልጣን እና የከተማ አስተዳደሩ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት ምላሽ ሳይካተት ዘገባው ታትሞ እንዲወጣ ተደርጓል።
በእኛ በኩል ህዝባችን እንዲያውቅልን የምንፈልገው የከተማ አስተዳደሩ በህዝብ ሀብት ያስገነባቸውን መሰረተ-ልማቶች የምንጠቀመው በዘገባው ላይ እንደተገለፀው በግድ ወይም በጥገኝነት ሳይሆን የህዝብ ሀብት የሆኑ አውቶቡሶቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ በከተማ አስተዳደሩ በተሰጠን መብት እንደሆነ እንዲታወቅልን ነው፡፡
ሶስተኛው እና አስገራሚው የስም ማጥፋት አካል የሆነው አሉባልታ”ሸገሮች የሚፈሩ እና ትላልቅ ፈርኦኖች በመሆናቸው በአመት ሁለት ጫማ ይሰጣቸዋል”የሚለው ዘገባ ነው።በመሰረቱ ሸገር ለሰራተኞቹ በአመት ሁለቴ የደህንነት መጠበቂያ ጫማ
እና የደንብ ልብስ የሚሰጠው የሰራተኞቻችንን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ስላለብን እና ሰራተኞችም መብታቸው ስለሆነ እንጂ የሌሎች ድርጅቶችን ሰራተኞች ለማስቀናት አይደለም።
እውነት ነው።ለጋራዥ ሰራተኞቻችን፣ ለሹፌሮቻችን፣ ለትኬተሮቻችን፣ ለፅዳት ሰራተኞች እና ለሌሎችም ለሚገባቸው ሰራተኞቻችን በአመት የሚገባቸውን የደንብ ልብስ፣ የደህንነት መጠበቂያ፣ የንፅህና መጠበቂያ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳናጓድል እንሰጣለን።ምክንያቱም ስለሚገባቸው።የሰራተኞችን መብቶች ማክበራችን ሊያስወድሰን ሲገባ ግዴታቸውን ባልተወጡ አካላት የቅንጦት ተግባር እንደምናከናውን ታስቦ ስማችን በክፉ መነሳቱ፣ ሚዲያውም ይህቺን ትንሽ ጉዳይ ማመዛዘን አቅቶት እንደ ቅሬታ በጋዜጣ አትሞ ማውጣቱ በእጅጉ አሳዝኖል፡፡
ሌላው የአንበሳ ሰራተኞች አነሱት ተብሎ የተዘገበው ቅሬታ”በሸገር እና በአንበሳ መካከል ያለውን ልዩነት አናውቀውም” የሚል ነው።የድርጅታችን ዋነኛ ተግባር ከሁሉም የግል እና የመንግስት የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቋቋመበትን ዓላማ በቅንነት እና በታታሪነት መወጣት እንጂ ከሌሎች ድርጅቶች ስለሚለዩን ጉዳዮች በማስተማር ጊዜ ማጥፋት ባይሆንም ድርጅታችንን ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋቸውን ዋነኛ አገልግሎቶቻችንን እንደሚከተለው እናስቀምጣለን።
ሸገር በ2008 ዓ.ም በደንብ ቁጥር 70/2008 ዓ.ም ሲቋቋም በአዋጅ የተሰጡት ሶስት ዋና ዋና ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው።
- ለከተማዋ ሕዝብ ቀልጣፋና ተደራሽ የፈጣንና የመደበኛ የከተማ አውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት፣
- ለተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ወይም ሰርቪስ መስጠት፣
- ከሌሎች የህዝብ አገልግሎት ሰጪዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በሚጣጣም ሁኔታ የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ናቸው።
በመሆኑም ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በከተማችን ብቸኛው የተማሪዎችን አውቶቡስ አገልግሎት እና ፈጣን የከተማ አውቶቡስ BRT አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።ድርጅታችን ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሌሎች የከተማ አውቶቡስ ድርጅቶች ሁሉ መደበኛ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ሸገር ከተቋቋመበት ግንቦት 19/2008 ዓ.ም ጀምሮ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ፈጣን፣ ምቹ እና ዘመናዊ የብዙሃን ትራንስፖርቶችን በማቅረብ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በመደበኛ አገልግሎት በ49 መስመሮች በቀን ለ195 ሺህ ደንበኞቹ እና በ79 የተማሪ አውቶቡስ መስመሮች በቀን ለ4ሺህ ተማሪዎች አገልግሎትን በመስጠት ላይ የሚገኝ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው፡፡
የአዘጋጁ መልዕክት
የስም ማጥፋት ብቸኛው መከላከያ እውነት ብቻ ነው።የሀሰት ዘገባ ቢሆን ኖሮ ስም ማጥፋት ይባል ነበር።በአምዱ የተስተናገደው ጉዳይ የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች የሰጡትን መረጃ መሰረት በማድረግ የተሰራ ነው። እናንተ እንዳላችሁት በአዋጅ የተሰጣችሁን የድርጅታችሁን ህልውና ለመካድ፤ የድርጅታችሁን፣ የሰራተኞቻችሁን እና የደንበኞቻችሁን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል፤ እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ያላችሁን መልካም ዝና እና ተቀባይነት ለማጠልሸት የተቀነባበረ ልብ ወለድ ወይም የፈጠራ ዘገባ አይደለም።
የአምዱ ዋና ዓላማ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለሌሎች ተቋማትም መማሪያ እንዲሆን እና ችግርን ለማስተካከል የቀረበ ነው።እንጂ የተቋማትንና የግለሰቦችን ስም ማጥፋት፣ ተቀባይነትንም ማሳጣት ዓላማው ያደረገ ገጽ አይደለም።በጥቅሉ ኢ ፍትሃዊ አሰራርን ለማረም እንጂ ስም ለማጥፋት የቀረበ ዘገባ አለመሆኑን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።
በርግጥ ምላሽ እንድትጽፉ ያነሳሳችሁን ምክንያት ስንመለከት ስራው በተገቢው መንገድ መሰራቱን መስክሮልናል።ሰራተኛን ማፈን ሳይሆን እንዲናገር መፍቀድ፣ ችግሩን ማዳመጥ፣ ትክክል ያልሆነውን ማረም የተሳሳተውን ተሳስተሃል ብሎ ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።ካኮረፈ አገልጋይ ይልቅ መብቱ የተከበረለት ሰራተኛ መልካም አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ከእናንተ ተቋምም እንዲማሩ የተነጻጸሩ ጉዳዮች አሉ።የአንበሳ ሰራተኞች መብታቸውን እና አቅጣጫን በጠየቁበት ዘገባ ስም ማጥፋት ብላችሁ ጋዜጠኛው ላይ ጣት መጠቆማችሁ ተገቢ እንዳልሆነ ልንገልጽ እንወዳለን።በጽሁፉ የተንጸባረቀው ሃሳብ አዘጋጁ ያንጸባረቀው ሃሳብ ሳይሆን ሰራተኞቹ ችግራቸውን የገለጹበት ነው።ይህ በመረጃ ተይዟል።ጋዜጠኛውን ለማሸማቀቅ የተጠቀማችኋቸው አንዳንድ ቃላቶች በርካታ ሰራተኞችን በሆደ ሰፊነት አስተዳድራለሁ ከሚልና ሃላፊነት ከተሸከመ አካል የሚጠበቅ አይደለም።
“ሸገር የማን እንደሆነ አይታወቅም” የሚል የሀሰት መረጃ መውጣቱ በእጅጉ እንዳሳዘናችሁ በምላሻችሁ ጠቅሳችኋል።ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ገበየሁ ዋቄ በምላሻቸው ‹‹ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት እና የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ሁለቱም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ናቸው›› በማለት ማብራሪያ መስጠታቸውን በግልጽ ማስፈራችንን ጽሁፉን በጥሞና ብታነቡት ታገኙት ነበር።
የለውጥ አመራሩ ወደኃላፊነት ከመምጣቱ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ የነበሩ ችግሮች ምን እንደነበሩ በእዚህ ጽሁፍ ማንሳት ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆናል።ሪፎርም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ችግሮችን ለማስተካከልና ለማረም ነው።ፍትሃዊነት የተጓደለበትን አሰራር ለማስተካከል እና ሕዝባዊ አገልግሎትን እርካታ ለማሳደግ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል።በእኛም ዘገባ በአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ቀድሞ ሲንከባለል የነበረ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበረ ለማመልከት ሞክረናል።
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ገበየሁ በነገሩን መሰረት፤ የተቋሙን ችግሮች የመለየት ሥራ መሰራቱን የሥራ ማነቆዎች ተብለው የተለዩ እንደ የሠራተኞች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ፤ የደንብልብስ፣ በአውቶቡሶች የትኬት ቆራጭ ቦታ አለመኖር፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የመጠባበቂያ ገንዘብ ጥያቄዎች መኖሩንም አስነብበናል።
ሠራተኛው ከለውጡ በፊት እድገት፣ ማበረታቻ፣ ማነቃቂያና መሰል የማትጊያ ስርዓቶች ሳይዘረጉለት መቆየቱን ዘገባው አመላክቷል።ይልቅ ሰራተኞች እንዲሰጉና እንዲሸማቀቁ ይደረግ እንደነበርም አስገንዝቦናል።ጥያቄን ከመመለስ ይልቅ የመገሰጽ፣ የማፈን፣ የማስፈራራትና አልፎ ተርፎም ርምጃ የመውሰድ ዝንባሌዎች እንደነበሩ መጠቆማቸውን እናስታውሳችሁ።
በጊዜው የደንብ ልብስ ግዢ አለመፈጸም፣ ቢገዛም ጥራት የጎደለው አሰራር ነግሶ እንደነበር፣ በተወሰነ መልኩም ቡድንተኝነት የሚንጸባረቅበት ሁኔታ እንደነበረም ማመናቸውን በአቤቱታቸው ተነስቶ እንደነበር እናስታውሳለን።ሂደቱ በተለመደው መንገድ መቀጠል የለበትም በሚል ማስተካከያ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ጠቁመውናል።ሂደቱ እንዲቀጥል ሊፈቀድም አይገባውም።በአንበሳ ጊቢ ያለው ችግርም ታርሞ ለማየት እንናፍቃለን።ተቋሙ መልካም አገልግሎት አሰጣጡን እንደሚያስቀጥል፤ ሰራተኞቹም ደስ እያላቸው እዲያገለግሉ መደረግ እንደሚገባውም እናምናለን።በለውጥ አመራሩ ተስተካክሎ እንደምናየውም ተስፋ ጥለናል።
የሁለቱም ተቋማት የበላይ ሃላፊ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሆኑን ጠቁማችኋል።በሚገነቡ መሰረተ-ልማቶች እኩል የመጠቀም ህጋዊ መብት እንዳላችሁም አመልክታችኋል።እንደ እውነቱ ከሆነ የስም ስያሜ እንጂ በአንድ ግቢ፣ በአንድ ነዳጅ ማደያ፣ በአንድ ጋራዥ እየተጠቀማችሁ እና በአንድ አስተዳደር ስር እያላችሁ የደመወዝም ሆነ የጥቅማ ጥቅም ልዩነት ሊደረግ አይገባም ነበር።በአንድ አመራር ስር ከሆናችሁ በጥቅማ ጥቅም መለያየታችሁ ተገቢ አለመሆኑን ነው የታዘብነው።ለሸገሮች የተፈቀደው ጥቅም ለአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ሰራተኞች መከልከል አይገባም።ልዩነቱ የስም እንጂ ሁለቱም ተቋማት በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሆኑ አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ መሆን የለባቸውም።
በርግጥ መላው የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አመራሮች እና ሰራተኞች ከትንሽ እስከ ትልቅ በመዲናው ነዋሪዎች ህይወት ውስጥ የ75 ዓመታት የታሪክ አሻራ ላለው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ትልቅ ከበሬታ እንዳላችሁ ገልጻችኋል።ይህ ይበል ያሰኛል።ምክንያቱም ስለሚገባቸው ነው።
ግን በሁለቱ ተቋማት ሠራተኞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች እንዳሉ፣ ግጭቶቹ መነሻቸው ያለመግባባት መሆኑን፣ ተቋማቱ ለተቋቋሙላቸው ዓላማ ሊሰሩ ሲገባቸው ሀብት የመቀማማት፣ በሀብት አጠቃቀም የመጋጨት፣ መስመር ላይ አለመግባባት መኖሩን አስነብበናል።ይህም የጋዜጠኛው የፈጠራ ወሬ ሳይሆን በመረጃ የተደገፈ ነው። በተለይም ሹፌሮች እርስ በእርሳቸው፣ የስምሪት ሠራተኞችና ትኬተሮች ከመሰል የሙያ አጋሮቻቸው ጋር የመጋጨት ሁኔታ መኖሩን ለመገንዘብ ችለናል። ይልቅ የጋራ ችግሩን ማስተካከል ትልቅ የቤት ስራችሁ ሊሆን ይገባል።
‹‹ሸገር ድርጅት የተሟላ ነገር የለውም። የራሱ ዴፖና የነዳጅ ማደያም የለውም። ጥገና የሚያደርግበት ጋራዥም አላሟላም። በመሆኑም የአንበሳን ሀብት እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ተቀምጧል። ይህን ተከትሎም አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል››።ያልነው በመረጃ እንጂ በፈጠራ ወሬ አይደለም።ሰራተኞች የነገሩንን ስራ አስኪያጁም አረጋግጠውልናል።
ሶስተኛው እና አስገራሚው የስም ማጥፋት አካል ሆኖ እንዳገኛችሁት የገለጻችሁት “ሸገሮች የሚፈሩ እና ትላልቅ ፈርኦኖች በመሆናቸው በአመት ሁለት ጫማ ይሰጣቸዋል” የሚለው ዘገባ መሆኑን ገልጻችኋል።በእዚህ ረገድ የሚፈሩ ፈርኦኖች ተብሎ በአንበሳ ሰራተኞች የተጠቆመው የራሳቸውን የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አንዳንድ አመራሮች እንጂ የሸገሮችን እንዳልሆነ ለመጠቆም እንወዳለን።በእዛ መልኩ ይታረም።
በጥቅሉ በተስተናገደው ዘገባ የተገለጹት መረጃዎች ከሰራተኞች፣ ከሰራተኛ ማህበሩና ከአመራር የተገኘ መረጃ ነው።የጋዜጠኛው አስተያየት አይደለም።እንዲህ አይነት ዘገባ የየተቋማትን አድሎአዊ አሰራር ለማረም ይጠቅማል።የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተድበስብሰው እንዳይሄዱ ለማስተካከልም ያግዛል።ሪፎርሙ ሊሳካ የሚችለው አገልጋዮችን ባግባቡ መያዝ ሲቻል ነው።ሰራተኞች እያኮረፉ የሚሰጡት አገልግሎት ስኬታማ ሊሆን አይችልም።
የአምዱ ዋነኛ ዓላማ የማይደፈሩ ጉዳዮችን መዳሰስ እውነታውን ለህዝብ ማድረስ ነው።የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተድበስብሰው በማለፍ ቆይተው ግዙፍ ችግር እንዲወልዱ መፈቀድ የለበትም።ተጋልጠው እንዲታረሙ ማድረግ ይገባል።
በእርግጥ ጋዜጠኛ ህገ ወጥ ስራ እንዲሰራም አይፈቀድም። በአንጻሩም በስጋት ተሸብቦና በሙያ ተሸማቅቆ እንዲዘግብም መደረግ የለበትም። የተደበቀን ነገር ፈልፍሎና አነፍንፎ ችግርን ማሳየት አለበት። በዘገባው ያደረግነውም ያንኑ ነው። ጋዜጠኛና ወታደር አንድ ናቸው። ወታደር በጦርነት ሜዳ ለታጠቀለት ዓላማ ሕይወቱን እስከመስዋት መዋጋት ነው። ጋዜጠኛው ደግሞ መንግስትን ማገዝ ነው። በህዝብና በመንግስት መካከል ድልድይ መሆን፣ በብዕራችን ኢ ፍትሃዊነትን ማጋለጥ ነው።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የረጅም አመታት ታሪኩ እናንተ በጻፋችሁት መንገድ የተቃኘ አይደለም።ጋዜጠኞች በግብታዊነት የሚሰሩት ሥራም አይደለም።በተጣራ መረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ኃላፊነት ተሰምቷቸው የሚሰሩና ብቃት ባላቸው የሙያው ባለቤቶች ተረጋግጦ የሚዘገብ ነው።
አበቃሁ! አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012