የሰው ልጂ በየዘመኑ ሕልውናውን የሚፈታተኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። አንዳንዶቹ እራሱ የፈጠራቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በድንገት ተከስተው ከቁጥጥር ውጭ በመሆን የሰውን ልጅን የከፋ ዋጋ ያስከፈሉ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በዘመናችን የተከሰተውና ዓለምን በከፋ ጭንቀትና ግራ መጋባት ውስጥ የከተተው የኮሮና ቫይረስ አንዱ ነው። ይህ እስካሁን መድሃኒትም ሆነ ክትባት ያልተገኘለት በሽታ በመላው ዓለም በሚባል መልኩ የሁሉንም አገር በር አንኳኩቷል።
በሽታው የጤና ሥጋት ከመሆን ባልተናነሰ መልኩ እያስከተለ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከዚህ በፊት ካጋጠሙ ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ቀውሶች የከፋ እንደሆነ በስፋት እየተነገረለት ይገኛል።
ይህ በሽታ በሀገራችን ከተከሰተ ጀምሮ ሥርጭቱ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ዛሬ ላይ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ 82 አሻቅቧል። ችግሩ የቁጥር ማሻቀቡ ብቻ ሳይሆን በሽታው ወደ ሕብረተሰቡ ዘልቆ በመግባቱ የውጭ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች ላይ ጭምር መከሰቱ ነው።
በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ለመተላለፍ ሰፊ ዕድል ያለው በመሆኑ ችግሩን በመከላከል ማስቆም ካልተቻለ ሊያመጣ የሚችለው አደጋ የከፋና አሰቃቂ ሊሆን መቻሉ ነው።
በተለይም እንደእኛ ባሉ አብዛኛው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው ሰፊ ማህበራዊ መስተጋብር ባላቸው ህዝቦች ውስጥ ያለው የአኗኗር ዘይቤ በራሱ ለቫይረሱ መስፋፋት ትልቅ አቅም መሆኑ ነው።
የበለጠ የሚከፋው ደግሞ እነዚህ ህዝቦች ስለበሽታው ያላቸው ግንዛቤ ዳብሮ በመከላከሉ ሥራ ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት ካልቻሉ ሁኔታዎች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በመሆን በሽታው አስከፊ አደጋ እንዲያስከትል አስቻይ ሁኔታ መሆናቸው ነው ።
ይህ እውነታ በኛ ሀገር በግልጽ የሚስተዋል እና እጅግ አሳሳቢ ደረጃ የደረሰ መሆኑ ነው። ስለበሽታው አደገኝነት ዕለት ከዕለት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየተነገረ፤ በተጨባጭም በሽታው ዕለት ከዕለት አድማሱን እያሰፋ ወደ እያንዳንዱ ጓዳ እየፈጠነ ባለበት ሁኔታ የማህበረሰቡ መዘናጋት ለአዕምሮ የሚከብድ ሆኗል።
ዛሬም በበሽታው ሥርጭት ወገኖቻችንን አጥተን እስከ ትናንትናው ዕለት ድረስ 82 ዜጎቻችን በበሽታው መጠቃታቸውን እየሰማን በሽታው ወደ ወረርሽኝ ከመሸጋገሩና ያልተጠበቀ ዋጋ ከመክፈላችን በፊት ተገቢ የሆኑትን ብዙም ሊከብዱን የማይችሉትን ትዕዛዛት እንኳ ለመፈፀም ዳተኞች ሆነናል።
እጅን ደጋግሞ በሳሙና መታጠብ፣ የአካል ርቀትን መጠበቅና በቤት ወስጥ መታቀብ የሚሉትን ትዕዛዛት በመፈፀም ነፍሳችንን መታደግ ተስኖናል። ከዚህ ይልቅ እጃችንን የምንታጠበው ለራሳችንና ለምንወደው ቤተሰባችን ደህንነት መሆኑን መረዳት አቅቶን ተዘናግተን ለራሳችንና ለቤተሰባችን የከፋ አደጋ እየጠራን እንገኛለን።
የአካል ርቀታችን ከመጠበቅ ይልቅ በየጎዳናው ከመተቃቀፍ ባልተናነሰ መልኩ ተሰብስበን በሽታው እንደ ህዝብ ሊያስከትልብን የሚችለውን ለማሰብ የሚከብድ አደጋ በራሳችን መዘናጋት ወደየ ቤታችን እየጋበዝን ነው።
መንግሥት ቢሮ ዘግቶ በቤታችሁ ታቀቡ ያላቸው ሳይቀሩ ከቢሮ የቀሩበትን ትልቁን ጉዳይ እረስተው በየመንደሩ ተሰባስበው ቫይረሱ ሊያስከትል ስለሚችለውና እያስከተለ ስላለው አደጋ እየደሰኮሩ አንዳቸው ለሌላኛቸው የአደጋ ምንጭ እየሆኑ ነው።
ከብዙ ህልምና ተስፋ የሚቆርጥ ዳግም ላንመለስ ከህይወት ከሚለየን ሞት እጅ በመታጠብ፣ የአካል ርቀትን በመጠበቅና በቤት ውስጥ በመታቀብ ለማሸነፍ ተነሳሽነትና ታዛዥነት የምናጣ ከሆነ ችግሩ ከዚህ የበለጠ የሚጠይቀን ቢሆን ምን እንሆን ነበር።
እጅ ከመታጠብ፣ የአካል ርቀት ከመጠበቅና ከቤት ውስጥ ከመታቀብ የበለጠ የህይወት አላማ የለንምን ?፤ እነዚህን ትዕዛዛት ከመፈፀም ባሻግር ያለምነው የህይወት ተስፋ የለንምን ?
እነዚህን ትዕዛዛት በመፈፀም ከሞት የምንታደጋቸው አባት፣ እናት፣ ወንድም እህትና ልጅ የለንምን። ለአዕምሮ የሚከብድ ሰብአዊ እልቂትን ለማስቆም ከዚህ የቀለለ ትዕዛዝ ሊኖር ይችላል?
ወደ ቀልባችን እንመለስ፤ ወደ ማስተዋላችን እንምጣ። ለሁሉም ጊዜው አልረፈደም፤ እንንቃ፤ ከተያዝንበት አደጋን ያለማስተዋል መፍዘዝ እንውጣ። ስለራሳችን እና ስለሌላው ወገናችን ደህንነት በአግባቡ እናስብ፡፡ ሁሉም ነገር የፈሰሰ ውሃ እንደማይታፈስ ከመሆኑ በፊት!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012