በኑሯቸው ሁሉ ሰዎችን መርዳትና ችግረኞች ሲደሰቱ ማየት ያስደስታቸዋል። በራሳችው ጥረት የተማሩም ቢሆኑ ዝቅተኛ ከሚባለው የመልዕክት ሰራተኛነት ተነስተው፣ የሰው ፊት ገርፏቸው፣ ችግር ፈትኗቸው ነው ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የደረሱት። ችግር ጥረትን ያመጣል፤ ጥረት ደግሞ ውጤታማ ያደርጋል የሚለውም የጥንካሬያቸው መለያ ነውና አስቡት ባለሀብት የሚለው ደረጃ ላይ ደርሰዋል የቤካስ ኬሚካልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በቀለ ጸጋዬ።
ዛሬ ደግሞ ሀገርና ህዝብ የድረሱልኝ ጥሪ እያቀረቡ ባሉበት ወቅት እኔም ለወገን ደራሽ ነኝ ብለው ለኮሮና ቫይረስ መከላከል አጋዥ የሆነውን የንጽህና መጠበቂያ በማምረት ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ኬሚካል ማኑፋክቸር ማህበር ፕሬዚዳንት፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የቦርድ አባል ናቸው። የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን አቶ በቀለ ጸጋዬ። እናም ከእርሳቸው የህይወት ውጣውረድ ትማሩ ዘንድ ልምዳቸውን ልናጋራችሁ ወደናል።
በጎ ምግባር
ብዙ አትሌቶቻችን ከፈለቁባት አርሲ ዞን ሌሙ እና ቢልቢሎ ወረዳ በቆጂ ከተማ ውስጥ በ1946 ዓ.ም ህዳር 19 የተወለዱት አቶ በቀለ፤ ለቤተሰባቸው የበኩር ልጅ ናቸው። ቤተሰቦቻቸውን በእርሻ ሥራ በሚገባ አግዘዋል። ከብትም ይጠብቁ ነበር። በቤት ውስጥም የታዘዙትን የሚፈጽሙ ታዛዥ ሰው ናቸው። እንዳውም በቤታቸው የሚያስፈልገውን ቀድመው በመረዳት አስፈላጊውን ስራ ሁሉ ይከውናሉ።
አድርግ መባል የእርሳቸው መገለጫ አይደለም። በዚህም ስራ ወዳድነታቸው እናታቸው ብዙ ጊዜ ይደነቁባቸው እንደነበር ያነሳሉ። በጎነትን የተማሩት ገና በልጅነታቸው ከአባታቸው መሆኑን ይናገራሉ ። አባታቸው ለአካባቢው ሰው ሁሉ አለኝታ ናቸው። ለራሳቸው ሳይበሉ ያድራሉ እንጂ ጎረቤት ተቸግሮ አይተው አያልፉም። እሳቸውም የአባታቸው መልካምነት ተጋብቶባቸው ኖሮ ጎረቤቱን በቻሉት ሁሉ ይደግፋሉ።
ለጎረቤት እንቢ የሚሉት ነገርም የላቸውም። በዚህም ሁሉም ሰው እንደመረቃቸው ነበር ልጅነታቸውን ያሳለፉት። አቶ በቀለ ጭምት ከሚባሉት ልጆች ተርታ የሚመደቡ ናቸው፤ በጨዋታ ብዙም ጊዜያቸውን አላሳለፉም። ከጨዋታ ይልቅ መጽሐፍትን ማንበብ ይመርጣሉ። ጨዋታ ላይ ከታደሙ ደግሞ ምርጫቸው እግርኳስ ነው። ከጨዋታ ይልቅ ለንባብ ብዙ ጊዜያቸውን መስጠታቸው አንዳንድ ምርምሮችን ለመሞካከር እድል ከፍቶላቸዋል። መመራመር ስለሚወዱ ሳይንቲስት የመሆን ህልም እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን የጓሮ አትክልትና የዛፍ ችግኝ እያፈሉ መትከልም እንደሚወዱ አጫውተውናል።
ከበቆጂ እስከ አዲስ አበባ
ትምህርት ቤት ለመግባታቸው መሰረቱ ያልተማሩትና ፊደል ያልቆጠሩት አባታቸው ናቸው። መማርን በልጆቼ እወጠዋለሁ ሲሉም ከትውልድ ቦታቸው 30 ኪሎሜትር በምትርቀው አሰላ ከተማ ወሰዷቸው። በተለይም ብቸኛ ልጃቸው በመሆናቸው እንዲማሩ ብለው በዘመድ ቤት እንዲቆዩ ማድረጋቸው አባታቸውና እናታቸው እንዲጋጩ ምክንያት መሆኑን ያስታውሳሉ። ሆኖም አባት ግን መማር ለለውጥ ጉልበት መሆኑን ያውቃሉና እያስገደዷቸው ጭምር እንዲማሩ አድርገዋቸዋል። እርሳቸው ግን ይህንን ግዳጅ በፍጹም አይወዱትም ነበር። እንዳውም ከቤተሰቤ የሚለየኝ ትምህርት ጥንቅር ብሎ ይቅር ብለው ያስቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዘመናዊ ትምህርትን በበቆጂ መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጀመሩት እንግዳችን፤ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል። ሆኖም የቤተሰብ ናፍቆት አየለባቸውና የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ‹‹መማር ለምኔ ››በማለት ትምህርቱን ትተው ወደ ቤተሰብ ሄደው ነበር። በእርግጥ ናፍቆት ብቻ ሳይሆን ያሉበት የዘመድ ቤት እንደቤተሰባቸው በነጻነት ቦርቀው የሚኖሩበት አልሆነላቸውም። በዚያ ላይ ብዙ ችግሮችን ያሳልፉ ነበር። ስለዚህም ለቤተሰቡ ቢናገሩ የሚሰማቸው አልነበረምና በራሳቸው ፈቃድ ትምህርቱን አቋርጠው ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመለሱ። ይህ በመሆኑ ደግሞ ግማሽ መንፈቅ ዓመት ሳይማሩ ቀሩ።
ነገር ግን ወደሚቀጥለው ክፍል ተዛውረው መማር ችለዋል። ለዚህ ደግሞ የአባታቸው ሚና የላቀ እንደነበር አይረሱትም። ከትምህርት ውጪ አማራጭ እንደሌለ የሚያምኑት አባት ዳግም መማር አለብህ በማለት ወደዚያው ቦታ መልሰዋቸዋል። ከአንድ እስከ 12ኛ ክፍል ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፉት አቶ በቀለ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን የሳይንስ ትምህርት መርጠው ተምረዋል። በእርግጥ ስለ ሳይንስ ትምህርት ሲያነሱ የኬሚስትሪ ትምህርት የመማር ማስተማር ሥራው አይረሳቸውም።
ገሚሱ ፊዚክስና ባዮሎጂ ተምሮ ኬሚስትሪ ሳይማር በረብሻ ምክንያት ትምህርት ይቋረጣል። አንዳንዱ ደግሞ ኬሚስትሪና ሌላ የሳይንስ ትምህርት ተምሮ እንዲሁ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሁለቱ ተማሪዎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር አድርጎ ነበር። ‹‹እኔ ቀደም ባሉት ክፍሎች ኬሚስትሪን በደንብ ካልተማሩት መካከል ነበርኩ›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ ኬሚስትሪን በሚገባ መማር የጀመሩት 11 እና 12ኛ ክፍል ነበር።
ከዚያ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሌሎች ኬሚስትሪን ሳያቋርጡ በመማራቸው ሲበልጧቸው ይበሳጩ እንደነበር ያስታውሳሉ። 11ኛ ክፍል ላይ ከሁሉም ትምህርት የከበዳቸው እርሱ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በማጥናት ከትምህርት ቤቱ የተሻለ ውጤት አምጠተው ተሸልመዋል። ይህ ደግሞ የቀጣይ ጉዟቸውን የተቃና አድርጎላቸው በኬሚስትሪ ትምህርት ተመርቀው ህይወታቸውን በኬሚስትነት እንዲመሩ አስችሏቸዋል። አቶ በቀለ የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግቢያ ውጤት በማምጣታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲሳይንስ ፋካሊቲን ተቀላቅለዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኬሚስትሪ አጠናቀዋል። ከዚያ በኋላ ግን ትምህርታቸውን አልቀጠሉም። ለዚህም ዋናው ምክንያት የተመረቁበት ነጥብ አነስተኛ በመሆኑ ነው። በወቅቱ ሁለተኛ ዲግሪ ለመቀጠል የሚጠየቀው የመመረቂያ ነጥብ( ጂፒኤ ) ከ 2 ነጥብ 5 በላይ ሲሆን የእርሳቸው ነጥብ ደግሞ ከሚጠየቀው በታች ነው። በትምህርት ወደ ከፍታ መውጣት ባይችሉ በስራ ግን ይሄንን የሚነፍጋቸው የለምና በተማሩበት ሙያ ማፍራት እንደሚችሉ አምነው ወደ ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ ። በስራ ላይ ቆይታቸው በትምህርት ያገኙትን እውቀት በማዳበር ሙያቸውን እንዳጎለበቱ አጫውተውናል።
ሳሙና አምራቹ
የሥራ ሀሁ የተጀመረው በረጲ ሳሙና ፋብሪካ ኬሚስት ሆነው ነበር የተቀጠሩት። እዚያው ሆነው የምርት ጥራት ቁጥጥር ተጠባባቂ ሀላፊ፣ ከዚያ ዋና ሀላፊ ፣ የምርትና ቴክኒክ ሥራ አስኪያጅ በመሆንም ለአስር አመት ከስድስት ወር ሰሩ። ከዚያ ቀጥለው በረጲ ሳሙና ፋብሪካ ደመወዝ በኬሚካል ኮርፖሬሽን በተመራማሪነት ተዛውረው በርካታ የምርምር ውጤቶችን በመስራት ግልጋሎት ላይ እንዲውሉ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ። በሳሙና ዙሪያ የጠለቀ አቅምና እውቀት ስላላቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በመሆን እንዶድን ለሳሙናነት ማዋል ከሰሩት አንዱ መሆኑን ነግረውናል። የተለያዩ ፈሳሽ ሳሙናዎችን በተማሩትና ባነበቡት መነሻነት ሰርተው ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል። ከሁለት ዓመት የተመራማሪነት ቆይታ በኋላ ወደነበሩበት ረጲ ሳሙና ፋብሪካ ሲመለሱ እጅጉን ተበሳጭተው እንደነበር የሚያነሱት እንግዳችን፤ በምርምር ሥራቸው ብዙዎች ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሻለ ቦታ በዚያው እንደሚሰጣቸው አምነው ነበር።
ነገር ግን በዚያው ክፍያ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ተደረጉ። ይህ ደግሞ የመስራት ወኔያቸውን አዳከመው። እንደውም ከዚያ መውጣትን ያሳሰባቸውም ሥራውን ደስተኛ ሆነው መቀጠል አለመቻላቸው እንደነበር አጫውተውናል። የቅርብ ሰው ያሏቸው አቶ ግዛቸው ሽፈራው የህይወት መስመራቸውን እንደቀየሱላቸውና በግላቸው መስራት እንደሚችሉ እንዳበረቷቸው ያጫወቱን አቶ በቀለ፤ የግል ስራ መስራት አገር መካድ ነው ተብሎ ይታመናል። እናም እንዴት ይሆናል ሲሉም መጨቃጨቁን ከወደድከው ቀጥል አሏቸው። በዚህም አስበውበት የስራ ፕሮፖዛል ጽፈው እንዲሰጧቸው ሆነ። ሥራውም ወደ ትግበራ ገባ።
አቶ በቀለ ታናናሽ እህትና ወንድሞቻቸውን ያስተምሩ ስለነበር በድንገት ስራቸውን ለመተው መወሰን ከብዷቸው ነበር። ሆኖም ግን ሥራውን ሳያቆሙ ጎን ለጎን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት ለማህበረሰቡ ያደርሱ ጀመር። ወደ ውጤታማነትም የመራቸው ይህ ስራቸው እንደነበር ይናገራሉ። የፋብሪካ ስራቸውን ሲለቁ መጀመሪያ መስራት የጀመሩት ከሙጫና ቡላ ማጣበቂያ ነው ። ከዚያ መርካቶ በመግባት ካኪ ወረቀትን ለሚለጣጥፉ ሰዎች አሳዩዋቸው። ሆኖም በሙቅ ከሚሰሩበት ዋጋ በላይ ስለጠየቋቸው አንገዛም አሏቸው። ቀጥለውም ወደ ሬሳ ሳጥን ሻጮች ዘንድ አመሩ። የሬሳ ሳጥን ሻጮቹ ሳጥኑን ለማሳመር ቫርኒሽ ይቀባሉ።
በወቅቱ ግን የቫርኒሽ ዋጋ ውድ ነበርና ይህንን ሊተካ ይችላል ብለው ገዟቸው። በዚህ ሥራም 400 ብር ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ። ትንሽ ሰርተው በወር የሚከፈላቸውን ደመወዝ ያህል ማግኘት ካስቻላቸው በብዛት ቢሰሩ ምን ያህል ትርፋማ እንደሚሆኑ አሰቡ። በዚያ ላይ የእንጨት ማሳመሪያ (ቫርኒሽ) ምን ያህል በሌሎች ተፈላጊ እንደሆነ አመላከታቸው። በተለይ ጥቁር ለማድረግ ጥቁር አፈር ፈጭተው ሲጨምሩ ማየታቸው የበለጠ በዚያ ዙሪያ የተሻለ ለመስራት ተሳቡ። የተማሩትእና የሰሩቡት ሙያ የተለያየ ቀለም እንዴት መስራት እንደሚችሉ ያግዛቸዋልና ለመጀመሪያ ጊዜ ጎማ አቃጥለው እህታቸው እንድትፈጨው ሰጧት።
እርሷም የታዘዘችውን አድርጋ አስረከበች። ከስራ ቦታቸው ሲመለሱም ተከታዩን ስራቸውን ሰርተው ወደ መሸጫ ስፍራው አቀኑ። በወቅቱም በገበያው ተፈላጊ ሆኑ። አራት መቶ ብር ከማግኘት ከፍ ብለውም እስከ 1ሺህ 200 ብር ገቢ ማግኘት ቻሉ። አቶ በቀለ ትምህርታቸውን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከተመረቁ በኋላ እናታቸው በሞት ስለተለዩአቸው እህትና ወንድሞቻቸውን የማገዙና የመደገፉ ሀላፊነት በእርሳቸው ትከሻ ላይ የወደቀ ነበር።
ይሄ የገቢ ማግኛ መንገድ ደግሞ እነዚህን ቤተሰቦች ለመደገፍ ጥሩ መንገድ ሆነላቸውና በቤት ውስጥ እህት ወንድሞቻቸው በጉልበት እያገዟቸው እርሳቸው ደግሞ እውቀትና ትጋታቸውን ጨምረው በየጊዜው የተሻለ ምርት በማምረት ውጤታማ ለመሆን መብቃታቸውን አጫውተውናል። አቶ በቀለ ከደመወዛቸው በተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ ቢፈጠርም እርሳቸው ግን ባገኙት ገቢ ብቻ ረክተው አልቆሙም።
እንዳውም ሌሎች የገቢ ማግኛ ነገሮችን ማሰብ ቀጠሉ ። ቀጥለውም የእንጨት ማጣበቂያ (ኮላ) መስራት ጀመሩ። ኮላ የሚሰራው የቆዳ ተረፈ ምርቶችን በመልቀም ነበር። በዚህም የተሻለ ገቢ ማግኘት ችለዋል። ሆኖም ፈተናው ከባድ እንደነበር በተለይም ሽታውና ቆዳ መልቀሙ ዝቅ ያለ ስራን መስራት ለማይወድ ሰው አይወጣውም ። እነርሱ ግን ህልማቸው ትልቅ ስለነበር እንዳደረጉት ይናገራሉ። ሌላው የሰሩት ሥራ የመስታወት እስትኮ ነው፤ እስትኮ መስታወት እንዳይነቃነቅ ማድረጊያ ሲሆን፤ ከውጪ እየመጣ ነው አገልግሎት ላይ የሚውለው። ስለዚህም ዋጋውም ውድ ነበር። እርሳቸው ግን በአገር ውስጥ በመስራት ሥራ ላይ እንዲውል አድርገውታል። እነዚህ ሁሉ መመቻቸታቸውና ውጤታማ እያደረጓቸው መምጣታቸው በተለይም ለእህት ወንድሞቻቸው የሥራ እድል መፍጠራቸው እፎይታን ሰጥቷቸውና በሙሉ ሀይላቸው ከእነርሱ ጋር ለመስራት ሲሉ የአገልግሎታቸውን 10 ሺህ ብር ተቀብለው ሥራቸውን ለቀቁ። አቶ በቀለ ካዩትና ከገዙት ነገር ጭምር መማርና ያንን ለመስራት መሞከር ልምዳቸው ነው።
ለዚህም ማሳያው ቤታቸውን የቀለም እድሳት ለማድረግ አስበው የገዙት ኮላ ሲሆን፤ ተፈላጊ ሥራን እንዲሰሩ ያስቻላቸው እንደነበር ያወሳሉ። ከዚያ በአንድ ሺህ ብር መነሻነት የአሁኑን ቤካስን መስርተው ፈቃድ አውጥተው ከውጪ ድረስ ጥሬ እቃዎችን በማምጣት የጽዳት ሳሙናዎችን በፈሳሽና በተለያየ መልኩ በማምረት መስራታቸውን አጧጧፉት። ካምፓኒያቸውን ‹‹ ቤካስ›› ያሉት በቀለና አስራት የሚለውን እንዲይዝ ለማድረግ እንደሆነ የሚናገሩት እንግዳችን፤ አስራት ወንድማቸው ሲሆን፤12ኛ ክፍል ጨርሶ ቤት ተቀምጧል።
ስለዚህም ለእርሱና ለሌሎቹ እህትና ወንድሞቻቸው የሥራ እድል በመፍጠራቸውና ለዚህ ሥራ ውጤታማነት የእርሱ ድርሻም የላቀ ስለሆነ በእርሱና በእርሳቸው ስም ቤካስ ሲሉ ሰየሙት። በአሁኑ ወቅትም ቤካስ መቀሌ እና አዳማ ላይ ይገኛል። በሥሩም ለ550 ሰዎች የሥራ እድል ፈጥሯል። ‹‹መላላክና የሰውን ፊት ማየት ጊዜያዊ ሥራዎቼ ነበሩ። ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ደግሞ ጊዜያዊ ለሆኑ ሥራዎች መጨነቅ የለብኝም። ስለዚህም በፋብሪካው ከ200 ሰራተኛ በላይ እየመራሁ በተቃራኒው ደግሞ መርካቶ ሄጄ የሰራሁትን የፈጠራ ውጤት እንዲገዙኝ አግባባለሁ።
ግን በሁለቱም ደስተኛ ነበርኩ›› የሚሉት አቶ በቀለ፤ ሥራ ሲሰራ ውጤቱን እንጂ የሰውን ይሉኝታ መመልከት አይገባም። ዛሬ 10 ብር ከተረፈ ነገ 50ና ከዚያበላይ እንደሚገኝ አስቦ መስራትም ነው ለውጤት የሚያበቃው። ስለዚህም ‹‹የዛሬ ይሉኝታ ነገን እንዳይቀማን መጠንቀቅ ይገባል›› የሚለው እምነታቸው ነው።
የህዝብን የማርካት መጠን ከፍ ማድረግ ለነገ መሰረት የሚሆን ስንቅን መሰብሰብ እንደሆነ የሚያምኑት እንግዳችን፤ ተቀባይነት በማግኘት ብቻ ያለምንበት ላይ ያደርሰናል። ስለዚህም ለራሳችን እንደምንሰራው ሁሉ ለህዝባችንም መጨነቅ አለብን። ያንጊዜ የማይደረስበት ማማ ላይ እንቀመጣለን ይላሉ። ከአንድ ሺህ ወደ 130 ሚሊየን ካፒታል ባለቤትነትም የተሸጋገርነው ያለምክንያት አይደለም ሲሉ ልፋታቸው ጥረትና ትጋታቸው አሁን ለደረሱበት ደረጃ እንዳደረሳቸው በልበሙሉነት ይናገራሉ።
አሁን የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ኬሚካል ማኑፋክቸር አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ሆነው እየሰሩ ሲሆን፤ ወንድሞቻቸውንም የሸር አጋር አድርገዋቸው ለገሚሱም በዚያው እንዲሰሩ እድሉን አመቻችተውላቸዋል። የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበር የቦርድ አባልም በመሆናቸው ባለሀብቱ የሚሰራበትን መንገድ ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን ማመቻቸትም አንዱ ሥራቸው እንደሆነ አውግተውናል።
ፈተና
በርካታ ፈተናዎችን አሳልፈዋል። ሆኖም ሁለቱን ግን መቼም የሚረሱት አይደለም። በተለይም በመንግስት ቢሮዎች የደረሰባቸው ፈተናና ያጡት ገንዘብ ዛሬ ድረስ እንደሚያናድዳቸው ያወሳሉ። በወቅቱ ሥራ እንዲሰራ የማይፈልጉ የበዙበትና ሙሉ ለሙሉ የግል የሚባል ነገር እንዳይኖር የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው። ክልከላቸውን ደግሞ በጣም የሚያከብደው በጉቦ መሆኑ ነው። ያንን ያልተረዳ ከጨዋታ ውጪ የሚሆንበት መንገድ ብዙ ነው። ‹‹በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጁ ተብሎ በዚያም ቢሆን ብዙ በጉቦ መንገዶችን መራመድ ይጠይቅ ነበር። እናም ረጅሙን ጉዞ ከመጓዝ ይልቅ አማራጮችን ከእውቅና ውጪ አድርገን እንድንሰራ ተገደናል›› የሚሉት አቶ በቀለ፤ ይህም ቢሆን ብዙ የሚያሰራቸው እንዳልነበረ ያስታውሳሉ። ስለዚህ ትራክተር ገዝተው ቤተሰቡ እያረሰ እንዲኖር ወደ ገጠር በመላካቸው ከሚወዱት ቤተሰባቸው ነጥሏቸው ብቻቸውን እንዲሰሩ አድርጓቸዋል።
ፈቃድ ካወጡም በኋላ ቢሆን ያው የጉቦ ነገር ተከትሏቸው ቤት ገዝተው ስም ለማዘዋወር ባለመቻላቸው ጥሬ እቃቸው ለብዙ ጊዜ እንዲያዝና ሥራ እንዲያቆሙም አድርጓቸው እንደነበር አይረሱትም። የኢንዱስትሪ ቦታም ለማግኘት እንዲሁ ብዙ ፈተናዎችን አልፈዋል። ለአብነት ለሙስና እጃቸውን አልዘረጋም በማለታቸው 20 ሺህ ብር ያወጡበት 500 ካሬ ሜትር ቦታ ተወርሶባቸዋል።
የአገር አበርክቶ
ገና በደንብ ሳይጠነክሩና አቅም ማግኘት ሳይጀምሩ ነበር ሰዎችን ለማገዝ ጥረት ያደርጉ የነበረው። በዚህም ከሚያገኙት ገንዘብ ቀንሰው ከአጋሮች ጋር በመሆን በትውልድ ቀያቸው ትውልዱ ይማር ዘንድ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርት ቤት አስገንብተው ለመንግስት አስረክበዋል። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ ለቸገረው አርሶአደር መድረስ ነበር። በወቅቱ 55 የሚደርሱ ገበሬዎች የሚዘሩት እህል አጥተው መሬታቸውን ጦም ሊያሳድሩት ነበር ። ሆኖም እርሳቸው ይህንን ሲሰሙ ለአገሬ ልጅ ማን መከታ ይሆናል በማለት ስም ዝርዝራቸውን በመቀበል እህል በብድር መልክ ሰጥተዋቸው ሰርተው እንደከፈሏቸውና ምርታማም እንደሆኑበት አጫውተውናል።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እርሳቸው እንደነበሩም ይናገራሉ። ውጤታማ ምርት እንዴት ማምረት እንደሚቻል ስልጠና የሚሰጧቸው አካላት አመቻችተውላቸው ሥራውን ሲሰሩ በተማረ አቅም ነበር። ሌላው ክረምት በገባ ቁጥር ለችግር የሚጋለጥበትን መንገድ መንግስት እንዲሰራ በማድረግ እነርሱም መንግስትን በማገዝ ሁለት ድልድዮችን በተሻለ ጥራት እንዲሰራ አድርገዋል። ከዚያ ባሻገር በእርሳቸው አሰባሳቢነት የተጀመረ የአካባቢው ተወላጅ ልጆች ማህበር አለና ብዙ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው።
ይህንን ለማገዝ ደግሞ ከድርጅታቸው አምስት መቶ ሺህ ብር መድበው በየዓመቱ እንደሚሰጡም ነግረውናል። ማህበሩ አራት ሥራዎችን በዋናነት የሚሰራ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በተለያዩ መንገዶች የልማት ሥራዎችን ማከናወን ነው። በተለይ ደን ላይ መስራት በስፋት ይከናወናል። ሁለተኛው የሥራ ፈጠራ ላይ መስራት ሲሆን፤ ሦስተኛው ድህነትን ከአካባቢው በማጥፋት የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው።
የመጨረሻው ደግሞ መልካም አስተዳደር ላይ መስራት ነው። ሌሎች በርካታ ሥራዎችም ሰርተዋል። ግን የሰራ ብዙ ማውራት አይፈልጉምና በተግባር ይታይ ይላሉ። ዛሬ ደግሞ አገር ኮሮናን ለመከላከል ጥሪ ስታደርግ እርሳቸውም እጃቸውን ዘርግተዋል። በርካታ ማሽነሪዎችን ለመግዛት ያላቸውን አሟጠው በመስጠታቸውና የባንክ ብድርም መቀነሱ የተቻላቸውን ያህል እንዳያደርጉ ቢገድባቸውም 500 ሺህ ብር ቃል እንደገቡ አጫውተውናል። ነገሮችሲስተካከሉ ደግሞ እኛ በአገር ሰርተን ያተረፍነው በመሆኑ ለአገር መስጠት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነውና እናደርጋለንም ብለውናል።
ውሃ አጣጭ
አቶ በቀለ ለብዙ ዓመታት ድርጅታቸውን ቤካስን እንደ ትዳር አጋራቸው አድርገው ኖረዋል። ወንድምና እህቶቻቸውንም ለቁም ነገር ማብቃት ነበረባቸውና ከስራቸው ውጪ ሌላ ነገር አይታያቸውም። ግን አንድ ቀን ወንድማቸው የተሻለ ነገር መምጣት የሚቻለው የተሻለች የትዳር አጋር ስታገኝ ነው በሚል ይጎተጉታቸው ገባ። በዚህም ማግባት እንዳለባቸው ወሰኑ። ግን ማንን የሚለው ነገር አሳስቧቸው እንደነበር አይረሱትም። የውስጣቸውን ቶሎ መረዳት የሚችለውም ወንድማቸው አንድ ሀሳብ አቀረበ። አብራው የምትማረው ብርሃን የተሰኘችው መልከመልካም ሴት ለእርሳቸው የትዳር አጋር መሆን እንደምትችል ነገራቸው። የታናሽ ምክሩንም ለገሳቸው። እርሳቸውም እስኪ ልያት ብለው በዙሪያዋ ያለውን ነገር ማጥናት ጀመሩ።
እውነትም እንደተባለችውና እንደ ስሟም ለኑሮ ብርሀን የምትሆን ነችና የትዳር ጥያቄ አቀረቡላት። በብዙ ትግልም እሽታዋን ገለጸችላቸውና ትዳር ተመሰረተ። ዛሬ ሶስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ ሁለቱ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። አንዱ ደግሞ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው። በዚህም ደስተኛ ህይወትን እየመሩ ይገኛሉ። እንደውም አንዷ የእርሳቸውን እግር ተከትላ ባዮ ኬሚስትሪ እያጠናች ስለሆነ በሚገባ እያገዟት እንዳሉ አጫተውናል። መልዕክት ‹‹እያንዳንዱ ሰው ሌሎችን ሀብታም ለማድረግ ከሰራ አገር ሀብታም ትሆናለች።
ሁሉም ሰው ሀብታም የሚሆንበት እድል ይፈጠርለታል›› የሚል ፍልስፍና ዕለተ ሰንበት አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4ቀን 2012 ዓ.ም ያላቸው እንግዳችን፤ አስተሳሰቡ ምቀኝነትን የሚገልና በጎነትን የሚያሰፋ በመሆኑ አብሮ ማደግን ያመጣል። በዚህም ለማኝ አይኖርም። እናም እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ብቻ ሀብታም ለመሆን ሳይሆን ሌሎችንም ጭምር ሀብታም አደርጋለሁ ብሎ ሊሰራ ይገባል የሚለው የመጀመሪያ መልዕክታቸው ነው።
በአገር ደረጃ ሰው ተጋገዘ ማለት ብር መስጠት አይደለም። የሚሰራበትንና የሚለወጥበትን መንገድም ማሳየት አንዱ እርዳታ ነው። ስለዚህም አገሬን እወዳለሁ የሚል ሁሉ ለሌሎች መበልጸግ መስራት አለበት። ለምን በለጠኝ ሳይሆን እንዴት ከችግሩ ተላቆ ድህነቱን ያስወግድ የሚለው ላይ መስራት ይገባል። በተለይም ሃሳብ ማጋራት ላይ ንፉግ መሆን አይገባም ይላሉ። ‹‹ኢትዮጵያውያን ለብዙ አፍሪካውያን ምሳሌ የምንሆንበት በርካታ ነገሮች ነበሩን። ነገር ግን የአስተሳሰባችን ጥግ የተበላሸ በመሆኑ ዛሬም ድሃ እየተባልን እንፈረጃለን።
ስለዚህም ይህንን አስበን መስራትና መለወጥ አለብን›› ሌላው መልዕክታቸው ነው። የኮሮና መምጣትን ሲያነሱ ችግሩ አስከፊ ቢሆንም ወደ እድል መቀየር እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። በተለይ ይህ ጊዜ መረዳዳት ምን አይነት ዋጋ እንዳለው የሚያሳየንና አንድነታችንን የሚያጠነክርልን ነው።
የወጣቱን የአስተሳሰብ ብልሹነት ለማረምም ያግዛል። የሥራ ፈጠራ ላይም ትልቅ አወንታዊ ጠቀሜታን የሚያመጣ ነው። በተመሳሳይ ለሥራ ጊዜ የሰጠን ሰዎች አለንና አገርን ለመጥቀም የምንሰራበትም እድል ይሰጠናል። ስለዚህም ይህንን እድል መጠቀም ላይ ማተኮር አለብን ማሳረጊያ መልዕክታቸው ነው። እኛም መልዕክታቸውን በተግባር እናውለው እያልን ለዛሬ ተሰናበትን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው