ምሁራኑን፣ ሳይንቲስቱን ፣ የጤና ባለሙያውን ሁሉ እረፍት የነሳው ኮቪድ 19 ዛሬም ዓለምን እያስጨነቀ ይገኛል። የዓለም መንግስታት ህዝባቸውን ለመታደግ የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተዋል። የእምነት ተቋማት እና አማኞች ፈጣሪያቸውን በጸሎት እየተማጸኑ ይገኛሉ። የሀብት ሆነ የስልጣን ደረጃ የወረርሽኙን አቅም ሊያስቆመው አልቻለም ። የዓለም ህዝቦች ቤታቸውን ምሽግ አድርገው ይሄንን ክፉ ቀን ለማለፍ ጥረት እያደረጉ ናቸው ። ያም ሆኖ ግን አሁንም በቫይረሱ እየተጠቃ ያለው ህዝብ ቁጥር ሽቅብ እንጂ ቁልቁል አላለም። አስደንጋጭ የሞት ቁጥር መስማትም የየእለት ዜና ሆኖ ቀጥሏል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ1ሚሊየን 701 ሺህ 718 በላይ ህዝብ በወረርሽኙ የተጠቃ ሲሆን ከ102 ሺህ 867 በላይ ሞት ተመዝግቧል። ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ በህዝባችን ዘንድ የስጋትና የፍርሀት ምንጭ ሆኗል ። እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት 69 ህሙማን በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ፤ ሶስት ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። ዛሬም የጤና ሚኒስቴር እና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይሄንን ወረርሽኝ በጥበብ እንድናልፈው ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን እያስተማሩና እየመከሩ ናቸው። በርግጥ ኢትዮጵያውያን በወረርሽኝ ስንጠቃ ይሄ የመጀመሪያ አይደለም ።
የወረርሽኙ አይነትና ደረጃ ቢለያይም ጥቃቶችን ግን በየጊዜው አስተናግደናል፤ የምንወዳቸውን ብዙዎችንም በጥቃቶቹ አጥተናል። ብዙ ክፉ ቀናቶችን አንድ ሆኖ ተናቦ በመስራት፣ በመረዳዳት እና በጥበብ አልፈናል ። አሁንም የገጠመንን የኮቪድ 19 ወረርሽን በጥበብ ፣በመተሳሰብና በመደማመጥ ልናልፈው እንደምንችል ከትናንት ታሪኮቻችን የምንማረው ብዙ አለ ። ከሁሉም በላይ እንደ ግለሰብ ሆነ እንደ ህዝብ ከመንግስት እና ከጤና ተቋማት በኩል የሚሰጡ መመሪያዎችን በተገቢው መንገድ መተግበር ይጠበቅብናል ።
አንድ ሰው በሽታውን ለመከላከል የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡ ፣ለማህበረሰቡ ከፍ ሲልም ለሀገር መሆኑን መረዳት አለበት።ይሄ ሲሆንና ልብ ለልብ መገናኘት ሲቻል የመጣውን ጠላት መቋቋምና መመከት ይቻላል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎንም ችግረኛ ወገኖችን መደገፍ ወሳኝ ነው።እስካሁን ባለው ሂደት አቅሙና በጎነቱ ያላቸው ሰዎች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። ህንጻቸውን፣ መኪኖቻቸውን፣ መኖሪያ ቤታቸውን ፣ የህክምና ተቋማታቸውንና ሰራተኞቻቸውን ጭምር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና ለህክምና አገልግሎት እንዲውሉ ሰጥተዋል።
ይሄ ኢትዮጵያውያን ድሮም በችግር ወቅት ደራሽ ናቸው የሚለውን ታሪክ ዳግም ያደሰ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ለቤት አከራዮች ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት በርካታ የመኖሪያና የንግድ ቤት አከራዮች ምላሽ በመስጠት ወገናዊነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ችግሩ እስኪያልፍ ድረስ ከክፍያ ነፃ ሲያደርጉ ቀሪዎቹ ደግሞ በከፊል እንዲከፍሉ በማድረግ ላይ ናቸው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንም ለተከራዮች የሚያዝያን ወር የቤት ኪራይ 50 በመቶ መቀነሱን አስታውቋል። ይሄ ከላይ እስከታች የመተሳሰብ ባህሉ እየጎለበተ መምጣቱን የሚያሳይና የሚያስመሰግን ነው። ይሁን እንጂ አሁንም አእምሯቸውን ለዝርፊያ እንጂ ለበጎ ተግባር የማያውሉ መኖራቸው ሀቅ ነው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኪሳቸውን እንጂ ወገናቸውን የማይመለከቱ አሉ። በህዝብ ስቃይ ለማትረፍ የሚተጉም አይጠፉም ።ይሄ ዘመን አንዱ ለሌላው አስቦና ተሳስቦ የሚያልፍበት እንጂ አንዱ ሰጪ ሌላው ነጣቂ የሚሆንበት ስላልሆነ ሁኔታዎችን በትኩረትና በጥንቃቄ መከታተል ያስፈልጋል !፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2012
አንዱ ሰጪ ሌላው ነጣቂ እንዳይሆን !