በጎነት ዋጋ የሚወጣለት ተግባር አይደለም::ዘላቂነት ያለው እርካታ ለአዕምሮ እንደሚያስገኝም የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ:: ከመቼውም በተሻለ የዜጎች አንድነት እንዲጎለብት እና እጅ ለእጅ ተያይዘው ራስንና ወገንን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመታደግ ጥሪ የቀረበበት ነው::ይሄን ተከትሎም በየአውራ ጎዳናዎች ታዳጊ ወጣቶችና ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ ለወገኖቻቸው ጤና ደፋ ቀና ሲሉ በሰፊው ይስተዋላል:: ከወረርሽኙ አቅመ ደካሞችን ለመታደግ የመርካቶ ወጣቶች የተገኘውን ለማሰባሰብ እግራቸው እስኪቀጥን ይማስናሉ::
ዓላማቸውን በማስረዳት ከነጋዴዎች፣ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከነዋሪዎች እና ከተገኙ ሰዎች የሚሰጣቸውን ይሰበስባሉ:: ልፋታቸውና ድካማቸው በሕሊናቸው ርካታ ይካካሳል:: ሌላ ትርፍ የሚፈልጉ ባለመሆናቸው ከልባቸው ይሰራሉ:: የተገኘውን ስጦታም በትከሻቸው ተሸክመው ወደሚያከማቹበት ያደርሳሉ:: በዚህ ሁኔታ ለወገኖቻቸው የክፉ ቀን ስንቅ በማሰባሰብ የተጠመዱት ወጣቶች አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ናቸው::
አሁን ላይ በኮሮና ወረርሽኙ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እንደዚህ አይነት የበጎ ፈቃድ ተግባር ለማከናወን እንደሚያመች የተናገረው ተማሪ ሄኖክ ተካልኝ ነው:: ክረምቱን የበጎ ፈቃድ ተግባር በማከናወን ሁሌም እንደሚያሳልፍ ተማሪ ሔኖክ ይናገራል::የዚህ ዓመት የበጎ ፈቃድ ዘመቻው አስደሳችም አስፈሪም ነው::ምክንያቱም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ ለራስህ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል:: የተዘናጋ ሰው ከራሱ አልፎ ለቤተሰቦቹ ሊተርፍ የሚችል ጦስ ወረርሽኝ ይዞ ሊመለስ ይችላል::‹‹አተርፍ ባይ አጉዳይ ›› ላለመሆን ሲባል ማህበራዊ ርቀታቸውን ጠብቀው የበጎ ፈቃድ ተገባራቸውን እንደሚወጡ አስረድቷል፡፡
የዓለም ሕዝብ እርስ በርሱ ከሰው ባህሪ በተለየ ደረጃ የግፍ ተግባር እየፈጸመ መምጣቱ እንዲህ አይነት አንድ አይነት በሽታ መከሰቱ ፈጣሪ ሰዎችን ለማስተማር ፈልጎ ያደረገው እንደሆነ የተናገረው ተማሪ ሄኖክ፤ በዚህ አይነት ጊዜ ለማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ያስደስታል::በመሆኑም ሁሉም ወጣት በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በእንደዚህ አይነት ተግባር ላይ መሰማራት እንዳለባቸው ገልጿል:: በጎ ተግባር ከበጎ አስተሳሰብ ይወለዳል::በተለይም በተማሪነትና በወጣትነት ጊዜ የተሰማሩበት የበጎ ፈቃድ ተግባር በስተእርጅና ስንቅ እንደሆነ ወጣቶች መረዳት አለባቸው::
ለአቅመ ደካሞች ከጉልበታቸው እስከገንዘባቸው በሚሰጡበት ጊዜ ለአነሱም ፈጣሪ እንደሚሰጣቸው ጥልቅ እምነት ሊኖራቸው ይገባል::ምክንያቱም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከውስጥ ፈንቅሎ በሚወጣ ስሜት የሚሰራ እንደሆነ ተማሪ ሔኖክ አብራርቷል፡፡ ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንዲሉ ኢትዮጵያውያን በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ትንሽም ስጦታ ቢሆን ዋጋ አለው:: ከስራዎቻቸው ተለይተው ቤት በመዋል ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው የሚላስ የሚቀመስ የሚያጡት ቁጥራቸው ቀላል እንደማይሆን ተማሪ ሄኖክ ተናግሯል::
በመሆኑም አነሰ በዛ ሳይሉ መተጋገዛቸውን መቀጠል አለባቸው፡፡ ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ በጦርነት ላይ ነች:: ኢትዮጵያውያንም ይበጃል ያሉትን የመከላከያ መንገድ ሁሉ በመተግበር ላይ ይገኛሉ:: ተማሪዎቹም የዚህ ዘመቻ አካል ሆነው መሰለፋቸውንም አክሎ ተናግሯል:: ተማሪዎች በጥናት እና በተለያዩ ሚዲያዎች ትምህር ታቸውን ለማስታወስ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በበጎ ፈቃድ ተግባር ወገኖቻቸውን ለማገዝ ባላቸው አቅም የሚያሳዩት ጥረት ሊበረታታ የሚገባው ነው:: ለዚህ ተግባር የምስራቅ ሐረርጌ ቀርሳ ወረዳ ነዋሪው ተማሪ ጀማል ኢንሰርሙ ጥረት ተጠቃሽ ነው:: የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ መሆኑን የገለጸው ተማሪ ጀማል፣ የእድሜ እኩዮቹን በማስተባበር የኮሮና ወረርሽኝ ዋና ዋና ምልክቶች፣ መከላከያዎችና መተላለፊያዎችን ለማህበረሰቡ እንደሚ ያስተምሩ ይገልጻል::
ከዚህ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ በሽታ እድሜያቸው በሳል በሆኑ ተጨማሪ የጤና እክል ባለባቸው ሰዎች ላይ እንደሚበረታ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ሁሉም ወጣት ማስተማርን ከቤት ከሚገኙት ወላጆችና አያቶች መጀመር እንዳለባቸው በበጎ ፈቃድ የሚሰሩ ወጣቶችን ይመክራል::በጎ ፈቃድ ያደግክበትን ማህበረሰብ ለማገልገል ለወጣቶች እድል የሚሰጥ ተግባር እንደሆነም ተናግሯል፡፡
ሌላው በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲቀባበሉት የታዘብነው የ19 ዓመት ወጣት ተዓምራዊ በጎ ተግባርን ነበር::ወጣቱ ተማሪ በማህበረሰቡ ዘንድ ለሚያስ ታውላቸው ችግሮች መፍትሄ መሻትን የተካነ ነው:: በአዳዲስ ፈጠራዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችል አእምሮን የተለገሰ ታዳጊ ነው:: በኮሮና ለተያዙ ሰዎች ለመተንፈሻነት የሚያግዝ ማሽን (ቬንትሌተር) ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ መግለጹ ግርምትን ፈጥሯል:: ከዚህ ሐሳብ ቀደም ብሎ ወጣቶች የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ሰዎች ንጽሕናቸውን ይጠብቁ ዘንድ እጅ ሲያስታጥቡ የተመለከተው ይህ ባለምጡቅ አዕምሮ ወጣት ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነና አውቶማቲክ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ሰርቷል::
ይሄ የፈጠራ ሥራውም በወልቂጤ ሆስፒታል እና በአካባቢው በስፋት እየተመረተ በመሰራጨት ላይ እንደሆነ ተናግሯል::ወጣቱ ተማሪ ኢዘዲን ካሚል ይባላል፤ የ19 ዓመት ተማሪ ነው::28 የፈጠራ ሥራዎች ባለቤት ነው:: በ13ቱም ዓለም አቀፍ የፈጠራ ባለቤትነት እንዳገኘባቸው ይናገራል፡፡ ተማሪዎች ከወረርሽኙ ይጠበቁ ዘንድ የትምህርት ተቋማት መዘጋጀታቸውን ተከትሎ ወገኖቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ለማገልገል ከመንግስት ጎን በበጎ ፈቃድ ተሰልፈዋል:: አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሎች በሚገኙበት አካባቢ ተማሪዎች በተለያዩ ተግባሮች ይሳተፋሉ::
የኮሮናን ወረርሽኝ ለመከላከል በበጎ ፈቃድ እጅ በማስታጠብ፣ ሳኒታይዘር በመቀባት፣ ተራ በማስከበር እና እንደ የአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ አስፈላጊ ባሉት ተግባር ላይ ብዙዎቹ ተሰማርተዋል:: ነገር ግን የወረርሽኙን አንዱን መከላከያ ሲተገብሩ ከሌለው መተላለፊያ መንገድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል የሚሉት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ክንዴ ውብሸት ናቸው::
እርሳቸው እንደሚሉት ወጣቶች በየመንገዱ ላይ ቆመው ሌላውን የሚያስታጥቡበት መንገድ አደጋን ሊያስከትል የሚችል ነው::መስተካከል ይኖርበታል:: ምክንያቱም ማህበራዊ ርቀትን በተገቢው የጠበቀ ባለመሆኑ በትንፋሽና በተለያዩ መንገዶች ወጣቶቹን ለወረርሽኙ ሊያጋልጥ የሚችል እንደሆነ በመግለጽ ሳሙናና ውሃ ማስቀመጥና መንገደኛው ንጽሕናውን ከጠበቀ (እጁን ከታጠበ) በኋላ እጁን በሚያዳርቅበት ሶፍት የውሃ ቧንቧውን ዘግቶ ወደ ጉዳዩ መሄድ ይገባዋል ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተዋል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2012
ሙሐመድ ሁሴን