እፀገነት አክሊሉ – ዶክተር ወልደሰንበት ዋጋነው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛና ጽኑ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በአደጋ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ህክምና ቡድኖች አስተባባሪ የኮሮና ቫይረስ እንደየትኛውም የቫይረስ አይነት ነው። ከዛሬ ሁለት አስርተ ዓመታት በፊት ደግሞ ብዙ ትኩረት ያላገኘና እንደ የትኛውም ቫይረስ ጉንፋን የሚያመጣና በህይወት ዘመን አንድ ጊዜ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ቀላል ቫይረስ እንደነበር ነው በህክምና ደረጃ የሚታወቀው።
እኤአ በ 2002 ላይ የኮሮና ቫይረስ አንደኛው ዓይነት ሳርስ የሚባለው እስከሚመጣ ድረስ ይህኛው ቀላል በሽታ እንደሆነም ታምኖ ቆይቷል። ወደ ህክምና የማያስኬድና ከጉንፋን የዘለለም ቫይረስ ስላልነበር በህክምናም የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነበር። ሆኖም በ 2002 ሳርስ ሳውዲ አረቢያ አካባቢ በተነሳ ጊዜ ነው ኮሮና ቫይረስ በሳይንስም በህክምናም ትልቅ ትኩረት ያገኘው።
ኮሮና በህክምና የራሱ ሽፋን ያለውና አር ኤን ኤ (rna) የሚባል ሲሆን ከተፈጥሯዊ ባህሪው አንጻር በህክምና ለመከላከልም አስቸጋሪ ነው። የሰውን ልጅ ሊያጠቁ የሚችሉ ሰባት ዓይነት የኮሮና ቫይረሶች አሉ፤ ከነዚህ መካከል እስከ አሁን ድረስ በሰው ህይወት ላይ አደጋን ያስከተሉት ሳርስ ፣ ሜርስ ሚድል ኢስት ሪስፓይራቶሪ ሲንድረም ሲሆኑ በተለይም ሶስተኛው በቅርብ ጊዜ ማለትም እኤአ በ 2012 የተከሰተ ነው።
አሁን ደግሞ ህዳርና ታህሳስ ወር ላይ የተከሰተው ኮቪድ 19 የሚል ስያሜ የተሰጠው ኮሮና ቫይረስ ብዙኃንን ሊጎዳ የሚችልና አደጋ አድራሽ የሰውን ልጅም ከበድ ያለ የህክምና አገልግሎት በሚፈልግ መልኩ የመጣና ሞትንም የሚያስከትል መሆኑ በጣም ከባድ አድርጎታል። በአዲስ ዘመን የተጠየቅ አምድም የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ያለበትን ወቅታዊ አቋምና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የዘርፉ ባለሙያ ከሆኑትና በቅዱስ ዻውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛና ጽኑ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በአደጋ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ህክምና ቡድኖች አስተባባሪው ከዶክተር ወልደሰንበት ዋጋነው ጋር ቆይታን አድርጓል።
አዲስ ዘመን ፡- ኮረና ቫይረስ በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ በባለሙያ አንደበት ምን ሊባል የሚችል ነው?
ዶክተር ወልደሰንበት፡- ዛሬ ላይ ቆመን ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በምናወራበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ቁጥሩ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ይታያል። ግን ደግሞ ቫይረሱ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ከተነገረበት ጊዜ አንጻር ስናየው ቁጥሩ ያን ያህል ብዙ ነው ማለት አይቻልም። ይህንንም ከሌሎች አገሮች አንጻር ማነጻጻር ይቻላል። አዲስ ዘመን፡- ምናልባት በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህንን ያህል ቁጥር መመዝገቡ ትንሽ ነው ሊባል ይችላል፤ ሆኖም የመመርመር አቅማችን ወደማህበረሰቡ ወርዷልስ ማለት ይቻላል?
ዶክተር ወልደሰንበት፡- አዎ ጥሩ ነው ማለትማ ባረጋገጥነው ልክ ነው፤ ሆኖም ማህበረሰቡ ውስጥ ስርጭቱ አለወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ ብዙ ምርምሮች እየተካሄዱና በርካታ ተግባራትም እየተከናወኑ ነው። እንደ ጤና ተቋምም ሆነ እንደ ባለሙያ ሁላችንም ተሳስረን እያንዳንዱን ታማሚ የሞት ሁኔታና የሳንባ ምች ምልክቶች ሁሉ ሪፖርት እንዲደረጉ እየተደረገ ነው ያለው።
ይሁንና በዚህ መልኩ እየተሰራ ቢሆንም ምርመራው ግን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚወክል አይደለም። ይህ ለመሆኑ ደግሞ ዋናው ምክንያት የመመርመሪያ ተቋሙ አንድ ማዕከል መሆኑ፣ ለምርመራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በሙሉ ከውጭ አገር የሚመጡ ከመሆናቸው አንጻር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ እድል የሚሰጥ አልነበረም፤ አሁን ላይ ግን ሁለት ሶስት ቦታዎች ላይ የምርመራ ማዕከላት እየተደራጁ መሆናቸው ከአሁን በኋላ በርከት ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመመርመር እድል ይፈጥራል።
በዚህ ልክ መመርመር ስንችል ደግሞ አብዛኛውን ህብረተሰባችንን እንደርሳለን የመከላከል ስራውም የተጠናከረ ይሆናል። በሌላ በኩልም እንደዚህ ያለው የተጠናከረ የመመርመር ስራ ከተከናወነ በኋላ ቁጥሩ በዚህ መልኩ መጠነኛ ከሆነ ጥሩና ጊዜ የሚሰጥ ይሆናል። አዲስ ዘመን፦ እስከ አሁን ባከናወነው የምርመራ ስራ እያገኘን ያለነው ውጤት ወይም የታማሚ ቁጥር ውስን ነው ካለን ወደፊት ደግሞ የምርመራው ስራ እርስዎ ባሉት መልክ ሲጠናከር በአንድ ጊዜ መሸከም የማንችለው ቁጥር ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋትስ በእናንተ በባለሙያዎቹ ዘንድ የለም?
ዶክተር ወልደሰንበት፦ በዚህ ሳምንት የነበሩ የምርመራ ሂደቶች ቀደም ካለው ጊዜ አንጻር ጥሩ ነበሩ፤ በሌላ በኩልም የምርመራ ስራውን ወደ ክልሎች ለማዳረስ እየተሞከረ ነው፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ጅምር ነው።በዛ ብለን ምርመራውን መጀመራችንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዛ በሚልበት ወቅት ምን ያህልማስተናገድ እንችላለን የት ላይ ነን የሚለውን ለማየትም ያግዛል።
አሁን ላይ ወይም ቀድሞ በምርመራ ታውቆ በእጃችን ላይ ያለው ቁጥር ህብረተሰቡን የሚወክል አይደለም። እዚህ ላይ አንድ ጥሩና የከፋ ነገር ላይኖር ይችላል ብለን እንድንገምት ያደረገን ለምሳሌ የሳምባ ምች መልዕክት ከኮሮና ጋር ስለሚመሳሰል በየጤና ተቋሙ በዚህ ህመም የሚታመሙም የሚሞቱም ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው የተለየ ቁጥር አለማሳየቱ ነው። በመሆኑም በላቦራቶሪ ምርመራችን ሁሉንም ተደራሽ ማድረግ ባንችልም ያን ያህል የከፋ አደጋ እያደረሰ አለመሆኑ በተወሰነ መልኩ ልብ የሚያሳርፍ ነው።
ይህ ማለት ግን ምርመራውን ሰፋ አድርገን አንቀጥልም ማለት ሳይሆን ምልክት ሳያሳዩ ወይም ደግሞ በመጠነኛ ህመም ደረጃ ላይ ያሉ ያልተለዩ ግን በሽታውን የሚያሰራጩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ አለብን። አዲስ ዘመን ፦ ዞሮ ዞሮ ኮሮና ቫይረስ አገራችን ገብቷል፤ ግን ደግሞ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው በሽታውን ለመከላከል የሚያሳየው ተነሳሽነት በጣም ውስን ነው? እርስዎስ እንደ ጤና ባለሙያ ምን ታዘቡ?
ዶክተር ወልደሰንበት፦ እንግዲህ ማህበረሰቡ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት በመጠኑ ጥሩ ነው። አብዛኛው ኅብረተሰብ ከፍል የሚነገረውን ነገር ወደ መስማት ደረጃ ደርሷል፤ ለምሳሌ በከተማዋ ላይ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ ቀንሷል፤ ሰዎች በብዛት መንቀሳቀስም በተወሰኑ ቦታዎች ላይ መሻሻልን አሳይቷል።
ሆኖም በዛው ልክ ደግሞ በተለይም ሆቴሎች አካባቢ በጣም መዘናጋት ይታያል፤ በቢሮዎች አካባቢም በብዛት ሆኖ መቀመጥ ይስተዋላል ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የገበያ ቦታዎች ለምሳሌ ፒያሳ፣ መርካቶ እንዲሁም መሰል ቦታዎች ላይ የሚታየው የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ እንዲሁም እየተወሰዱ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎች እጅግ ተስፋ የሚያስቆርጡ ለበሽታውም አጋላጭም የሆኑ ምልክቶች እየታዩ ነው።ይህንን ሳይ እንደ አንድ የጤና ባለሙያ ያስጨንቀኛል ህብረተሰቡም የሚባለውን በዚህ ልክ የማይሰማ ከሆነ በቅርብ ቀናት ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች ታመው ሊመጡ የሚችሉበት አጋጣሚም ይፈጠራል የሚል አረዳድ ነው በእኔ በኩል ያለው።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ተስፋን ከማስቆረጡ ጎን ለጎን ጠንክረን እንድንሰራም ያደርጋል ምክንያቱም ሰዎች በዚያ አካባቢ በአንድም በሌላ መልኩ ገበያውም አንድ ቦታ ላይ ስለሆነ ይህንን ለመበተን ጥረቶች እየተደረጉም ነው። ህብረተሰቡ በጣም መዘናጋቱን ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል አሁን ላይ አልባሳትን ለመግዛት ገበያ መውጣት በጣም የሚያስገርም ነው፤ በመሆኑም ይህንን ተግባራችንን ለራሳችንም ለሌሎችም ስንል ገታ ማድረግብንችል።
ሌላው በሽታውን ሊያሰራጩ የሚችሉ የገበያ ቦታዎችን ማለትም እንደ አትክልት ተራ ያሉትን ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወሩ ትልቅ የጥንቃቄ እርምጃ በመሆኑ ሌሎች የገበያ ቦታዎችንም በመበተን ለህብረተሰቡም በየቦታው ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ አንድ ቦታ ላይ እንዳይሰበሰብ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ ህብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ከመንግስት ትልልቅ የስራ ኃላፊዎች ስለ በሽታው መተላለፊያ መንገዶች የሚነገረውን ነገር መስማት ያስፈልጋል፤ አንድ ሰው ራሱን ባልጠበቀ መጠን እራሱን የጠበቀውንም ሰው አደጋ ላይ ስለሚጥል።
በተለይም ወጣቶቹ የሚዘናጉ ሰዎች አዘውትረው እጃቸውን ሲታጠቡ የማሽሟጥጡ እና ያልተገቡ ሁኔታዎችን የሚየሳዩ ከዚህ ተግባራቸው ቢቆጠቡ መልካም ነው። እነዚህን ወጣቶች የሚገስጹ እናቶችም አሉና እነዚህም በዚሁ ሁኔታ መቀጠል ያለበት ከመሆኑም በላይ ማህበረሰቡ በእድሜ ታላላቅ የሆኑ ሰዎችን የሚያከብር ከመሆኑ አንጻር እነሱን ተጠቅመን ሁሉም ማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ማስተማር ብንችል መልካም ነው።
በሌላ በኩልም ስለ ተከታዮቻቸው ኃላፊነት ያለባቸው የሀይማኖት አባቶች በማስተማር ስራው ላይ የነቃ ተሳትፎን እንዲያደርጉ ብናደርግና ተቋማቱምትምህርቱን በማስኬድ የበኩላቸውን ቢወጡ፤ ምዕመናኑም ፈጣሪን ከመፈታተን ወጥቶ በተሰጠው አእምሮ እያመዛዘነና እያሰበ ችግሩን ከሀይማኖት ጋር ከማገናኘት ይልቅ ለራሳቸው ሀላፊነትን መውሰድ ቢችሉ ይመከራል።
በጠቅላላው ግን ተሰሚነት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ፈጠራ ስራው ላይ የጎላ ሚናን እየተጫወቱ ቢሆንም አሁንም ይቀራል ለቅሶ ላይ ገበያ ላይ እንዲሁም ሆቴሎች ላይ የሚታየው ነገር ገና በሽታውን ለመከላከል ዝግጁ አለመሆናችንን የሚያሳይ ነው። የአገራችንን የጤና ሁኔታ ሁላችንም እንደምናውቀው ብዙ ችግር ያለበትና ገና ተደራሽ ለመሆንም ብዙ ስራዎች የሚቀሩት ነው፤ እንደ ኮሮና ቫይረስ ዓይነት ከባድ ችግሮችን መሸከም የሚችልም አይደለም፤ በመሆኑም ማህበረሰቡ ይህንን ተገንዝቦ እራሱን ከበሽታው ቢከላከል ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኅብረተሰቡ በተለይም ለይቶ ማቆያ ( ኳራንታይን) በሚባለው ቦታ ላይ የተዛባ አረዳድ ከመያዙ የተነሳ የህመም ስሜቶች እያሉበት እንኳን አለማሳወቅ ማቆያ ውስጥም ከገቡ በኋላ በተለያዩ መንገዶች አምልጦ የመውጣት ሁኔታን እየሰማን ነውና ለይቶ ማቆያ ማለት ምን ማለት ነው? ለይቶ ማቆያ የገባ ሁሉስ በሽተኛ ነው?
ዶክተር ወልደሰንበት፦ ከኳራንታይን ቀደም የሚለው ጉዞ ነው። አሁን ላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ አላስፈላጊ ጉዞዎችን ከማድረግ ብንቆጠብ፤ የግድ ሆኖ ከተንቀሳቀስን ደግሞ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስንመለስ ራሳችንን ገታ አድርገን በተመቻቹልን የማቆያ ቦታዎች ላይ የምናርፍ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ምናልባት እንኳን ቫይረሱ ቢኖርብን ለምንወዳቸው ቤተሰቦቻችን ፣ ለልጆቻችን፣ ለጎረቤቶቻችን እንዲሁም ለማህበረሰቡና ለአገር እንዳንተርፍ እራሳችንን ገታ አድርገን የምንቆይበት ነው። ለዚህ የምንከፍለው ዋጋ ለምንወዳቸው ለምናከብ ራቸው ሰዎች እንደሆነና ለአገራችንም አንዳች አስተዋጽኦ እያበረከትን እንዳለን ሊሰማን ይገባል። አንድ ሰው ከቤቱ ወይም ከለመደው ሁኔታ ወጥቶ በአንድ ቦታ ላይ ተወስኖ እንዲቆይ መደረግ ብዙ ምቾትን ላይሰጥ ይችል ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ ቦታ ላይ ስለገባ ሰውየው ታሟል ማለት ሳይሆን እንደ አጋጣሚ ቫይረሱ ቢኖርባቸው ሌላው ሰው እንዳይተላለፍበት ለማድረግ መሆኑም በህብረተሰቡ ዘንድ መታወቅ ይኖርበታል። ሁሉም መረዳት ያለበት ለይቶ ማቆያ ለምንወዳቸው ለምናከብራቸውና ለምንሳሳላቸው ቤተሰቦቻችን እንዲሁም ለአገራችን ፍቅርን ማሳያ መንገድ እንደሆነ መገንዘብ ነው።
ከዚህ አንጻር ሁላችንም የምናምነው ሀይማኖት ያለን ሰዎች ከመሆናችን አንጻር የትኛውም ሀይማኖት ደግሞ በሌላው ሰው ላይ ክፉ እንዲደርስበት ስለማይመክር ከየትኛውም አቅጣጫ ግዳጃችንን የምንወጣበት ልናደርገው ይገባል። አልታመምንም ምልክት አይታይብንም ግን ደግም ቫይረሱን ለሌላው የምናስተላልፍ ከሆነ ኳራንታይን ደግሞ ቫይረሱን ከላያችን ላይ የምናራግፍበት መንገድ በመሆኑ በዚህ ልክ ማየትና ትኩረት በመስጠት የግንዛቤ እጥረትም ካለ የማስተማሩ ስራ ሊሰራ ይገባል።
እዚህ ላይ አንዳንድ ሾፌሮች፣ የደህንነት አባላትና ሌሎችም በጥቅም በመደለል ኳራንታይን የገቡ ሰዎችን ለማስወጣት ሲሞክሩ ተስተውሏል፤ ሆኖም ምንም ዓይነት የጥቅም ማማለል ቢኖር እንኳን መፍቀድ የለባቸውም ምክንያቱም ኅብረተሰቡ አምኖ ሀላፊነት ስለሰጣቸው ይህንን ሀላፊነታቸውን መወጣት ይገባል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን እኛ የኢትዮጵያም ባለውለታ ነን ብለው በማሰብ በትንሽ ነገር ከመደለል ሊቆጠቡ ይገባል።
ይህንን ባለማድረግና ለትንሽ ጥቅም ብለው የብዙኃን ህይወት መቅጫ መንገድ የሆነውን ቫይረስ ባለማሰራጨትና የኢትዮጵያን ስቃይ ባለመጨመር ኃላፊነታቸውን መወጣት ለጠላት ወይም ለበሽታ እጃችንን ባለመስጠትና የምንወዳቸውንና የምናከ ብራቸውን ሰዎች አሳልፈን ባለመስጠት ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት ያስፈልጋል። ለትንሽ ነገር የብዙኃን ነብስ ባይሸቀጥ ጥሩ ነው ምክንያቱም ቫይረስ ነው እየተሸጠ ያለው በዚህ ልክ ብንገነዘብ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሩህ ሩህ ከመሆናችን አንጻር ወደ እኩይ ተግባሩ እንደማንገባ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን እናንተ የህክምና ባለሙያዎቹ ሁሉም ሰው መጠቀም የለበትም ትላላችሁ፤ ከበሽታው ያገገሙ እንደ ቻይና ያሉ አገራት ነዋሪዎች ደግሞ እንደ አንድ መከላከያ መንገድ ተጠቀሙ ይላሉና በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ወልደሰንበት፦ ግልጽ ነው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ጥቅም አለው፤ ነገር ግን መቼ ነው መጠቀም ያለብን የሚለውን ለይቶ ማወቅ ደግሞ ያስፈልጋል። አንድ አካባቢ ላይ ተነስቶ ስርጭቱ መላውን ማህበረሰብ የሚያጠቃልል ሲሆን ሁሉም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን መልበሱ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። አሁን ላይ ግን ማህበረሰቡ ላይ በተፈጠረው ነገር በየታክሲውና ሆቴሎች ውስጥ እንዲሁም ሌሎች ቦታዎች ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርገን መንቀሳቀሳችን ተገቢ አይደለም ።
ትንሿ ማስክ እኛን ከበሽታው አትከላከልልንም። አሁን ላይ በአላስፈላጊ ሁኔታ በየአካባቢው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መልበስ ለእኔ አንድ ወታደር ጠላት በሌለበት አቅጣጫ ከባድ መሳሪያ እየተኮሰ እንደማባከን ነው። ነገ ልበሱ በምንባለበት ጊዜ የማናገኛቸውን ነገሮች ዛሬ ላይ እያባከንን መሄድ ትክክል አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ጤና ባለሙያው የእርሱን ሙያዊ እርዳታ ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎችን በሚረዳበት ወቅት እንዲለብሰው ይመከራል።
አዲስ ዘመን ፦ ግን አንዳንዶች እንደሚሉት ለምሳሌ በትራንስፖርት ጉዞ ወቅት አጎናችን ያለው ሰው በምን ዓይነት የጤንነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ስለማናውቅ ነው የምንለብሰው ይላሉና ይህስ አያስኬድም?
ዶክተር ወልደሰንበት ፦ አሁን ላይ ሰዎች በዛ ብለው እንዳይሰበሰቡ ነው ትልቁ ምክራችን፤ የግድ ሆኖ ከተሰበሰቡ ደግሞ አንድ ሜትር ያህል ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ትራንስፖርትም ላይ ተራርቀው እንዲቀመጡ ነው እየፈለግን ያለነው እንጂ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርጉና ተፋፍጋችሁ ሂዱ የሚለውን አናበረታታም።
ይህንን ርቀት ሳንጠብቅ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረጋችን ብቻውን የእኛን በቫይረሱ የመያዝ ሁኔታ ይቀንሳል ለማለት አይቻልም።ይህ መሸፈኛ የሚጠቅመን ለአፍና አፍንጫችን ብቻ ነው ቫይረሱ ደግሞ በአይናችንም ሊገባ ይችላል፤ በመሆኑም ምልክቱ ያለው ሰው ለሌሎች ለመጠንቀቅ ብሎ ማድረግ ጥሩ ነው ግን ጤናማ የሆነ ሰው ምንም አይጠቅመውም።
ከዚህ ይልቅ ተጋላጭነትን መቀነስ፣ ርቀትን መጠበቅ የግል ንጽህናን መጠበቅ የግድ የሚል ነገር ሲሆን በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ መቀመጥ፤ መውጣት አለብን ካልን ደግሞ በእግራችን መጓዝን ብናዘወትር እነዚህን ግብዓቶች መጠቀም ትክክል የሚሆነው በበሽታው የተጠቃ ሰውን የምናስታምም ከሆነ ምልክቱ ከሚታይበት ሰው ጋር አብረን የምንኖር ከሆነ እራሱ ታማሚ ከሆነ ወይም ምልክት እየታየበት ካለ ነው። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የሚጠቅመው በሽታው ለሌሎች እንዳይተላለፍ ለማድረግ ነው እንጂትንሿ ማስክ እኛን ከበሽታው አትከላከልልንም።
አሁን ላይ በአላስፈላጊ ሁኔታ በየአካባቢው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መልበስ ለእኔ አንድ ወታደር ጠላት በሌለበት አቅጣጫ ከባድ መሳሪያ እየተኮሰ እንደማባከን ነው። ነገ ልበሱ በምንባለበት ጊዜ የማናገኛቸውን ነገሮች ዛሬ ላይ እያባከንን መሄድ ትክክል አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ጤና ባለሙያው የእርሱን ሙያዊ እርዳታ ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎችን በሚረዳበት ወቅት እንዲለብሰው ይመከራል።
አዲስ ዘመን ፦ ግን አንዳንዶች እንደሚሉት ለምሳሌ በትራንስፖርት ጉዞ ወቅት አጎናችን ያለው ሰው በምን ዓይነት የጤንነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ስለማናውቅ ነው የምንለብሰው ይላሉና ይህስ አያስኬድም?
ዶክተር ወልደሰንበት ፦ አሁን ላይ ሰዎች በዛ ብለው እንዳይሰበሰቡ ነው ትልቁ ምክራችን፤ የግድሆኖ ከተሰበሰቡ ደግሞ አንድ ሜትር ያህል ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ትራንስፖርትም ላይ ተራርቀው እንዲቀመጡ ነው እየፈለግን ያለነው እንጂ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርጉና ተፋፍጋችሁ ሂዱ የሚለውን አናበረታታም። ይህንን ርቀት ሳንጠብቅ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረጋችን ብቻውን የእኛን በቫይረሱ የመያዝ ሁኔታ ይቀንሳል ለማለት አይቻልም።
ይህ መሸፈኛ የሚጠቅመን ለአፍና አፍንጫችን ብቻ ነው ቫይረሱ ደግሞ በአይናችንም ሊገባ ይችላል፤ በመሆኑም ምልክቱ ያለው ሰው ለሌሎች ለመጠንቀቅ ብሎ ማድረግ ጥሩ ነው ግን ጤናማ የሆነ ሰው ምንም አይጠቅመውም። ከዚህ ይልቅ ተጋላጭነትን መቀነስ፣ ርቀትን መጠበቅ የግል ንጽህናን መጠበቅ የግድ የሚል ነገር ሲሆን በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ መቀመጥ፤ መውጣት አለብን ካልን ደግሞ በእግራችን መጓዝን ብናዘወትርበትራንስፖርት የምንሄድ ከሆነ ደግሞ ተጨማሪም ቢሆን ከፍለን አቅራቢያችንን ክፍት ማድረግ ብንችል ነው የሚመከረው።
አዲስ ዘመን፦ ጓንትስ? እሱም በአብዛኛው እየተጠቀምንበት ነውና በሽታውን ከመከላከል አንጻር ሚናው ምን ያህል ነው? ዶክተር ወልደሰንበት ፦ ይህ እንደውም ትክክል ያልሆነና ራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ተጋላጭነትን ከፍ የሚያደርግ ተግባር ነው። እኛ የህክምና ባለሙያዎቹ የምንመክረው ማንኛውም ሰው አዘውትሮ እጁን እንዲታጠብ ነው።
አሁን እየተደረጉ ያሉት ጓንቶች እኮ በሽታውን የሚያስተላልፉና አደራረጋቸውና አወላለቃቸውም ሳይንሳዊ መንገድን ያልተከተለ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን አብዛኛው ሰው እያደረጋት ያለችው ትንሿ ጓንት ለምንም የማትጠቅምና ከዛ ይልቅ ተጋላጭነትን የምትጨምር እንዲያውም እጃችንን ቶሎ ቶሎ እንዳንታጠብ የምታዘናጋ ናት። ጓንት ማድረግ ካለብንም ማድረግ ያለብን የቀዶ ጥገና ጓንት ነው እርሱንም ቢሆን በጣም ለአጭር ጊዜ ማድረግና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ማስወገድ ነው የሚገባን።
አሁን ለምሳሌ በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩና የሆቴል ቤት አስተናጋጆች ትንሿን ጓንት ቀኑን ሙሉ እጃቸው ላይ አድርገው ሰዎችን ሲፈትሹና ሲያስተናግዱ ይውላሉ ይህ ደግሞ ለበሽታው መተላለፊያ ጥሩ መንገድ ነው፤ በመሆኑም እባካችሁ ይህ ሁኔታ እናንተንም ሌላውንም ከኮሮና ቫይረስ አይጠብቅምና እጅን አዘውትሮ መታጠብ ይሻላል።
አዲስ ዘመን ፦ቀጣይ እንደ አገርና ህዝብ ለመዳን በምን መልኩ ነው መሰራት ያለበት? ከማንስ ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ወልደሰንበት፦ ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው፤ የሚጠቅመንም ይህ ነው። አብዛኛው ሰው ቤቱ ስለተቀመጠ የጤና ባለሙያው ተዋግቶ ሲጨርስ አሸንፎ ድሉን የሚያበስር መስሎ መታሰብ የለበትም፤ ሰው የሆነ ሰው ሁሉ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፤ አንድ ሰው እራሱን ከመጠበቅ ጀምሮ ለአገሩ በጉልበትም በገንዘብም በእውቀቱም ማድረግ የሚችለው ብዙ ነገር አለ።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ለምሳሌ ቻይና ላይ ሁሉን አቀፍ ማህበረሰብ የኮሮና ቫይረስ የመከላከልና ምላሽ ዘዴ ነው የተጠቀሙት፤ ይህ ማለት ኢንጂነሩ ፣ቴክኖሎጂስቱ፣ የደህንነት ሰዎች፣ ኢኮኖሚስቱም የስነ ልቦና ባለሙያውና ሌሎችም ባላቸው ሙያ ሁሉ ተሳትፈውና አስተዋጽኦ አበርክተው ነው በሽታውን በቁጥጥር ስር ማዋል የቻሉት።
ወደእኛ አገር ስንመጣም የጤና ባለሙያው፣መንግስት እንዲሁም የግል ድርጅቶች የሀይማኖት ተቋማትና ሌሎችም የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባ ቸዋል። በዚህ ልክ ተጋግዞ መስራት ካልተቻለ ወታደር የውስጥ ጉዳይ ሲኖር ድል ማድረግ እንደሚሳነው ሁሉ ጤና ባለሙያዎች፣ ተቋማትና ጤና ሚኒስቴር ማህበረሰቡ ካልደገፋቸው ብቻቸውን ውጤታማ የሆነ ሰርተው ቫይረሱን ድል መንሳት አይችሉም።
ምንም እንኳን የምንለያይባቸው አመለካከቶች ቢኖሩንም በዚህ ጊዜ መንግስትን የምንደግፍበት ጤና ተቋማትን የምናግዝበት ምን ልስራ የኔ ድርሻ የቱ ነው ብለን ተሳትፏችንን የምናሳይበት የአንድነት ጊዜ ሊኖረን ነው የሚያስፈልገው።
በመሆኑም በዚህ ልክ ሁሉም ሰው አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል፤ ማድረግም ይገባል። አሁን ላይ ለምሳሌ የጎዳና ተዳዳሪዎች ካሉበት ሁኔታ አንጻር ለኮሮና ቫይረስ በጣም ተጋላጭ ናቸው፤ ስለዚህ ለእነዚህ ልጆች ምን ይደረግላቸው፤ ቤትም ኖሯቸው ደግሞ ኑሯቸው ከእጅ ወዳፍ የሆኑ ሰዎችስ በምን መልኩ ነው መደገፍ ያለባቸው የሚለውን በማየትን ያለንን ርቀታችንን በመጠበቅ አካፍለን አብልተን አጠጥተን ብንቆይና ይህንን የችግር ጊዜ በጋራ ብናልፈው ነገ ለመመሰጋገን ትልቅ ምክንያት ይሆነናል። የግድ ይህንን ለማድረግ ህጎችና ፖሊሲዎች መቀረጽ የለባቸውም። እኛ ኢትዮጵያውያን ያካበትናቸው በርካታ እሴቶች ያሉን ታላላቆቻችን እንዲሁም በየእምነታችን ያሉ አባቶች የሚነግሩንን የምንሰማ በመሆኑ ይህንን በማዳበር ኮሮናን ማሸነፍ መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፦ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ወልደሰንበት፦ ለትብብርዎ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2012
እፀገነት አክሊሉ