
ከልጅነቱ ጀምሮ ነው ሩጫን የሚወደው:: የሚኖርበት አካባቢ ከከተማ ውጭ በመሆኑ ለጉዳይ ወደ ከተማ ለመሔድ ከፈረስ ይልቅ በእግሩ መሄድን ይመርጥ ነበር:: መሐመድ ከድር ‹‹ከፈረስ ይልቅ እኔ እፈጥናለሁ›› የሚል ብሂል ነበረው::
መሐመድ ከድር ትምህርት ከጀመረ ወዲህ እሱን የሚቀድም ጠፋ:: ከዚህ የተነሣ ሮቤና ጐባ የሚገኙ ት/ቤቶች እኔጋ ተማር እኔጋ ተማር እያሉ ያስቸግሩት ነበር:: ይህ በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድ ት/ቤት ወደ ሌላ ት/ቤት እንዳይሄድ ተደርጓዋል::
የመሐመድ ከድር ችሎታ በት/ቤት ብቻ አልቀረም፣ ከኢትዮጵያ ውጭ የሀገራችን ባንዲራ በዓለም አቀፍ አደባባይ ከሌሎች ሀብታም ሀገሮች በላይ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ ያደረገ ጀግና ነው:: የኢትዮጵያ ስምም ለመላው የዓለም ሕዝብ ጆሮ እንዲደርስ ካረጉ ጀግኖች ውስጥም ይጠቀሳል:: መሐመድ ከድር ከሌሎች ቀደምት አትሌቶች አደራ በመረከብ የአፍሪካ ወጣቶች እንዲነቃቁ አድርጓል::
ሻምበል መሐመድ ከድር በተለያዩ የዓለም፣ የአፍሪካና የሀገራችን ውድድሮች በመካፈል ከጓደኞቹ እነምሩፅ ይፍጠር፣ ቶሎሳ ቆቱ፣ እሸቱ ቱራ፣ ግርማ ወልደሐና፣ ብርሃኑ ግርማና ወዘተ… ጋር በመሆን ኢትዮጵያ በተለያዩ የውድድር ሻምፒዮኖዎች የሜዳሊያ ባለቤት እንድትሆን አድርገዋል::
በዓለም አቀፍ ውድድሮች በግሉና በቡድን አሸናፊ በመሆን በወቅቱም የሻምፒዮኖች ሻምፒዮን ለመባል በቅቷል:: በተለይም ዘጠነኛ የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ስፔን ማድሪድ ላይ መጋቢት 19 ቀን 1993 (እ.ኤ.አ 1981) ዓ.ም በተደረገበት ወቅት በመሐመድ ከድር የሚመራው ቡድን በለበሱት አረንጓዴ ሹራብ የሌላውን ሀገር አትሌቶች ጣልቃ ሳያስገቡ ሰብሰብ ብለው አንድ ላይ በመሮጣቸው አረንጓዴው ጐርፍ የሚል አድናቆት የሚፈጠር ስያሜ ሊያገኙ ችለዋል:: እስከ አሁንም የኢትዮጵያ አትሌቶች ስያሜ ሆኖ ቀጥሏል::
በዚህ ውድድር ላይ ከ43 አገሮች የተውጣጡ 228 አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን ውድድሩን የፈጸሙት የ27 ሀገር አትሌቶች ብቻ ናቸው:: ይህም የውድድሩን ከባድነት የሚሳይ ነው:: በወቅቱ ኢትዮጵያን በመወከል የተወዳደሩት ምሩፅ ይፍጠር፤ መሐመድ ከድር፣ ብርሃኑ ግርማ፣ እሸቱ ቱራ፣ ቶሎሳ ቆቱ ፣ ደረጀ ነዲ፣ ከበደ ባልቻ፣ ግርማ ወልደሐና ናቸው::
እነዚህ አትሌቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደሩበት በዚህ ውድድር ላይ ሲመሩ ቆይተው በዙር ስህተት ጨርሰናል ብለው ሲዝናኑ ውድድሩ አለመፈጸሙ ሲነገራቸው በዚህ አጋጣሚ ቀድመዋቸው የነበሩትን እንደገና ለመቅደም ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት መሐመድ ከድር በአሜሪካዊው ክሬግ ቫርጅን በሁለት ሰከንድ ተቀድሞ በ35:07 ደቂቃ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል:: ይህች ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ነበረች:: የፖርቺጋሉ ፈርናንዴ ማሜድ በ35:09 ደቂቃ በመግባት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሊሆን በቅቷል::
በአትሌቶቻን ስህተት የወርቅ ሜዳሊያው ከእጃችን ቢወጣም ብርሃኑ ግርማ 7ኛ፣ ደረጀ ነዲ 3ኛ ፣ ከበደ ባልቻ 14ኛ፣ ምሩፅ ይፍጠር 15ኛ፣ እሸቱ ቱራ 30ኛ፣ ግርማ ወልደሐና 32ኛ፣ ቶሎሳ ቆቱ 75ኛ በመውጣት ኢትዮጵያ በ81 ነጥብ በቡድን አሸናፊ እንድትሆን አድርገዋል::
መሐመድ ከድር ተወልዶ ያድገው በወቅቱ በባሌ ጠቅላይ ግዛት መንድዬ አውራጃ ሲናና ወረዳ ሂዱራ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በባሌ ሮቤ ከተማ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ጐባ ከተማ በሚገኘው በባቱ ተራራ ት/ቤት ነበር::
መሐመድ ከድር የ10ኛ ክፍል ተማሪ በነበረ ጊዜ የመላው ኢትዮጵያ ት/ቤቶች ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ ተዘጋጅቶ ነበር:: ባሌ ጠቅላይ ግዛት ደግሞ ሜዳሊያ ማግኘት ይፈልጋል:: ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች ግንባር ቀደሙ መሐመድ ከድር ነበር:: ይኸው ተስፈኛ አትሌት ለእሱ የመጀመሪያ የሆነችውን የብር ሜዳሊያ በማሳካት የትምህርት ቤቱን ሕልም እውን ማድረግ ችሏል::
“የዛሬ ጥጃ የነገ ኮርማ በበረት ይታወቃል”:: እንደሚባለው መሐመድ ከድር ገና ከጅምሩ ብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር:: ያኔም ሆነ አሁንም ብዙ ታዋቂ አትሌቶችን እያደነ የሚሰበስበው መከላከያ (መቻል) መሐመድ ከድርን በእጁ ለማስገባት የቀደመው አልነበረም::
ከዚህ የተነሣ መሐመድ ከድር በ1963ዓ.ም በ4ኛ ክፍል ጦር ተቀላቅሎ ለሥልጠና ወደ ነጌሌ ቦረና (የአሁንዋ ጉጂ) ነጌሌ አቀና:: ከአንድ ዓመት ሥልጠና በኋላ የተለያዩ ውድድሮች በሻምበል ደረጃ፣ በሻለቃና በብርጌድ ደረጃ መካፈል ጀመረ:: በ1964 ዓ.ም በተካሄደው የመላው ጦር ሠራዊት የስፖርት ውድድር የደቡብ ዕዝን በመወከል ተሳትፎ በ3ሺ እና በ5ሺ ሜትር 3ኛ በመውጣት የሁለት ብር እና የአንድ ነሐስ ሜዳሊያ በአንገቱ በማጥለቅ ጥንካሬውን አሳየ:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እንዲቀላቀል ምክንያት የሆነውም ይኼው ድል ነው::
ሻምበል መሐመድ ከድር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርናሽናል ወድድር ያደረገው በ1967 ዓ.ም በቻይና ሦስት ከተሞች ነበር:: የያኔዋ ፔክንግ በ5ሺ ሜትር፣ በቻንግቹ በ10 ሺ ሜትር 4ኛ፣ በሻንጋይ ደግሞ በ10ሺ 2ኛ በመውጣት የሁለት ብር ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ስሙን በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ማስመዝገብ ጀመረ::
በ1972 (እ.እ.አ በ1980) 22ኛው የሞስኮ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን ሻምበል መሐመድ ከድር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ለትንሽ በፊላንድ ታዋቂ አትሌት ካርሎስ ማንካንን ተቀድሞ ሦስተኛ ሊወጣ ቻለ:: ልዩነቱ የአንድ ርምጃ ነበር::
የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የወርቅ ሜዳሊያ በመሐመድ ከድር ዙሮቹን ማክረርና የሌሎች ሀገሮች አትሌቶች ማዳከም በመሆኑ ድሉ ሲነሳ አብሮ መሐመድ ከድር አብሮ ይነሳል:: በዚህ ውድድር መሐመድ ከድር ሦስተኛ ሆኖ የነሐስ ሜዳሊያ በማስገኘት መደነቁ ብቻ ሳይሆን ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር አንደኛ እንዲሆን የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነበር:: በዚህ ላይ የሻምበል ቶሎሳ ቆቱ 4ኛ መሆን በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: መሐመድ ከድር በአንድ ውድድር ላይ የቡድን ሥራ /Team work/ በመሥራት ከሱ የሚስተካከል በወቅቱ አልነበረም::
በ1974 ዓ.ም ጣሊያን ሮም ላይ በተደረገው 10ኛው የዓለም የሀገር አቋራጭ ላይ በሚያስደንቅ ሁኔታ በማሸነፍ በስፔን ማድሪድ በዙር ስህተት ያጣነውን ውጤት በጀግንነት አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያዋን በአንገቱ በማጥለቅ ቁጭቱን ተወጥቷዋል::
በዚህ ውድድር ላይ ታዋቂ አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን ያኔ በዓለም ላይ የሚታወቀው የአሜሪካ አትሌት አልቤርቶ ሳላዘር ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት “ማንም አትሌት ይካፈል የፈለገ ዶፍ ዝናብና በረዶ ይዝነብ እኔ ሮም የመጣሁት በውድድሩ ለመካፈል ብቻ ሳይሆን አንደኛ በመውጣት ለማሸነፍ ነው” ሲል ፎክሮ ነበር:: “አፍ ዳገት የለውም ሁሉንም ነገር ይናገራል” እንደሚባለው ሳላዘር ቢፎክርም በሥራ መተርጐም አልቻለም:: በ3:90 ደቂቃ በመሐመድ ከድር ተቀድሞ ሁለተኛ ሆኖ ቃሉ ሳያከብር ወደ ሀገሩ ተመልሷል::
‹‹መሐመድን ለማሸነፍ አንድ ዙር ሲቀር መውጣት ነበረብኝ ለመቅደምም ጥረት አድርጌ ነበር:: ታዲያ ምን ያደርጋል ከኔ በላይ ጠንካራ ስላጋጠመኝ መቅደም አልቻልኩም::›› በማለት የመሐመድ ከድርን ጥንካሬ ለማረጋገጥ ችሏል:: በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ በማስገኘት መሐመድ ከድር የመጀመሪያ አትሌት ያደርገዋል፣፡ በዚህ ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወቅቱ ኢትዮጵያ በተከታታይ ለ5 ዓመታት በቡድን አንደኛ ስትሆን ይህንን ውጤት ካስገኙት መካከል መሐመድ ከድር አንዱ ነበር::
በ1973 ዓ.ም መጋቢት ወር ውስጥ ለ26 ቀናት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች 22 ዋንጫዎች ተገኝተዋል:: ከተገኙት ዋንጫዎች ውስጥ አራቱ ዋንጫዎች በቡድን የተገኙ ሲሆን በይበልጥ ዋንጫዎችን ያስገኘው ሻምበል መሐመድ ከድር መሆኑን ታሪክ አይረሳውም:: እሸቱ ቱራ፣ ቶሎሳ ቆቱና ከበደ ባልቻ እያንዳንዳቸው በግላቸው ሦስት ሦስት ዋንጫዎች አስገኝተዋል:: ደረጀ ነዲና ብርሃኑ ግርማ ደግሞ ሁለት ሁለት፣ ምሩፅ ይፍጠር አንድ ዋንጫ በማስገኘታቸው የታሪክ ተቋዳሾች ናቸው::
መጋቢት 26 ቀን 1974 ዓ.ም በጣሊያን ሚላን ከተማ በተካሄደው ግማሽ ማራቶን በወቅቱ የዓለማችን ታዋቂ አትሌት የነበረው አውስትራሊያዊው ሮበርት ዲካስቴላን ከማሸነፉም በላይ በወቅቱ የዓለም ሪከርድን መቆጣጠር ችሎ ነበር:: በዚህ ውድድር ታዋቂው አትሌት ሻምበል እሸቱ ቱራ የዘመኑ ታዋቂ አትሌት በመባል ከወቅቱ የጣሊያን ፕሬዚዳንት እጅ ልዩ ሽልማት በመቀበል ኢትዮጵያን የበለጠ ታዋቂ የአትሌት ሀገር መሆኑን አረጋግጠዋል::
ሻምበል መሐመድ ከድር በ1973 ዓ.ም ጣሊያን ሮም ላይ በተደረገው 3ኛ የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ ላይ በመካፈል በ27:37:44 በአንድ ርምጃ ተቀድሞ ሁለተኛ በመሆን ለአፍሪካ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል:: ይህ ሰዓት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሪከርድ በመሆን ተመዝግቧል:: ሻምበል መሐመድ ከድር በተለያዩ የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ በመካፈል ለሀገሩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካንም ስም በዓለም አደባባይ በማሳወቅ ድርብ ድል ያስመዘገበ ጀግና ነበር::
በጥቅምት ወር 1975 ዓ.ም በተካሄደው ዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር በጊኒ ኮናክሪ ከተማ በተደረገው ጉባኤ ላይ መሐመድ ከድር የ1974 ዓ.ም የዘመኑ የአፍሪካ ኮከብ አትሌት ተብሎ ከመመረጡም በላይ የሻምፒዮኖች ሻምፒዮን የሚል ስምም አግኝቶ ነበር::
ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ በወቅቱ የዛየር ፕሬዚዳንት ሞቡቱ ሴሴኮ ስም ተሰይሞ ይሰጥ የነበረውን የምርጥ አትሌቶች የዋንጫ ሽልማት ሰኔ 2 ቀን 1975 ዓ.ም ተሸልመዋል:: እንደዚህ ክብር ከተሰጣቸው መካከል የክለቡ ጓደኛና የልብ ወዳጁ እሸቱ ቱራም ይገኝበት ነበር::
ሻምበል መሐመድ ከድር ውድድሩን ካቆመ በኋላ የክለቡ የመቻል (ምድር ጦር) የቴክኒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈፃሚ አባል በመሆን አገልግሏል:: የመንግሥት ለውጥ በ1983 በመደረጉ ምክንያት የሠራዊቱ የስፖርት ክለቦች ሲፈርስ የሻምበል መሐመድ ከድርና ጓደኞቹ ዕጣ ፋንታ መበተን ሆነ:: በኋላ በተደረገው የባለሙያ ድልድል በኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን የጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሆን ተመድቦ በዚያው ቡድኑን ይዞ ወደ ውጭ ከወጣ በኋላ አልተመለሰም::
ሻምበል መሐመድ ከድር በውድድር በቆየባቸው ዘመናት በሀገር ውስጥ፣ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአሜሪካና አውሮፓ በማሸነፍ ወደ 300 የሚጠጉ ሜዳሊያዎችና ከ20 በላይ ዋንጫ፣ ጦርና ጋሻ ተሸልሟል:: ይህ አትሌቲክ ባለውለታ እና ጀግና መሐመድ ከድር በአሁኑ ሰዓት በስዊዘርላንድ ኑሮውን እየገፋ ነው::
ተሾመ ቀዲዳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም