ከዝቅተኛ ስራና ትንሽ ንግድ ተነስተው ወደ ከፍተኛው የኢንቨስተርነት ማማ መዝለቅ ችለዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት መኮንን ነበሩ። ሠራዊቱ በ1983 ሲበተን ሰርቶ ለማደር ያደረጉት ፈታኝ ግብግብ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ቢያልፍም ከራሳቸው አልፈው የዜጎችና የሀገር ፈርጥ ለመሆን በቅተዋል። በቀን 4 ብር ብሎም በወር 75 ብር ተቀጥረው ሰርተዋል። በቅቤና ማር ንግድ፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና ዘርፎች፣ በአስመጪና ላኪነትም ሰርተዋል። ጨውና ሌሎች ሸቀጦችን ከአዲስ አበባ ወደ ክልል እንዲሁም ከክልል ደግሞ የግብርና ምርቶችን ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ ነግደዋል።
ሥራቸውን ለማሳደግ ሲሉ የእናታቸውን ቤት ለባንክ በማስያዝ የተበደሩት 30 ሺ ብር ንግዳቸውን ይበልጥ አሰመረላቸው። በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች አልፈው ደረጃ በደረጃ ወደ ታላቅ ኢንቨስተርነት ተሸጋግረዋል ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ። አቶ በላይነህ ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፉ በመጀመሪያ የተሰማሩት በ2005 ዓ/ም ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሁለት አሮጌ ሆቴሎችን ገዘተው ነው።
የአዲስ አበባውን የኢትዮጵያ ሆቴልና የአዳማውን የራስ ሆቴል። ከዚያም በመቀጠል በቤንች ማጂ ዞን እርሻ ፤ በኦሮሚያ ክልል ገላን አካባቢ እንዲሁም የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በታጠቅ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ውስጥ መሰረቱ። በትንሽ ሥራ አዲሱን የሕይወት ግብግብ የጀመሩት ባለሀብቱ አሁን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎቻቸው ለ3 ሺ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል።
ባለሀብቱ የኢትዮጵያ ሆቴልን ወደ 46 ፎቅ ለማሳደግ ራዕይ ነበራቸው። ‹‹ሰው በኪሱ ገንዘብ ባይኖረውም ጥሩ ራዕይ ካለው ከባንኮች ተበድሮ ይሰራል›› የሚሉት አቶ በላይነህ፣ ‹‹46 ፎቅ እሰራለሁ ስል ከኪሴ የሚመነዘር ዶላር አለኝ ብዬ አልነበረም›› ይላሉ። ይሄንን ግዙፍ ራእይ ይዘው ሲነሱ አጋሮችን አቅፈው አቅማቸው የሚችለውን ያህል ለማድረግ በማሰብ ገንዘብ አዘጋጅተውም ነበር። ይሁንና ‹‹ቦታችን ለማስፋፊያ ተሰጠብን›› ያሉ ወገኖች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህ ሰዎች እሳቸው ሳያውቁ ክስ ይመሰርቱባቸዋል።
ይህን ሲረዱም ለልማቱ ያዘጋጁትን ገንዘብ ለዘይት ፋብሪካ፣ ሆቴሎችና እርሻ ኢንቨስትመንቶች ያውሉታል። እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተሻለ መስራት ሀገር ያሳድጋል የሚል አቋም ያላቸው ባለሀብቱ፣ ሆቴሉን አፍርሰው በአዲስ ለመገንባት ያሰቡት ሀገር ያቀናል ብለው አስበው እንጂ ኢትዮጵያ ሆቴል በወቅቱ በወር ከፍተኛ ገንዘብ እያስገኘ ነበር። አፍርሶ መገንባት በጣም አዋጪ እንዳልሆነ ቢረዱም በወቅቱ ሀገር ለማልማት ካላቸው ጽኑ እምነት በመነሳት ነው ራእዩን የሰነቁት።
ሆቴሉ በአዲስ መልክ ቢገነባ በስራ ላይ ካሉት ሠራተኞች በተጨማሪ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል የሚል ጽኑ እምነትም ነበራቸው። ባለሀብቱ ከወቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ጋር በኢትዮጵያ ሆቴል ጉዳይ ላይ ተነጋግረዋል። ከንቲባው ሆቴሉን አፍርሰህ ለመስራት የምትገዛ ከሆነ ጥሩ ነው ፤ አለበሊዚያ በዚህ አይነት ሁኔታ ከተማ መሀል ልትቀመጥ አትችልም ብለዋቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ይህን የከንቲባውን አቋም የተረዱት ባለሀብቱ ሆቴሉ ታሪካዊ ይዘቱ ሳይናጋ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ማሰብ ይጀምራሉ። ፕሮጀክቱ ገና በሂደት ላይ እንደሆነም ነው የሚናገሩት። ውሳኔ ያገኛል ብለውም እየጠበቁ ናቸው። የቦታውንና የቤቶቹን ዲዛይን እዛው ላይ አስቀምጦ ወደ ላይ ማሻሻል እንደሚቻል ነው የሚገልጹት። ‹‹በቴክኖሎጂ በመታገዝ ይህን ማድረግ ይቻላል፤ ለሁሉም በጉዳዩ ዙሪያ እንወያይበታለን። አሁንም በስሜ ሊዝ እየተከፈለበት ነው›› ይላሉ። የባለሀብቱ ሌላው ኢንቨስትመነት የዘይት ፋብሪካ ነው።
ሀገራችን እስከ አሁን ምንም አይነት የምግብ ዘይት ማጣሪያ (ሪፋይነሪ) የላትም ማለት ይቻላል። 110 ሚሊዮን ሕዝብ ይዘን ከ50 ቶን እስከ 75 ቶን ብቻ ዘይት ነው የሚጣራው ሲሉ ይገልጻሉ። እሳቸው ቡሬ ከተማ እያስገነቡት የሚገኘው የዘይት ፋብሪካ ማምረት ሲጀምር ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የምግብ ዘይት ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በራሷ ምርት መሸፈን ያስችላታል። ግንባታው ሰኔ 2006 ዓ/ም የተጀመረው ይህ ፋብሪካ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ አሁን ወደ መጨረሻው ምእራፍ ደርሷል። 95 በመቶ ተጠናቋል።
‹‹ፋብሪካው ስራ ሲጀምር በአመት 500 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ያመርታል። ይህንን ለ365 ቀናት ማካፈል ነው፤ በቀን 1 ሺ 400 ቶን ማለት ነው። ከሁለት ሺ እስከ ሶስት ሺ ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ እድል ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል›› ሲሉ ባለሀብቱ ያብራራሉ። ፋብሪካው ለኢትዮጵያ ህዝብ በሚፈልገው መጠንና አይነት ጥራቱን የጠበቀ ዘይት ያቀርባል። ‹‹እስከ አሁን ሰሊጥ በጥሬው ወደ ውጭ እየላክን ውጤታማ ሆነናል። አሁን ዘይት ለማምረት የሚያስችል በዓለም አንደኛውን ቴክኖሎጂ (የአውሮፓ ማሽነሪ) አስገብተናል።
ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ የምንልከው ያለቀለት የታሸገ የሰሊጥ ምርት ነው፤ ዋጋ ተደራድረን እንሸጣለን›› ሲሉ ያብራራሉ። የሀገሪቱ ሰሊጥ ወደ ቻይናና እሥራኤል ተልኮ እነሱ አዘጋጅተውት ለሌላው ዓለም ሲሸጥ ቆይቷል። አሁን በሀገራችን ከእነዚህ ሀገሮች ቴክኖሎጂ የተሻለ ቴክኖሎጂ በፋብሪካው ተተክሏል። ምርቱም ለአፍሪካ፣ ለአውሮፓ፣ ለቻይና፣ ለጃፓንና ለሌሎችም መሸጥ ይጀመራል። ፋብሪካው የተገነባው የኢንዱስትሪ መንደር በሚባል ደረጃ ነው። በአንድ ጊቢ ውስጥ 7 ፋብሪካዎች ተተክለዋል።
ከእነዚህም መካከል የካርቶን እና የሳሙና ፋብሪካ ይገኙበታል። ከዘይት ተረፈ ምርት ካርቶንና ሳሙና ይመረታል። የአትክልት ቅቤም እንዲሁ ከተረፈ ምርቱ ይመረታል። የፊሊንግ ጀሪካን ፋብሪካ አለ። እስከ አሁን ወደ ሀገሪቱ የሚገባው የታሸገ ዘይት ብቻ ነው። አሁን ድፍድፉ ብቻ እንዲመጣ ይደረግና እዚሁ ይጣራል። ባለሀብቱ በፈለገው መጠን ፓልም ኦይል፤ ሰን ፍላወር ፣ ሶያ ቢን እየተመረተ 80 ብር ሲሸጥ የነበረው ዘይት በ 50 እና 60 ብር እንዲሸጥ በማድረግ መካከለኛ ኑሮ ለሚመራው ሕዝብ ዋጋው ዝቅ እንደሚደረግለት ይጠቁማሉ።
ዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖረው ሕዝብ ደግሞ የሚችለውን በትኩሱ እዚሁ ተጣርቶ እንዲጠቀም ይደረጋል ይላሉ። ‹‹በምንፈልገው ደረጃ አቅማችን በቻለው መንገድ ከውጭም የዘይት ድፍድፍ እናስመጣለን። በሀገር ውስጥ ድፍድፉ ቢኖር ከውጭ ማምጣት አይጠበቅብንም ነበር›› በማለትም ለፋብሪካው የሚውል ግብአት ችግር እንዳለም ያመለክታሉ። በሀገር ውስጥ የሚመረተው ግብአት በቂ አይደለም።
ይህ ግብአት ለፋብሪካው ከሚያስፈልገው 10 በመቶውን እንደማይሸፍን አቶ በላይነህ ይገልጻሉ። የዘይት ፋብሪካው ፕሮጀክት ብቻ 20 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህል ይፈልጋል። የሀገራችን ገበሬ የቅባት እህል በበቂ መጠን አያመርትም። አካባቢው ትርፍ አምራች ቢሆንም፣ ለፋብሪካው የሚያስፈልገውን 20 ሚሊዮን ኩንታል ማሟላት አይችልም። ይህን ችግር ለመፍታት ባለሀብቱ ከአርሶ አደሩ ጋር ለመስራት ሀሳቡ አላቸው። ከአርሶ አደሮች ጋር በመተጋገዝ ተጨማሪ የአኩሪ አተር፤ የኑግ፤ የጎመን ዘር ሁሉም የቅባት እህሎች በስፋት እንዲያመርቱ ለማበረታታት እንሰራለን ሲሉ ይገልጻሉ። ‹‹የፋብሪካው በአካባቢው መከፈት አርሶ አደሩን በከፍተኛ ደረጃ ለስራ ያነሳሳል፤ ትርፋማ ያደርገዋል›› የሚሉት አቶ በላይነህ፣ ይህም የዘይት ምርቱን ለሕብረተሰቡ በሚገባ ለማድረስ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት። ተረፈ ምርቱ አንድ ስራ እንደሚሆንም ይገልጻሉ። በዚህም ከብት እርባታ እና ማድለብ ለሚያካሂዱ፣ ለዶሮ መኖ፤ ለወተት ልማት ሁሉ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው፣ በእነዚህ ሁሉ በኩልም ሌላ ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠቁማሉ። አቶ በላይነህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከተሰማሩባቸው ዘርፎች ሌላው የተሸከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ነው። ይህ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ የሚገኘው ፋብሪካ ከባድ ተሳቢ እና ትናንሽ መኪኖች እንዲሁም አውቶቡስ ይገጣጥማል።
የመኪኖቹ አካላት በኮንቴይነር ከአውሮፓ እንዲመጡ ተደርጎ ነው ሀገር ውስጥ የመገጣጠሙ ስራ የሚካሄደው። ፋብሪካው ሁለት ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን አውቶቡሱ የሚገጣጠመው በቢኬ (በላይነህ ክንዴ) ሜታል ኢንጂነሪነግ አማካይነት ሲሆን፣ በቅርቡም ስራ ይጀምራል። ባለሀብቱ ሌሎች ኢንቨስትመንቶችም አስበዋል። በባህር ዳር ሒልተን ኢንተርናሽናል ሆቴል ለመገንባት፣ የአዳማ ራስ ሆቴልን ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ባለአራትና አምስት ኮከብ ሆቴል ለማድረግ ሃሳቡ አላቸው።
በእርሻ ኢንቨስትመንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመሰማራት 7ሺ ሄክታር መሬት ተሰጥቷቸዋል። ከውጭ አልሚዎች (አውት ግሮወርስ) ጋር በመሆንም በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ለፋብሪካው የሚያስፈልገውን የቅባት እህል ምርት የበለጠ ለማሳደግ አቅደዋል። በቤንች ማጂ ዞን የቡና እና የሰሊጥ እርሻ አላቸው። የግብርና ኢንቨስትመንት እርሻዎቻቸውን በማበልጸግ ለኢንዱስትሪ የሚውሉ ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚሰሩ የሚናገሩት ባለሃብቱ፣ ‹‹ዘይት ሙሉ በሙሉ በሀገራችን ተመርቶ ለሕዝቡ ያለችግር የሚደርስበትን መስራት ከእኛ ይጠበቃል›› ይላሉ።
ባለሀብቱ የጠቀሷቸው ፕሮጀክቶች ስራ ሲጀምሩ ለ3000 ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ። ይህ ሲሆን አጠቃላይ የሰራተኞቹ ብዛት ወደ 5000 ይደርሳል። ድርጅታቸው በአፍሪካ ታዋቂና ቀዳሚ ለሌሎችም አርአያ እንዲሆን ተግተው ይሰራሉ። በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ሌሎች 5000 ሠራተኞችን የሚቀጥሩ ፕሮጀክቶችን ለመስራት አስበዋል። ‹‹በአቅሜ 10ሺ ኢትዮጵያውያን ሰርተው እንዲኖሩ ማድረግ ትልቁ አላማና ምኞቴ ነው። ከዚያም ወደ ጡረታ መግባት ነው›› ሲሉ ገልጸዋል። አቶ በላይነህ ክንዴ የማኑፋክቸሪንግ የስራ ዘርፍ ከባድ መሆኑንም ያስገነዝባሉ። ‹እንደ እሳቸው ገለጸ፤ ዘርፉ እንደ ትሬዲንግና አገልግሎት ዘርፍ ቀላል አይደለም።
ማሽኑን አስመጥቶ ተክሎ ስራ ማስጀመር በራሱ ከባድ ፈተና ነው። ስራው ከተጀመረ በኋላም የኃይል፣ የፋይናንስና የመሳሰሉ አቅርቦቶች ሰፊ ችግር ይስተዋልባቸዋል። ባለሀብቶች እዚህ ፈተና ውስጥ መግባት አይፈልጉም፤ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹አብዛኞቻችን ለራሳችን ነው የምናስበው፤ ይሄ ስህተት ነው›› ሲሉ ያስገነዝባሉ። ‹‹እኔ ክትፎ መብላት ሲያስፈልገኝ ሌላውም ሰው የሚፈልገውን አግኝቶ መብላት አለበት።
አለበለዚያ መኖር አንችልም›› ይላሉ። ባለሀብቱ የስራ እድል መፍጠር፤ ስራዎች እንዲሰፉ፤ ዜጎች የስራ እድል እንዲያገኙ መታገል፤ ሀገሪቱ መሰረታዊ ለውጥ እንድታመጣ መትጋት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ። ‹‹ሀገሪቱ የመሪዎች ብቻ አይደለችም፤ የእኛም ነች፤ በአጠቃላይ የ110 ሚሊዮን ሕዝብ የጋራ ሀገር ናት›› በማለት ያብራራሉ። ሁላችንም በጋራ ተረባርበን ሀገርን የመጠበቅ፣ የማልማት፣ የማሳደግ ከፍተኛ ኃላፊነትና ግዴታ አለብን የሚሉት ባለሀብቱ፣ በታሪክ አጋጣሚ ሀብት የፈጠረ ዜጋ ሁሉ ብዙ ሰው ሊቀጥር በሚችል መስክ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ነው የሚናገሩት። ‹‹በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግስት እንዲደግፈን በማድረግ ጠንክረን ካልሰራንና ወጣቱ ሰርቶ እንዲኖር ካላደረግነው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፤ ለእዚህም ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ በመስራት የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት አለብን ሲሉ ይገልጻሉ። እሳቸው የሚታያቸው ወደ ማኑፋክቸሪንግ፤ ዘመናዊ እርሻ (አግሪካልቸር) ሌሎች በርካታ የሰው ኃይል ሊቀጥሩና ከፍተኛ ሀብት ሊያመነጩ ወደሚችሉ በሀገር ደረጃ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጡ ወደሚችሉ ትላልቅ ስራዎች መግባት ነው።
ከተማ ውስጥ ፎቅ እየሰሩ መኖር ከራስ አልፎ ለሀገርና ሕዝብ አይጠቅምም ይላሉ። ለወጣቱ የስራ እድል ሳንፈጥር ለራሳችን በመኖር ብቻ ሀገር ተረጋግታ ልትቀጥል እንደማትችልም ነው የሚያስገነዝቡት። መንግስት ኢንቨስተሮችን ሊያበረታታ እንደሚገባም ባለሀብቱ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሥራት ትልቁ ችግር ባለሀብት እንዲበረታታ አለመደረጉ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት በሥራ ሳይሆን በቅርበት የመመዘን ችግር ይስተዋልበት እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
‹‹ማህበረሰቡ ነጋዴ ሌባ ነው የሚል አመለካከት እንዲይዝ ተደርጎ ሁሉንም በጅምላ የመፈረጅ ችግር ይታይ እንደነበርም ነው የሚገልጹት። መንግስት ስህተቶቹን ሁሉ በነጋዴው ላይ አያላከከ እንዲሁም የዋጋ ንረት በተፈጠረ ቁጥር ነጋዴው ያመጣው ነው ይል ነበር ሲሉ ይጠቁማሉ። እንደ እሳቸው ገለጸ፤ አጭበርባሪውንና ለፍቶ አዳሪውን፣ በአግባቡ እየሠራ ካለው ለይቶ አለማየት፣ ትክክለኛ መመዘኛዎች አለመኖር፣ መመዘኛዎቹ ሲኖሩም ከቅርበት የመነጩ መሆናቸው የመንግስት መሰረታዊ ችግሮች ነበሩ።
ኢንቨስተሩን የሚያበረታቱም የማያበረታቱም ሁኔታዎች እንደነበሩ ጠቅሰው፣ እነዚህ ሁኔታዎች ግን ኢንቨስተሩን እንደማያበረታቱ ይጠቅሳሉ። ‹‹ኢንቨስተር መሆን ሁልጊዜ በስጋት መኖር ነው፤ በመስራትህ፤የሥራ እድል በመፍጠርህ ፤ሠርተህ በመብላትህ ችግር አለ›› ይላሉ። አንዳንዱ የመንግስት አሰራር የሚያበረታታ ነው ሲባል የማያበረታታ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ።
ሁሉንም የድርጅታችንን ሰራተኞች ተቆጣጥረን አንችልም ሲሉ አመልክተው፣ ይህን አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ አንድ የድርጅታቸው አሽከርካሪ የ15 ሺህ ብር ኮንትሮባንድ እቃ በመኪና ጭኖ መያዙን፣ በዚህ የተነሳም መኪናቸው ተወርሶ መሸጡን ይገልጻሉ። ‹‹መኪናው የእኔ እንጂ ተቀጥሮ የሚሰራው ሾፌር አይደለም›› ሲሉ ገልጸው፣ ይህን አይነቱን የመንግስት እርምጃ አስገራሚ ሲሉ ነው የጠቀሱት። ‹‹ዞሮ ዞሮ ዓለም የፈተናዎች ምንጭ ናትና ያንን ፈተና ታግሎ ያሸነፈ ወይም ዕድል የቀናው ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። እኛ ታግለን ከእግዚአብሄር ጋር እዚህ ደርሰናል›› ይላሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
ወንድወሰን መኮንን