መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተሾሙ።ቃለመሀለ ፈጸሙ።በብዙዎች ዘንድ “ታሪካዊ” የተባለ እና ኢህአዴግን አምርረው የሚጠሉት ወገኖች ጭምር በአድናቆት ለጭብጨባ እጃቸውን ከፍ ያስደረገ ንግግርም አደረጉ።
የንግግሩ ጭብጥ ሲታወስ
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ንግግር አንዳንድ ነጥቦችን እናስታውስ፡፡
ከኤርትራ መንግሥት ጋር እርቅ ለመፍጠር ጥሪያቸውን ያቀረቡት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዩ ተቃውሞዎች ሰበብ ህይወታቸው ለተቀጠፉ ግለሰቦች ይቅርታን መጠየቅ፣ በአገሪቱ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችን እንደ ተፎካካሪ ማየትና ማሳተፍ፤ የጋራ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ መኖር አስፈላጊነት በንግግራቸው ከጠቀሷቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።
በዶክተር አብይ የሹመት ንግግር ውስጥ፤ ይቅርታ፣ እርቅ፣ ካሳ፣ ዲያስፖራ፣ ኤርትራ፣ ሙስና፣ ተቀናቃኝ ኃይሎች፣ የባከነ እድል፣ ስለ ዘረኝነት በሽታ እና የኢትዮጵያ ታላቅነት ተነስተዋል።
“በቅጡ ሳይቧርቁ ሕይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ለሥነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡
በተለያየ ጊዜያት መስዋዕትነትን ለከፈሉ፤ የመብት ተከራካሪዎች እና የፖለቲካ ሰዎች ለደረሰው ጉዳት፣ ለፈሰሰው ደም እና ለጠፋው ህይወት፤ ይቅርታ ብቻ ብለው አላለፉም። ለተፈጠረው ችግር እልባት፤ ለተበደለ ወገን ደግሞ ካሳ እንደሚከፍሉም ተናግረዋል። “ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው!” ማለታቸው ራሱ ንግግራቸውን በተግባር ለመተርጎም ያላቸውን ቁርጠኝነት አጉልቶ ያሳየናል። የመርህ እና የእምነት ሰው ናቸውና፣ ይህንን ለማድረግ እንጂ ለማለት ብቻ አልተናገሩትም።
ከየት ጫፍ ተነስተው የት ጫፍ ላይ እንደደረሱ ለተመለከቷቸው ሁሉ፤ ከአንደበታቸው የወጣው ይህ ቃል ምን ያህል በተግባር ሊመነዘር እንደሚችል ይገምታሉ።
አገሪቷን ሸብቦ የያዛት የዘረኝነትን በሽታ እናጥፋ ብለዋል። “ማንነታችን የተሳሰረ፣ የተጋመደ እና የተዋሃደ ነው” ይላሉ። ይኸችን አባቶቻችን በደማቸው የቆዩዋት ኃያል አገር ወደ ቀደሞዋ ታላቅነትዋ እንመልሳት፤ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ታሪክ አለን ብለው ሲናገሩ ለሚሰማ ሰው እውነትም ይህ ሰው ሊመራኝ ይገባል ማለቱ እንግዳ አይሆንም። ይኸ በእኛ ዘመን አልተለመደማ!
ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ለመገንባት የህዝብ ፍላጎት እና ይሁንታ ያለው መንግሥት መመስረት እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል። ተቀናቃኝ ያሉዋቸውን የተቃዋሚ ኃይሎችም ጥሪ አቅርበዋል። ለአገሪቱ ባይተዋር ሳይሆኑ የለውጡ አካል እንዲሆኑ ጋብዘዋል።
የሰው ልጆች ነጻነት ከመንግሥት የሚቸር ስጦታ ሳይሆን የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘው ጸጋ እንደሆነ መናገራቸው ስለ ፕሬስ ነጻነት መቆማቸውን ይጠቁመናል።
ከዲያስፖራ ጋር ያለው የሻከረ ግንኙነት ጠፍቶ ዲያስፖራውም በሂደቱ እንዲሳተፍ ተማጽነዋል። ያለፈውን ምዕራፍ ዘግተን በአዲስ ምዕራፍ እንጓዝ ሲሉ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ጠርተዋል። ጽንፈኛ ብሎ የሚሳደብ እንጂ፤ ይቅር እንባባል የሚል ልብ የሚነካ ጥሪ ከየትኛውም መሪ አልሰማንም። “ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ” ብሎ የተናገረ መሪ እስካሁንም አላየንም። “ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች” ብሎስ የተናገረ የኢህአዴግ ሰው መች ተሰምቶ ይታወቃል።
ከኤርትራ መንግሥት ጋር ስለሚኖረው እርቅ እና ሰላም እቅድም ጥቅሰዋል። ሁለቱ አገር ህዝቦች በደም የተሳሰረ መሆናቸው እና ለክልሉ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ለኤርትራ መንግሥትም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ የለውጥ እድል እንደነበራት እና በአመራር ድክመት ሳቢያ እነዚህ እድሎችዋን ሳትጠቀም መቅረትዋን ብቻ አልነበረም የተናገሩት፤ እሳቸውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያመጣውን ይህንን እድልም ይጠቅሳሉ። የንግግራቸው ቁልፍ ይህ ይመስላል። ይህ እድል እንዳያመልጥ የሚል ይመስላል። ብሄራዊ መግባባትን ፈጥሮ ሁሉን ያቀፈ ፍትሃዊ ስርዓትን መመስረት።
ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተረከበው ይኸ የሥልጣን ሽግግር ከጊዜው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በህዝብ ፍላጎት የሚገዛ፤ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባ መሆኑን አብስሮናል።
የዶክተር አብይ ንግግር ፓርላማው ለመጥራት እንኳ ይቀፈው በነበረው ኢትዮጵያዊነት ጀምሮ በዚያው ነው የጨረሰው። “ኢትዮጵያ የሁላችን ቤት ናት። ልዩነት እርግማን ሳይሆን በረከት ነው” ብለዋል፡፡
በርግጥ ይህ የሥልጣን ሽግግር ብዙ የተከፈለበት የህዝብ ትግል ውጤት መሆኑ ባይዘነጋም፣ መላው ሕዝብ በእኝህ መሪ ደስተኛ መሆኑ ከፈጣሪ የመጣ ተዓምር ነው ያሰኛል።
ዓለም በስጋት እና በጉጉት እየጠበቀው ያለው ይህ የለውጥ ሽግግር በተግባር ሲተረጎም ፈተናዎች ሊገጥሙት ይችላል። የሁሉም ድጋፍ ሲታከልበት የተሳካ ለውጥ እንደሚመጣ እርግጥ ነው። የቀድሞው ወዳጃቸው፣ ኸርማን ኮኸን በትዊተር ለዶክተር አብይ በላኩት መልዕክት “አይዞህ ሥራህን በድፍረት ሥራ፤ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ካንተ ጋር ነው” ብለዋል።
የሹመት ንግግር በተናጋሪው መጻኢ ዘመን ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የኦባማ ንግግር በተግባር ባይተረጎምም ብዙዎችን ልብ ገዝቶ ነበር። ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በቀዝቃዛው ጦርነት ሰሞን ምዕራብ በርሊን ተሰብስቦ ለነበረ ህዝብ Ich bin ein Berliner በርሊናዊ ነኝ፤ ሲሉ በመናገር የመላ ጀርመንን ልብ ሰልበው እንደነበርም ታሪክ ያወሳል። ይህን ያሉት ኮሚኒዝምን ለመምታት እንጂ ለሕዝበኝነት አልነበረም።
የዶክተር አብይ ንግግር የሕዝብን ልብ ለመግዛት የሚደረግ ቢሆንም ይህ ክፋት የለውም። የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ … በቃሉ የሚኖር ሰው ከአነሳሱ ያስታውቃል።
ኹለት ዓመቱ እንዴት አለፈ?
ያለፉት 731 ቀናት ስኬታማ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ከባድ ፈተና የተደቀነበት ወቅቶችንም አሳይቶን አልፏል።የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ቁርጠኛ እርምጃ ተከትሎ በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ተደርጓል።በእስር ላይ የነበሩ የፖለቲካኛ የህሊና እስረኞች፣ ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ሆኗል።አገር ውስጥ መግባት ተከልክለው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች እንዲሁም ስመጥር ሰዎች፣ አክቲቪስቶች በነጻነት ወደአገራቸው እንዲገቡ በር ከፍቷል።ተቀማጭነታቸው በውጭ አገር የነበሩና በአገር ውስጥ እንዳይታዩ ተከልክለው የነበሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ የኢንተርኔት ድረገጾች ከአፈና እንዲላቀቁ አድርጓል።የፕሬስ ነጻነቱ አንጻራዊ በሆነ መልኩ መሻሻል በማሳየቱ አዳዲስ የሕትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከኤርትራ ጋር ሁለት አሥርት ዓመታት የዘለቀው ቁርሾ በእርቅ መደምደሙ ዓለምን ጭምር በአድናቆት አፍ ያስከፈተ እርምጃ ነበር።ከምንም በላይ በአገር ውስጥ የተፈጠረው የተቃውሞና ያለመረጋጋት ድባብ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ተቀርፎ ጠ/ሚኒስትሩን የሚደግፉና ከጎናቸው ለመቆም የቆረጡ ኢትዮጵያውያን በብዛት ማፍራት መቻላቸው ትልቁ ስኬታቸው ነበር።እነዚህ ትልቅ ዋጋ የነበራቸው የጠ/ሚኒስትሩ ጥረቶች ድምር ውጤት የዓለም የሠላም ኖቤል ሽልማትን እንዲቀዳጁ የማድረጉም ክስተት በስኬታቸው መንገድ ላይ በደማቁ ተጽፎ የሚገኝ ነው፡፡
ባለፉት ኹለት ዓመታት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የመደመር ፍልስፍናን የተነተኑበት መጽሐፍ ለንባብ ያበቁበት ሲሆን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ወደሶስት አሥርት ዓመታት የተጓዘው ኢህአዴግ ተዋህዶ ብልጽግና በሚባል ፓርቲ ተተክቶ ለማየት የቻልንበትም ጊዜ ነበር፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ጥንታዊውን የምኒልክ ቤተመንግ ሥትን እድሳትና ግንባታ እንዲከናወን በማድረግ ለሕዝብ ጉብኝት ክፍት ማድረገቸው ከኸለት ዓመቱ ቆይታ የሚጠቀስ አስመስጋኝ ተግባራቸው መካከል ይጠቀሳል።የታላቁ ቤተመንግሥት አንድነት ፓርክ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች በተገኙበት መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም የተመረቀ ሲሆን በቀን ከ1 ሺ 500 በላይ ጎብኚዎች እያስተናገደ ይገኛል።በቤተመንግሥቱ ሰባት ታሪካዊና ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠሩ ሕንጻዎች ጨምሮ ከስድስት በላይ መስህቦችን ለሕዝብ እይታ በቅተዋል፡፡
የኹለት ዓመቱ የጥላሸት መልኮች
እንደ ተግዳሮት ከሚነሱ በርካታ ችግሮች መካከል የተገኘውን ለውጥ የማይፈልጉ ኃይሎችና ግለሰቦች ስፖንሰር የሚያደርጓቸው ግጭቶች እዚህም እዚያም መከሰታቸው በዋነኛነት ይጠቀሳል።በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል… ክልሎች ዜጎች በማንነታቸው ብቻ በግፍ የተፈናቀሉበት፣ የተገደሉበት፣ የተዋረዱበት ታሪክም ጎልቶ የታየው በእነዚህ ኹለት ዓመታት ነበር ማለት ይቻላል።“ከክልሌ፤ ከዞኔ፤ ከወረዳዬ፤ ከቀበሌዬ ውጡ!” የሚሉ አክራሪ ብሔርተኞች ጉልበት አግኝተው፣ ደረታቸውን ነፍተው የታዩትም በእነዚህ ጊዜያት ነበር።ዘር ተኮር የጥላቻ ንግግር ጣራ የነካው እንዲሁ በእነዚህ ኹለት ዓመታት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ምክንያት አድርጎ የእምነት ተቋማትን መድፈርና ማፍረስ ፣ማቃጠል፣ መዝረፍ፤ የእምነቱ ተከታይ ምእመናንን መግደል፣ መደብደብና የአካል ጉዳት ማድረስ፣ ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች በማሳደድ ማፈናቀል፣ ንብረታቸውን መዝረፍ እና ማቃጠል በተደጋጋሚ ተከስቶ ብዙ ኢትዮጵያውያንን በሐፍረት አንገት ያስደፋበት ዓመታት አልፈናል፡፡
በእነዚህ ዓመታት እኩይ ዓላማ ያነገቡ ወገኖች ጠ/ሚኒስትሩ የታደሙበት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ቦምብ ወርውረው የግድያ ሙከራ እስከማድረግ ደፍረዋል።የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተቀራራቢ ሰዓታት በአዲስ አበባ እና በባህዳር በመግደል የጭካኔያቸውን ጥግ አሳይተዋል፡፡
እነዚህን መጠነ ሰፊ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት የተለሳለሰ አቋም ማሳየቱ፣ አንዳንድ ችግሮችንም አይቶ ባለየ ማለፉ በብዙ ወገኖች ዘንድ ከትችት ያለፈ ተቃውሞን ጭምር መቀስቀሱ እውነት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በአንድ ወቅት በሰጡት መግለጫ “መንግሥት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ሆደ ሰፊነቱን አብዝቶ ሲያስታምም ከርሟል…መንግሥት ከኃይልና ጉልበት ይልቅም፤ ትምህርት እና ምክክር ይሻላል ብሎ መታገሱን፣ ይህ ትእግስቱ ግን ፍርሃት፤ ማስታመሙ ድካም፣ የመሰላቸው ካሉ ተሳስተዋል። አንዳንዶች እንዲማሩ ተብሎ ሰፊ ልብ እና ትከሻ ሲሰጣቸው አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት ቀርተው የዜጎች ህይወት ለአደጋ የሚጋለጥበት ምክንያት ተፈጥሯል። መንግሥት የዜጎችን እና የተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ የሀገሪቱ ህግ ባስቀመጠው መሰረት ይሰራል” ማለታቸውን ሰምተናል፡፡
በሌላ በኩልም ባለፉት ዓመታት የታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዳይቀጥል ያደረጉ በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ፣ መዋቅራዊ እና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ችግሮች መኖራቸውም ተስተውሏል።የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ደካማ አፈፃፀም፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የመንግሥት ገቢ የመሰብሰብ ችግሮች፣ የዋጋ ንረት… በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት፣ ፈታኝ ነበሩ።በተለይም በሀገሪቱ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት እያደገ ካለው የሥራ አጥነት ቁጥር ጋር ተደማምሮ የማህበረሰቡን በተለይም የወጣቱን ህይወት ከድጡ ወደ ማጡ እየመራው መሆኑ በአሳሳቢነቱ ተደጋግሞ ሲነገር የቆየ ተግዳሮት ነው፡፡
እንደመቋጫ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኹለተኛውን በዓለ ሲመታቸውን አስመልክቶ ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት “የለውጡን ጉዞ ኹለተኛውን ዓመት የምናከብረው በአንድ በኩል ፈተናና ሥጋትን በሌላ በኩል የተስፋ ውጋገን ከፊታችን እየታየን ነው፡፡… የታጠቁ ኃይሎች በወለጋና በሌሎች የምዕራብ ኦሮሚያ ክፍሎች ላይ የጥፋት በትራቸውን አሳርፈው ባንክ እየዘረፉ፣ ሰው እየገደሉ፣ ቤት እያቃጠሉ፣ ትምህርት ቤቶች እየዘጉ፣ …መንግሥታዊ መዋቅርን እያፈራረሱ… የነበረውን መጥፎ ጊዜ መታለፉንም አንስተዋል፡፡
…በአንድ ቀን በአማራ ክልል ጠንካራ ጓዶቻችን በግፍ አጥተን፣ በአዲስ አበባ ተወዳጅ የጦር መሪዎቻችን ተገድለው ውጥረቱ ለድፍን ኢትዮጵያ ተርፎ የነበረበት ጊዜ አልፏል፡፡
ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ንግግር ወንድም እህቶቻችን የተቀጠፉበት፤ በትንሹ በትልቁ የህግ የበላይነት ያበቃለት፣ ኢትዮጵያም ያበቃለት እንዲመስል ተደጋጋሚ የጥፋት እርምጃዎች የተካሄደበት ወቅት አልፎ ከሞላ ጎደል ወደሠላማችን ተመልሰናል ብለዋል፡፡
በእርግጥም ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር በያዘው የተለሳለሰ አቋም ሲተች የነበረው መንግሥት ፊቱን ሙሉ በሙሉ ሕግን ወደማስከበር ማዞሩ፣ በአጭር ጊዜም ውጤት ማስመዝገቡ ለሠላም ወዳድ ኃይሎች ትልቅ የምስራች ነው።የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ይኸንኑ መልካም ጅምር በኢኮኖሚውም በመድገም ስር እየሰደደ የመጣውን ድህነት ለመቅረፍ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ይጠበቃል።(ማጣቀሻዎች፡ – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ይፋዊ ድረገጽ፣ የጀርመን ድምጽ፣ ሪፖርተር፣ የክንፉ አሰፋ መጣጥፍ…)
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
ፍሬው አበበ