ዓለም ገረገራዋን ዘግታ ኮረና ሆይ እለፈኝ እያለች እየተማፀነች ነው፡ ከታላቅ እስከ ታናሽ ለኮረና እጅ ላለመስጠት ደፋ ቀና ቢሉም እንዲሁ ግን በቀላሉ ሊራራላቸው አልቻለም፡፡በጤና ፖሊሲያቸው በከፍተኛ ደረጃ የሚመኩትና በሀብታቸው የሚመጻደቁት በበርካታ የአውሮፓ አገራት በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን እየቀበሩ ነው።
በታዳጊ አገራት ደግሞ ለጊዜው የሞት መጠኑ የከፋ ባይሆንም ምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ቀላል የማይባል ነው።ወትሮም ቢሆን በቋፍ ላይ ያለው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዛሬ ለይ በኃይለኛ የአውሎ ንፋስ እንደተመታች ከተማ እርቃኑን የቀረ ይመስላል።ችግሩ እየከፋ ከሄደ አገራት አንዱ ለአንዱ የሚያውሱት ቀርቶ ለራሳቸውም የሚቀምሱት እንደ ሌላቸው በማወቃቸው ወደ አውሮፓ እና ቡድን 20 አገራት የድረሱልን ተማጽኖ እያደረሱ ነው። ኮረና ብዙ ነገር እያሳየ ነው። ረብጣ ዶላሮችን ያከማቹ ባለሀብቶችን ሆነ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በእኩል እያስተናገደ ያለ ክፉ ወረርሽኝ ሆኗል። በዚህም የተነሳ ዓለም ወደ ከፋ ቀውስ እያመራች ነው። የዓለም ምጣኔ ሀብትም እድገቱ በግማሽ የሚቀንስ መሆኑን ባለሙያዎች ተንብየዋል። ታዲያ የኮረና ቫይረስ ፍዳ ቀማሽ የምስራቅ አፍሪካ አገራትም ከወዲሁ እየተፈተኑ መሆኑ እየተገለጸ ነው።
ሶማሊያ
ሶማሊያ ከዚህ ቀደም ከኬኒያ የሚገባው ጫት ወደ አገሬ ፍንክች እንዳይል ብላ ካገደች በኋላ የሞቃድሾ ነዋሪዎች ኑሮ ከበደን ሲሉ እየማረሩ ነው።እንዲህም ይኖራል ወይ በሚያስብለው አኗኗራቸው የጫት ከገበያ ላይ መጥፋት የጫት ቃሚዎችን ክፉኛ እያማረራቸው ነው።ምንም እንኳን ኮረና በዓለም እጅግ አሳሳቢ በሽታ ቢሆንም ለጫት ቃሚዎቹ ግን ነገሩን የበለጠ ያወሳሰበባቸው ይመስላል። አንዳንድ ቃሚዎች ከበሽታው አሳሳቢነት በላይ እንዴት አድርገው ጫት እንደሚያገኙ ላይ ታች እያሉ የመፍትሄ ያለህ እያሉ ነው።
ታዲያ በጫት ፍቅር ናላቸው የዞረው ሱማላውያን ፊታቸውን ከኬኒያ ወደ ኢትዮጵያ ቢያዞሩም የፍላጎታቸውን ሊያገኙ አልቻሉም።ኢትዮጵያም ድንበሯን ጥርቅም አድርጋ ዘግታለችና ጫት እንዲሁ የቅንጦት ሆኖባቸው እያፋሸኩ ነው።ታዲያ እነዚህ ሶማላውያን የጫት ሱሳቸውንም ለማስታገስ መላ እየዘየዱ እንደሆነና እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል ሁነኛ መፍትሄ እንዳላገኙ ዓለም አቀፍ መገኛኘ ብዙሃን ዘግበውታል።
በበርካታ ሱማላውያን ዘንድ ጫት አነቃቂ፤ ድብርት የሚያባርር እና የደስታ ስሜት የሚፈጥር ተክል አድርገው ስለሳሉት እንዲሁ አምነው መቀበል አልቻሉም።ጫት ነጋዴዎችም ከአጎራባች አገራት ጫት እንዳይገባ መባሉን ተከትሎ ኑሯቸው መዘበራረቁንና የዕለት ጉርስ ለማግኘት መቸገራቸውንም ይናገራሉ።
በሱማሊያ ዋና ከተማ ሞቃድሾ በጫት ንግድ የምትተዳደረው ሃሊማ አልመሐመድ ኮረና ቫይረስ ነገሮችን ብልሽትሽት እንዳደረገባት ለቢቢሲ ተናግራለች።እርሷ እንደምትለው ‹‹እኔ ምራቅ ከወጣኩኝ ጀምሮ የማውቀው የንግድ ዓይነት ከአጎራባች አገራት ወደ ሶማሊያ የሚገባውን ጫት ለደንበኞች ማከፋፈል እና የዕለት ጉርሴን መሸፈን ነው።የጫት ንግድ ትርፋማ በማድረግ ረገድም ሸጋ ነው፡ በዚህ ላይ ቤተሰቤን በሙሉ የምደጉመውና የእለት ጉሯሯቸውን የምደፍነው በዚሁ ንግድ ነው።ይሁንና አሁን ከኮረና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በጫት ንግድ ላይ የተጣለው እቀባ ግራ አጋብቶኛል፤ ኑሮዩንም አመሳቅሎብኛል›› ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ጫት በሱማሊያ በአነስተኛ ንግድ ላይ ለተሰማሩ አያሌ ዜጎችም የሕይወታቸው የጀርባ አጥንት እንደሆነ እና ጓዳ ጎርጓዳቸውን በዘገባው የዳሰሰው ቢቢሲ ብዙዎች የመበሳጨት ስሜት ውስጥ እንደገቡም ያትታል።ጫት እና ሱማላውያንም ያላቸውን ፍቅር በቅንጭቡ ለማሳየት ይሞክራል ዘገባው።
የሶማሊያ መንግስት ጫት በእጅ የሚነካ እና የኮረና ቫይረስ አምጭ ተዋህሲያንን መሸከም የሚችል ነው በሚል ስጋት ከኢትዮጵያ እና ኬኒያ የሚገባውን ጫት እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፏል።ከተለያዩ አገራት የሚደረገውን በረራ ከማቋረጧም በተጨማሪ ሶማሊያ በርካታ ውሳኔዎችን አስተላልፋለች።በሌላ በኩል ደግሞ በጫት ላይ የተጣለው እቀባ በባለስልጣናቱም መካከል መግባባት ላይ ስለመደረሱ አጠራጣሪም ሆኗል።
የሱማሌው የአየር ትራንስፖርትና ሲቪል አቪየሽን ሚኒስትር ሞሃመድ አብደላ ዑመር እንደሚሉት፤ ጫት በብዙ ሰዎች የእጅ ንክኪ ውስጥ ስለሚያልፍ ለኮረና ቫይረስ አጋላጭ በመሆኑ ከሌሎች አገራት የሚገባውንም ሆነ በሞቃድሾ ከተማ በሰፊ የተንሰራፋውን ንግድ ለጊዜው ጋብ ማደረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።በዚህም የተነሳ የአገሬው መንግስት ለዜጎቹ ሲል የወሰደው ጠቃሚ እርምጃ አንደሆነ በመሳሳብ ለውሳኔ ተግባራዊነት ዜጎች መትጋት እንዳለባቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሱማሌ ኮረና ቫይረስን ለመከላል በተቋቋመው ታስክ ፎርስ ውስጥ ቃል አቀባይ የሆኑት ዶክተር አብዱራዛቅ የሱፍ በበኩላቸው፤ ‹‹ጫት ተክል ላይ የኮረና ቫይረስ ይቆይ አይቆይ በጥናት የተረጋገጠ ነገር የለም።በጫት ንክኪ ስለመተላፉም በሣይንስ ይህ ነው የሚል ሁነኛ መረጃና ማስረጃ እስካሁን አልሰማሁም›› ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።የሆነው ሆኖ ግን በሞቃዲሾ የጫት ምርት እጥረት መቀኑሱ ቃሚዎች ቅር እንዲሰኙ አድርጓቸዋል።ኮረና ከአገራቸው ጠፍቶ መልሰው ከሚወዱት ጫት ጋርም ለመገናኘት ናፍቀዋል።
ኤርትራ
በርካቶችን ዓጃዒብ እያሰኘ ያለው ደግሞ በኤርትራ የኮረና ቫይረስ ስርጭትና እና የአገሬው መንግስት ውሳኔ ነው።በምስራቅ አፍሪካ ብዙም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ያላደገውና በሰብዓዊ መብት አያያዝ በዓለም አቀፍ መድረኮች በብዛት የምትከሰሰው ኤርትራ የአየር በረራዎች መዳረሻ በመሆን ረገድም ብዙ ተመራጭ አይደለችም።ይሁንና ግን ከኮረና ቫይረስ ማምለጥ አልቻለችም።በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ የቫይረሱ ስርጭት እያሰጋት ከመሆኑም ጋር ተያይዞ በርካታ ውሳኔዎችን እያሳለፈች ትገኛለች።
የኮረና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ፈተና መሆኑ የገባት ኤርትራ ዜጎቿ ጥንቃቄ እንዲያደረጉ በተደጋጋሚ ያሳሰበች ሲሆን ከቤት እንዳይወጡም አስጠንቅቃለች።በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም የአስመራ ጎዳናዎች ከሰው እንቅስቃሴ ነፃ መሆናቸውንና ንፋስ ብቻ ሽው እልም ይልበታል ሲሉ ገልፀውታል።
የኤርትራ መንግስትም ውሳኔውን የሚተላለፉ ዜጎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳሰበ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር በተያየዘ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በሚያደርጉት ላይም የከፋ እርምጃ እንደሚወስድ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል።በተለይም ዜጎች ከመደበኛው ጊዜ በተለየ ሸቀጥም ይሁን ሌላ ግብዓት በውድ የሚሸጡ ስግብግብ ነጋዴዎች ንብረት እስከመውረስ የሚያበቃ ውሳኔ አስተላልፋለች።ይሁንና በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ለሚኖሩ ኤርትራውያን ኮረና ቫይረስ እጅግ ፈተና ሆኖባቸዋል።
ኬኒያ
ጎረቤት አገር ኬኒያም የኮረና ቫይረስ በእጅጉ ካሰጋት የምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናት። ይህን ዓለም አቀፍ ሥጋት ለመቀነስም የአገሪቱ መንግስት በርካታ ውሳኔዎችን እያሳለፈ ሲሆን በርካታ ዓለም አቀፍ በረራዎች ወደ ታዋቂው ጆሞ ኬናይታ አየር መንገድ ድርሽ እንዳይሉ አስጠንቅቃለች።የኬኒያ አውሮፕላኖችም ከማኮብኮቢያቸው እንዳይንቀሳቀሱ አግዳለች። ዜጎቿም ቢሆኑ እንቅስቃሴዎቻቸው የተገደበ እንዲሆን ወስናለች።ይህንንም ተፈፃሚ እንዲያደርጉ የአገሪቱ የበላይ መሪዎች ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ይሁንና በናይሮቢ ጎዳናዎች ላይ በሰፊው የሚታዩት እጅ አጠሮችና አነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ምንይዋጣቸው ሲሉ በናይሮቢ መቀመጫቸውን ያደረጉ በርካታ ዓለም አቀፍ እና የአገሬው መገናኛ ብዙሃን ተቀባብለውታል።ከፍተኛ ድህነት በተንሰራፋባት ኬኒያ የአንዳንድ ሰዎች ሕይወት ‹‹እንዲህም ይኖራል?›› በሚያስብል የሕይወት ምስቅልቅል ውስጥ እያሉ ሌላ ችግር ሲመጣባቸው ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኖባቸዋል። ይሁንና የአገሪቱ መንግስትም የተቻለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ ለመፍትሄውም በጋራ እንስራ ሲል በተደጋጋሚ የተማፀነ መሆኑም ተነግሯል።
በእርግጥ የኮረና ቫይረስ የመላው ዓለም ስጋት መሆኑ የማይካድ ቢሆንም በምጣኔ ሀብታቸው ዳዴ የሚሉና በሁለት እግር በቅጡ ያልቆሙ አገራትን ክፉኛ እየፈተነ ነው። በተለይም ደግሞ በሠላም ረገድም ብዙም መረጋጋት የማይታይባት ምስራቅ አፍሪካ ኮረና ቫይረስ ከዚህ የባሳ እየተስፋፋ ከመጣ በምጣኔ ሀብት ሆነ በዜጎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ዓለም አቀፍ ተንታኞች እየተናገሩ ነው።በመሆኑም የከፋ አደጋ ሳይፈጠር በመከላከሉ ላይ በሰፊው እንዲሰሩ ዓለም አቀፉ ጤና ድርጅትን ጨምሮ አያሌ ደርጅቶችና ሊቃውንት እየመከሩ ነው።እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት፤ በአፍሪካ ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን 6000 የሚጠጉት ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር