በቻይናዋ ዉሃን ግዛት የተቀሰቀሰውና ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በመዛመት ላይ ያለው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) እንዴት ከእንስሳት ወደ ሰዎች እንደተላለፈ ለማወቅ ተመራማሪዎች ከባድ ጥናት ላይ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ያለው መላምት በቻይና ጫካ ውስጥ ከተገኘ የሌሊት ወፍ እንጥብጣቢ ፈሳሽ በራሪ ነፍሳትን ወደሚመገቡ እንስሳት ተላልፎ፣ በመጨረሻ ወደ ዱር እንስሳት ተዛምቷል የሚል ነው።
ከዚያም በቫይረሱ የተያዘ እንስሳ ሰው እጅ ወደቀ፤ ቫይረሱ ከዚህ ሰው የዱር እንስሳት መሸጫ ገበያ ውስጥ ወደሚሰሩ ሰዎች ተላልፎ በመጨረሻ የዛሬው ዓለም አቀፍ የኮሮና ስርጭት ላይ ተደረሰ።በአሁኑ ወቅት ሳይንቲስቶች በዚህ መላምት ላይ እርግጠኛ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።
በለንደኑ መካነ አራዊት ማህበረሰብ ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሪው ከኒግሃም እንደሚሉት ኮሮናቫይረስ ከየት መጣ የሚለውን ነገር ወደ ኋላ ተመልሶ ማየት የወንጀል ምርመራ ያህል ውስብስብ ነው ይላሉ። በርካታ የዱር እንስሳት በተለይም የበርካታ ዓይነት ኮሮናቫይረስ ተሸካሚ የሆነችው የሌሊት ወፍ የዚህኛው ኮሮናቫይረስ አስተላላፊ እንደሆነች ይገምታሉ።
በየትኛውም አህጉር የሚገኙትና በቡድን ረዥም ርቀት የሚበሩት አጥቢ ነፍሳት ራሳቸው የመታመም እድላቸው እጅግ አነስተኛ ሲሆን ቫይረሶችን በስፋት የማስተላለፍ እድላቸው ግን ሰፊ ነው። የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጇ ፕሮፌሰር ኬት ጆንስ እንደሚሉት የሌሊት ወፎች ዘረመላቸው ቢጎዳ መልሰው መጠገን ስለሚችሉ ምንም እንኳ የብዙ ዓይነት ቫይረስ ጫና ቢኖርባቸውም ሳይታመሙ ይቋቋሙታል። እናም ይህ የሌሊት ወፎች ባህሪ ለቫይረሶች መራባትና መሰራጨት ምቹ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።
የሌሊት ወፎች ቫይረሶችን ወደ ሰዎች የማስተላለፍ እድላቸውም ከፍተኛ እንደሆነ የኖትንግሃም ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጀናታን ባል ይናገራሉ።ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በዉሃኑ የእንስሳት ገበያ ኮሮና ቫይረስን በመርጨት የተጠረጠረው እንስሳ ፓንጎሊን ነው። ጉንዳን በሊታው ፓንጎሊን በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በህገወጥ መንገድ የሚሸጥ እንስሳ ሲሆን በመጥፋት አደጋ ላይ ያለ እንስሳም ነው።
ይህ እንስሳ እስያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለመድኃኒትነት ይፈለጋል። በሌላ በኩል የፓንጎሊን ስጋ ለበርካቶች ምርጥ የሚባል ምግብ ነው።ኮሮናቫይረስ በፓንጎሊኖች ላይ የተገኘ ሲሆን አንዳንዶች ቫይረሱ አሁን በሰዎች ላይ ከተገኘው ኮሮና ቫይረስ ጋር ከፍተኛ መመሳሰል አለው ይላሉ። ምናልባትም የሌሊት ወፍ ኮሮናቫይረስና ፓንጎሊኑ ኮሮናቫይረስና የዘር ቅንጣት ተለዋውጠው ይሆን?
ሳይንቲስቶች በችኮላ ድምዳሜ ላይ ላለመድረስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ ነው። ከፓንጎሊን ጋር በተያያዘ ያለው ሙሉ ሳይንሳዊ መረጃም እስካሁን ይፋ አልተደረገም።ኮሮናቫይረስ ላይ ምርምር እያደረጉ ያሉ ሳይንቲስቶች እንደሚያመለክቱት የፓንጎሊኖች የተለያዩ ዝርያዎችና እንዲሁም የሌሊት ወፎች የሚሸጡባቸው ገበያዎች ቫይረሱ ከአንዱ እንስሳ ወደ ሌላው ለመተላለፍ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ ለቫይረሱ ወደ ሰዎች መተላለፍም እድል ይፈጥራል።
ከኮሮናቫይረስ መቀስቀስ በኋላ የተዘጋው የዉሃኑ የእንስሳት ገበያም እንስሶች እዚያው ታርደው ስጋቸው የሚቀርብበት ነበር። በዚህ ገበያ ግመሎች እና ወፎችም ለእርድ ይቀርባሉ። በዚህ ገበያ ፓንጎሊን እና የሌሊት ወፍ ይሸጣሉ ባይባልም የቻይና ደህንነት ተቋም ግን ምን ዓይነት እንስሶች በገበያው እንደሚሸጡ መረጃ አለው።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ባለፉት ቅርብ ዓመታት የሰው ዘር የተዋወቃቸው ቫይረሶች ከዱር እንስሳት ወደ ሰዎች የተላለፉ ናቸው። በዚህ ረገድ ኢቦላን፣ ኤች አይ ቪን፣ ሳርስን እና የአሁኑን ኮሮናቫይረስ መጥቀስ ይቻላል።የሰው ዘርን እንዲህ ላሉ ቫይረሶች የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በሚገባ ማወቅ ከተቻለ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ያስረግጣሉ ተመራማሪዎቹ።
የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?
የኮሮናቫይረስ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ሲሆን ሲጀምር በትኩሳት ሲሆን በማስከተልም ደረቅ ሳል ይኖረዋል። ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል፤ በዚህ ሳቢያም አንዳንድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
የእነዚህ ምልክቶች መታየት ግን በበሽታው የመያዝ ምልክት ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ምልክቶቹ ከተለመዱት የጉንፋንና የኢንፍሉዌንዛ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ነው። ኮሮናቫይረስ የከፋ በሚሆንበት ጊዜ ኒሞኒያን፣ ሳርስን፣ የውስጥ አካላት ሥራ ማቆምን እንዲሁም ሞትን ሊያስከትል ይችላል።
በዕድሜ የገፉና አስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመምን የመሳሰሉ ቀደም ሲል የነበሩ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች በበሽታው ሲያዙ በጠና የመታመም ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ሰዎች በበሽታው ከተያዙ በኋላ ምልክቶችን እስከሚያሳዩ ድረስ እስከ 14 ቀናትን ሊወስድ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። ነገር ግን አንዳንድ አጥኚዎች ምልክት የማየቱ ነገር እስከ 24 ቀናት ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ጠቁመዋል።
እንዴት እራሴን መጠበቅ እችላለሁ?
የጤና ተቋማት እንደሚሉት በሽታውን ለመከላከል እጅን በመደበኛነት በደንብ መታጠብ እጅግ ጠቃሚ ነው።
እስካሁን በሽታው እንዴት እንደሚተላለፍ በእርግ ጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን የኮሮና አይነት ቫይረሶች በበሽታው የተያዙ ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት በሚያወጧቸው ጥቃቅን ጠብታ ዎች አማካይነት ነው።
ስለዚህም ስናስልና ስናስነጥስ አፍንጫና አፋችንን በሶፍት ወይም በክርናችን እንሸፍን፤ ፊታችንን እጃችንን ሳንታጠብ አንንካ። በተጨማሪም ከታመሙ ሰዎች ጋር የቀረበ ንክኪ ከማድረግ መቆጠብ በሽታውን ለመከላከል ያግዛል።
የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች የሚፈለገውን ያህል በሽታውን ለመከላከል አያስችሉም።
‘የኮሮናቫይረስ አለብኝ ብዬ ካሰብኩ ምን ማድረግ አለብኝ?’
በበሽታው ተይዣለሁ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አስፈላጊውን ምክርና የህክምና ድጋፍ ለማግኘት ለሚመለ ከታቸው የጤና ተቋማት ማሳወቅ አለባቸው።
በበሽታው ተያዞ ይሆናል ተብሎ ከሚታሰብ ሰው ጋር የቀረበ ንክኪ ከነበረዎት፤ እራስዎን ለተወሰነ ጊዜ ከሌሎች ሰዎች አግልለው እንዲቆዩ ሊነገርዎት ይችላል። ስለዚህ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር የሚኖርን የቀረበ ንክኪ ማስወገድ ይኖርብዎታል።
በሽታው ከተከሰተባቸውና ከሌሎች አገራት የተመለሱ ከሆነ ምናልባትም ለተወሰነ ጊዜ እራስዎን አግልለው መቆየት ሊያስፈልግዎት ይችላል።
ኮሮናቫይረስ ምንያህል አደገኛ ነው? ሊድንስ ይችላል?
የዓለም ጤና ድርጅት ከ56 ህሙማን ላይ በሰበሰበው መረጃ መሰረት በኮሮናቫይረስ ከተያዙ አምስት ሰዎች መካከል አራቱ ቀለል ያሉ የበሽታውን ምልክቶች ብቻ ያሳያሉ። በዚህም መሰረት፡
80 በመቶው ቀለል ያሉ ምልክቶችን ያሳያሉ
14 በመቶው ከባድ ምልክቶችን ያሳያሉ
6% በመቶው ክፉኛ ይታመማሉ
ምንም እንኳን አሃዞቹ አስተማማኝ ባይሆኑም በበሽታው ከተያዙት መካከል የሚሞቱት ሰዎች ብዛት ዝቅተኛ እንደሆነ ተስተውሏል፤ ይህም ማለት በበሽታው ከተያዙ ሰዎች መካከል ከመቶው አንድ ወይም ሁለቱ ብቻ የሚሆኑት ናቸው ለሞት የሚዳረጉት።
በአሁኑ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩት በህክምና ላይ ያሉ ሲሆን ሊሞቱ ይችላሉ። በዚህም ሳቢያ የሞት መጠኑ በመቶኛ ከፍ ሊል ይችላል።
ራሳችንን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ስልካችንን እንዴት እናጽዳ?
የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ እንደሆነ ገልጿል። ድርጅቱ ይህ ወረርሽኝ ራሳችን ልንከላከለው የምንችለው መሆኑንም አስታውቋል።
ይህንንም ለማድረግ እጃችንን በተደጋጋሚ መታጠብ፣ ፊታችንን በተደጋጋሚ አለመነካካት፣ በምናስነጥስበት አልያም በምናስልበት ወቅት አፍና አፍንጫችንን በሶፍት አልያም በክርናችን መሸፈን የሚጠቀሱ መከላከያዎች ናቸው።
በቤታችንም ሆነ በምንሰራበት ስፍራ በተደጋጋሚ የእጅ ንክኪ የሚበዛባቸው ስፍራዎችን ማጽዳት ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል አንዱ ነው።
ነገር ግን ስልካችንን በየደቂቃው የምንጠቀም እንደመሆናችን እንዴት ማጽዳት እንዳለብን እስካሁን ካላሰብን ቀጣዩ ጠቃሚ ነጥብ ይሆናል።
ስልክዎን በኪስዎ፣ በቦርሳዎ አንዳንዴም ወደ በፀዳጃ ቤት ሲሄዱ ይዘውት ይሄዳሉ። ምን ያህል ጀርም ስልክዎ ብቻ ተሸክሞ እንደሚገኝ አስበውታል? ኮሮናንስ ስላለመያዙ ምን ያህል እርግጠኛ ነዎት?
የአሜሪካን የጤና ስርዓት በበላይነት የሚቆጣጠረው ሲዲሲ በምናስነጥስበት አልያም በምናስልበት ወቅት ከሰውነታችን የሚወጣው ጀርም በሚረጭበት ስፍራ ላይ ለሰዓታት በሕይወት ይቆያል ብሏል። ስለዚህ ቆሽሸው የሚታዩን ነገሮችን በአጠቃላይ እንድናፀዳ ይመክራል።
በማጽዳትና ከቫይረሱ ነጻ በማድረግ ረገድ ልዩነት እንዳለም ተቋሙ ያሳስባል። መጀመሪያ ቆሻሻውን ማጽዳት ቀጥሎም ከቫይረሱ ነፃ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል።
ስልካችንን ለማጽዳት 70 በመቶ አልኮል ያለው ዋይፐር መጠቀም የሚቻል ሲሆን በረኪና ግን አይመከርም። ቀላል ሳሙናና ውሃም ለማጽዳት እንደሚያገለግልም ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ዶ/ር ሌና ሲሪክ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን ማይክሮባዮሎጂስት ናቸው። እርሳቸው እንደሚመክሩት ከሆነ ስልክዎን ለማጽዳት ከቻርጀሩ መንቀል፣ መሸፈኛ ካለው ማውለቅ ቅድሚያ ልትወስዷቸው የሚገባው ተግባር ነው።
ዋና ዋና የሚባሉት የስልክ አምራቾች ስልካችንን ለማጽዳት ኬሚካሎች፣ ለእጃችን ማፅጃነት የምንጠቀ ምባቸው ሌሎች እንዲሁም ሸካራ ነገርን ለማጽዳት የሚያገለግሉ ዋይፐሮችን መጠቀምን አይመክሩም።
ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው የስልክዎን ስክሪን መከላከያ ይጎዳሉ አልያም ያወድማሉ የሚል ነው። ስለዚህ ይላሉ ዶ/ር ሌና፣ በቀላሉ በውሃና በሳሙና በተነከረ ጥጥ ወይም ከጥጥ በተመረተ ጨርቅ ማጽዳት በቂ ነው።
በጥጥ ወይም በጨርቁ የስልክዎን ስክሪንም ሆነ ጀርባ እንዲሁም ጎኖች ማጽዳት ይችላሉ። በዚህ ወቅት ግን የሚያጸዱበት ፈሳሽ በስልኮቹ ክፍተቶች በኩል እንዳይገባ ጥንቃቄ ያድርጉ።
በርግጥ አንዳንድ ውሃን የሚቋቋሙ ስልኮች ቢኖሩም ከጊዜ በኋላ ግን ይህንን ብቃታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በአግባቡ ከወለወሉ በኋላ በለስላሳ ጨርቅ ማድረቅ አይርሱ። ዶ/ር ሌና እንደሚሉት በሳሙናና ውሃ ስልክዎን ማጽዳት ቫይረሶችንና ጀርሞችን ከስልክዎት ላይ ያፀዳል።
አይፎንን ስልኮችን የሚጠቀሙ ከሆነ፣ አፕል ስልክዎን በአግባቡ 70 በመቶ አይሶፕሮፔል አልኮል ባላቸው ዋይፐሮች ማጽዳት እንደሚችሉ ይመክራል። እነዚህን ዋይፐሮች ከኮምፒዩተር መለዋወጫዎች መሸጫ ሊያገኟቸው ይችላሉ።
በዚህ ሁሉ ስልክዎን ካፀዱ በኋላ ባልታጠበ እጅዎ ከሆነ የሚጠቀሙት መልሶ ስልክዎ በጀርሞች ይሞላል። ስለዚህ እጅዎን በየጊዜው መታጠብ አይርሱ!
ምንጭ -የዓለም ጤና ድርጅት እና ቢቢሲ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012