በድንገት ያቃጨለውን የእጅ ስልኳን ፈጥና አላነሳቸውም። ጥሪው አሁንም እየደጋገመ ነው። ስራ ላይ የነበረችው ወይዘሮ በዝግታ ተራምዳ ወደ ስልኩ ቀረበች። እጇን ሰንዝራ ስልኩን ከማንሳቷ በፊት ጥሪው ተቋረጠ። ጠጋ ብላ በሞባይሉ ግንባር ላይ የተመዘገበውን የምልክት ቁጥር አነበበች። ስልክ ቁጥሩን አላወቀችውም። ደዋዩን እያሰበች ስለማንነቱ ተመራመረች። በድጋሚ ስልኩ በእጇ ላይ ጠራ። የቀድሞው ቁጥር ነው። ፈጥና አነሳችው።
‹‹ሄሎ!ሄሎ!…›› አላት አንድ ድምፅ። እሷም መልሳ ሄሎ!ሄሎ! አለችው።ደዋዩ የተረጋጋ አይመስልም። ቁርጥ ቁርጥ ከሚለው ትንፋሹ ውስጥ ስጋትና ድንጋጤ ይነበባል። ወይዘሮዋ ከሰውዬው ቀጣዩን ለመስማት ዝም አለች። አሁንም ባልተረጋጋ ድምጹ ቀጠለ።
ሄሎ!ሄሎ! የበላይ ስልክ ነው;-ጠየቀ። ድምጹን የምታውቀው መሰላት። ተረጋግታ ባለቤቱ እንደሆነች መለሰችለት። እእ… እእ… .እ … እ… .ደዋዩ አሁንም ተርበተበተ። ማንነቷን ቢያውቀውም ስሟ ከአፉ ጠፋበት። ጥቂት ቆየና እንደምንም ስሙን ነገራት። የባለቤቷ የቅርብ ጓደኛ ነው። ማንነቱን ስታውቅ ሰላም መሆኑን ደጋግማ ጠየቀችውና የሚለውን ለመስማት ጆሮዋን አሰላች።
ሰውዬው ጥቂት ለመረጋጋት ሞክሮ ሀሳቡን ቀጠለ። ‹‹እእ.. ከወይንሸት ጋር ጥቂት ተጋጭተን መትቻታለሁ። ሳልጎዳት አልቀርም። እኔ ስለተናደድኩ ሰፈር የለሁም። እባክሽ ቤት ሂጂና ሳትሞት ድረሺላት ››ይህን ተናግሮ ስልኩን ጆሮዋ ላይ ዘጋው።
ወይንሸት የሰውዬው ባለቤት ነች።በትዳር አመታትን እንደዘለቁ የምታውቀው ወይዘሮ ንግግሩን ስትሰማ ከልቧ ደነገጠች። ስለ ዝርዝር ጉዳዩ ሊነግራት ዕድል አልሰጣትም። ንግግሩ ከነከናት። ሁኔታውን ለመጠየቅ መልሳ ደወለችለት ። ስልኩ አይመልስም።
ወይዘሮዋ ‹‹ሳትሞት ድረሺላት›› የሚለው ቃል ደጋግሞ ረበሻት ። መልዕክቱ ፈጽሞ ሰላም አልሰጣትም። ጊዜ ሳታጠፋ ነጠላዋን ደርባ ወደ ጥንዶቹ ቤት ገሰገሰች። ሰፈር መንደሩን አቋርጣ ከግቢያቸው ለመድረሰ መንገዱ እጥፍ ሆነባት።
ኳስ ሜዳ አካባቢ ስትደርሰ ልቧ ይበልጥ ሲመታ ተሰማት። እንደምንም በርትታ ከግቢው ደረሰች። የውጩን በር ከፍታ ስትገባ የቤቷን አከራይ ከደጅ ቆመው አገኘቻቸው። ሰላም ብላቸው ወይንሸትን አይተዋት እንደሆነ ጠየቀች።
ሴትዬዋ ተረጋተው መለሱላት። ከጥቂት ሰአት በፊት ባለቤቷን እንዳገኙትና እሷንም ቢሆን ትናንት ምሽት ከባሏ ጋር ውሀ ስትቀዳ እንዳይዋት አረጋገጡ። ወይዘሮዋ የሴትዬዋ ንግግር አላሳመናትም። አብረዋት ወደ ቤቱ እንዲዘልቁና መኖሯን እንዲያረጋግጡ ጠየቀቻቸው። አላንገራገሩም።እሷን አስከትለው ገረበብ ወዳለው ቤት አመሩ።
ከአመታት በፊት
አባተ ስንትአየሁ ከትውልድ አገሩ ወላይታ አርቆ አዲስ አበባ ያደረሰው የእንጀራ ጉዳይ ነው። ወላይታ እያለ አልተማረም። ዕድሜው ከፍ ሲል የአቅሙን እየሰራ ራሱን ሲደግፍ ቆይቷል። አመታትን ያሳለፈበት የወርቅ ማንጠር ስራ ገቢው ቢያንስበት ጀብሎ እያዞረ ቆየ።እሱም ያሰበውን ያህል አላዋጣውም።
አዲስ አበባ ከተማን ለኑሮ ሲመርጥ ሌላ መተዳደሪያ ያስፈልገው ነበር። ልባሽ ጨርቆችን በርካሽ እየገዛ አትርፎ መሸጥ ጀመረ። አባተ ይህ ብቻ አልበቃውም። ለተሻለ ህይወት ርቆ መሄድ እንዳለበት ሲያስብ ቆየ። ኑሮውን እንደሌሎች ለውጦ ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ የመጀመሪያ ምርጫው አዲስ አበባ ሆነ ።
አዲስ አበባ ሲመጣ እንግድነት አልተሰማውም። የአገሩን ልጆች አገኛቸው። ከነሱ ተጠግቶም ያገኘውን እየሰራ ቆየ። ማደሪያውን ከዘመድ አድርጎ አገሩን ሲላመድ ራሱን ለመቻል ሞከረ። ጥቂት ቆይቶ ዣንጥላ ከማከፋፈያ እያመጣ አዙሮ መሸጥ ጀመረ። ስራው ውጤት ያለው ሲመስለው በጀመረው ቀጠለ። ሙከራው መልካም ሆነለት።
አባተና አዲስ አበባ በሚገባ ተላምደዋል። የከተማውን መውጫ መግቢያ ጠንቅቆ የሚያውቀው ወጣት አሁን ሁሉ ዘመዱ እየሆነ ነው። አልፍ አልፎ አገሩ ብቅ እያለ
ወላጆቹን ይጠይቃል። ሁሌም የአቅሙን ለግሶ ምርቃትን ተችሮ ሲመለስም ቤተሰቦቹ ስለእሱ ህይወት መልካሙን ይመኛሉ። አግብቶና ወልዶ የልጅ ወጉን እንዲያሳያቸው ከመጠየቅ ቦዝነው አያውቁም።
አባተ ዣንጥላ እያዞረ መሸጡን ቀጥሏል። ከትናንት ዛሬ የኑሮ አቅሙ ስለተሻለም የወላጆቹን ፍላጎት ለመሙላት እያሰበ ነው። ይህን ሲያቅድ ሁሌም ለትዳር የሚመኛት ወይንሸትን ውል ትለዋለች። በሚገናኙ ጊዜ የውስጡን ፍላጎት ሊነግራት ይሞክራል። እሷም ብትሆን ለትዳር ያላት ፍላጎት የተለየ ነው።
ወይንሸት አባተን በጓደኝነት ታውቀዋለች።ስለሱ ያላት ስሜትም ጥሩ የሚባል ነው። የሁለቱም ሀሳብ አንድ ሆኖ በአንድ ጎጆ ቢኖሩ ምኞቷ ነው።
ሶስት ጉልቻ
አሁን አባተና ወይንሸት በአንድ ጎጆ መኖር ጀምረዋል። አዲሱ ትዳር መተሳሰብና ፍቅር አልጎደለውም። ‹‹አንተ ትብስ‹እኔ›› ብለው የጀመሩት መንገድ ብዘዎቹን አስደንቋል። እሱ የወላጆቹን ፍላጎት መሙላቱና የግራ ጎኑን ማግኘቱ እፎይታ ሰጥቶታል።እሷም ብትሆን ከብቸኝነት ተላቃ ጎጆ ማቅናቷ አስደስቷታል ።
የጥንዶቹ ትዳር ጥቂት አለፍ እንዳለ ጎጇቸውን የሚያሞቅ፣ ሕይወታቸውን የሚያደምቅ የምስራች ሆነላቸው። ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ የታቀፈችው ወይዘሮ ለባለቤቷ ደስታን አብስራ ለቤተሰቦቹ የልባቸውን ሞላች። ይህኔ አዲሱ ትዳር ይበልጥ በፍቅር ተሞላ። መተሳሰቡ ጨምሮም ለአዲሱ ጨቅላ መኖር ተጀመረ።
አባተ ዣንጥላ እያዞረ መሸጡን አልተወም። ክረምትና ዝናብ ባለ ጊዜ የተሻለ ገንዘብ ያገኛል። ወይንሸትም ብትሆን የእሱን እጅ ብቻ አትጠብቅም። ያገኘችውን እየሰራች ለልጇና ለጎጆዋ ትደጉማለች። ሳቂታዋ ወይንሸት ከሰው የመግባባት ችግር የለባትም። ሁሉን እንደአመሉ ተቀብላ ማስተናድ ልማዷ ነው።
አሁን የጥንዶቹ ትዳር አራት አመታትን አስቆጥሯል። የሶስት አመቱ ልጃቸው ለሁለቱም ደስታ ሆኖ አብሯቸው ይኖራል። ስለሱ ህይወት አጥብቀው የሚጨነቁት ጥንዶች ጠዋት ማታ በሚሮጡበት ስራ ያለ እረፍት እየተጉ ነው።
ቅያሜ
በጥረትና በመተሳሰብ የቆመው ጎጆ ቀናትን አልፎ አልፎ ቅያሜን ማስተናገድ ይዟል። በየምክንያቱ የሚነሳው ጭቅጭቅም ኩርፊያን አስከትሎ ያለንግግር የሚቆጠሩ ቀናት በርክተዋል። አባተ የሚስቱን ሰርቶ መግባት አይጠላም። በስራ ሰበብ ከብዙዎች ያላትን ቅርበት ግን ወዶት አያውቅም። የሁልግዜው ፈገግታና ሰላምታዋ ለእሱ የራስ ምታቱ ነው። በተለይ ደግሞ ከወንዶች ጋር ያላትን ግንኙነት በጥርጣሬ ማየት ከጀመረ ቆይቷል ።
ወይንሸት በባሏ ጭቅጭቅና ጥርጣሬ መማረሯ በዝቷል። አንዳንዴ ቤቱን ትታ ልትወጣ ታስባለች። እንዲህ ብታደርግ የልጇ ጉዳት እንደሚያመዝን አይጠፋትም። ሁሉን ትታ እንዳትቀመጥ ደግሞ ጎጆዋን እንድትጠላ የሚያደርግ ምክንያት ብዙ ነው። ሁሌም በነዚህ ፈታኝ ስሜቶች መሀል ትተክዛለች። ባስ ባላት ጊዜም አንገቷን ደፍታ ትንሰቀሰቃለች፡
አባተ በቅናት ሰበብ ከባለቤቱ ጋር መጨቃጨቁ ብሶበታል። ሚስቱ ትዕዛዙን እንድታከብርለት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። እንዲህ መሆኑን ከንቀት ቆጥሮም በጥላቻ መንፈስ ማየቱን ቀጥሏል። ባያት ቁጥር ይነደዋል። ለሚጠይቃት ሁሉ በቂ ምላሽ ያለመስጠቷም ያበሽቀዋል።
አባወራው ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ክፉኛ የሚያስጨንቀው ጉዳይ ከጥርጣሬ አልፎ ሰላሙን እየነሳው ነው። ባለቤቱ ከአንድ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት እንደጀመረች እርግጠኛ ሆኗል። ይህን እንድታውቅም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየተሳደበ ይነግራታል። ከሰውየው ጋር ፍቅር ጀምራለች የሚለው አባተ በየመዝናኛው አብረው እንዳያቸው እርግጠኛ ለመሆኑ ደጋግሞ አሳውቋታል።
የጥንዶቹ ትዳር ንፋስ ገብቶት ያለ ሰላም ውሎ ማደሩ ቀጥሏል።ሁለቱም በየፊናቸው እየሰሩ የሚያመጡትን ገንዘብ እንደቀድሞው ለጎጇቸው ማዋሉን ትተውታል። ወይንሸት ውስጧ ሰላም ቢያጣም በሌሎች ዘንድ ተከፍታ መታየትን አትሻም። በፈገግታ ውላ በፈገግታ ትመለሳለች። እንዲህ ማድረጓ የማይዋጥለት ባለቤቷ ድርጊቷ ሁሉ ውሽማ ብሎ ለሚጠራው ሰው ደስታ እንደሆነ ያምናል።
ሰሞኑን አባተ ጤንነት እየተሰማው አይደለም። ሆስፒታል ሄዶ ምርመራ ማድረግ ፈልጓል። አንድ ቀን ሀኪም ዘንድ ቀረበ። ሀኪሙ ከምርመራው በኋላ የሰጠው ውጤትና ምክር ግን ይባስ ጥርጣሬውን አጎላው። ከሚስቱ ጋር የነበረውን ቅራኔ አድምቆም ለማያባራ ጠብ ተዘጋጀ።
አባወራው ከሆስፒታሉ የተሰጠው ውጤት የአባላዘር በሽታ እንደተገኘበት ያመለክታል። ይህን ከሰማ በኋላ ደግሞ ለጉዳዩ ተጠያቂ ያደረገው ባለቤቱን ብቻ ሆኗል። ሀኪሙ ከውጤቱ በኋላ ሚስቱን አምጥቶ በጋራ እንዲታከሙ አሳውቆታል።የሰማውን እውነት ለሚስቱ ሲነግራት ግን ያለመታመሟን ጠቅሳ መታከም እንደማትሻ ነግራዋለች።
አባተ ከህክምናው በኋላ ከሚስቱ ያገኘው ምላሽ ንዴቱን አብሶታል። ለብቻው እየተመላለሰ ሲታከም በእሷ በኩል አንዳች ህመም ያለመታየቱ እያስገረመው ነው። ለጉዳዩ ትኩረት ያለመስጠቷ ደግሞ ይበልጥ ውስጡን አግሞታል። የቤቱ ሰላም እጦት ጨምሮ ንትርኩ ተባብሷል።
ጥር 25 ቀን 2011 ዓም
ገና በማለዳው መጨቃጨቅ የጀመሩት ባልና ሚስት ያለ አንዳች መስማማት ሲጣሉ አርፍደዋል። አራት ሰአት ተኩል ሲሆን ሚስት ወደስራ ለመሄድ መዘጋጀት ያዘች። ይህን ያየው አባተ ከመንገዷ ተመልሳ ቤት እንድትቀመጥ አዘዛት። ሚስት ሁኔታው እያናደዳት ወደውጭ ለመውጣት በሩ አጠገብ ደረሰች።አባተ በእጁ እየከለለ እንዳትወጣ ታገላት። እጁን ከላይዋ አንስታ በድጋሚ በሩ ዘንድ ደረሰች።
አባተ የሚስቱን ለመሄድ መቁረጥ ባወቀ ጊዜ እሷ ዘንድ የተቀመጠውን አራት መቶ ብር እንድትሰጠው ጠየቃት። ይህን ስትሰማ ሁለት መቶ ብሩን ጸጉሯን ለመሰራት ቀብድ እንደሰጠችውና ቀሪውን ብር መውሰድ እንደሚችል ነገረችው። ሰበብ ፈላጊው ሰው በምላሽዋ ተናደደ። ጸጉሯን የምትሰራው ለውሽማዋ ቀጠሮ መሆኑን አምኖም እሱ ሳይመለስ ከቤት እንዳትወጣ ነገራት።
ወይንሸት በተራዋ በባሏ ሀሳብ በሸቀች። ቤት ቀርታ ለእሱ ምሳ እንድትሰራና ልብስ እንድታጥብ በሰጣት ትዕዛዝም የበታችነት ተሰማት። ጸጉሯን የምትሰራው ለውሽማዋ ቀጠሮ እንደሆነ ደጋግሞ ሲነግራት የንዴት ላብ አጠመቃት። በንግግሩ እንደበሸቀች የተዘጋውን በር ለመክፈት ወደ ፊት ተንደረደረች።
አባተ መታገስ አልቻለም። በሩን ከፍታ ለመውጣት ጥቂት የቀራት ሚስቱን እጇችዋን አፈፍ አድርጎ ወደ ኋላ መለሳት። መታገሉ ቀጠለ። አንዳቸው በሌላቸው ላለማሸነፍ ጉልበታቸውን ፈተሹ። ጥቂት ቆይቶ የአባተ ሀይል በረታ። አንገቷን አንቆ ወደኋላ እየገፋ ከግርግዳው ጥግ አደረሳት። ትንፋሽ ያጣችው ወይዘሮ እጁን ከአንገቷ ለማላቀቅ የአቅሟን ያህል ሞከረች። አልቻለችም። የባሏ ፈርጣማ ክንዶች ከአንገቷ እንደጠበቁ ከመሬቱ ተዘረጋች።
ንዴታሙ አባወራ ከወደቀችው ወይዘሮ አንገት እጆቹን ሳያነሳ ዓይኖቹን ከወዲያ ወዲህ አማተረ። አጠገቡ ያለውን አዲስ ምላጭ ከዓይኑ ገባ። ምላጩ ሰሞኑን ለጥፍር መቁረጫ የተገዛ ነው። አንገቷን ሳይለቅ ፈጠን ብሎ ከእጁ አደረሰው። ወይንሸት ይህን ስታይ በምልክት ‹‹አትግደለኝ›› ስትል ተማጸነችው። አልሰማትም። ስል ምላጩን ከማሸጊያው አላቆ ወደፊቷ ቀረበ።
አባተ በግራ እጁ አንገቷን፣ በቀኝ እጁ ምላጩን ይዞ የወይንሸትን ፊት መሸርከት ያዘ። ስ ል ምላጩ ፊቷን እየገመሰ ወደውስጥ ሲዘልቅ ደስ አለው።ወይንሸት ከታላቅ ጩኸት ጋር እንዲተዋት ተማጸነችው።አባተ አሁንም አልሰማትም። ደም ያራሰውን ፊቷን እያየ መሸርከቱን ቀጠለ። ከግንባሯ ወደ አፍንጫዋ፣ ከዛም ወደ አገጯ፣ ቀጥሎም ወደ ጉንጮቿ በምላጩ ተመላለሰ።
ወይንሸት ሲቃ በሞላው ድምጽ እየታገለች ‹‹አትግደለኝ፣ አትግደለኝ፣›› ሰትል ተማጸነቸው። መስሚያ ጆሮ አልነበረውም። ከነበረበት ተነስቶ የአንገት ሻርፕዋን ጠቅልሎ ተጠጋት።ጨርቁን በፊቷ ሸፍኖም ትንፋሽ እስክታጣ አስጨነቃት።ደም የነካ እጁን ጠራርጎ ከበሩ ሲደርሰ ሚስቱን መለስ ብሎ አያት። አልተንቀሳቀሰችም። በሩን የኋሊት ዘግቶ እርምጃውን አፈጠነ። ከመሀል መንገዱ ሲደርስ ለአንድ ሰው ማሳወቅ እንዳለበት አመነ። ስልኩን አንስቶ ወደ ቅርብ ጓደኛው ደወለ። ከአንድ ጊዜ ሙከራ በኋላ ባለቤቱ አንስታ ሄሎ ስትል መለሰችለት።
አከራይዋና ወይዘሮዋ
ሁለቱ ሴቶች ገርበብ ያለውን በር በዝግታ አንኳኩ። ከውስጥ መልስ የለም። አሁንም ደግመው አንኳኩ። አልተከፈተም። ሙከራቸውን በሀይል የደጋገሙት ሴቶች በቤቱ ዝምታ ቢጨነቁ በሩን ከፍተው ወደውስጥ ዘለቁ። የሁለቱም አይኖች ያዩትን ማመን አልቻሉም። ወይዘሮዋ በአንገት ልብስዋ ተሸፍና ከፍራሹ ወድቃለች። ጨርቁ በደም ርሷል። ፈጥነው ለፖሊስ አሳወቁ።
የፖሊስ ምርመራ
ጥቆማ የደረሰው የአካባቢው ፖሊስ ከስፍራው ሲደርስ ወይንሸት በህይወት አልነበረችም። የአይን እማኞችን አቅርቦ ምርመራውን እንደቀጠለ የጠቋሚዋ ስልክ አንቃጨለ። ወይዘሮዋ ቁጥሩ የአባተ መሆኑን አሳወቀች። ፖሊሶች ሁሉም ሰላም መሆኑንና ሚስቱ ታክማ እንደተመለሰች እንድትነግረው አዘዟት። ተረጋግታ የተባለችውን ፈጸመች። በመርማሪ ምክትል ሳጂን ቢኒያም በሪሁን የሚመራው ቡድን ተጠርጣሪው በአገር እንደሌለ ባረጋገጠ ጊዜ በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴውን ጀመረ። የሚገኝበትን የትውልድ አገሩን አረጋግጦም ጉዞ ለማድረግ ተዘጋጀ። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን አባተ የሚስቱን መሞት በማወቁ ለወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ እጁን ሰጠ። ፖሊስም ካለበት ይዞ በማምጣት ምርመራውን አጠናቆ ለፍርድ አቀረበው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
መልካምስራ አፈወርቅ