አዲስ አበባ፤- ከጅቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ እና ወደተለያዩ አካባቢዎች እቃዎችን የሚያጓጉዙ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የኮሮና በሽታ ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤የተለያዩ ገቢ እና ወጪ እቃዎችን የሚያጓጉዙ 450 የድርጅቱ አሽከርካሪዎችንና ከጅቡቲ በኢትዮ-ጅቡቲ የንግድ መስመር ላይ የሚንቀሳቀሱ የግል የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች አስፈላጊው የኮሮና ቫይረስ መከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በየጊዜው ቁጥጥር እየተደረገ አስፈላጊው የመከላከል ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል።
እንደ አቶ አሸብር ገለጻ፤የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅትን የኮሮና ቫይረስ የቁጥጥር ስራን ለመከታተል በዋና ስራ አስፈጻሚው የሚመራ ኮሚቴ አቋቁሟል።ኮሚቴውም የኮሮና በሽታ እንደሃገር የሚያደርሰው ተጽእኖ እስኪገታ ድረስ ከተቋሙ የህንጻ አጠቃቀም ጀምሮ እስከ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እና ሌሎች ክንውኖች ያጠቃለሉ ጉዳዮች የሚመሩበት ሰነድም አዘጋጅቷል። በዚህ መሰረት ከጅቡቲ ወደብ ባለፈ ከባድ ተሽከርካሪዎች በብዛት የሚገኙበት ቃሊቲ የየብስ ተሽከርካሪዎች ማቆያ ውስጥ አስፈላጊው የበሽታው ቁጥጥር እንዲደረግ እና መረጃዎች በወቅቱ እንዲደርሱ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የሎጂስቲክ ስራ በባህሪው ለየት ያለ በመሆኑ በኮሮና በሽታ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ስራው አለመቆሙን የገለጹት አቶ አሸብር፤ በአሁኑ ወቅትም ለሀገር የሚጠቅሙ እቃዎች እና ወደውጭ ሀገራት የሚላኩ ምርቶችን ከአስፈላጊው ጥንቃቄ ጋር የማመላለሱ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በዚህ ወቅት ግን ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ለምግብ እና ለመኝታ በሚያርፉባቸው አካባቢዎችም ሆነ በስራ ወቅት የግል ንጽህናቸውን ከመጠበቅ ባለፈ የበሽታው ምልክት በሚታይበት ጊዜ ሁሉ አስፈላጊውን መረጃ ለጤና ተቋማት እንዲያስተላልፉ ጥብቅ ትዕዛዝ ተላልፏል።
የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ባዘጋጀው የኮሮና በሽታ መከላከል እርምጃ መሰረት ለተቋሙ አገልግሎት የሚውሉ የበሽታ መከላከያ ቁሳቁሶች በየጊዜው እየተገዙ ለሰራተኛው ይቀርባሉ። በሰነዱ የተቀመጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችም በኢትዮጵያ የሚገኙ ስምንቱም ደረቅ ወደቦች ላይ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት የኢትዮጵያን 90 በመቶ የወደብ እቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባ ተቋም ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ከውጭ ሀገራት በወደቦችና በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በኩል እንዳይገባ የዕለት ተዕለት ክትትል በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
ጌትነት ተስፋማርያም