በሕዳር ወር 2012 ዓ.ም በቻይና የተነሳው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ሊያዳርስ ጥቂት አገራት ቀርተውታል። የአለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ወረርሽኙ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። እድሜ፣ ጾታ፣ ቀለም፣ ወጣት፣ አዛውንት፣ ጎልማሳ የሚመርጥ አይደለም። የሥርጭት ፍጥነቱም ካለፉት የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች በእጅጉ የተለየ ነው። በመሆኑም በአጭር ጊዜ ዓለምን መቆጣጠር እንዳስቻለው የዓለም የሚዲያ አውታሮች ያትታሉ።
የኋሊት ዳሰሳ
አለም በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የወረርሽኝ ዓይነቶች ተፈራርቀውባታል። በመቅሰፍቶቹም አያሌ ዜጎች እንደጤዛ መርገፋቸው ይነገራል። እኤአ በ1918 የዓለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የተከሰተው ‹‹ስፓኒሽ ፍሉ›› የተሰኘ ወረርሽኝ የ50 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት መቅጠፉ ይነሳል። እኤአ በ1957 በአገረ ሲንጋፖር የተነሳው የ‹‹ኤዥያን ፍሉ›› የተሰኘው ወረርሽኝ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሕይወት ቀጥፏል። ‹‹ሆንግ ኮንግ ፍሉ›› አምስት መቶ ሺ፣‹‹ስዋይን ፍሉ›› ሁለት መቶ ሺ፣ ‹‹ኤች አይ ቪ ኤድስ›› 32 ሚሊዮን፣ ‹‹ጥቁር ሞት›› 30 ሚሊዮን ሕዝብ ሕይወት ቅርጥፍ አድርገው የበሉ ወረርሽኞች ናቸው። እኤአ በ1518 የተከሰተው የፈንጣጣ ወረርሽኝም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ያደረሰው እልቂት ቀላል አይደለም። ሌሎችም በርካታ ወረርሽኞች እየተፈራረቁ የአለም ሕዝብ ፍዳ አስከፍለውታል።
ዘመን ዘመንን እየተካ ከሃያኛው ከፍለ ዘመን ወዲህ በኢንዱስትሪው እየጎለበቱ መምጣታቸውን ተከትሎ የበለጸጉ አገራት ባካሄዱት ግብግብ የብዙ ወረርሽኝ በሽታዎች መንስኤዎችና መድሐኒቶች ማግኘት ችለዋል።
ይሁን እንጂ አንዱ ችግር ሲራገፍ ሌላው እየተተካ፣የተፈጥሮው ችግር ረገብ ሲል ሰው ሰራሹ እየተተካ ዛሬም ድረስ የዓለም ሕዝብ በሰቆቃ እየታመሰ ዓለም እያጣጣረች መቀጠሏ የሚስተዋል ሐቅ ነው። አሁንም ኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ዓለምን ተረክቦ ግብሩን በማድረስ ላይ ይገኛል።
ዛሬ
በኢኮኖሚ የበለጸጉትም ሆኑ ያልበለጸጉት፣ በዴሞክራሲ የዘመኑትም ሆኑ የተንቀረፈፉት፣ ፌዴራሊስትም ሆኑ አሃዳዊስት አገራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙ ተሽመድምደዋል። ሰዎች በየቀኑ እንደ ቅጠል እየረገፉ ይገኛሉ። በዘርፉ አንቱ የተባሉ ተመራማሪዎች አንገታቸውን ደፍተዋል፤ ለወገኖቻቸው መፍትሄ መውለድ አልቻሉም። መሪዎችም የሕዝባቸውን እንባ ከማበስ ይልቅ አብረው በማንባት ላይ ናቸው። ቀን ሲከፋ ታላቅም ታናሽም አብረው ያንሳሉ። የኮሮና ወረርሽኝ እንዲህ ዓይነት ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስን ይዞ ለዓለም ሕዝብ ስጋትን ደቅኗል።
በእንዲህ ዓይነት መከራዎች የብርቱ አገራት ብርቱነት ይፈተናል፤የመሪነት አቅም ይለካል፤ የሕክምና ሊቅነት ጥበብም ይመዘናል። ከአፍ እስከ ገደፋቸው በዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ የተደራጁ ሆስፒታሎች፣ ዘመኑ ያፈራቸው መድሐኒቶች የታጨቁበት መድሐኒት ሱቅ እና በነፍስወከፍ ሊባል በሚችል ደረጃ የተካኑ ዶክተሮች የሞሉባትና በሕክምናው ዘርፍ በዓለም ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቆናጠጠችውም ጣሊያን በወረርሽኙ ርዕደ መሬት የተከሰተባት ያህል ደቅቃለች። የሕክምና ግብዓት መታጠቅ የዜጎቿን ሕይወት ሊታደግ ባለመቻሉም አንዳች ተዓምር ከሰማይ መጠበቋን በይፋ አውጃለች።
ለወትሮው በችግር፣በበሽታና በቸነፈር ቆዳቸው የደነደነ ተደርገው የሚቆጠሩት አፍሪካውያን ለችግርና መከራ ምንጭ ተደርገው ይታዩ ነበር። ይህ እውነት በኮሮና አይሰራም። ከሃያላኑ ጉያ የበቀለው ኮሮና ለዓለም ሕዝብ እኩል ፈተና ደቅኗል፤የሞትን መራራ ጽዋ እኩል በማቅመስ ላይ ይገኛል። የችግሩ የሰለባ መጠን አሁናዊ ንጽጽር አፍሪካውያን የተሻሉ ይመስላሉ። ምንም እንኳን ወረርሽኙ ገና ነዳጅ ያገኘ ያህል በመቀጣጠል ላይ የሚገኝ ቢሆንም።
የኮሮና ቫይረስ ምን ጭንቀት ወለደ ?
የኮሮና ቫይረስ በቀላሉ ተገማች ወረርሽኝ እንዳልሆነ ይነገርለታል። በጤናው ዘርፍ በምርምር የዓለምን ቁንጮ ለተቆናጠጡ፣ በገንዘብ አቅም ተዝቆ የማያልቅ ሐብት ላካበቱ ድርጅቶችም በሽታው አልጨበጥ ያላቸው ይመስላል።
የየአገራት የጤና ዘርፍ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተላሚዎች አቅጣጫ ለመንደፍ ተቸግረዋል። ለወረርሽኙ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆን መድኃኒትም በማማተር ላይ ናቸው። አዎ ወረርሽኙ ለተመራማሪም ሆነ ለተመርማሪ እስትንፋስ አይሰጥም፤ይልቁንም እስትንፋስን ይሻማል እንጂ። የወረርሽኙ ተለዋዋጭ ባህሪና የመዛመት ፍጥነት ተዳምሮ የአለምን ሕዝብ ብርክ አስይዟል።
አገራት ምን መፍትሄ ዘየዱ?
በአለም ላይ ለሽርሽር ተመራጭ የሆኑ ዘናጭ ከተሞች አሁን ላይ ሰው ርቧቸዋል። የወረርሽኙ ማብቀያ የቻይናዋ ውሃን ከተማ የዜጎቿን ነፍስ ተሻምታ ያተረፈችበትን ስልት ሌሎች ቀስመውታል። ወረርሽኙ በቀላሉ መቆጣጠርና መግታት የሚችሉት አልሆነም። በዚህ የተነሳም አገራት በራቸውን ከርችመው ማሳለፉን እንደዋና መፍትሄ ቆጥረውታል። ለወረርሽኙ የተጋለጡ ዜጎቻቸውን በለይቶ ማቆያ(ኳረንታይም) በማስገባት ከንክኪ እንዲርቁ በማድረግ መንከባከቡ ወረርሽኙን ለመግታት ሌላው ተመራጭ ስልት ነው።
የየአገራት የኢኮኖሚ አቅም እዚህ ላይ ሚናው ላቅ ያለ ሆኖ ይስተዋላል። ቻይና በርካታ ለይቶ ማቆያዎችን የእኛ ቢጤዎቹ አይናቸውን ጨፍነው እስኪገልጡ ድረስ በሚያስብል ፍጥነት ገንብታ ለዜጎቿ ነፍስ ደርሳለች። የእሷን ፈለግ ተከትለው የአለም አገራት የጥረታቸውን ፍሬ እያጨዱ ይገኛሉ።
ወረርሽኙ ክትባትም ሆነ መድሐኒት ሊገኝለት ባለመቻሉ ከአለም ጫፍ እስከ ጫፍ በመፍትሄነት የሚወሰዱት ርምጃዎች እስከ አሁን ባለው ሂደት ተመሳሳይ ናቸው። የወረርሽኙ ተጠቂም ሆነ የሞት ሰለባ ልዩነት የሚስተዋለው በቂ ትኩረት በሰጡ እና ባልሰጡ አገራት መካከል እንደሆነም ይነገራል።
ይሄን ያህል ጉዳት ለማድረስ የበቃውም ከመነሻው ሳይሰፋ በቂ ቁጥጥር ስላልተደረገበት እንደሆነ በርካታ መረጃዎች ይገልጻሉ።
ዶክተር ሊ የኮሮና ቫይረስን አስከፊነት ለቻይና መንግስት ለማስረዳት በተደጋጋሚ ጥረት አድርጎ እንደነበረ ይነገራል። እንዲህ የሥርጭቱ ፍጥነት ‹‹ለያዥ ለገናዥ›› ያስቸገረው የወረርሽኙ በትር ሳይከፋ አስቀድሞ መላ ይገኝለት ዘንድ ሲወተውት የነበረው ዶክተር አድማጭ ጆሮ በመነፈጉ ነውም ይላሉ።
ይሁን እንጂ ቻይና ይፋ ካደረገችበት ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙን በቀላሉ እንዳልተመለከተችው ከተቆጣጠረችበት መንገድ መረዳት አዳጋች እንዳልሆነ የሚገልጹ አያሌ ወገኖችም አሉ። ከዚህ የጀመረው የአለም አገራት ጭንቀት መቋጫው የት ሊሆን እንደሚችል የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ የዘለቀ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ምን መማር ይገባታል?
የወረርሽኙን የዓለም ጭንቀት ለመረዳት ኢትዮጵያ መጠነኛ የመመልከቻ ጊዜ አግኝታለች። የወረርሽኙ ተጠቂ በአገር ውስጥ መገኘቱ ይፋ ከተደረገበት መጋቢት ወር መባቻ ጀምሮ ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ ውትወታው ቀጥሏል። መንግስት የወሰዳቸው ርምጃዎች በተለይም ከመጋቢት 13 እስከ 15 ድረስ የተወሰዱ የአየር በረራዎችን ማቋረጥ፣ የአገሪቱን ድንበሮች መዝጋት፣የመንግስት ስራ እስከ 90 በመቶ መዝጋት፣ የግል ንጽህናን የመጠበቅ፣መሸታዎችን መዝጋት እና ሌሎችም ርምጃዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ነገር ግን በአለም አገራት ከሚስተዋሉ ሁኔታዎች ጋር ሲነጻጸር ወረርሽኙን በዚህ ሂደት መቆጣጠር የሚቻል አይመስልም። ሕብረተሰቡ በእምነት ተቋማት፣ በጤና ሚኒስትር፣በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በመንግስት በኩል የሚሰጡ የመከላከያ ምክሮችን ሰምቶና ተቀብሎ የመተግበር ሰፊ ችግር እየተስተዋለ ይገኛል። በተለይም ማህበራዊ ርቀትን በመጠበቅ በኩል እና በትራንስፖርት አጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› የሚያስብሉ በመሆናቸው ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ሙሐመድ ሁሴን