ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን
ውድ የሀገሬ ሕዝቦች
የለውጡን ጉዞ ሁለተኛውን ዓመት የምናከብረው በአንድ በኩል ፈተናና ስጋት በሌላ በኩል የተስፋ ውጋገን ከፊታችን እየታየን ነው። ሀገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በለውጥ ሂደት ያገኘቻቸውን ተስፋዎች ለማፍካት፣ ያጋጠሟትን ሳንካዎች ደግሞ ለማስተካከል እየጣረች ባለችበት ወሳኝ ወቅት መላው ዓለምን በጥቂት ወራት ውስጥ በቁጥጥሩ ስር ያዋለው የማይታየው ጠላት የኮሮና ቫይረስ በእኛም አገር አሻራውን አሳርፏል። በእስካሁን ጉዞው 200 የሚጠጉ ሀገራትን ያዳረሰው ይህ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችንም ገብቶ 29 ሰዎችን የቫይረሱ ተጠቂ አድርጓል። ነገ ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ በእርግጠኝነት ባናውቅም ሁላችንም ተረባርበን በዝቅተኛ ጉዳት እንደምናስቆመው ግን ሙሉ እምነት አለን።
ሀገራችን በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ስታልፍ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም፤ የመጨረሻዋም ላይሆን ይችላል። በለውጡ ጉዞ የመጀመሪያው ምዕራፍ ወቅት በሶማሌ ክልል የተነሳውና በመሳሪያም፣ በጭካኔም እስካፍንጫው ታጥቆ የነበረው ኃይል በስልጣን ጥም ታውሮ አጎራባች ክልሎችን ሰላም ከማናጋት አንስቶ ክልሉን እስከመገንጠል የተለጠጠ ፍላጎት የነበረው ሲሆን፤ የለኮሰው እሳት የአፍሪካ ቀንድን እስከመረበሽ ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ መፈጠሩ አይካድም። ያም ሆኖ የለውጡ ዓላማ ኢትዮጵያን በፍትሕ የላቀች፣ በዴሞክራሲ የዳበረች፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ የተመሰገነች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በሰላምና በደህንነት የተረጋጋች ሀገር ማድረግ ነበርና ከፈተናው ጎን ለጎን በተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ያ መጥፎ አጋጣሚ አልፎ እዚህ ደርሰናል።
በተመሳሳይ የታጠቁ ኃይሎች በወለጋ እና በሌሎች የምእራብ ኦሮሚያ ክፍሎች ላይ የጥፋት በትራቸውን አሳርፈው ባንክ እየዘረፉ፣ ሰው እየገደሉ፣ ቤት እያቃጠሉ፣ መንገድ እየዘጉ፣ ትምህርት ቤት እየዘጉ ነዋሪውን እያማረሩ የነበረበት፤ ከገጠር ቀበሌዎች አልፎ እንደ ነቀምት፣ ጊምቢ እና ሻምቦ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ መንግሥታዊ መዋቅርን ለማፈራረስ የተንቀሳቀሰበት፤ የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎች ያለወታደራዊ አጀብ የሚያስቸግሩበት
ጊዜያትን አስተናግደናል። የለውጥ ጉዞው ይሄንንም መጥፎ ጊዜ አልፎ አሁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን እያጣደፍን፣ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶቻችንን በማጠናቀቅ ተስፋችንን ሳይሆን ሪቫን እየቆረጥን ዛሬ ካለንበት ደርሰናል።
በአንድ ቀን በአማራ ክልል ጠንካራ ጓዶቻችንን በግፍ አጥተን፤ በአዲስ አበባ ተወዳጅ የጦር መሪዎቻችን ተገድለው፤ ውጥረቱ ለድፍን ኢትዮጵያ ተርፎ የነበረበት ጊዜ አልፏል። እዚህና እዚያ እሳት በተለኮሰ ቁጥር ጥፋተኛው ይህና ያኛው ቡድን ነው እየተባለ፤ በየአካባቢው ሃያና ሰላሳ የታጠቀ ጦር ሠራዊት ያለ እስኪመስል ድረስ በየቦታውና በየጊዜው ሰዎች እየተገደሉ፤ አንድ ሰው አልበቃ ብሎ መንደር በሙሉ በእሳት ይጋይ የነበረበት፤ እልቂቱ በአንድ አካባቢ ሳይወሰን፣ ሁለትና ሦስት ክልሎችን ያነካካበት፤ ዜጎች ኢትዮጵያ ልትበታተን ትችላለች በሚል ስጋት ውስጥ እንዲቆዩ የሆነበት አስጨናቂ ጊዜን ተረማም ደናል።
ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ንግግር ወንድም እህቶቻችንን የተቀጠፉበት፤ በትንሽ በትልቁ የህግ የበላይነት ያበቃለት፣ ኢትዮጵያም ያከተመላት እንዲመስል ተደጋጋሚ የጥፋት ርምጃዎች የተካሄዱበት ወቅት አልፎ ከሞላ ጎደል ወደ ሰላማችን ተመልሰናል። የለውጥ ጉዞው በየጊዜው የሚገጥሙትን ጋሬጣዎች ከመሻገር ባለፈ የተለያዩ የሪፎርም ተግባራትን ለማከናወን የተንቀሳቀሰበት ወሳኝ ወቅትም ነበር። በዚህም፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያችንን መሬት እንዲረግጥ ለማድረግ፤ ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችል የዱይንግ ቢዝነስ ማሻሻያን በፍጥነት ለመተግበር፤ ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር ስኬታማ ድርድር ለማካሄድ፤ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የብድርና የእርዳታ ተቋማት ጋር ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የሚያስችሉ ውጤታማ ስምምነቶችን ለማድረግ ችለናል። በባንኮች ላይ የነበሩ የአሠራር ጫናዎችን ለማቃለል፣ ለሰብዓዊ መብትና ለጋራ ተጠቃሚነት እንቅፋት የሆኑ ሕጎችና አሠራሮችን ለማስተካከል፤ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ሳይከሰቱ ለማምከን የሚያስችል አቅማችንን ለማደርጀት፤ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ግለሰቦችን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል በሙሉ አቅማችን ተንቀሳቅሰናል። ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እያመሩ የነበሩ በዩኒቨርሲቲዎችን ወደ መልካም መማር ማስተማር ሂደት ማምራት የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ሀገራችን ብልጽግና እና ስለ ወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ ማሰብ በጀመርንበት ወቅት እነሆ ሌላ ጋሬጣ ከፊታችን ቆሟል። ምንም እንኳ ፈተናው የመጣው ለመላው ዓለም ቢሆንም ከፊታችን የተደቀነውን ችግር ለመጋፈጥ እንደ ቀደሙት ጊዜያት ጉልበታችን ላፍታ ሸብረክ እንደማይል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ሁሌም እንደምናደርገው ሕዝባችንን አስተባብረንና አቅማችንን ደምረን በድል ከተሻገርነው በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጀመርናቸው ሀገራዊ ሪፎርሞች ፊታችንን እንደምናዞር ጥርጥር የለኝም።
ሀገራዊ ለውጥን በጽኑ መሰረት ላይ የመትከል ትግላችንን ጊዜያዊ ፈተና አይገታውም። አሁን በዓለም ደረጃ የተከሠተውን ዓይነት ፈተና ወደፊትም ይገጥመን ይሆናል። “ስለ ነገ በትክክል ለመተንበይ የተሻለው ዘዴ ዛሬ ላይ ሆኖ የወደፊቱን መፍጠር ነው” እንዲሉ ለሚገጥሙን ፈተናዎች የዝግጁነት አቅማችንን እያሳደግን እንቀጥላለን። ኢትዮጵያን ከፈተናዎች በላይ እንድትሆን አድርገን ለመገንባት የሁላችንም ርብርብ ይጠይቃል። እስካሁን ባለው ጉዟችን የሀገራችንን ኢኮኖሚ፣ ተቋማቶቿን፣ የፍትሕ ሥርዓቷን፣ ማኅበራዊ ደህንነቷን፣ የሕግ አስከባሪ አካላትን፣ የጤናና የትምህርት ሥርዓቷን በማጠናከር ፈተናዎችን መቋቋም በሚችሉበት ደረጃ ለማደራጀት ጠንካራ የአቅም መሠረት መጣል ጀምረናል። አቅም ግንባታ ስትራቴጂያዊ ዕይታን የሚጠይቅ፣ ተከታታይ ስራን የሚፈልግ እና ፈጽሞ የማያቋርጥ ረጅም ሂደት መሆኑ ግልጽ ነው። ይህም ደግሞ እንደኛ ድሀ በሆኑ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ግንባር ቀደም የሆኑትን ጭምር የሚመለከት መሆኑ የሰሞኑ ዓለም አቀፋዊ ፈተና ምስክር ነው።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንኳን እኛን ጠንካራ የጤና መሠረተ-ልማት የገነቡትን ምዕራባውያን ምን ያህል እያስጨነቀ እንዳለ ሁላችንም እንገነዘባለን። በብዙ ሀገራት ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ ሰነባብተዋል። በድንበሮች አካባቢ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፤ የንግድና ሥራ እንቅስቃሴዎችም በከፊል ተቋርጠዋል።
የዶላር ግኝት አለኝታችን የሆነው እና ከሀገራችን አልፎ የአፍሪካችን የኩራት ምንጭ የሆነው አየር መንገዳችን እንቅስቃሴው በከፊል ተገቷል። የአበባ
ኤክስፖርት ንግዳችን የሚያንሰራራበት ጊዜ በውል ባልታወቀ አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅሯል። በኤክስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፋይናንስ ዘርፎቻችን ላይ የተደቀነው ተግዳሮት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምንም እንኳ እየገጠመን ያለው ችግር ከዚህ በፊት እንዳየናቸው አደጋዎች የማያልፍ ቢመስልም ማለፉ ግን አይቀርም። ስለተመኘን ሳይሆን በትብብር ስለምንሰራ ይህ ጊዜ ያልፋል። ከወዲሁ እውቀታቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በመስጠት የትብብር አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ እያሳዩን ያሉ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ምስክር ናቸው።
ውድ የሀገሬ ህዝቦች!
የለውጡን ጉዞ ሁለተኛ ዓመት ስንዘክር ምን ዓይነት ኢትዮጵያ እንገንባ የሚለውን እያሰብን መሆን አለበት። ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች፤ለኢንቨስትመንት ተመራጭ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ማዕከል የማድረግ ርዕይ በውስጣችን ልንሰንቅ ይገባል። ሰላሟና ደህንነቷ የተረጋገጠ፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያገናዘበች፤ በአፍሪካ ለቱሪስቶች ተመራጭ የሆኑ መዳረሻዎች ያሏት፤ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶቿን በሚገባ ማልማት የምትችል ሀገር መገንባትን ታሳቢ ማድረግ ይጠበቅብናል።
ይህችን ብሩህ ተስፋ የሰነቀች ሀገር ተሳክቶላት ለማየት ካለፉት ስህተቶቻችን እየተማርን፣ ያሉንን ወረቶች ይዘን፤ ከሚያራርቁን ይልቅ ለሚያቀራርቡን ነገሮች ትኩረት እየሰጠን፤ ከትናንት ይልቅ ነገ ላይ እያተኮርን መጓዝ አለብን። ዓለም ከነገ ጋር ለመወዳደር እየሮጠ ነው።ተወዳድረን ማሸነፍ ከፈለግን መሮጥ ቀርቶ መራመድ፣ መራመድ ቀርቶ መቆም፣ መቆም ቀርቶ መተኛት ለእኛ ፍጹም አያዋጣንም። ያለችንን ጥቂት ጉልበት ይዘን ሽምጥ ለመፈትለክ መፍጨርጨር ነው ምርጫችን። ሙሉ ትኩረታችንን ታላቁ ሀገራዊ ዓላማ ላይ አድርገን ከተጓዝን ከወጀቡ ባሻገር በስኬት እንሸለማለን።
በመጨረሻም ቀጣዩ የለውጥ ዘመን ካሳለፍናቸው ሁለት የለውጥ ምዕራፎች የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ሀገራችንን ወደሚገባት ምእራፍ እንደምናደርሳት አምናለሁ። ለዚህ ደግሞ የሁላችን የሥራና ጸሎት ሕብረት ያስፈልጋታል። ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ባሉ የተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች፤ ከአርሶና አርብቶ አደር ማህበሮች እስከ ንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከላት፤ በተለያየ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሙያተኞች፤ ልሂቃን፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፤ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ በየግንባሩ የተሰለፋችሁ የሠራዊት አባላት፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ይመለከተናል የምትሉ ሁሉ ለሀገራችን ጉልበታችሁን ሳትሰስቱ እንድትሰጧት በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ተባበርን፣ ተደመርን፣ በአንድነት ወቅታዊ ፈተናችንን እንሻገራለን፤ የምንመኛትን፣ የምንጓጓላትን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገነባለን። የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፣ መስሪያ ቤቶችና ድንበሮች ይከፈታሉ፤ የተቀዛቀዘ ኢኮኖሚያችን ዳግም ያንሰራራል።ላልተወሰነ ጊዜ የምናደርገው መራራቅ በመቀራረብ ይተካል። እንቅስቃሴዎች ሁሉ ወደነበሩበት ይመለሳሉ። ሞትም በሕይወት ይሸነፋል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
መጋቢት 24/ 2012 ዓ.ም
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መልዕክት ያልፋል አትጠራጠሩ!