ከረፋዱ 4፡00 ሆኗል፤ ፒያሳ አትክልት ተራ ተገኝቻለሁ። የአትክልት ተራ የሸማችና የሻጭ ትርምስ እንደተለመደው ቀጥሏል። ምነው ጊዜውን አልተገነዘባችሁም? የኮሮና ወረርሽኝ ፍራቻውስ እንዴት የለም? ስለ አካላዊ ርቀት ምን ያህል ግንዛቤው አላችሁ? ስል ጥያቄ በቦታው ላይ ላገኘኋቸው ሸማቾችና ሻጮች ጥያቄ አነሳሁ።
‹‹እንዴት አልገነዘብም? ወቅቱ ዓለም በወረርሽኝ ፍዳዋን እየያች የምትገኝበት ነው። ኢትዮጵያ መግባቱንም ሰምቻለሁ፤ ሃያ ምናምን ሰው ተይዟል ያሉ መሰለኝ። ሰው ቤቱ እንዲቀመጥ መንግስት እየመከረ ይገኛል። ሰው ከሰው መነካካት እንደሌለበትም እያስተማሩ ነው። አትክልት ተራ ይሄን መተግበር እንዴት ይቻላል? እስኪ ተመልከት! ከዚህ ግብግብ ውስጥ እንኳን አለመነካካት ደህና ጉልበት ያልያዘም መግባት አይችልም። እኔ ሥራ አቁሜ ከቤቴ ብቀመጥ ከልጆቼ ጋር ከኮሮና በፊት ርሃብ ይጨርሰኛል። ሶስት ልጆች አሉኝ። እዚህ አትክልት ተራ በቀን ስራ (እየተሸከምኩ፣ እየጫንኩ፣ እያደረስኩ) በማገኘው ገንዘብ ነው ቤተሰቦቼን ቀጥ አድርጌ የማስተዳድረው። በተጨማሪም በሴፍትኔት የሚከፈለኝ ትንሽ ገንዘብ ያግዘኛል። አሁን እንደውም ጭንቀቴ ስራ ከነአካቴው የቆመ እንደሆነ ብዬ ነው›› ያሉት በሸክም ስራ ተሰማርተው ያገኘናቸው አቶ በቀለ እሸቴ ናቸው።
ሌላዋ በፒያሳ አትክልት ተራ በአስቤዛ ሸመታ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ፋንታው ይባላሉ። የሁለት ልጆች እናት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ወቅቱ እርሱ(ፈጣሪ) መድኃኒቱን ካልፈጠረልን የከፋ እንደሆነ ገልጸዋል። ፈጣሪ መድኃኒት እስኪያስገኝለት ድረስ ለምን በእጃችን ያሉትን መከላከያዎች መጠቀም አቃተን? ከንክኪ ብንርቅና ከቤታችን መቀመጥ ብንችል ከበሽታው ልንድን እንደምንችል ባለሙያዎቻችን እየመከሩ እኮ ነው፤አልሰሙም እርስዎ? በሚል ያነሳሁላቸውን ሲመልሱ፤ “ማን ቤቱ ቢቀመጥ የሚጠላ ይመስልሃል? አብዛኛው ማህበረሰብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ከቤቱ ሳይወጣ መዋል የሚችል ሰላልሆነ እንጂ” ሲሉ ችግሩን ገልጸዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል ማህበራዊ ርቀትን ጠብቆ ለመንቀሳቀስ ቦታ መምረጥ አስፈላጊ እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ ኤልሳቤት፣አትክልት ተራ ይሄን መተግበር እንደማይቻል አስረድተዋል።
‹‹ ስንቱን አትንካኝ ብለህ ትዘልቀዋልህ? እንደምታየው ሕብረተሰቡ እኮ ስጋት አድሮበታል። አልፎ አልፎ አፍና አፍንጫውን የሸፈነ ሰው ትመለከታለህ። አለመነካካትን ግን ለመተግበር የሚሞክር ሰው ምንም የለም። በሰው ጢሻ ውስጥ ፈልፍለህ በማለፍ እኮ ነው የምትፈልገውን እቃ የምትገዛው›› በማለት ተናግረዋል ወይዘሮ ኤልሳቤጥ።
በፒያሳ አትክልት ንግድ ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው አቶ ሙሰማ ሽፋ በበኩላቸው፤ ኮሮና እዚህ የተከሰተ እንደሆነ በጅምላ እልቂት ሊያደርስ እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል። አሁን ላይ በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት የተነሳ የሚሸተው የአትክልት ተረፈ ምርት በአጭር ጊዜ እየተነሳ መሆኑን ገልጸው፣ ማህበረሰቡ አለመነካካትን በመጠበቅ እና መተፋፈግን በመቀነስ በኩል ግን ምንም ጥንቃቄ እየተደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሰው ግንዛቤ የሌለው ስለሆነ አይደለም። አትክልት ተራ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች የሚሸጡና የሚገዙበት ቦታ በመሆኑ ነው። የሰዎች ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ ሲሄድ ቦታው ጠባብ በመሆኑ መጨናነቁ ይፈጠራል። አሁንም ወረርሽኝ ተከስቷል ብሎ የሰው ቁጥር አልቀነሰም።
እንደውም ስራ የዘጉት ሁሉ ጊዜ ስላለኝ በሚል እዚህ አትክልት ተራ እየመጡ አስቤዛቸውን እየሸመቱ እንደሆነም አቶ ሙሰማ አብራርተዋል።
አሁን አትክልት ተራው ወደ ጃንሜዳ በጊዜያዊነት ይዛወራል ቢባልም ማህበራዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ እና ባለመነካካት ወከባ የበዛበትንና ሕገወጥ ስራዎች ከሕጋዊው ባልተናነሰ የሚስተዋሉበትን የአትክልት ንግድ መልክ ማስያዝ አስቸጋሪ እንደሚሆን አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ሙሐመድ ሁሴን