ወጣት ረሺድ ተሺታ በአንድ ጥግ ላይ በእጁ የያዘውን አነስተኛ ሻንጣ ጉልበቱ ላይ አድርጎ ተንተርሶ ተኝቷል፡፡ አብረውት ያሉት ሶስት ጓደኞቹ ላይም የድካም ስሜት ይነበባል፡፡ ረሺድና ጓደኞቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሻሸመኔ ለመሄድ ቃሊቲ መለስተኛና አገር አቋራጭ መናኸሪያ ግቢ ውስጥ ሆነው ትራንስፖርት ሲጠብቁ ነው ያገኘኋቸው፡፡ እነርሱ ወደሚፈልጉበት ሥፍራ የሚሄድ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለ ቢነገራቸውም ተስፋ አልቆረጡም:: ችግራቸውን እንደነገሩኝ ከአንድ ወር በፊት ተቀጥረው ይሰሩበት የነበረው የህንጻ ግንባታ ሥራውን በማቋረጡ ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ሥራ ከሌላቸው መኖሪያም ሆነ የዕለት ኑሮአቸውን ለመምራት ይቸገራሉ:: ያላቸው ምርጫ ወደቤተሰቦቻቸው መመለስ ነው፡፡
እንደ ወጣት ረሺድና ጓደኞቹ በመናኸሪያው ግቢ ውስጥ ብዙ መንገደኞች እንደነበሩ በሥፍራው በነበርኩበት ወቅት ከአንዳንዶች ተረድቻለሁ፡፡ ለወትሮ
ከመግቢያው በር ጀምሮ ወከባ የነበረበት ግቢ እንቅስቃሴው ተቀዛቅዟል፡፡ በመካከለኛ ሀገር አቋራጭ ወደ ዱከም፣ቢሾፍቱ፣ሞጆ፣ናዝሬት ከሚያጓጉዙት በስተቀር የሀገር አቋራጭ ጉዞ ከሁለት ቀናት በፊት መቆሙን በትራንስፖርት ዘርፉ ካሉት ባለሙያዎች መረዳት ችያለሁ፡፡
መርካቶ የሚገኘው ከፍተኛ ሀገር አቋራጭ አዲስ ከተማ መናኸሪያ በደረስኩ ጊዜ በግቢው ውስጥ ተሽከርካሪዎች አልነበሩም፡፡ መናኸሪያው ዝግ ነበር፡፡ በመናኸሪያው የክትትልና ስምሪት ሰራተኛ አቶ ታፈሰ በረደድ እንደገለጹልኝ፣ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ አገልግሎቱ ተቋርጧል:: ተቸግረው የነበሩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን መታወቂያቸውን በማየት ትናንት ወደ ባህርዳርና ደብረማርቆስ ሁለት ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ውስጥ 60 ተማሪዎች በታሪፉ አገልግሎቱ እንደተሰጣቸውና ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭነቱ እንዳይኖር አስፈላጊው ቅድመ መከላከል በማድረግ እንደተሸኙ አመልክተዋል፡፡ ተማሪዎች በመሆናቸውና
ሰሞኑንም ወደየ አካባቢያቸው ይሸኛሉ የሚለው መረጃ በመገናኛ ብዙሃን በመተላለፉ በሚደርሱበት ሥፍራ እንደማይጉላሉ ተስፋ አድርገዋል፡፡
በወትሮው በመናኸሪያው በቀን ቁጥሩ እስከ 80 የሚደርስ ተሽከርካሪ አገልግሎት እንደሚሰጥና እስከ አምስት ሺ የሚደርስ ተገልጋይም እንደሚስተናገድ ይናገራሉ፡፡ በየዕለቱ የሚሰጠው አገልግሎት በዙሪያው ያለው ግርግር በሁለት ቀናት ውስጥ ያ ሁሉ እንዳልነበር መሆኑ እንግዳ ሆኖባቸዋል:: የበሽታው አሳሳቢነትንም እንደሚያሳይ
ይገልጻሉ፡፡ በሽታው ተወግዶ ወደ ቀድሞ ተግባራቸው ለመመለስ ተመኝተዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ከእርሳቸው ጀምሮ እያንዳንዱ ሰው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
የመናኸሪያዎቹ ሥራ መቀዛቀዝ በዙሪያቸው የምግብና የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት የሚተዳደሩና የቀን ሠራተኞችንም ከሥራ ያስተጓጎለ መሆኑም ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ግን በፍጥነት እየተዛመተ ያለውን ወረርሽኝ ለመከላከል ያለው ቁርጠኝነት እጅግ አናሳ እንደሆነ በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ታዝቢያለሁ፡፡ በተለይ ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው አትክልት ተራ በሽታው ስለመኖሩ የሚታወቅ አይመስልም፡፡ ከጥቂት ነገዴዎችና ሸማቾች በስተቀር ግብይታቸው ጥንቃቄ የጎደለው ነው፡፡
ርቀታቸውን ለመጠበቅ ገመድ ያሰሩ ቢኖሩም የገንዘብ እና የዕቃ ቅብብሎሹ በጥንቃቄ ሲከናወን አላየሁም፡፡ አንዳንድ ያነጋገርኳቸው ሸማቾች በሰጡት አስተያየት የሰው ብዛቱ ይኖራል ብለው ከገመቱት
በላይ ሆኖባቸዋል፡፡ ከወትሮው ይቀንሳል ብለው በማሰብ እንደሄዱም ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹም በአካባቢያቸው የዋጋ ውድነት በመኖሩ ቅናሽ ፍለጋ እንደመጡ ይገልጻሉ፡፡
በገበያው ሥፍራ ውሃና ሳሙና በተወሰነ የርቀት ቦታ ቢኖርም የሚያስተውለው ሰው አልነበረም፡፡ ሁሉም የሄደበትን ጉዳይ ሲፈጽም ነው ያስተዋልኩት፡፡ በአካባቢው በጥበቃ ሥራ ላይ ያገኘኋቸው አቶ አረጋ እውነቱ ሸማቹ ለጥንቃቄው ቦታ የሰጠው አይመስልም ይላሉ፡፡ በአካባቢው በድምጽ ማጉሊያ ቅስቀሳ በመደረግ ላይ መሆኑን እና እርሳቸውም በሚችሉት ሁሉ ሰው እንዳይዘናጋ ጥረት ቢያደርጉም የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡
አትክልት እየሸጠ ያገኘሁት ረሺድ ሁሴንም አብዛኛው ሸማች ትኩረቱ የሚገዛው ዕቃ ላይ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ረሺድ አፉን ቢሸፍንም ከሸማች ጋር ያለውን ንክኪ የሚከላከልበት የቅድመ ንጽህናም ሆነ የእጅ ጓንት እየተጠቀመ አልነበረም፡፡ ሥራው ለቅድመ ጥንቃቄ ምቹ እንዳልሆነ ነው የገለጸልኝ፡፡
በስፍራው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መሳሪያዎች (ማሽነሪ) መሸጫ ሱቅ ውስጥ ያገኘሁት ፈይሳ ታደሰም ትዝብቱን አካፍሎኛል፡፡ እርሱ እንዳለው፤ በአካባቢው ይቆሙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ አላስተዋለም፡፡ ቀደም ሲል እስከ ረፋድ ሶስት ሰዓት ድረስ በስፍራው የሚቆዩ አትክልት የሚያራግፉ ተሽከርካሪዎችም የሉም፡፡ የሰው ቁጥር ግን አልቀነሰም፡፡ ህዝቡ ማድረግ ስላለበት ጥንቃቄ ትኩረት አድርጓል ብሎ አያምንም፡፡ አካባቢው እንደተባለው ከህዝብ ንክኪ አለመራቁ ብቻ ሳይሆን የጽዳት ጉድለቱም እንዳለ ነው፡፡ ቸልታው እስከ መቼ ይቀጥላል?
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012
ለምለም መንግሥቱ
የትራንስፖርት አገልግሎት ትዝብት በአትክልት ተራና መናኸሪያ ዙሪያ