አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አገልግሎቱን እንደማያቋርጥ አስታወቀ፡፡ የቫይረሱ መከሰት በባንኩ ላይ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳስከተለም የባንኩ ፕሬዚዳንት ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤ ሳኖ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ባንኩ በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ተከትሎ አገልግሎቱን አያቋርጥም፡፡ ምናልባት ሁኔታዎች ተባብሰው አንዳንድ የመንግስት ተቋማት እስከ መዘጋት ቢደርሱ እንኳን ባንኩ በተወሰነ የሰው ኃይልም ቢሆን አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል፡፡ ባንኩ ከ70 እስከ 80 በመቶ ለሚሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት አቶ አቤ ደንበኞች በኮረና ቫይረስ ምክንያት የባንክ አገልግሎት እናጣለን የሚል ስጋት ሊይዛቸው አይገባም ብለዋል፡፡
‹‹በዚህ ወቅት የባንክ አገልግሎት ከሆስፒታል አገልግሎት ተለይቶ አይታይም›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሆስፒታሎች በዚህ ችግር ወቅት ለህብረተሰቡ ደራሽ እንደሆኑ ሁሉ ባንኩም ደንበኞቹ የኢኮኖሚ ችግር እንዳይገጥማቸው ያለበትን ሕዝባዊ ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል፡፡ ይልቁንም ህብረተሰቡ ‹‹ባንክ ይዘጋል›› በሚል የተሳሳተ አረዳድ በባንክ ቤቶች አካባቢ በርከት ብሎ መገኘቱ የቫይረሱን ስርጭት የሚያባብስ ስለሆነ ገንዘብ በሚያስፈልግ ጊዜ ብቻ የተለያዩ አገልግሎቶችን ተጠቅሞ ማግኘት እንዲችል መክረዋል፡፡
በባንኩ አሰራር መሰረት የደንበኞች ምልልስ በጥሩ ጎን የሚተረጎም መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ አሁን
ካለው አስገዳጅ ሁኔታ አንጻር ደንበኞች ጉዳያቸውን በአንድ ጊዜ ፈጽመው ቢሄዱ ለራሳቸው ደህንነትም ሆነ ለተያዘው የቫይረሱን ስርጭት የመቆጣጠር ዘመቻ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ከእኛ ቀድመው በችግሩ ከተፈተኑ ሀገራት የመማር ዕድል ማግኘታችን ዕድለኞች ነን›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ ባገኘነው አጋጣሚ ተጠቅመን የቫይረሱን ስርጭት በመቆጣጠር በአጭር ጊዜ ከገባንበት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ቀውስ በፍጥነት ለመውጣት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ ከጉዳዩ ክብደት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን በመጠቆምም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚተላለፈውን መልዕክት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው መክረዋል፡፡
በሌላ በኩል ባንኩ ከኮረና ቫይረስ መከሰት ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳጋጠመው ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውርን እየጎዳ ያለ ክስተት እንደመሆኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይም ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል፡፡ የገቢና የወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በባንኩ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ ወረርሽኙ በተለይም በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ እጥረት እንዳስከተለና የግብይት ስርዓቱን እንዳስተጓጎለው፤ የሃዋላ አገልግሎ ንም እያደናቀፈ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይበልጥም በገቢ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደንበኞችን እንቅስቃሴ ገድቦታል ብለዋል፡፡ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩና በእጃቸው ብዙ ምርት የያዙ ደንበኞችም ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል፡፡ ኮሮና ቫይረስ በባንኩና በደንበኞች መካከል ያለውን ግንኙነት እያጠበበውና ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ለጊዜው የኮሮና ቫይረስ መከሰት በባንኩም ይሁን በደንበኞች ላይ ያደረሰውን ጉዳቱ በዝርዝር ማወቅ ባይቻልም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እየገታ መምጣቱ ግን በይፋ እየታየ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012
ኢያሱ መሰለ