•ምዕመናን ፀሎት በየቤታቸው እንዲፈፅሙ ወሰነ
•መንፈሳዊ አገልግሎት በተወሰኑ ካህናት እንዲሰጥ አሳሰበ
•የተለያዩ ተቋማትን ለህሙማን መርጃ እንደሚያውል ገለፀ
•የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከዛሬ ጀምሮ ምዕመናን በየቤታቸው በፀሎት እንዲወሰኑና መንፈሳዊ አገልግሎት ሥርዓተ ቅዳሴን ጨምሮ በተወሰኑ ካህናት እንዲሰጥ ውሳኔ አሳልፏል።
ሲኖዶሱ በዓለምና በአገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን ወቅታዊውን የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምክንያት በማድረግ ትናንት በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው፤ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የቆየውና በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ መግባቱ የተረጋገጠው የኮሮና ቫይረስ በሽታ ዕለት ዕለት እየተስፋፋ ጥቂት የማይባሉ ወገኖች በወረርሽኙ መያዛቸውን ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ወረርሽኙ ከዚህ በላይ እንዳይስፋፋና በቀጣይም ሌሎች ወገኖች በበሽታው እንዳይጠቁ መከላከሉ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ በመሆኑ ቋሚ ሲኖዶስ በትናንትናው ዕለት ስብሰባ በማድረግ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል።
በውሳኔውም በአሁኑ ጊዜ ወረርሽኙን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለውን የጤና አጠባበቅ ምክርና ትምህርት እንዲሁም በፍትህ መንፈሳዊ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በጣም በተወሰኑ ካህናት መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ፤ ሌሎች ካህናትና ምዕመናን ለጊዜው በየቤታቸው በጸሎት እንዲወሰኑ፤ በአገልግሎት ላይ ለሚገኙ አገልጋይ ካህናትም በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ እንዲወሰኑ ሆኖ አስፈላጊው ሠርከ ህብስት (የምግብ አቅርቦት) እንዲዘጋጅላቸው እንዲደረግ፤
በዚህ ወቅት የወረርሽኙን ፍጥነት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ በቀጣይ በበሽታው ለሚያዙ ወገኖች ማቆያ የሚሆን ቦታ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ከአዲስ አበባ ጀምሮ በመላው አህጉረ ስብከት የሚገኙ መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማትና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግላቸውና መሟላት የሚገባቸው ሁሉ ተሟልቶ ለሕሙማን ማቆያ እንዲውሉ፤ ተቋማቱም ወረርሽኙ እስኪያልፍ ድረስ ለህሙማን አገልግሎት መስጫ እንዲሆኑ የሚመለከተው አካል ተረክቦ ህሙማንን እንዲያስተናግድባቸው ተውስኗል።
በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በወረርሽኙ ምክንያት መንግሥት ሕሙማንና የተቸገሩ አካላትን ለመርዳት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ከመንበረ ፓትርያርኩ ለጊዜው ብር ሶስት ሚሊዮን ብር በመንግሥት ደረጃ ለተቋቋመው ዕርዳታ አሰባሳቢ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የተሰጠ ሲሆን፤ በቤተ ክርስቲያኗ ሥር በሚገኙ የሕጻናት ማሳደጊያ ቦታዎች የሚገኙ ሕጻናትንና ችግረኞችን በምግብና በንጽሕና መጠበቂያ መደጎም የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ፤ አስፈላጊውን ዕርዳታ የማሰባሰብ ሥራ በቤተ ክርስቲያኗ ሥር በተቋቋመው ተስፋ ግብረ ኃይል በኩል የማስተባበሩ ሥራ እንደሚሰራ ተገልጿል።
እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተያዘው የጾምና የጸሎት ጊዜ ምክንያት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ጸሎት ቅዳሴውን በመምራትና በመባረክ መቆየታቸውን ቋሚ ሲኖዶሱ ጠቁሟል፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ያለው ወረርሽኝ በእጅጉ እየተስፋፋ በመሆኑ የተለየ አባታዊ ጸሎትና ሱባኤ የሚያስፈልግ ወቅት ሆኖ በመገኘቱ፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከትናንት መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለዓለም ሰላምና ለሕዝቦች ደህንነት ሲባል ለጊዜው ለብቻቸው ተለይተው በልዩ የጾምና የጸሎት የሱባኤ ጊዜ እንዲቆዩ ቋሚ ሲኖዶስ ወስኗል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012
ሶሎሞን በየነ