አዲስ አበባ፡- በተለያዩ መንገዶች ስለ ኮሮና ቫይረስ ግንዛቤዎች እየተሰጡ ቢሆንም ህብረተሰቡ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ክፍተቶች በመታየታቸው ተጨማሪ እርምጃዎች በቀጣይ ሊወሰድ እንደሚችል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ተገለጸ፡፡
ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በአዲስ አበባ በጦር ኃይሎችና በአየር ጤና አካባቢ በመገኘት ለነዋሪዎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን አስተምረዋል። ዶክተር ሂሩት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ህብረተሰቡ እርቀቱን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ በተለያዩ ጊዜያት ግንዛቤ ቢሰጥም ተግባራዊ አልሆነም፡፡ በዚህ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አስፈላጊ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡
ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት ከቤት ውጭ በመውጣት በገበያና በትራንስፖርት አካባቢዎች ላይ ያለ ጥንቃቄ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዶክተር ሂሩት፤ በተለያዩ መንገዶች እየተሰጡ ያሉ የግንዛቤ ሥራዎች ውጤት አለማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ዶክተር ሂሩት እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እና የጥንቃቄ መንገዶቹን ተግባራዊ ለማድረግ መጀመሪያ ህብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚነገረውን የጥንቃቄ መንገድ መተግበር አለበት፡፡ስለዚህ ኮሮና ምልክት ሳያሳይ እንደሚቆይና በቀላሉ እንደሚተላለፍ በመገንዘብ ጥንቃቄ ላይ ለመበርታት የሚያስችል አመለካከት መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዜጎች ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ባለመሰባሰብ፣ ከተቻለ ከቤት ባለመውጣት፣ ከወጡ ደግሞ ሁለት የአዋቂ እርምጃዎችን በመራራቅ፣ በማንኛውም ጊዜ እጃችንን ደጋግመን በመታጠብ እና ፊትን በምንም ምክንያት ባልታጠበ እጅ ባለመንካት፣ባለመጨባበጥ ቫይረሱን መከላከል እንደሚገባ ዶክተር ሂሩት አስተምረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012
መርድ ክፍሉ