አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በአረብኛ ቋንቋ በመጠቀም የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በግብጽ መገናኛ ብዙሃን በሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎች አማካኝነት የተዛባውን የአረቡ ዓለም አመለካከትን መቀየር እንደሚገባ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስተባባሪነት ‹‹ፍትሃዊነት እና የጋራ ተጠቃሚነት›› በሚል መሪ ሃሳብ የኢፌዴሪ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በተዘጋጀው መድረክ የአረብኛ ቋንቋ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ተንታኞች ትናንትና ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱን የመሩት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል አቶ ነስሩ አባጀበል እንደገለጹት፤ ግብጽ ስለግድቡ እያሰራጨች ያለውን ሃሰተኛ መረጃ ተከትሉ የተዛባውን የአረቡን ዓለም አመለካከት ለመቀየር በኢትዮጵያ ሰፊ የአረብኛ ቋንቋ ዘገባ እና መረጃ የማስተላለፍ ሥራ ሊከናወን ይገባል።
እንደ አቶ ነስሩ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ያለው የአረብኛ ቋንቋ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ የተዳከመ እና ትኩረት ያልተሰጠው ነው። በዚህ አጋጣሚ ደግሞ ግብጾች ሰፊውን የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ስለህዳሴው ግድብ የተዛባ መረጃ በሰፊው በማቀበል እየሰሩ ይገኛል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ዜጎች በአረብኛ ቋንቋ ተገቢውን እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለአፍሪካ አገራት አረብኛ ተናጋሪ ሀገራት በማሰራጨት ስለግድቡ በሰፊው ማስተዋወቅ አለባቸው። በኢትዮጵያ ሲዘጋጅም የመጀመሪያው በሆነውና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት የተካሄደው የአረብኛ ቋንቋ ላይ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃንን ያሰባሰበው የህዳሴ ግድብ ውይይትም የግብጽን የተሳሳቱ መረጃዎችን በማረም ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ይጠበቃል።
ሱዳናዊው ጸሐፊና ጋዜጠኛ ሃሊ ያህያ እንደገለጸው ደግሞ፤ ግብጽ በአረብኛ ቋንቋ የሚያስተላልፉ ጠንካራ መገናኛ ብዙሃን አሏት። መገናኛ ብዙሃኑንም ተጠቅማ ግድቡ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው የሚገልጽ ሰፊ የሃሰት መረጃዎች ለዓረቡ ዓለም ስታስተላልፍ ቆይታለች። በመሆኑም በኢትዮጵያ ደካማ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የአረብኛ ቋንቋ የመገናኛ ብዙሃን ሥራ በማሳደግ ጥራት ያለውና ትክክለኛ መረጃ በብዛት ስለማዳረስ ማሰብ ያስፈልጋል። የሱዳንና የግብጽ እንዲሁም የሌሎችም የአረብ ሀገራት ዜጎች ስለግድቡ ግንባታ እና ውሃ አሞላል በዋነኛነት መረጃ የሚያገኙት ከግብጽ መሆኑን የተናገረው ሱዳናዊው ሃሊ፤ ይህ ከአንድ ወገን የሆነ መረጃ በርካቶች ስለኢትዮጵያ ግድብ ያላቸውን አመለካከት መጥፎ አድርጎታል።
በመሆኑም ህዳሴ ግድብ ለተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም እንጂ ጥፋት እንዳልሆነ በአግባቡ ለማስረዳት ኢትዮጵያ የአረብኛ ቋንቋ መገናኛ ብዙሃንን በዋናነት መጠቀም አለባት። በኢትዮጵያ የአልአይን ዜና ማዕከል ዳይሬክተር ጋዜጠኛ አንዋር ኢብራሂም በበኩሉ እንደገለጸው፤ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ስለህዳሴ ግድብ በተመለከተ ከፍተኛ የመረጃ ጦርነት እያከናወኑ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቷ ያሉ የአረብኛ ቋንቋ መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅሞ ስለግድቡ አስፈላጊ መረጃዎችን ማስተላለፍ የሚችልበት እድል አለ። መረጃው መተላለፉ አረብኛ ቋንቋ የሚከታተሉ አድማጮችን እና አንባቢዎችን ከኢትዮጵያ ጎን ለማሰለፍ አይነተኛ ሚና አለው።
ለዚህም በኢትዮጵያ የሚገኙ የአረብኛ ቋንቋ ላይ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃንን በማጠናከር መጠቀም እንደሚያስፈልግ የአረብኛ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጠቃሚ ውይይት አካሂደዋል። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ስለህዳሴው ትንተና የሚሰጠው መሃመድ አልአሩሲ በበኩሉ እንደተናገረው፤ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሱዳን ፤ ግብጽ እና ኢትዮጵያን በጋራ የሚያስተሳስር እንጂ ግብጽን የሚጎዳ አለመሆኑ እስከአሁን በአረብኛ በሚገባው ልክ አልተነገረም። ግብጽ በፊናዋ ከምታሰራጨው ግድቡ ይጎዳኛል ከሚል የተሳሳተ መረጃ ውጪ በኢትዮጵያ በኩል አረብኛን ተጠቅሞ እምብዛም ሥራ አልተከናወነም።
በመሆኑም በቀጣይ በአረብኛ የሚካሄዱ መድረኮችን በማስፋት የዓለም ህዝብ በተለይም ዓረቡ ዓለም በአፍ መፍቻ ቋንቋው ስለግድቡ ትክክለኛ መረጃዎች እንዲደርሱት ማድረግ ይገባል።በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በተካሄደው ውይይት ላይ ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አልጀዚራ፣ አልአይን እና ሱዳናዊው ጸሐፊ ሲገኙ፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ አልዓለም ጋዜጣ እና የህዳሴ ግድብ በተመለከተ በግብጽ መገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ትንተና የሚሰጠው ኢትዮጵያዊው መሃመድ አልአሩሲ ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012ጌትነት ተስፋማርያም