የምትመለከቱት ምስል ከቀናት በፊት በአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ቁልቁል ወደ መርካቶ ከሚወስደው አትክልት ተራ ጎራ እንድል ያደረገኝ የትዝብቴ መነሻ ትዕይንት ነው፡፡ ከስፍራው ስደርስ እንደ እድል ሆኖ ጠንከር ያለ ፀሐይ በመኖሩ የወትሮው ጭቃማ የአትክልት ተራ መተላለፊያዎች መጠጥ ብለዋል፡፡ እንግዳ ለሆነ በገበያው ግራ ቀኝ ያለው ግፊያ ትንፋሽ ያሳጥራል። ድባቡን ለተላመዱት ግን ብዙም አስጨናቂ አይመስልም::
የአትክልት ተራ ጓዳ እንደ ፍራፍሬው ሁሉ መልከ ብዙ ሕይወትን በመቀየጥ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› የሚያስብሉ አግራሞትና አድናቆት የሚያጭሩ አያሌ ትእይንቶችን ያስመለክታል፡፡ የልጆችዋን ሆድ ለመሙላት ከኑሮ ጋር ተናንቃ አቧራና ጸሐይ፣ቁርና ዝናብ እየተፈራረቁባት ከምትሸጥ ምስኪን እናት አንስቶ ከአራት በላይ ሳጥኖች ጭንቅላታቸው ላይ መደራረብ ሰርከስ የሚሰሩ የሚመስሉ ወጣቶች የአትክልት ተራ ተዋናይ ናቸው፡፡
እኔ ከመሸመት ይልቅ በየቦታው እየቆምኩ በሃሳብ የምባዝንበት ብሎም በትዝብት የምብከነከንበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ አትክልት ተራም በአሥር ሺዎች በሚገመቱ ገበያተኞች፣ በጭንቅላታቸው ቅርጫትና ዘንቢል ተሸክመውና በመደብ ከፋፍለው ሸጠው ለማደር ላንቃቸው እስኪደርቅ ደንበኛ በሚጣሩና በአፈ ቀላጤ ደላሎች ተዋክባለች፡፡
ከአትክልት ተራ እንዲህ በገበያኞች ትተረማመስ እንጂ ዓለም በአንፃሩ ዘር፣ቀለም፣ቋንቋ ፣የስልጣን ከፍታ፣ የሀብት ደረጃ ሳይለይ በሚቀጽፈው የኮቪድ 19 ቫይረስ ጭንቅ ውስጥ ትገኛለች፡፡በየአገራቱ ለወትሮ የሰው ግርግር የሚያደምቃቸው ከተሞችና ቦታዎች የኮሮና ቫይረስ መምጣትን ተከትሎ ፀጥ ረጭ ብለዋል፤ ተዘግተዋል፡፡
ያልጠበቀችው ጨለማ ድንገት የዋጣት ዓለምም ቀናት አልፈው፣ሳምንታት ቢተኩና ወራት ቢፈራረቁም ወረርሽኙን በተመለከተ እያደር አስደንጋጭ፣አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ እንጂ በጎና አስደሳች ዜና መስማት አልሆነላትም፡፡ በእያንዳንዱ ቀን በሺ የሚቆጠሩ ዜጎቿን እያጠቃ፣ ወግ ሥርዓቱን እንኳን መጠበቅ ከልክሎ በመቶ የሚቆጠሩትን በሚያሳዝን መልኩ እንድትቀብር አስገድዷታል፡፡
ይህ ሁሉ አሰቃቂ ክስተት ግን አትክልት ተራ ያስጨነቃት አይመስልም፤ መርካቶንም እንዲሁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና የጤና ባለሙያዎች ‹‹ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳትሆኑና ስርጭቱንም ለመቆጣጠር ንጽሕናችሁንና ማህበራዊ ርቀታችሁን ጠብቁ እያሉ ሌት ተቀን ለዜጎች ደህንነት የተለያዩ የጥንቃቄ መልእክቶችን ቢያስተላልፉም ገበያዋ ግን ለዚህ ተማፅኖ ጆሮና ቀልቧን የሰጠች አትመስልም፡፡
አንዳንዶች ከግፍያና ከሸክማቸው እየታገሉ አፍና አፍንጫቸውን ሸፈን ለማድረግ ሲሞክሩ ባስተውልም እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከወትሮው የተለዩ ሆነው አይታዩም፡፡ ማህበራዊ መስተጋብሮች እንደወትሮው ይከናወናሉ፡፡ሰላምታ የመለዋወጡ ሂደት ላይም ለውጥ አይታይም፡፡በርካቶች ጅምላ ጨራሹን ቫይረስ አንኳሰው እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሄዳሉ፡፡ በገበያ መሃል የቸልተኝነት አስተሳሰብ የወለደው ግትርነትና አልሸነፍም ባይነት ከፍ ብሎ ተሰቅሏል፡፡ ተጠንቀቁ የሚለውን መልዕክት ለመተግበር ኋለኛና አርፋጅ የሆኑት ቁጥር ያስደነግጣል፡፡
ትዝብቴን ለአፍታ በማቋረጥ በገበያው መሃል ደፋ ቀና ከሚሉበት መካከል ወይዘሮ ጀማነሽ አንድነት የተባሉ ነጋዴን ተጠግቼ፣ ለመሆኑ ይህን ቸልተኝነት ምን አመጣው ስል ጥያቄ አቀረብኩላቸው፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን ለፈጣሪ ብቻ ሰጥቶ እጁን አጣጥፎ መቀመጡ የፈጠረው ነው›› ሲሉ መሰከሩ፡፡
‹‹ማመን መልካም ቢሆንም አማኞች መሆናችን አደጋውን አያስቀርም፣ መጠንቀቃችን ከምንም በላይ ዋጋ አለው›› የሚሉት ወይዘሮዋ፣ህዝቡ ‹‹በቫይረሱ ምን ያህል ሰው ተያዘ›› የሚለውን ከማዳመጥ ውጭ በዚህ በግብይት ስፍራ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ቦታዎች ጥንቃቄን ሲተገብር አለማስተዋላቸውና ይህም አሳሳቢ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
ወቅታዊውን ቀውስ ለመሻገር መሆን ስለሚገባው ሲጠቁሙም፣ከሁሉ በላይ ቸልተኝነትና እንዝላልነትና የምንወዳቸውን እንደሚያሳጣን መገንዘብ ይኖርብናል ያሉት ወይዘሮዋ፣በመሰል የፈተና ወቅት ይበልጥ ተጎጂ የሆኑ አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ወይዘሮ አስቴር ሰይፉም፣ ‹‹የዜጎቹን ደህንነት ለማረጋገጥና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ብሎም ለመቀነስ መንግሥት በሚችለው መጠን የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፏል፣ይሁንና እያደር በመጠጥ ቤት፣በአምልኮ ቦታዎች የሚስተዋለው እንዝላልነት እጅጉን ግራ የሚያጋባ ነው›› ይላሉ፡፡
ለአብነት ጭፈራ ቤቶች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ቢተላለፍም አንዳንዶቹ በር ዘግተው ደንበኞቻቸውን በተጨናነቀ መልኩ እንደሚያስተናግዱ መስማታቸውን የሚጠቁሙት ወይዘሮ አስቴር፣ ‹‹ይህ ህዝብ በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሞቱ እስኪባልና ከቤት እንዳይወጣ በወታደር እስኪጠበቅ የቫይረሱን አስከፊነት ለመረዳት የተዘጋጀ ይመስላል ይላሉ፡፡ ይህ የሚያመላክተው ወረርሽኙን ለመመከት ግንዛቤ ብቻውን በቂ አለመሆኑንና ተግባሩ ከሕግ ማስከበር ተግባራት ጋር ተጣምረው መጓዝ እንዳለበት ስለመሆኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ የምግብ መድኃኒት ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤት የጤና ባለሙያ አቶ አለማየሁ መስፍን፣ በተለይ የኮሮና ቫይረስ እያደር ጨካኝ መሆኑን እያስመሰከረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በአትክልት ተራና በሌሎች ስፍራዎች የሚመለከቱት የህዝቡንም ቸልተኝነት እጅጉን አሳሳቢ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
ሕዝቡ ከሚሠጠው መረጃ ይልቅ ሌሎች የኑሮ ቀዳዳዎችን ያሳሰቡት እንደሚመስል የሚገልፁት ባለሙያው፣ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ይቻል ዘንድ የሚደረገውን ርብርብ ወደ ኋላ የሚጎትትና ስጋት የሚፈጥር ፣የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም የቫይረሱን ጨካኝነትን የነፍስ መቅጠፍ አቅሙም ከፍታ በሚያሳዩ ብሎም ተፅእኖ ፈጣሪዎች ግለሰቦችን ባካተተ መልኩ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት የሚጠቁም ስለመሆኑ ያነሳሉ፡፡
አሁን ቫይረስን በተመለከተ ስለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለማህበረሰባችንም ሲባል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፣ ወቅቱ የሚጠይቀውም ከሁሉ በላይ ይሄንን ኃላፊነት መወጣት ነው›› የሚሉት አቶ አለማየሁ፣ ከቸልተኝነት ፅልመት በመላቀቅና በላቀ ጥንቃቄ እንዲሁም ለሌሎች ማሰብ ይህንን ወቅት ልናልፍበት የምንችለው ትክክለኛው መፍትሄ መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግም ነው ያሰመሩበት፡፡
‹‹ከዚህ በተጓዳኝ ማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ሁለንተናዊ ቀውስ ታሳቢ በማድረግ እንደ ሌሎች አገራት የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ለአብነት መንግሥትም ሆነ አከራዮች የቤት ኪራይን መቀነስ ብሎም ማስቀረት፣ ዝቅተኛ አቅም ላላቸውም የምግብና ሌሎች አቅርቦቶችን ተደራሽ ስለማድረግ ሊታሰብበት ይገባል ነው›› ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ሀገሪቱ በኮሮና በሽታ ሳቢያ ሊያጋጥም የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት ህብረተሰቡ ከምንም በላይ ሊተባበርና ራሱን ለዲስፕሊን ሊያስገዛ እንደሚገባ ማስገንዘባቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012
ታምራት ተስፋዬ