አዲስ አበባ፡- ‹‹አባይና ሌሎች ወንዞቻችንን ማልማት በህዳሴው ግድብ ብቻ የሚቆም አይደለም ›› ሲሉ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት የሕዳሴ ግድቡ የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት፣ ወንዞችን ማልማት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚቆም ተግባር ብቻ አይደለም፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለሌሎች ወንዞች ልማት ትልቅ ማሳያ ነው፤ ሌሎች ወንዞችን የማልማት ሥራው ወደፊት የሚቀጥል ነው፡፡
የህዳሴው ግድብ የዘጠኝ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በኮንትራት ሁኔታና የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ለሥራው እንቅፋት መሆናቸው ሥራውን ውስብስብ አድርጎት ከርሟል ያሉት ሚኒስትሩ በአሁኑ ሰዓት ግን ለተፈጠሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል::
የህዳሴው ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግብፅ ግድቡ ይጎዳኛል ከሚል መነሻና ውሃውን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎት የመነጨ ኢትዮጵያ የሌለችበትን አባይን የመጠቀም መብቷን የሚከለክሉ ውሎችን በመጥቀስ ለመከራከር የምታደርገው ሙከራ ግልፅ ሆኖ መምጣቱን በመናገር ኢትዮጵያ ግን በተቃራኒው የሁሉም ሀገሮች ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ነገሮችን ማመቻቸቷን አብራርተዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡ መገንባት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ህዝቦችም ጭምር የዘመናት የራስን ሀብት የመጠቀም ፍላጎትን ወደተግባር መለወጥ የመቻል አቅም ማሳያም ጭምር ነው ያሉት ሚኒስትሩ ግድቡን ለመጨረስም አስፈላጊው ነገር ሁሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ መርሆዎችን በመከተል ለመብትና ሉዓላዊነቷ እንደምትሰራ የተናገሩት ሚኒስትሩ ግድቡን በድል እንደምታጠናቅቅ ያላቸውን ሙሉ እምነት በመናገር ሀገሪቷ የደረሰችበትን የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ የሚጠይቀውን ያህል ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ተልዕኮ በወሳኝነት ለማሳካት በርካታ የኃይል ልማት ሥራዎች መታቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ 72 ነጥብ 4 በመቶ የደረሰ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ህዳሴ ግድቡ ላይ ህዝቡ እስከዛሬ ድረስ በህዝቡ ትብብር እውቀትና ሀብት እየተሰራ መሆኑን በመናገር ግድቡን ለማስፈፀምም የተለመደ ትብብሩን 8100A ላይ በመላክ እና የቦንድ ግዢን በማካሄድ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ በ2003 ዓ.ም በቀድሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት በጉባ መቀመጡና ግንባታው መጀመሩ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012
ዳግማዊት ግርማ