የሽሮ ሜዳ ቁስቋምና የአቃቂ ቱሉ ዲምቱ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በይፋ ተጀመረ፡፡
በይፋ የተጀመሩት የአስፋልት የመንገድ ፕሮጀክቶችን የአቃቂ ከተማ ቱሉ ዲምቱና የሽሮሜዳ ቁስቋም ሲሆኑ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ከሚኖራቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥቅም ባሻገር የከተማዋን ገፅታ ያሻሽላሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የአቃቂ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ከ5 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመትና 25ሜትር ጎን ስፋት ያለው ሲሆን የሽሮሜዳ ቁስቋም አስፋልት መንገድ 1.4 ኪ.ሜ ርዝመት እና 30 ሜትር የጎን ስፋት እንዲሁም 4.5 ሜትር የእግረኛ መንገድ አካቶ የሚገነባ መሆኑ በመንገድ ግንባታ ጅማሮ ስነ ስርአቱ ላይ ተገልጿል፡፡
መንገድ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በየጊዜው በመዲናዋ አዳዲስ መንገድ እየሰራ እንደሚገኝ በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ ተናግረዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ክፍሌ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በወጣቶች ያለ የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋኦ እንዳለው በመግለጽ መላው ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ዮቴክ በተባለ አገር በቀል ተቋራጭ የሚከናወን ሲሆን 161 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ እንደሚገነባና በ 2 ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በስነስርአቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በማዕረግ ገ/እግዚአብሄር