ኮሮና ኢትዮጵያ ገብቶ ሲሳዮቹን መቁጠር በጀመረበት ማግስት አገሪቱን የነቀነቀ ዜና ተሰማ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ምርምር ሲካሄድ ነበር። የኮሮና ቫይረስን በሳይንሳዊ ምርምር በተደገፈ የሀገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ቫይረሱን ለማከም የተሰራው መድሃኒት መሰረታዊ የምርምር ሂደት በማለፍ ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሞዴሊንግ ሂደቶችን በስኬት አልፏል። ወደ ቀጣይ የእንስሳት እና ክሊኒካል ፍተሻ ስራዎች እንዲሸጋገርም ተደርጓል። መድኃኒቱ የመከላከል አቅም የሚጨምር፣ መርዛማነት የሌለው እና አዋጭነቱ የተረጋገጠ ነው። የምርምር ሂደቱ ተጠናቅቆ ወደ ምርት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ።
ተያይዞም ባህላዊ ህክምናን እና ሳይንሳዊ ምርምርን በማጣመር ከእጽዋት የኮሮና ቫይረስ መድኃኒት ለማግኘት ባለሙያዎች እያደረጉ ያለው ሙከራ የመጀመሪያ የቤተ ሙከራ ሂደት ያለፈ ሲሆን፤ ወደቀጣይ የምርምር ሂደቶች እንዲሸጋገር የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መፈራረማቸውን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።
በመግለጫው የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ከኢትዮጵያውያን የባህል ሃኪሞችና የህክምና ተመራማሪዎች ጋር በመሆን የሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንሳዊ ሂደቶች በማሳለፍ ለዘመን አመጣሹ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ህክምና የተዘጋጀውን መድኃኒት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ስራ በመስራት ላይ ይገኛል አሉ።
በመድረኩ ሌላኛዋ ተናጋሪ የነበሩት የሀገር በቀል መድኃኒቶች አዋቂም ‹‹የሊቃውንትና የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒቶችን ነው ለቫይረሱ የሰጠነው፤ እናመሰግናለን። በጥንቃቄ፣ የሀገራችን ሕዝቦች የጤና ቢሮ የሚሰጣቸውን መግለጫ እየተቀበሉ በተለያየ ነገር ሳይጠመዱ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ አሳስባለሁ። … ከኢኖቬሽን ሚኒስቴር እና ከጤና ሚኒስቴር ካልተሰጠ ምንም ዓይነት መድኃኒቶች እንዳይሞክሩ፤ ከተሞከረም በእነርሱ ሥር የሚያልፍ መሆን አለበት።” ሲሉ ተደመጡ።
ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የህክምና ባለሙያዎችና ሌሎችም መንግስትን ማብጠ ልጠል ያዙ። ኢትዮጵያ ይህን ማድረግ አትችልም፤ ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ፤
የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ብቻ የተናፈሰ የፈጠራ ወሬ፤ ቫይረሱን ለመከላከል ስንደክም ብንቆይም ጥረታችን ላይ መንግስት ውሃ ቸለሰበት፤ እንዲህ እያላችሁ ህዝቡን አዘናጉት፤ ደግሞ እዚህች አገር ላይ ምን ምሁር አለና ነው ምርምር የሚካሄደው … ሌላም ሌላም ተባለ።
መረጃውን አሉታዊ አድርገው በሚያቀርቡት ተዋንያኖች አራጋቢነት ህብረተሰቡ ውዥንብር ውስጥ ገባ። በቀናነት መንፈስ ተሞልተው መድኃኒቱ ሁሉንም ሂደቶች ጨርሶ ለገበያ መቅረብ ከመጀመሩ በፊት እንዲህ ያለ መግለጫ መሰጠቱ ዜጎችን ሊያዘናጋ ይችላል በሚል ስጋት መንግስት መረጃውን ባደረሰበት መንገድ አለመደሰታቸውን በመግለጽ እርምት እንዲደረግ የጠየቁ ዜጎችም ነበሩ።
ይህን የህብረተሰቡን ሁኔታ በመረዳት ይመስላል የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ሚኒስቴር ቀደም ብሎ የሰጠውን መግለጫ በመቀየር የእርምት እርምጃ ወሰደ። “የምርምር ሂደቱ ተጠናክሮ ወደ ምርት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው” የሚለውን ዐረፍተ ነገር አስተካክሎ ወደ ምርምር ሂደት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው በሚል ተካ።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትሯም “ እንቅስቃሴው በአለም አቀፍ ደረጃ ሌሎች አገራትም ለበሽታው ክትባትና መድኃኒት ለማግኘት የሚያደርጉት የምርምር ጥረት አንዱ አካል ነው። ምርምሩ በመድኃኒት ግኝት ሂደት መመሪያ መሰረት ብዙ የምርምር ሂደቶች የሚቀሩት ነው። በአሁኑ ወቅት በሽታውን ለመከላከል ያለው ብቸኛ አማራጭ እየተሰጡ የሚገኙትን የጤና ምክሮችን መተግበር መሆኑን ለማሳሰብ እወዳለሁ” አሉ።
ሚኒስትሮቹ ማብራሪያ ለመስጠት ዳግም ወደ አደባባይ ብቅ እንዲሉ የተገደዱት ከፖለቲካ ትርፍ ይልቅ ለዜጎች ህይወት መትረፍ ግድ ስለሚላቸው ነው። የተዥጎደጎደው ትችት ዋነኛ ምንጭ ራስን፣ ወገንና አገርን አሳንሶ የማየት አባዜ ውጤት መሆኑ ጠፍቷቸው አይመስለኝም። ዝንት ዓለም ተቀባዮች ሆነን ለመኖር የቆረጥን ቁራጮች መሆናችንን ዝንባሌያችን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል። የአያት ቅድመ አያቶቻችን ቅጣዮች ብንሆንማ አበርካቾች እንደሆንን እናምን ነበር። ነገር ሁሉ ከማመን ነው የሚጀመረው። እንደ ህዝብ ይህ እምነት ኖሮን ቀደምቶቻችን ባቆዩልን ጥበብ ለመጠቀም ጠንክረን ብንሰራ ኖሮ ከአንድ አይደለም በሺ ከሚቆጠሩ በሽታዎች የሚፈውሱ መድኃኒቶችን ለዓለም ማበርከት በቻልን ነበር። የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት በኬፕ ቨርዴ ባካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የጤና ፎረም ላይ ባወጣው ሪፖርት በአፍሪካ በበሽታ ምክንያት በየአመቱ ሁለት ነጥብ አራት ትሪሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ገልጿል። ሩቅ ሳንሄድ ለአፍሪካ የጤና ችግር ብቻ መፍትሄ በመሆን አገራችንን ማሳደግ እንችል ነበር።
አንድ የታሪክ ምሁር እንዳሉት ፣ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ለምሁራን ያላቸውን ንቀት ገለጹ ብለው የወረፏቸው ሰዎች ዛሬ መልሰው ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ለኮሮና ቫይረስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር እያደረጉ መሆናቸው ሲገለጽ ምሁር የታለና ማለታቸው አጃኢብ ያሰኛል።
ሲሆን አድናቆትንና ድጋፍን መግለጽ እንደዜጋ ተጠባቂ ተግባር ነበር። ይህን ማድረግ ባይቻል እንኳን የተመራማሪዎቻችንን ሞራል የሚነኩ ንግግሮችን ከማድረግ መቆጠብ ይገባ ነበር። ሁለቱን አማራጮች ፊት ነስተው ማብጠልጠልን የመረጡ ወገኖች ለዚህ ተግባራቸው በቂ ምክንያት አላቸው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ለእነዚህ ወገኖች በሰጡት ምላሽ፡- “ትላንት ኮረና ቫይረስን አስመልክቶ በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች እየተካሄደ ያለውን ምርምር እና የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ በሰጠነው መግለጫ እንዴት በኢትዮጵያውያን ይህ ሊሆን ይችላል በሚሉ ሃገራቸውን እነሱ የሚያውቁዋትን ያህል እውቀት ብቻ ያላት በሚመስላቸው እና ይህ ስራም ፖለቲካዊ ገፅታ ሰጥተው እኛ ያላወቅነው እንዴት ይሆናል በሚሉ አካላት ባልሆነ መንገድ ተርጉመው እያቀረቡ ያሉት ትርክት የለመዱትን የአሉባልታና የውሸት ዜና መስራት መቅረቱን ያልተረዱ እና ሀገራችን ለችግር ግዜ የሚደርሱ አዋቂዎችና ተመራማሪዎች እንዳሉዋት የማያውቁ ወይም ማወቅ የማይፈልጉ ሰዎች ናቸውና የነሱ ማላዘን ይቀጥላል ሃገራችንና ህዝቦችዋ ወደ ከፍታ ማማ ይጓዛሉ።
አሁንም በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ነገር የተጀመረው የምርምር ስራና እስካሁን የተገኘው ውጤት በጣም አበረታች ብቻ ሳይሆን በአጠረ ጊዜ ቀሪ ስራዎች በማጠናቀቅ ለሕዝባችን የተጀመረውን የምንጨርስ እና ያልነውን የምናደርግ መሆኑን እንደምናሳይ ነው። የምርምር ቀሪ ስራዎች ማለትም የአኒማል ቶክሲስቲ እና ክሊኒካል ቴስት ስራዎች በተፋጠነ መንገድ እየተሰሩ የሚገኘውን ውጤት ለህዝባችን እንገልፃለን። የምርምር ቀሪ ስራዎች የራሳቸው ግዜ የሚወስዱ በመሆናቸው በዚህ መልካም ዜና ምክንያት በፍፁም መዘናጋት አይገባም፤ አያስፈልግም። በመንግስት የሚሰጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንተግብር”ብለዋል። እኔም በእርሳቸው መልዕክት ጽሁፌን አበቃሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
የትናየት ፈሩ